ኢህአዴግ ከ5 የአዲስ አበባ ሃላፊዎች 3ቱን አባረረ

ከስልጣን የሚወርዱት፤ ምክትል ከንቲባው አቶ ከፍያለው አዘዘ እና ሁለት የከንቲባው አማካሪዎች ናቸው።
“የአዲስ አበባ ኮር” ተብሎ የሚታወቀው የኢህአዴግ አመራር ቡድን፤ የከተማዋን ከንቲባና ስራአስኪያጅን ጨምሮ አምስት አባላትን ያካተተ ሲሆን፤ ሰሞኑን በተካሄደ ግምገማ ሶስቱ አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ እንደተወሰነ ምንጮች ገለፁ።

በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ በተጀመረው ግምገማ ከሃላፊነት እንዲነሱ የተወሰነባቸው የአመራር አባላት፤ “አላግባብ የቡድን ትስስር የመፍጠር (የኔትዎርኪንግ)” ጥፋት ፈፅመዋል የሚል ግምገማ ቀርቦባቸዋል ተብሏል።

አምስቱ የኢህአዴግ የአዲስ አበባ “ኮር አመራሮች”፤ በከተማዋ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛውን የስልጣን ደረጃ የያዙ ሲሆን፤ ከሃላፊነት እንዲነሱ ከተወሰነባቸው ባለስልጣናት መካከል አንዱ፤ ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘ ናቸው። ምክትል ከንቲባው፤ ከከተማ የበላይ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ አላግባብ የቡድን ትስስር የሚፈጥር አሰራር (ኔትዎርኪንግ) ተከትለዋው የሚል ግምገማ እንደተሰነዘረባቸው ምንጮቹ ጠቅሰው፤ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተወሰነባቸው በአቅም ማነስም ጭምር ነው የሚል ምክንያት እንደቀረበ ተናግረዋል።

ከከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ፤ በግል ትውውቅና ቅርበት ሰዎችን እየለዩ፤ እንዲሁም ታዛዥ የሚሆኑላቸውን ሰዎች እየመረጡ የሃላፊነት ቦታ ላይ በማስቀመጥ፤ የትስስር አሰራር (ኔትዎርኪንግ) ፈጥረዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል – ሶስቱ ሃላፊዎች።

የአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ልዑል ሰገድ ይፍሩ፤ የከንቲባው የሕዝብ ግንኙነትና የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ ሲሆኑ፤ “በኔትዎርኪንግ እና በአቅም ማነስ ተገምግመው ከሃላፊነት እንዲነሱ ተወስኖባቸዋል” ብለዋል – ምንጮቹ። በአዲስ አበባ የኢህአዴግ መዋቅር፤ የአባላትና የሥልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሊድ አሕመድ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሃሳቢነት እንደተነሱ ምንጮቹ ገልፀዋል። አቶ ካሊድ፤ የከንቲባው የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ናቸው፡፡

በዚህ ሳምንት የተጀመረው የ”ኮር አመራር ግምገማ” እየተጠናቀቀ እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰው፤ የመጪው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

(የላይኛው ዜና ዘገባ ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው)

E.M.F – ምክትል የአዲስ አበባ ከንቲባ፤ አቶ ከፍያለው አዘዘ ከአስር አመታት በፊት፤ ከደርግ የመጨረሻዎቹ አመታት ጀምሮ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ፤ የኢህአዴግ አንደኛው ቡድን አባል በሆነው ብአዴን ውስጥ አባል በመሆን፤ በስልጣን እያደጉ መምጣታቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ ኔትዎርክ ፈጥረዋል በሚል ከስልጣናቸው ሲሰናበቱ መውደቂያቸው ወዴት ሊሆን እንደሚችል አልታወቀም።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 16, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.