ኢህአዴግ ህዝባዊ ድጋፍ የለውም! ዶ/ር መረራ ጉዲና

የኢህአዴግ መንግስት ህዝባዊ ድጋፍና መሰረት የሌለውና ዜጉችን በጉልበ እየገዛ ያለ ሃይል መሆኑን ፕ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ:: ዶ/ር መረራ ይህንን ያስተወቁት እሁድ ጃንዋሪ 30 በአምስተርዳም ባደረጉት ህዝባዊ ስብሰባ ነው:: ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ቁጥራቸው በርካታ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት ጋር ዶ/መረራ ባደረጉት በዚህ ውይይት የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም የሚደግፈው ተቃዋሚ ሃይሉን ዕንደሆነ ገልጸው በ 97ቱም ሆነ በ2002ቱ ብሄራዊ ምርጫ ህዝቡ በነቂስ እንደመረጣቸው ተናግረዋል::

በምርጫ 97 የተደረገው ግልጽ የሆነ የምርጫ ማጭበርበር እና በ 2002ቱ ምርጫ ደግሞ በጠራራ ጸሃይ የተከናወነ የህዝብ ድምጽ መዘረፍ አስመልክቶም ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል::

ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ሕዝቡ በነቂስ እየወጣ ድጋፉ አሳይቶናል ድምጽ በመስጠትም መርጦናል:: ኢህአዴግ ድምጹን በሰረቀበት ጊዜ ግን “ይህ አይሆንም!” ብሎ ድምጹን ለማስመለስ የሚያስችለውን ያህል ሕዝባችን አልተደራጀም:: ይህ ደግሞ ድክመታችን ነው: ድክመታችን የመነጨው በአቅማችን መዳከም ምክንያት ነው ሲሉ አስታውቀዋል::

በምርጫ 2002 ኢህአዴግ የምርጫ ውጤቱን በግልጽ ሲገለብጠው ምእራባውያን አይተዋል:: የአውሮፓ ታዘቢ ቡድንም የምርጫ ታዛቢዎቻችን አይን እንዳያዩ ሲታሰር: እንዳይጮሁም አፋቸው ሲታፈን እያዩ ዝም ነበር ያሉት:: በምርጫው ወቅት የተገደሉ አባሎቻችንን አስከሬን እንኳን እንዲያዩ ጠይቀናቸው ችላ ነበር ያሉት: ያሉት ዶ/ር መረራ ለተንኮል የተሰናዳውን የምርጫ ስነ ምግባር ሰነድ (ኮድ ኦፍ ኮንዳክት)አንፈርምም በማለታችን ምእራባውያን ዲፕሎማቶች ቂም ይዘውብን አሳፋሪውና አይን ያወጣውን የ99.6% የምርጫ ውጤት ካዩት በኋላ ግን የኢህአዴግ ጨዋታ ገባቸው:: ሲሉ ተናግረዋል:: ይኽንን ሰነድ በተለይ መኢአድ መፈረሙ የአኢሃዴግን ጫወታ ማሳመሩን እና መድረክን በእጅጉ እንደጎዳው ዶ/ር መረራ ገልጸዋል::

በምርጫ 97 የታየው ህዝባዊ ሱናሚ:የተንቀሳቀሰው በተደራጀ መልኩ ቢሆን ኖሮ መሪዎቹ 2 አመት ሙሉ በቃሊቲ ሊታሰሩ አይችሉም ነበር ያሉት ዶ/ር መረራ:: በሚሊዮኖች የተንቀሳቀሰው ያ የህዝብ ማእበል – ጎርፍ ሆኖ እንደቀረም ተናግረዋል::

ተቃዋሚ ሃይሎች አቅማቸው ቢጠናከር: ይህንን ድክመታቸውን ቀርፈው ህዝቡን በማደራጀት ፍትሃዊና ሰላማዊ ለውጥ እንደሚያመጡ ተናግረዋል::

ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ፓርላማ በመግባጣችሁም ወይ ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር መረራ ሲመልሱ: ህዝቡ አልቀጣንም: የተሸነፍነውም ህዝቡ ሰላልመረጠን ሳይሆን የህዝቡ ድምጽ ስለተሰረቀ ነው:: በወቅቱ ፓርላማ መግባት አንድ ክስተት ነው መታሰር ሌላው ክስተት: ውጤቱን ስናየው ግን አንድ ነው::ፓርላማ የገባነውም ተከፋፈልን ቃሊቲ የገቡትም ተከፋፈሉ:: እንደኔ እንደኔ ሁላችንም ፓርላማ መግባት አልበለዚያ ሁላችንም መታሰር ነበረብን::ብለዋል::

የፓርላማውን እንቅልፍ ጉዳይም ሲተቹ: እኔ ፓርላማ እገባ የነበረው አቶ መለስ የሚገቡበትን ወቅት በመጠበቅ ጥያቄዎችን ለማንሳት ነበር:: ሶስት ወይንም አራት ጊዜ በገባ ነው:: የምኖረውም በዩኒቨርሲቲ ደሞዜ እንጂ በፓርላማው ደሞዝ አይደለም:: ስለማንቀላፋት እና ስለዚህም ጉዳይ የሰጠሁት አስተያየት አልነበረም ሲሉ ተናግረዋል::

በስብሰባው ሲነሱ ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ የተሰብሳቢውን ትኩረት የሳበው ሰሜን አፍሪካ እየተከሰተ ያለው ህዝባዊ አመጽም እና ይህም በኢትዮጵያ ላይ ስላለው እንድምታ ነበር:: ህዝባዊ የለውጥ ማእበል በኢትዮጵያ ቢከሰት ተቃቀሚ ሃይሎች ይህንን እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ለተጠየቁት ጥያቄ ዶ/ር መረራ ሲመልሱ:: አሁንም የአቅም ጉዳይ ነው:: ድምጹን በመስጠት የመረጠንን ህዝብ ድምጹ ሲሰረቅ እንዲከላከል ማድረግ ያልቻልነው አቅማችንን ባለማናከራችን ነው:: ቱኒዚያን በሰላማዊ ሰልፍ ቤን አሊ ሃገር ከወጣ በኋላ መንግስት ለመመስረት ላይ ሌላ ችግር መፈጠሩንም ከዚህ ከአለመጠናከር አለመደራጀት እና አቅም ማጠት ጋር አየይዘውታል::

የእድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ ጩኸት ኢአዴግ (አብዮታዊ ዲሞክራሲያ)የአምስት አመት እቅድ እያለ ከሚያወጣው የሚለየው : ለውጥ የሚለውን ትራንስፎርሜሽን በሚለው የማደናገርያ እንግሊዘኛ መጨመሩ ብቻ ነው: ፕላኑም: ካድሬውም.. በተቀረው ሁሉ የተለወጠ ነገር የለውም:: ውጤቱንም ከ 4 አመት በኋላ የምናየው ይሆናል:: የእድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ ጩኸት በጥቅሉ የህዝቡን እና የአለም አቀፉን ህብረተሰብ ትኩረት ከ2002ቱ አይን ያወጣ የህዝብ ድምጽ ዘረፋ ለማራቅ የተደረግ የተለመደ ማጭበርበር እንደሆነ ተናግረዋል::

ዶ/ር መረራ ጉዲና በመጭው እሁድ 13 ፈብሩዋሪ 2011በጄኔቭ ስዊዘርላንድ : ከዚያም በሌሎች አውሮፓ ከተሞች ተመሳሳይ ውይይት ያደርጋሉ::

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 31, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.