አንድ ብስጭት፤ጉድ በል ደቡቤ…!

Abe Tokichaw – ትላንት “የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሽጉጥ” በሚል ርዕስ ብሎግ ያፈራውን ትንሽ ወሬ ተቃምሰን ነበር። እኔ ያንን ወሬ ሳወጋ በታይፔ አልተናገርኩትም እንጂ፤ በውስጤ ወሬው የዘገየ እንደሆነ ይታወቀኝ ነበር። ነገር ግን አንድም መፈናቀሉ እየቀጠለ ስለሆነ አንድም ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ የተነሳ አንድ ነገረማ ማለት አለብኝ… በሚል እሳቤ ነበር ፅሁፉን ለመለጠፍ የበቃሁት።

ትላንት የአሜሪካ ራድዮ ድምጥ ሰምቼ ነበር። ታዋቂው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ ተፈናቃዮቹን በሚመለከት አንድ ዘገባ አቅርቧል። ዘገባውም የደቡብ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በደብዳቤ እደግመዋለሁ በደብዳቤ “ውጡልኝ” ብለው ያባረሯቸው ተፈናቃዮችን አስመልክቶ ነበር።

አዲሱ እንደነገረን፤ ተፈናቃዮቹ ከደብረ ብርሃን እስከ ወለጋ ድረስ ተበትነው በታላቅ ችግር ላይ እንደሚገኙ ነግሮናል።


VIDEO: A Campaign of Ethnic Cleansing Against Amhara (VOA)

ታድያ ከሁሉ ያስደነቀኝ እና “ጉድ በል ደቡቤ” ያስባለኝ ምን መሰልዎ የደቡብ ክልል ፕረዘዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ በክልላቸው እየተከናወነው ስላለው “እብደት” ምንም ነገር አለማወቃቸው ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ “ከክልሉ የተፈናቀለ ሰው ስለመኖሩ ገና እያጣራን ነው” ብለዋል።

የአቶ ታመነ ነገር ይቺን ቀልድ ብጤ አስታወሰኝ፤

የተለያዩ እንስሳቶች በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር አሉ። ሲኖሩ ሲኖሩ አሁንም ሲኖሮ ከእለታት በአንዱ ቀን ከቤተሰቡ አባላት ውስጥ ጥንቸል ታመመች። በዚህ ግዜ ለመድሃኒት የሚሆን ደማከሴ በጥሶ የሚመጣ ፈጣን እንስሳ ማን ይሆን? ተብሎ ሲፈለግ ጦጣ፤ “አይ እንግዲህ ፈጣኗ ተያዘች ከእርሷ ቀጥሎ ያለሁት እኔ ነኝ እና እኔው ልሂዳ… ብላ ሃሳብ አቀረበች። የሜዳ አህያም “አንቺን ብሎ ፈጣን እኔ እያለሁ አንቺ ሄደሽ እስክትመለሺ ጥንቸልዬ ትሙት እንዴ?” ብሎ በተቆርቋሪነት ጠየቀ፤ ሁሉንም ስትሰማ የቆየችው ኤሊ ድንገት ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች። ለቅሶዋም ከታማሚዋ ጥንቸል ማቃሰት የበለጠ ቤቱን ረበሸው። ምን እንደሆነች ስትጠየቅ እኔን ንቃችሁ ነው አይደል? የማትልኩኝ ብላ እየዬዋን አስነካችው። “ቶሎ የምትመጪ ከሆነ አረ ሂጂ” ብለው ከለቅሶዋ ለመገላገልም ላኳት።

ከዛልዎ… ኤሊ ሆዬ ጭልጥ ብላ ቀረች። ብትጠበቅ አትመጣም፤ ብትጠበቅ አትመጣም። ይሄኔ እነ ሜዳ አህያ እነ ጦጣ በቤቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም ማጉረምረም ጀመሩ። “ድሮውንም ኤሊን ሂጂ ብላችሁ ስትልኩ ነው ችግሩ የተፈጠረው። ታማሚዋ እንድትሞት ፈልጋችሁ እንጂ…” እያሉ ርስ በርስ መገማገም ጀመሩ። በዚህም ቤቱ ጭቅጭቅ በረታበት።

ይሄኔ የበር መከፈት ድምፅ ሰምተው ሁሉም እንስሳቶች ጭቅጭቃቸውን ቆም አድርገው ወደ በሩ ዞሩ። ኤሊ ናት… በሆዳቸው፤ “ጎሽ መጣች…!” ሲሉ እርሷ ግን አለቻቸው፤ “ገና እግሬ ሳይወጣ “ድሮም እርሷን መላክ” እያላችሁ ሃሜት ጀመራችሁ አይደል በቃ ቀርቻለሁ ራሳችሁ ሂዷት…!” ብላቸው ቁጭ።

ጉድ በል ደቡቤ ለካስ ይመሩናል ያልናቸው ገና ከኋላችን እየመጡ ነው! ለካስ ክልሉ ያለው በኪነ ጥበቡ ነው ያለው።  ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶቻችን ዋና ስራቸው ምን እንደሆነ ርስት አድርገውታል።

ይሄን ያህል ግዜ ሀገሩ ሲታመስ  መሪዎቻችን ገና ልናጣራ ነው ይሉናል! ነዋሪዎቹ የስደት ጉዞ አድርገው ከተቃዋሚው መኢአድ ቢሮ አደሩ ከተባለ እንኳ ስንት ግዜ ሆነው? አራት ኪሎ ስላሴ ደጃፍ ላይ ተገኝተው መንግስት አልሰማ ብሏቸው ለስላሴ አቤት ካሉስ ስንት ቀን አለፈው…? አረ ጎበዝ ሰው ይታዘባል? አረ ጎበዝ እግዜሩ ያያል…!

አቶ ታመነ እነሆ ጥያቄ፤

ነገሩን የሚያጣሩት በሱባኤ እና በፀሎት ነው እንዴ?

ይህንን ፍጥነትዎን ሌላው ይቅር ደቡቤዎች ሲሰሙ ምን የሚሸልሙዎት ይመስልዎታል? ጉድ እኮ ነው!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 5, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.