ኢሕአዴግ፣ መተካካትና ባለጫማዎቹ

(ግርማ ደገፋ ገዳ)
ከሉሳካ (ዛምቢያ) ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ይተላለፍ የነበረውን የኤ.ኤን.ሲ. ራዲዮ ጣቢያ፣ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጃም ያደርገው ነበር። ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ሆኖ በደቡብ አፍሪካ መወለድ፣ በገዥዎቹ ነጮች ዓይን ወንጀል ስለነበር፤ ዘረኛው የነጮች መንግሥት፣ አውሬ መሳይ ገዳይ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን በጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን አንጀት ላይ ነድቷል። ሸቀጥ የመግዛት መብታቸው በመስኮት ብቻ የነበረው ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን፣ በድንገት ወይም ሆን ብለው ሱቅ ውስጥ በበር ከገቡ፤ ‘ሱቁን አረከሱት’ ተብለው ይገደሉ ነበር። በገዛ ሀገራቸው፣ የመታወቂያ ካርድ በኪሳቸው ይዘው ሲገኙ ብቻ ነበር ነጮች የሚኖሩበትን ከተማ ለመጎብኘት የሚችሉ ሕጋዊ ሰዎች መሆናቸው የሚረጋገጥላቸው። ነጮቹን የማይመለከተውን የመታወቂያ ሕግ ያላሟላ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ፣ በደቂቃዎች ወደ እስር ቤት እንደሚጋዝ ምንም ጭቅጭቅ የለም። የመታወቂያው ሕግ፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ከነጮች ከተማ ገፍትሮ ማውጣት በመቻሉ በትናንሽና ችምችም ባሉ መንደሮች እንዲኖሩ ተገደዋል።
[Click here to read the whole article in PDF]

ያ ሁሉ ኢ─ሰብዓዊ ጭካኔ ሲካሄድ፣ የምእራብ ኃያላን መንግሥታት (በተለይም አሜሪካና እንግሊዝ) የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የነጻነት ትግል ሆን ብለው ከኮሚኒዝምና ከሽብርተኝነት ጋር መድበውት ስለነበር፤ እውቅና አልሰጡትም። በቆዳ የመመሳሰል ልክፍት፣ የምእራባውያን መንግሥታት የደቡብ አፍሪካን የነጮችን መንግሥት እንዲደግፉ ያስቻላቸው ቢሆንም፤ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች፣ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ተራ ነጭ ዜጎች፣ ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ፖለቲከኞችና የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪዎች (አምነስቲ ኢንተርናሽናል የለበትም)፣ ዘረኛውን የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን በኅብረትም ባይሆን ይቃወሙ ነበር። የዘረኞቹ መንደርደሪያ ከሆኑት ሎንዶንና አምስተርዳም ሆነው የነጻነት ትግሉ አካል በመሆን የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ ነጮችም ነበሩ። የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግሥት ይከተለው የነበረውን የዘር መድልኦ በመቃወም፣ በታላላቅ ከተማዎች ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። ኤ.ኤን.ሲም የራሱን ትግል ሌሎች እንዲታገሉለት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። መከራውን ሲዝቅ የነበረውን ጥቁር የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት፣ አራት ስልቶችን ነድፎ በሥራ ላይ አውሏል። እነሱም፤ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ፣ የውስጥ ህቡእ ትግል፣ የሽምቅ ውጊያ እና ለመንግሥት አለመገዛት ናቸው (ኢንዲፔንደንት ሌንስ፣ ሃቭ ዩ ሂርድ ፍሮም ጆሃንስበርግ)። በኢትዮጵያስ?

ኢትዮጵያ ውስጥ የመሰብሰብ ነጻነት የለም። ሕዝብ ብሶቱን ለመግለጽ አደባባይ ሊወጣ አይችልም። አደባባይ ላይ ተሰባስቦ መገኘት ወንጀል ሆኗል። እሱን የጣሰ፣ ፈሪው የኢሕአዴግ መንግሥት በጥይት ይደበድበዋል። ግን ኢሕአዴግ የራሱን ደጋፊዎች አሰልፎ ሲፎክር ከልካይ የለውም። እንዲያ አይነቱ እገዳና ፍቃድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይደረግ ከነበረው የዘር መድልኦ በምን ይለያል? በቆዳ ቀለም ብቻ። እሱም ቢሆን የጨቋኞቹ ቆዳ ነው የተለያየው እንጂ ተበዳዮቹ አንድ ናቸው። ኢትዮጵያዊው የራሴ የሚለው መሬት የለውም። የራሴ የሚለው ጣራና ግድግዳ ተፈቅዶለታል፤ ወለልን አይጨምርም። ከተማው ሁሉ የጨቋኞች ገነት ሆኗል። ደቡብ አፍሪካውያን በገዛ ሀገራቸው ‘አሸባሪና ኮሚኒስት’ እየተባሉ ረጅም ዓመታት እስር ቤት ይማቅቁት እንደነበር ሁሉ፤ ኢትዮጵያውያንም ‘አሸባሪ’ ተብለው ረጅም እስር መሸለም ጀምረዋል። ‘መብቴን’ ብሎ ለመከራከር የሚሞክረውን ዜጋ የሚቀጠቅጡ ወታደሮችም፣ አውሬ በሚመሳስሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ ሆነው እየሸለሉ ነው። ታላላቅ መንግሥታትም ዘረኛውን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ይደገፉ በነበረው ስልት፣ ኢሕአዴግን ‘ከጎንህ ነን’ ማለት ቀጥለዋል። በመንግሥት ደረጃ ያለው ፖሊሲ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግበት እገዛቸውን በሰብአዊና ልማት ሽፋን እያጎረፉት ነው።

ይህ ድርጊት፣ ደቡብ አፍሪካን በግፍ ይገዙ የነበሩ የአፓርታይት ፖሊሲ አራማጆች፣ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች 2 ላይ ያካሂዱ ከነበረው ሰቆቃና ገናና መንግሥታትም ከፈጸሙት በደል በምንም አይለይም። በእርግጥ፣ የዛሬው የኢትዮጵያ ገዥዎች ከእንግሊዝና ከሆላንድ አልመጡም፤ ‘እስኪበቃቸው ድረስ የመናዊና ሶማሊያዊ ለመሆን ተጣጥረዋል’ መባሉ ጸሐይ የሞቀው ነው።

አንዳንዴ ሰዎች ‘መለስ ዜናዊ ለምን አይሄድም!’ ሲሉ ይገርመኛል። ወዴት? ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ 2004 ዓ.ም ድረስ ሥልጣን ላይ ያለ ሰው ወዴት ይሂድ? በዚህ ሁሉ የሥልጣን ዘመን የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ የተገረፉና የተሰቃዩ ዜጎች በየትም አቅጣጫ ባለቡት ሁኔታ፤ እንዴት ነው አንድ አምባገነን መሪ መሄጃ ሊኖረው የሚችለው? የአንድ ዜጋ ሕይወትን ካስጠፋ በኋላ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም። ባለፉት ሃያ ዓመታት አዲስ አበባ ላይ ተሞክረው የነበሩት ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅቃሴዎችን ኢሕአዴግ ያጨናገፈው፣ ዜጎችን በመትረየስ እየቆላ ነው። ደረት፣ ደረታቸውን በጥይት እየሸነቆረ ነው። ባዶ እጃቸውን አደባባይ ለወጡ ወጣቶች፣ ‘ለውኃና ለጎማ ጥይት አልሰለጠንም’ ብሎ ብረት ለበስ ነው ያዘዘላቸው። በሀገሪቱ ዙሪያ የተካሄዱት ሰላማዊ የመብት ትግል ትንቅንቆች ወደ እልቂት ተገፍትረው የተጨመሩት በዚህ መንግሥት ነው። ያለቀው ሰላማዊ ዜጋ ቁጥርም የትና የት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በሥልጣን ላይ የነበረውና አሁንም ያለው አንድ ሰው ነው። እሱም ብጻይ መለስ ዜናዊ ይባላል። ወዴትም መሄድ አልቻለም። ፈልጎ አይመስለኝም። በዚያ ጭንቀት ሊሆን ይችላል ከፈንጆች ጋር ሲሆን ግማሽ ፊቱን በሁለት እጁ ሲሸፍን የሚታየው። ፓርላማ ውስጥ ከድንፋታ በቀር ያንን አይታችኋል? እኔ በበኩሌ አላየሁም። ወይም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለኔ የሚያሳየው ፓርላማ ሌላ ሊሆን ይችላል። አላውቅም።

አንድ በሕዝብ ያልተመረጠ መሪ ስልጣን ላይ ለረጅም ዘመን መጣበቁ አንዱ ጥቅም በሥልጣን ዘመኑ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ለመጠየቅ አመቺ መሆኑ ስለሆነ፤ በጠፋው ነፍስ፣ በቆሰለው ገላ፣ በታሰረው ዜጋ፣ በባሕር ጉዳይ፣ በመሬት፣ በአየሩ፣ በዛፉ፣ በወንዙና በመሳሰሉት ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ እንደ መለስ ዜናዊ የሚጠየቅ የለም። ተጠያቂነቱ በሚመጣ እለት፣ እንደዛሬው ለአምስት መቶ ምናም ሰዎች ጀርባ ሰጥቶ፤ የአፈ─ጉባኤ ጠረጴዛ ላይ ለተጣበቁ ሁለት የቻይና አሻንጉሊት መሰል ሰዎች ላይ በማፍጠጥ መሸለል የለም። የፓርላማ ውስጥ ድንፋታና ምሁርነት፣ ሥልጣኑን ያጡ እለት ብን ይላል። ሰላማዊ ዜጋን ለማስጨፍጨፍ ትእዛዝ በሰጠ ማግስት ማለቂያው በሚናፍቀው የስብሰባ ሰበብ ወደ አውሮፓ መብረር ዘላለማዊ ሊሆን አይችልም። የሆነላቸውም የሉም። የፈለጉና አቅደው የነበሩ የሉም ማለት ግን አይቻልም። አንገታቸውን ሲጨመቁ ተፍተውታል።

የሰሞኑ ማደናገሪያ ደግሞ፣ ‘መለስ ዜናዊ ያሁኑን ዙር ሥልጣን ከጨረሰ በኋላ፤ ሊተካው የሚችለው ቴዎድሮስ አድሃኖም ወይም አርከበ እቑባይ ነው’ የሚባለው ነው። አዎን፤ እነአርከበ ሊተኩት ይችላሉ። ስልጣን በመተካካት ያለው በሶሻሊስትና በወንጀለኛ መሪዎች ሀገር እንጂ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉት ውስጥ ባለመሆኑ፤ ‘መተካካትን’ ልናየው እንችላለን። ሊገርመን የሚገባው እነአርከበ ባያደርጉት ይሆናል፤ አንዱ በአንዱ ጫማ ውስጥ ዘሎ መግባቱ አይደለም። ኢሕአዴግ ዜጎችን በመግደልና ሀገር በመዝረፍ ስለሆኑ ረጅም ዘመኑን ያጋመሰው፣ መተካካቱ ገዳዮችንና ዘራፊዎችን ለመከላከል ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ፤ ገዳዮች ገዳዮችን እንደሚተኩ በቻይና፣ በኩባና በሰሜን ኮሪያ የታየ ነው። ከሱ ይልቅ ‘መለስ ዜናዊ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ያካተተ ብሔራዊ የጥምር መንግሥት ሊያቋቁም ይችላል’ እያሉ ተቃዋሚውን ለማዘናጋት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙት ናቸው የሚያስገርሙት።

ኢሕአዴግ ደጋግሞ በግልጽ ተናግሯል፤ በምንም ተአምር ‘ሥልጣን መጋራት’ የሚባል ስልት በኢሕአዴግ ዙሪያ የለም። ‘እኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊያን ነን፤ ከኒዮ─ሊበራል ዴሞክራቶች ጋር በምንም ተአምር አንድ ላይ ሆነን አንሰራም!’ ብሏል። ይልቁንም የደቡብ አፍሪካው ኤ.ኤን.ሲ ይጠቀምበት የነበረውን የትግል ስልት ማጠናከር ነው እንጂ፤ የጣምራ መንግሥት ለመመስረት እቅድ ከሌለው መንግሥት የሚወረውረውን ፕሮፓጋንዳ አምኖ ማላመጥ፤ ማዘናጋትና የመዘናጋት ወጥመድ ውስጥ ዘለው እየገቡ መጮኽ ነው የሚሆነው። ያ ዋጋ የለውም። ሁሉም የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፍልስፍናን የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ ኢሕአዴግ አብሯቸው ይሰራል? …..ደርግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ሕወሓት መች አብረው ሰሩ? ሁሉም የሶሻሊዝም ፖለቲካ ተከታዮች ነበሩ። አንገት ለአንገት ተያይዘው መገዳደላቸው ነው ከየታሪክ መጽሐፍ ላይ የተጻፈው።

ኢሕአዴግ፣ እንደ አጎቱ የአፓርታይድ መንግሥት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ትኩሳቶችን እየለካ፣ መጪው የኢሕአዴግ ዘመን ምን ሊመስል እንደሚችል መተንበይ የማይችል ግዙፍ ሳይሆን ግብዝ ድርጅት ነው። የሕዝብን ኡኡታ ማስታገስ የሚችለውና የቻለው በጥላቻ የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝና በመትረየስ ነው። ስለአረብ ንቅናቄ ሲጠየቅ ‘እኛ በ1980ዎቹ ጨርሰነዋል’ ነው ያለው። ያንን ያለው የጣምራ መንግሥት ለመስረት እቅድ ስላለው ሳይሆን፣ እንደ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት፣ ረጅም የሥልጣን ሕይወት የተጠናወተው ድርጅት በመሆኑ፣ ‘መተካካት’ በሚባለው የማሌሊት ኮሚኒስቶች የወንጀለኞች ስልት ራሱን ለመከለል ነው። ሀገርን ከኢሕአዴግ በተሻለ ሊያስተዳድር የሚችል በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ባለበት ሀገር፤ የአንድ ቡድን ሽማግሌዎች ለጎልማሶች፣ ጎልማሶችም ለታዳጊዎች፣ ብሔራዊ ሥልጣኑን እንደ ዱላ እየተቀባበሉ ከፍትህ ሲሸሹ የማየቱ ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ የግድ መቆም አለበት። ‘መተካካት’ መደበቂያ ዋሻቸው ሊሆን አይገባም። መቼም ይሁን መች ወደ ዋሻው የሚያሮጣቸው የፈላጭ ቆራጭነት መንገድ መዘጋትና ዋሻውም መደርመስ አለበት። ሥልጣን ከአባት ወደ ልጅ ሲወራረድባት መከራዋን ያያች ሀገር፣ ሌላ የሚተካካ የኢሕአዴግ አጼዎች ትውልድ ማየት አትፈልግም። የሚተካኩበት ቦታ ሄደው ይሰካኩ እንጂ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰካኩ እጁን አጣምሮ ሊያያቸው የሚችል ዜጋ ለመፈጠሩ ማረጋገጫ ለኢሕአዴግ የሰጠው ማንም የለም። ማነው ጭቁን ሽማግሌ ጭቆናውን ለሌላ ተጨቋኝ ጎልማሳ፣ ጭቁን ጎልማሳውም ለሌላ ተጨቋኝ ታዳጊ፣ ጭቆናን እንደ ውርስ ያስተላልፍ ያለው? ለኔ የመተካካት ትርጉሙ ያ ነው።

አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ በአፍቃሪ ኢሕአዴግ ስም ‘አላቢ ኢሕአዴግ’ የሆኑ ‘ገለልተኛ ነን’ ባይ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ዜጋ የኢሕአዴግን ሕግ አክብሮ እንዲኖር ይመክራሉ። ልጁን የመንግሥት ታጣቂ የገደለበት ቤተሰብ፣ ‘ኢሕአዴግን አክብሮ ዝም ብሎ ይቀመጥ’ ማለታቸው ነው። ‘መሬቱን ሲቀማ፣ የባንክ አካውንቱ ሲዘጋ’ ዝም ይበል፤ የነሱ ‘ዝም ይበል’ ማለቂያም የለውም። እንደዚያ ብለው የሚመክሩት ሰዎች፣ አንዱ የቤተሰባቸው አባል በግፍ ተገድሎ አይደለም፣ ከጫማ መደብር የገዙትን ጫማ ከሁለት ሳምንት በኋላ ‘አልተስማማኝም’ ብለው ከገዙበት መደብር የመመለስ የደምበኝነት መብት ያላቸው ናቸው። ብዙ መብቶች ባሉበት ሀገር ሆነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለገነቡት ኩሽናቸውና ያለቀረጥ ላስገቡት የሲሚንቶ ማቡኪያ ብለው፣ የኢሕአዴግን ችግር ሁሉ በሕዝብ ላይ ይደፈድፋሉ። ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ከቤት ውጭ በአደባባይ የመሰብሰብ መብት አለ ወይ?’ ….. ‘ለምንድ ነው ኢሕአዴግን ከቤት ውጭ የመሰብሰብ መብት የሚያቃዠው?’ ለዚህ መሰሉ ጥያቄ መልስ መስጠት አይፈልጉም። ለነሱ ኩሽናና ማቡኪያ ሲሆን፣ ሃያ ዓመት አጭር ናት፤ ዲሞክራሲም የሂደት ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም መትረየስ የተርከፈከፈበት ዜጋ ‘የኢሕአዴግን ሕግ አክብሮ ዝም ይበል’ ይላሉ። በነሱ ኩሽናዊ አመለካከት፣ የኢትዮጵያዊያን ነፍስ ደረጃ ከነሱ ኩሽናና ማቡኪያ በታች ናት። ዛሬ ብቻ አይደለም፤ የዛሬ ሃያ ዓመት፣ አስራ አምስት ዓመት፣ አስር ዓመት፣ አምስት ዓመትም እዚያው ናት። ከኩሽናና ከማቡኪያ ማስበለጥ አይደለም እኩል እንኳ አድርገዋት አያውቁም።

ኩሽና ውስጥ በመከራ መሰብሰብ ይቻላል፤ አደባባይ አይቻልም። የተወሰኑ ሰዎች የፕሬስ ፈቃድ ያወጣሉ፤ የተወሰኑ አይችሉም። ሚሊዮነር እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው አሉ፤ ያልተፈቀደላቸው ሞልተዋል። የራዲዮ ፕሮግራም የሚያሰራጩ አሉ፤ የተከለከሉ በሽበሽ ናቸው። ጳጳስ ለመሆን ኢሕአዴግ መሆን ያስፈልጋል። ‘ኢሕአዴግ ያልሆነ ቄስ ቤተክርስትያን አያስቀድስም’ እየተባለ ነው። የእስልምና ጉባኤ መሪ ለመሆን ኢሕአዴግ መሆን ነው መስፈርቱ። ሌላው ቀርቶ በየከተማው የሚገኙትን የኮቦሎት ድንጋይ ሥራዎች ለመሥራት የኢሕአዴግ ክንድ መሆን ያስፈልጋል። ኢሕአዴግ ካልሆኑ ምንም ነገር አይቻልም። ከአምስት ሚሊዮን የኢሕአዴግ አባላት ውስጥ ወህኒ ቤት የተመደቡ፣ በግፍ ወህኒ የወረደን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባልን ክፉኛ የሚደበድቡ እንዳሉ እየተሰማ ነው። ኢሕአዴግን እንዲያ ዓይነት ሁኔታ ነው የሚያስደስተው፤ የሰው ስቃይ ያስፈነድቀዋል። ብዙ ዓመት የፈረዱበትን አንድ ዜጋ፣ ያ ሁሉ ቁልል ፍርድ አላረካ ብሏቸው፤ የበግ ሙክት የሚያካክሉት ቅማሎችና የጉማሬ ግልገል የሚመሳስሉት አይጦች አንሰው፤ እስር ቤት ውስጥ ባላቸው አባል ያስቀጠቅጡታል። ብሔራዊ እፍረትና ውርደት ሳይሰማው የሀገሪቱን ፓርላማ ወደ ኢሕአዴግ ምክር ቤት ከለወጠ ድርጅት፣ የጥምር መንግሥት ምስረታን ፕሮፓጋንዳ ለምትሸምቱ ያ ትምህርት ካልሆናችሁ፤ በዚህ ዘመን ትምህርት የሚሆናችሁ ዶላር አስክሮት የራሱን ዜጋና ሀገር ያረከሰ ሰው ሠራሽ ድርጅት ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ኢሕአዴግ በሺህ ዘመን አንዴ ብቅ ብሎ፣ ሀገር ምድሩን አናጭቶ ወደ ጎሬው በሚሮጥ አውሬ ነው የሚመሰለው። የበረከት ስምኦን መጽሐፍ ላይ ያለው ከከፍተኛ ናዳ ለማምለጥ ባለ በሌለ ፍጥነት የሚሮጠውን ፍጡር ሊመስል አይችልም። እንዲያ’ማ ቢሆን ኖሮ ሁሉም በረዳው። ተጨማሪ ሳንባና ኦክስጂን በሆነለት። ናዳውን በተከላከለለት። የባለናዳውን እጆች በቆረጠለት።

አስተማሪዎች፣ የትናንሽ ከተማ ከንቲባዎች፣ የቀበሌ ሊቀመናብርት፣ ተራ የፖሊስ አባላት፣ የመንግሥት ሰራተኞች፣ ጦር ሜዳ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ለዓመታት የተቀመጡ ወታደሮች እና በአጠቃላይ ትናንሽ ባለስልጣናት፤ በተለያዩ ውንጀላዎች ሲዋከቡ፤ ዋና ዋናዎቹ የኢሕአዴግ ሰዎች ራሳቸው ባወጡት ሕግ ላይ ቆመው ግማሾቹ ሲደንሱ፣ ግማሾቹ የደናሾቹ እግር ሥር ቶሮምቦል ሲነፉ ነው ጊዜው ያለፈው። ሙስናው፣ የከተማው መሬት ዝርፊያና የቀረጡ መላቅጥ ማጣት የሚላከከው በሚጢጢ ባለሥልጣናት ላይ ነው። ውሉ የማይታወቅ ብሔራዊ ክፋት ለዓመታት በሕዝብ ላይ ሲካሄድ፣ እነዚያ ዓይናቸውን በመርዝ ያጠቡ ባለጫማዎች፤ ‘ኢሕአዴግ ምንም ዓይነት መድልኦ አያደርግም! አላደረገምም!’ ብለው ይከራከራሉ። ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ከአፓርታይድ ጋር አይገናኝም’ ባዮች ናቸው። በነሱ ትንተና፣ የዘር መድልኦ ነጮች ብቻ ሲፈጽሙት ነው ‘መድልኦ’ የሚባለው። እንዲያ’ማ ከሆነ ምድረ ኢሕአዴግ ዓይኑ ሰማያዊ፣ ጸጉሩ ወርቅማ፣ አፍንጫው ሰልካካ፣ ቁመቱ ዘለግ ያለና ጆሮው ሰፋፊ እንኪሆን ድረስ ሕዝብ ሊጠብቅ ነው።

እስቲ ከገና በዓል በኋላ ሲያትል ከተማ ከሚገኝ ከአንድ የጫማ መደብር በር ላይ ቁሙና ቃኙ፤ በሬዲዮ ልቡ እስኪጠፋ ኢሕአዴግን ደግፎ የሚከራከርን አንድ ሰው፣ የጫማ ማሰሪያውን ነክሶ ሲያለቅስ ታዩታላችሁ። አንድ ቀን ኢሕአዴግ ኩሽናውን ሲሞጨልፈው፣ ሌላ ነገር ሲያወራ እንደሚሰማ እርግጠኛ ነኝ። ያን ጊዜ ‘ዲሞክራሲ የሂደት ጉዳይ ነው’ የሚባለው አባባል ገደል ይገባል። ሲሚንቶ ማቡኪያ በእጃቸው ሲገባ ብቻ ነው ‘ዲሞክራሲ የሂደት ጉዳይ ነው’ ካርድን ሕዝቡ ላይ የሚረጩት። ሲቀሙ፣ ካርዱ አይሰራም፤ ባትሪው ያልቃል።

ታዝባችሁ ከሆነ የኢሕአዴግ ሰዎች፤ ቼጉ ቬራ፣ ሆች ሚኒህ አልያም ፊደል ካትሮ ለመሆን ይከጃጅላቸዋል። እንደነዚያ አብዮተኞች የራሳቸውን አሻራ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ደፍተው መሄድ አስጎምዥቷቸዋል። ባለጫማዎቹም ያንን ያስተጋቡላቸዋል። እነ ቼጉ ቬራ ሃብታም አይደሉም። የተዋጉለትን ዓላማ ሸጠው በገበሬው ነፍስ ለራሳቸው ቪላ እያነጹ አላከራዩም። የዶላር መስመር ዘርግተው ወደ ውጭ አልነዱትም። የየሀገራቸውን ጥቅም አሳልፈው አልሰጡም። የታዋቂነታቸውን ዘመን በመረረ ስቃይ ነው ያሳለፉት። አብዮትን ከዳር እስከ ዳር ለማስፈን ሞክረዋል። በሌላ ጎራ የነበረውን ታጋይ ጨፍጭፈዋል። ግን፣ የጉቦኝነት ኢንዱስትሪን አላስፋፉም። ሚስቶቻቸው፣ ባሎቻቸውን እየተመኩ የሁሉም ነገር የበላይ አልሆኑም። ሀገር እስኪስቅ ድረስ ‘የጉቦ እናት’ የምትባል አሳፋሪ የትዳር ጓደኛ አልነበራቸውም። እንዲያ ዓይነት ሁኔታ ቢገጥማቸው፣ ሕዝብ እያየ ሰማንያቸውን አብዮት አደባባይ ላይ ሊሸረካክቱ የሚችሉ ባለሙሉ ወኔ አብዮታዊያን ናቸው። ለብሔራዊ ቅሌት ቦታ አይሰጡም።

በመጨረሻም፤ አንድ ቀን ከዘር መድልኦ የነጻች ኢትዮጵያ መመስረቷ አይቀርም። ፍትህን እንደ ቆንጆ አበባ ቀጥፎና አፍንጫ’ጋ አስጠግቶ መዓዛዋን ማጣጣም አለ። ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዝዘው የነጻነት ዳንስ ይደንሳሉ። መዝሙራቸውም ከሰሜን ደቡብ፣ ከምስራቅ ምእራብ ይስተጋባል። ያ የሚቀር አይደለም። ከኢሕአዴግ ማክተም በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጹም ሊከለከሉ የማይችሉ መብቶች እንደ አሸን ይፈላሉ። ራዲዮ የማይታፈንበት፣ ቴሌቪዥን በሲግናል የማይጠለዝበት፣ ጋዜጠኛ የማይሰቃይበት፣ ፖለቲከኛ የማይታሰርበትና የባለሥልጣናት ሌቦች የሌሉበት ሥርዓት ይሰፍናል። የባልና ሚስት ኮርፖሬሽን ያልሆነ መንግስት ይመሰረታል። ዜጎች ሰው ስለመሆናቸው ዘራቸው ጠንቅ የማይሆንበት፣ በገዛ ሀገራቸው ደረታቸውን ነፍተው የሚሄዱበት ሁኔታ ይመጣል። ባለጫማዎችም ለማቡኪያቸው እና የዘይት ወፍጯቸው ብለው የመሪዎቻቸውን ጥፋቶች የማይደብቁበት ሥርዓት ይዘረጋል። ኢትዮጵያ፤ በውስጧ የሚኖሩ ነዋሪዎቿ ሀብት መሆኗ ይረጋገጣል። ነዋሪው በሙሉ፤ ከኢትዮጵያ ወንዞች፣ ሜዳዎች፣ ተራራዎች፣ ከአየሯ፣ ከጸሐይዋ፣ ከደኑ፣ ከበረሃው፣ ከእርሻው፣ ከኃይቁና ከደመናው ድርሻ እንዳይኖረው የሚያግድ ምንም ዓይነት ሕግ አይኖርም። በጋምቤላ ጎጆዎች ላይ እሳት የሚለኩሱ ጣቶች፣ በዜጋው ላይ ኮምባይነር የሚነዱ ክንዶች ዘመናቸው ያከትማል። ያንን ተስፋ እናደርጋለን።

ደርዘን ድሉን ሁሉም ላያይና ላይቀምስ ይችላል። 30 ዓመት በስደት ሆነው የኤ.ኤን.ሲን ትግል ይመሩ የነበሩት ኦሊቭር ታምቦ፣ ከስደት ወደ ሀገራቸው በድል ቢመለሱም፤ ይታገሉለት ከነበረው የዴሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ ለሆነው ‘የመምረጥ መብት’ ሳይታደሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የፀረ─አፓርታይድ ታጋዩ ስቲቨን ቢኮ’ም በተሟሟቀው ትግል ወቅት በዘረኛው የነጮች መንግሥት ተይዞ እስር ቤት ተገድሏል። “ውሻና መርዝ ይዘው ይከታተሉናል። ምን ለመሆን? …..እግዚአብሄር በፈጠራቸው የሃይቅ ዳርቻዎች ጭምር እንዳንዝናና!” ያሉት አቡነ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ታምቦ ኢምቤኬ፣ ዋልተር ሲሲሉ እና ሌሎችም ሕያው ምስክር ለመሆን በቅተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የመብት ትግል ይረዝም ይሆናል እንጂ የተጨቆነ፣ የተረሳ፣ የተበደለና የተገፋ ያሸንፋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 28, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.