“ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከከፋ የእርሃብ አደጋ እጅ ለዕጅ ተያይዘን እንታደግ!!” አንድነት ፓርቲ

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከከፋ የእርሃብ አደጋ እጅ ለዕጅ ተያይዘን እንታደግ!!
ዓለማቀፉ ማህበረ-ሰብ በአገራችን የተከሰተውን ድርቅ ስፋትና አጣዳፊነት ተገንዝቦ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን!

የድርቅና ጠኔ ታሪክ የሃገራችን ታሪክ አካል ከሆነ አያሌ ዓመታትን አሰቆጥሯል፡፡ ዓመታትን ማስቆጠር ብቻም ሳይሆን በተከሰተባቸው ዓመታት ሁሉ ሕዝባችንን በከፍተኛ ሁኔታ ቀጥፏል፡፡ እንስሳቶቻችን በገፍ ፈጅቷል፡፡ የአገራችንን ጥሪት በከፍተኛ ሁኔታ አሟጧል፡፡ ሃገራችን አንዳች በጐ ታሪክ የሌላት ያህል የሃገራችን መለያ ምልክት የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየደረስንበት አንገት አስደፍቶናል፡፡ ክብራችንንና ታሪካችንን በእጅጉ ነክቷል፤ አጉድፏል፡፡
ኢትዮጵያችንን የመሩ አምባገነን መንግሥታትም ድርቅን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ መፈክሮች ከማሰማት የዘለለ በድርቅ ምክንያት በሕዝባችን ላይ የሚደርሰውን መከራና ዕልቂት ለማስቆም አይደለም ለመግታት አልቻሉም፡፡ “ደርግ ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን”የሚል መፈክር ቢያሰማም ሕዝብን መቆጣጠርና ማፈን ላይ እንዳተኮረ ግባዓተ – መሬቱ ተፈፅሟል፡፡ ደርግን የተካው ኢህአዴግም በቀን ሦስት ጊዜ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመመገብ በዘለለ አያሌ አማላይ ነገሮችን አሳካለሁ እያለ ቢደሰኩርም ተቀዳሚ ተግባሩ ግን እንደደርግ ሁሉ ሕዝብን በጭቆና ሰንሰለት አስሮ መግዛት ሆኗል፡፡ በአገራችን ታሪክ ታይበቶ በማይታወቅ ሁኔታም አስራ አራት ሚሊዮን (14,ዐዐዐ,ዐዐዐ) ሕዝብ ያስራበ አገዘዝ ነው፡፡ አገዛዙ እንደቀድሞዎቹ ሁሉ በሃገራችን በተደጋጋሚ ለሚከሰተው ድርቅ፣ለሚቀጠፈው የሰው ሕይወትና ለሚወድመው የአገር ሃብት ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት አልቻለም፡፡

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡ ይሁን እንጂ አገሮች ለትንበያዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና አመርቂ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አደጋው ሊያደርስ የሚችለውን ጥፋት ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕይወትና ንብረትን ከውድመት ለመከላከል ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያችንን እየገዙ ያሉ አምባገነኖች ግን ትልቁ ጭንቀታቸው የእነርሱን ገጽታ እንዴት እንደሚጠብቁ እንጂ የሚረግፈው ሕዝብና የሚጠፋው የሃገር ሃብት አልሆነም፡፡ የአሁኑን ዓመት የድርቅ ሁኔታ እንኳን ብንወስድ ችግሩ እንዳንዣበበ የሚያሳዩ ትንበያዎች የወጡት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በፊት ቢሆንም አገዛዙ ግን የተረጅዎችን ቁጥር በማሳነስ ሕዝብንና ዓለማቀፍ ማህበረሰቡን ተገቢውን ርብርብ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኗል፡፡ መጀመሪያ ላይ የተረጅዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማሳነስ 2.8 ሚሊዮን ተረጅ ብቻ ነው ቢልም ነገሮች እየገፉ ሲመጡ 3.4 ሚሊዬ በኋላ ላይ ቆይቶ ደግሞ 4.5 ሚሊዬን መሆኑን አምኗል፡፡ ኢትዮጵያ አደገች ተሞሸረች የሚለውን የማማለያ ፕሮፖጋንዳ የሚያሳጣና አገር ለመምራት ብቃት እንደሌለው ሚያሳብቅበትን እንዲህ አይነት ነገር በይፋ ማመን የሚዋጥለት ጉዳይ አልሆነም፡፡

አሁን እንኳን የድርቅ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርጭት መረብ (Famine Early Warning systems Net work) የሚባል አሜሪካ በቀል ድርጅት ግንቦት 1 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም ችግሩን አሳውቋል፡፡ ይኸንም ተከትሎ ቢቢሲ በማግስቱ በአፍሪካ ቀንድ ያንዣበበውን የከፋ የድርቅ አደጋ በስፋት ገልፆ መጠነ ሰፊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግም ይፋ አድርጓል፡፡ አገዛዙ ግን በጉዳዩ ላይ ከአንድ ወር በላይ ዝምታ ከመረጠ በኋላ ሐምሌ 4 2ዐዐ3 ዓ.ም ለ4.5 ሚሊዬን ሕዝብ ዕርዳታ ጠይቋል፡፡ ሆኖም አሁንም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ለድርቁ የተሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ መሆኑን አንድነት ይገነዘባል፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን ለጉዳዩ እስካሁን የሰጠው ትኩረትና ምላሽ የሚገባውን ያህል ነው ብሎ አንድነት አያምንም፡፡

ሕዝባችን በአብዛኛው የሃገራችን ክፍል በከፍተኛ ርሃብ እየተጠቃ ነው፡፡ በተለይም በሶማሌ ክልል፣በቦረና፣በጉጂ፣በደቡብ ክልል ልዩ ልዩ ቦታዎች እጅግ የከፋ የርሃብ ደመና አንዧቧል፡፡ በተለይም አርብቶ አደሩ አካባቢ ከ5ዐ እስከ 6ዐ ከመቶ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 8ዐ ከመቶ የሚሆነው የዕንስሳት ሃብት እያለቀ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህም በላይ በሃገራችን ማባሪያ ባጣው የዋጋ ግሽበት ምክንያት የተጐጅዎች ሕይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛል፡፡ የአርብቶ አደሩ ከብቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል፡፡ መቶ ኪሎ የምትመዝን ላምና መቶ ኪሎ የሚመዝን ስንዴ ዋጋው ሰማይና መሬት ሆኗል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ከእርሃብ ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው ችግርም ቢሆን ተገቢው ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ ለአካባቢው የተወሰደው የተረጅዎች ቁጥርም 286,ዐዐዐ (ሁለት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ) ቢሆንም ግን በ46ዐ,ዐዐዐ (አራት መቶ ስልሣ ሺ) በላይ እንደሆነ እንዳውም ከከፋም እስከ 785,ዐዐዐ (ሰባተ መቶ ሰማንያ አመስት ሺ) ሊያሻቅብ እንደሚችልም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ችግሩ በመላ ሃገሪቱ የተከሰተ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለተረጅዎች እየተዳረሰ ነው የሚባለው የዕህል መጠን በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አንድነትን እጅግ ያሳስበዋል፡፡ ለአንድ ዜጋ በወር የመጨረሻ ትንሹ የሚያስፈልገው ፍጆታ 21 ኪ.ግ ቢሆንም አሁን ግን እየተሰጠው ያለው 15 ኪ.ግ በመሆኑ በህይወት እንኳን ለማቆየት በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይኸም ሆኖ ሰባት አባላት ላሉት ቤተሰብ የሦስት ቤተሰብ ብቻ የሚሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እየረገፉ ላሉት እንስሳት መኖ ማቅረብ እየተሞከረ ቢሆንም ከሚፈለገው አንፃር ፈፅሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በምግብ ራሳችንን ላለመቻላችን መንስዔዎች
1ኛ. በአጠቃላይ በአገራችን በአሁን ሰዓት በሴፍተኔት የታቀፉ 7.8 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያንና አሁን በከፋ ድርቅ ውስጥ የሚገኙት 4.5 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ቁጥር በአጠቃላይ የተረጅውን ቁጥር 12.4 ሚሊዬን ያደርሰዋል፡፡ ከዚያም በላይ በተረጅነት ያልተመዘገበው ኢትዮጵያዊ ከተሜም በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ ይገኛል፡፡ ይኸ የሚያሳየው በአለፉት 2ዐ ዓመታት የተመዘገበውን የውድቀት ደረጃ ነው፡፡ የውድቀቱ መንስኤም በዋናነት የፖሊሲ ውድቀት ነው፡፡ የተፈጥሮ ድርቅን ፈፅሞ እንዳይከሰት መከላከል አስቸጋሪ ቢሆን ሕዝቡ እንዳይራብ ማድረግ ግን የሚቻል ተግባር ነበር፡፡ አሁን የሚታየው ግብርና መር እየተባለ የሚቀለደው ቀልድ ሃገራችንን ምን አይነት አዘቅት ውስጥ እንደከተተ ነው፡፡ ግብርናው ዘላቂ የሆነና እራሳችንን የሚያስችል ልማት ሊፈጥር እንዳልቻለ ተግባራዊ ምስክር ከዚህ የዘለለ ሊቀርብ አይችልም፡፡
2ኛ. አገዛዙ እየተከተለው ያለው የመሬት ፖሊሲ ሌላው እራሳችንን መመገብ ላለመቻላችን ምክንያት ነው፡፡ መሬት ያራሹ ሳይሆን የመንግሥት ነው፡፡ ገበሬው መሬቱን በማልማት ራሱን ከችጋር ለመከላከል አልቻለም፡፡ መሬት የሌላቸውን ገበሬዎች መሬት ከመስጠት፣ገበሬውን የመሬቱ ባለቤት ከማድረግና ኢትዮጵያዊ ባለሃብቶች በግብርናው መስክ ተሰማርተው እንዲያመርቱ ከማበረታታት ይልቅ መሬትን ለውጭ ዜጐች መቸብቸብን አገዛዙ መፍትሄ አድርጐ ወስዷል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም መከረኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለርሃብ፣እርዛትና ሞት አደጋ ተጋልጧል፡፡
3ኛ. አሁን ያለው የተዛባ የግብርናና የመሬት ፖሊሲ እንዳለ ሆኖ የቴክኖሎጅ ስርፀቱም እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በጣም ዝቅተኛ የሆነ የማዳበሪያ ስርጭትና አጠቃቀም ከመኖሩም በላይ ክፍፍሉም በጣም የተዛባ ነው፡፡ እንዲሁም የምርጥ ዘር አቅርቦትም ቢሆን እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ የሚገኙት 65,ዐዐዐ (ስልሣ አምስት ሺ) የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በዋናነት ጊዜያቸውን የሚያጠፉት በየቀበሌው የፖለቲካ ሥራ ተጠምደው ነው፡፡ ለማዳበሪያ የተወሰነ ብድር የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ብዙ ቦታዎች በመቅረቱ ሕዝቡ ማዳበሪያ ለመጠቀም የነበረው ቲኒሽ እድልም ተመናምኗል፡፡
4ኛ. ደካማ በሆነ የገበያ ስርዓት፣ከደርጉ ጊዜ ባልተሻለ ሁኔታ የኢህአዴግ ካምፓኒዎች እነ ጉና፣ዲንሾ፣አምባሰልና ሌሎችም የሚቀልዱበት የገበያ ስርዓት መኖሩ ሌላው መንስዔ ነው፡፡
5ኛ. የንግድ እርሻዎች ወይንም (commercial farming) እንዲስፋፋ አመርቂ ጥረት አለመደረጉና ከዚህም ሊገኝ የሚገባው ተረፈ ምርት አለመገኘቱ፣
6ኛ. ሙያና ሙያተኛ ያልተገናኘበትና ካድሬዎች አዛዥና ናዛዥ የሆኑበት የግብርናና አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ መፈጠሩ፣
7ኛ. አገዛዙ ዕምነቱን በዋናነት በዕርዳታ ላይ የጣለ መሆኑ (aid syndrome) ያጠቃው መሆኑ፡- ዘላቂ መፍትሄ በቁርጠኝነት ከመፈለግ ይልቅ የዝናብና የዕርዳታ ጥገኛ መሆኑ፣
8ኛ. በዕውቀት፣በጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ቁርኝት አለመፈጠሩ እና
9ኛ. አገሪቷ እራሱን ዓላማ ባደረገና ከሕዝብና ከሃገር ጥቅም ይልቅ ለራሱ በሚጨነቅ ሥርዓት መዳፍ ሥር መገኘቷ ናቸው፡፡ ከሁሉ የማያሳስበው አሁን ባለው ሥርዓት ሥር ከዚህ የባሰ እንጂ የተሻለ መጠበቅ አለመቻላችን ነው፡፡

መውጫው መንገድ
1ኛ. የዝናብና የዕርዳታ ጥገኝነትን ለማስቀረት የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ መንቀሳቀስ ለምሳሌ የመስኖ ሥራን በስፋት ታስቦበት በስፋት መሥራት ተገቢ ነው፡፡
2ኛ. የግብርናና የኢንዱስትሪውን ቁርኝት መፍጠር ብሎም በማፋጠን ቴክኖሎጂው ከገበሬው ይልቅ በዓምስትና ስድስት እጥፍ እንዲያመርት ሁኔታዎችን ከወዲሁ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በሂደት የተመጣጠነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ኢንዱስትሪውን ገደል የከተተውን አካሄድ ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡
3ኛ. የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር እና የአገር ውስጥ ባለሃብቱና አገር በቀል ኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትና የሚስፋፋበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
4ኛ. ሁሉም ነገር ቢፈለግም በእንደዚህ አይነት አቅመ-ቢስ መንግሥት ሊሰራ አይችልም፡፡ ገበያው እራሱን የሚመራበትና የሚስተካከልበት ሁኔታ መፍጠር
5ኛ. በሕዝብ ያልተመረጠ ለ2ዐ ዓመታት አገር ማልማትና ሕዝብን መመገብ ያልቻለ፣ ተጠያቂነትን ፈፅሞ የማያውቅ ስርዓት በሩን ዘግቶ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያገባኝ እኔን ብቻ ነው ሊል ፈፅሞ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ የሚመክሩበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል፡፡

የዕርዳታ እህል መገኘት፣አቅርቦትና የምግብ አጠቃቀም ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ አንድነት ፓርቲ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ነጥቦችና ሊወሰዱ የሚገባቸውን ርምጃዎች እንደሚከተው ያቀርባል፡፡
1ኛ. አንድነት ፓርቲን የሚያሳስበው ጉዳይ የዕርዳታ እህል ዛሬውኑ ተጠይቆ ዛሬውኑ የሚገኝ አለመሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ለጋሾች ለመለገስ ሃሳብ እንዳላቸው መጠኑንም አክለው ቢገልፁም ከአገሮች ካዝና ገንዘብ ለማውጣት ያለው ሂደትና ገንዘቡም ከወጣ በኋላ እህል ተገዝቶ ለተረጅዎች እስኪደርስ ድረስ ያለው የጊዜ ዕርዝማኔ አሳሳቢ ነው፡፡ ስለሆነም ያለውን ችግር ለጋሾች አስንኦት ሰጥተውት ከወዲሁ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

2ኛ. የኢትዮጵያ ገበያ ላይ በመቶ ሺዎች ሚትሪክ ቶን የሜቆጠር እህል ለዛውም በድርቅ ወቅት የማግኘቱ ሁኔታ በጣም የማይታሰብ ነው፡፡ ገበሬው ባይራብ እንኳን ከየገበሬው 5 እና 1ዐ ኩታል ተለቅሞ ጠብ የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ከአገር ውስጥ ገበያ ገዝቶ ለተረጂው ወገናችን በአስቸኳይ የማቅረብ ዕድሉም የተሟጠጠ ነው፡፡ ለመጠባበቂያ ተብሎ የተያዘው (Strategic Reserve) ቢሆን ገበያ ለማረጋጋት ተብሎ ጥቅም ላይ ከመዋሉም በላይ ከነሐሴ 2ዐዐ3 ዓ.ም በኋላ የሚያወላዳ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሊኖር ከሚገባው 4ዐ5,ዐዐዐ (አራት መቶ አምስት ሺ) ሜትሪክ ቶን እህል ውስጥ በመጋዘን የሚገኘው 34,ዐዐዐ (ሠላሳ አራት ሺ) ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው፡፡

3ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የህብረት ሥራ ማህበራትም የካፒታል አቅማቸው አናሳ ነው፡፡ አቅም አላቸው ቢባል እንኳን በአገራችን ክረመት በሚገባበት ወቅት በገጠሩ ነዋሪ ዘንድ የዕህል ክመችት ተሟጦ የሚያልቅበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ማቃለል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከላይ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት ነጥቦች የሚያስገነዝቡት ለጉዳዩ ክብደት በመስጠት የተቀናጀና የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ሕዝባችንን ለመታደግ አጣዳፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባን ነው፡፡

4ኛ. የሚገኘውን የዕርዳታ እህል ወደሚፈለገው ቦታ የማድረስ ችግር ከወዲሁ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይም በአንዳንድ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች አሳሳቢ መሆኑን አንድነት ይረዳል፡፡ አንድነት ተገቢ ዕርምጃ ከወዲሁ እንዲወሰድ ያሳስባል፡፡ ከሁሉም በፊት ሕዝብን ማዳን ይቀድማልና አገዛዙና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ድርጅት ርዳታው ለወገኖቻችን እንዲደርስ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

5ኛ. ከዚህ በፊት በሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ለዕርዳታ የመጣን እህል የተቃዋሚና የአገዛዙ ደጋፊዎች እየተለዩ ይሰጥ እንደነበር መግለፁ ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት በሚረግፈው ወገናችን ላይ ይኸን መሰል አሣፋሪ ድርጊት እንዳይፈፀም እናሳስባለን፡፡

6ኛ. ሃገራችን በሞላ በተለይም በድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ የተጐዳው አካባቢ የተመጣጠነ ምግብ ችግር በተለይም በህፃናቶቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ተጋርጧል፡፡ ከዚህ አነፃር አቅም በፈቀደ መጠን ችግሩን ለመቅረፍ በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ከዕርዳታ ሰጪዎች ጋር በመመካከር አልሚ ምግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፣አጠቃቀሙን ማስረዳትና የህክምና አቅርቦት ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡

7ኛ. በተለይም በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሕዝባችንን ሕይወት መታደግ ቢቻለን እንኳን የሕይወቱ ዋልታና ማገር የሆኑትን እንስሳት በገፍ ማለቅስ አንዴት ሊገታ ይገባዋል የሚለው ጉዳይ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለእርዳታ ከተጠየቀው 398,439,73ዐ (ሦስት መቶ ዘጠና ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ሺ ሰባት መቶ ሠላሳ) ዶላር ውስጥ የጤናና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ የተጠየቀው ገንዘብ 69 (ስልሳ ዘጠኝ ሚሊዬን) ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይኸ ደግሞ አሁንም ያለው አገዛዝ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት ምን ማድረግ እንደሚገባው አለማወቁንና ሃገራችን ወደ ተሻለ ሁኔታ ሊመራት እንደማይችል በግልፅ ያሳያል፡፡ አሁንም ሳይውል ሳያድር ለእንስሳት ጤና ጥበቃ ተዛማጅ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ ይሰጥ፡፡ ስለዚህ የውሃ አቅርቦት የእንስሳት መኖና ህክምና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

8ኛ. በሃገራችን የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተተኮሰ ይገኛል፡፡ ከእህል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ዋጋ የባሰ የመጨመር አሊያም በጣም የመውረድ እና የወደቀውን ኢኮኖሚ ከነጭራሹ ከሃዲዱ የማሳት ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ አሁንም በጥራጥሬ እህሎች ላይ እጅግ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሚያዝያ እስከ ግንቦት 1ዐ.7% ጨምሯል፡፡ አገዛዙ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ምንም እያደረገ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከምግብ እጥረቱ በተጨማሪ የዋጋ ግሽበቱ በተለይም አርብቶ አደሩ እጅግ ፈታኝ ሆኖበታል፡፡ አሁንም የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል አስቸኳይ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ያሻል፡፡

9ኛ. ትንበያዎች እንደሚያሣዩት የችግሩ ስፋትና ጥልቀት በአጭሩ በአንድ ወቅት ዝናብ የሚመከት አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁንም በዝናብ ላይ እያሳየ ያለውን መተማመን በማቆም በሚቀጥሉት ወራት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የድርቅ አደጋ ለመቅረፍ አማራጭ መፍትሄዎችን ለማቅረብ አስቸኳይ ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

1ዐኛ. በአርብቶ አደሩ አካባቢ ለሚገኘው ሕዝብ በዘላቂነት ድርቁን እንዴት ሊቋቋም እንደሚገባ የተጠናከረና ዘላቂነት ያለው ትምህርት ከዕርዳታው ጐን ለጐን መሰጠት አለበት፡፡ በተለይም ከግጦሽ መሬትና ከከብት እርባታ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው ትምህርት ለሕዝቡ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
11ኛ. በሽታውን የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም እንዲሉ በገፅታ ግንባታ ምክንያት ሕዝባችን በዕርሃብ ሲያልቅ መደበቁ በአስቸኳይ ይቁም፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰዓት አገዛዙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዕርዳታ ድርጅቶችንም በከፍተኛ ሁኔታ በማዋከብና በማሸማቀቅ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ በቂ መረጃዎች እንዳይገኙ የሚያደርገውን አፈና በአስቸኳይ ያቁም፡፡

12ኛ. በአገራችን እየተከሰተ ያለው የተፈጥሮ አደጋ እንደ ሌሎች አገሮች አጣዳፊና ድንገተኛ ባይሆንም አገዛዙ ግን ተደራጅቶና ተቀናጅቶ በቂ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአሰቃቂ የእርሃብ አደጋ መታደግ አልቻለም፡፡ በዚሁ ድርቅ ምክንያት የኬንያ ዜጎች ያለመራብና ተመጣጣኝ ምግብ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተጥሷል በማለት መንግሥታቸውን ፍ/ቤት አቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው አገዛዝ ዜጎች ይህንን መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማይፈቅድ በመሆኑ ሥልጣኑን ለሕዝብ የሚያስረክብበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለሕዝብ ሊያስረክብ ይገባዋል፡፡
13ኛ. በመጨረሻም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጐን በመቆም ሕዝባችንን ከዕልቂት እንዲታደግ አበክረን ጥሪያያችንን እናቀርባለን!

14ኛ. በሴፍቲኔት የታቀፉ 7.8 ሚሊዬን ዜጎች ታቅፈው የሚገኙበት ፕሮግራም ይቋረጣል፡፡ ሂደቱን ለማስቀጠልም ይህ ነው የሚባል የገንዘብ አቅርቦት እስካሁን በውል አልተገኘም፡፡ አሁን ከተጠቀሰው 4.5 ሚሊዬን ተረጅ በተጨማሪ የእነዚህ ዜጎች ሕይወት ትኩረትን ይሻል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን የተረጅው ቁጥር 12.4 ሚሊዬንና ከዚያም በላይ ነው፡፡ የአንድነት አባላት ፣ደጋፊዎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ወገንን ከመታደግ በላይ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ የለምና በወገናችን ላይ እያንዣበበ ያለው ዕልቂት ለመቋቋም እጅ ለዕጅ ተያይዘን ልንነሳ ይገባናል፡፡

ሐምሌ 14 2ዐዐ3 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 21, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.