ኢሳትን በመደገፍ ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንታደግ፣

ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) የተሰጠ መግለጫ፣ጥር 7 ቀን 2003 ዓ/ም —

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ሥራ ከጀመረ ካለፈው የሚያዚያ ወር 2002 ዓም ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ያጋጠሙትን ችግር እየተቋቋመ በርካታ ፕሮግራሞችን በቀጥታ ወደ ሀገር ቤት በማስተላለፍ ከፍተኛ የህዝብ ቀልብ ለመሳብ በቅቷል፣ ይህን ሥራውን ዛሬም ቀጥሏል።

ኢሳትን ከምስረታው ጀምሮ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ያደረሱት ጥቂት ሀገርና ወገን ወዳድ የሆኑ ግለሰቦች ከግል ኪሳቸው እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት ያሉ ወገኖች በኢሳት ስም በዓላትን በማዘጋጀት በሰበሰቡት ገንዘብ ነበር።

ሆኖም ኢሳት አሁን ባለበት ደረጃ ወደ ሀገር ቤት የሚሰጠውን አግልግሎት እንዲቀጥልና በውጭ ሀገርም የቴሌቪዥን አገልግሎት ስርጭት ለመጀመር ያለውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በላይ ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ የማሰባሰብ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል።: ስለዚህ ከጥር 7 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚቆይ የ 1 (አንድ) ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ ዘመቻ ጀምረናል።
በዚህ ዘመቻ የሚገኝ ገንዘብ በቅደም ተከተል በሶስት ዋና ዋና ደረጃዎች በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል።

  • የመጀመሪያ ደረጃ፣ ዘመቻው የገንዘብ መሰብሰብ ዕቅድ 50% ሲሟላ፣ አሁን ወደ ኢትዮጵያ፣ መላው አፍሪካ፣ አውስትራሊያና መካከለኛው ምስራቅ ለምናስተላልፍበት ሳተላይት፣ እንዲሁም በአምስተርዳም፣ በለንደን፣ በዋሽንግተን ዲሲ ያሉትን ስቱዲዮች እና በዓለም ላይ ላሉን ጋዜጠኞች የዓመት ወጭ መሸፈኛ ይውላል።
  • የሁለተኛ ደረጃ፣ ዘመቻው የገንዘብ መሰብሰብ ዕቅድ 70% ሲደርስ፣ ለመጀመሪያ ደረጃ ከወጣው 50% የሚቀረው 20% ወደ ኢትዮጵያ ለምናስተላልፈው ፕሮግራም ተጨማሪ የኬዩ ባንድ ሳተላይት በመከራየት የስርጭት ሽፋናችንን በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ የሚያስችለን የአመት ወጭ የሚሸፍን ይሆናል።
  • የሦስተኛ ደረጃ፣ የዘመቻው የገንዘብ ማሰባሰብ ዕቅድ 100% ሲሟላ፣ ቀሪው 30% በአውሮፓና፣ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ ኢሳትን ለማስተላለፍ የሚያስፈልገውን ሁለት ሳተላይቶችና ተጓዳኝ አገልግሎቶች መከራየት የሚያስችለን የዓመት ወጭ የሚሸፍን ይሆናል።

ሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝቧ አሁን ከምንገኝበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመድረስ አስተዋጽዕዖ ከአደረጉ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ህዝቧ ስለ ሀገሩም ሆነ ስለ ራሱ የሚሰማውን በነፃነት የሚገልጽበት፣ ነፃና ሚዛናዊ መረጃ የሚያገኝበት አስተማማኝ ምንጭ አለመኖሩ ነው። ኢሳት ለዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት በኢዲቶርያል ፓሊሲው ላይ ካስቀመጣቸው ዋና ዋና መርሆዎች መካከል ‘ወገናዊነቴ ለእውነት እና ለእውነት ብቻ ነው’ የሚለውን መርህ በጉልህ አስቀምጦታል። ኢሳት ይህንን እምነቱን በወረቀት ላይ ያስቀመጠው ብቻ ሳይሆን በአስተላለፋቸው ፕሮግራሞች በተግባርም ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። እነዚህ የኢሳት ፕሮግራሞች በሀገራችን ህዝብ ዘንድ የቀሰቀሱት ወደር የማይገኝለት የነፃነት እና የተስፋ መንፈስ በገንዘብ እጥረት ቢዳከም ወይም ቢያቋርጥ ኢሳትን በጉጉት ለሚጠብቀው እና በነጻ መረጃ ጨለማ ውስጥ እንዲኖር ለተገደደው ወገናችን አሳዛኝ መርዶ ይሆናል:: ይህንንም ለሚያስበው፣ የህሊና እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ስለዚህም፣ በዚህ የሁለት ወራት የገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ ወቅት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለኢሳት የሚረዳው ገንዘብ እውነተኛ መረጃ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ የነፃነት ተስፋ በአስተማማኝ መሰረት ላይ የሚያቆም በመሆኑ፣ ለዚህ ዓይነት ታሪካዊ ለውጥ በሚያደርጉት የገንዘብ ዕርዳታ ኢትዮጵያንና ህዝቧን በመታደግ ሊኮሩበት ይገባል እንላለን። ዛሬ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተገድቦ የለውጥ ማነቆ በሆነበት ሁኔታ የኢሳትን ፕሮግራሞች በመላው ኢትዮጵያና የአለም ክፍሎች ለሚገኙ ወገኖቻችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማዳረስ ከምናደረገው ጥረት የበለጠ ሀገር እና ወገንን የሚታደጉበት ጥረት ስለሌለ የሚቻልዎትን ዕርዳታ እንዲያደርጉል ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ኢሳትን መርዳት በየቤትዎ የሚደርስ የቴሌቭዥን ስርጭት ከማግኘት በላይ የላቀ ትርጉም አለው።

ኢሳትን መደገፍ ባስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘውን ሀገራችንና ወገናችንን መታደግ ነው።

Read also: ESAT Campaign Online Brochure (amharic)

የኢሳት የነጻነት መንፈስ ለዘላላም ይኑር!!!
ኢሳት የኢትዮጵያዊያን ልሳን ነው!!!

ኢሳት፣ www.ethsat.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 15, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.