አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኦፊሴል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኑ

(EMF) ጠቅላይ ሚንስትሩ በሌለበት ወቅት አፈ ጉባዔው አስቸኳይ ስብሰባ የሚጠራ መሆኑ በህግ በመደንገጉ፤ የዛሬው ስብሰባ የተጠራው በአፈ ጉባዔው አባ ዱላ ገመዳ አማካኝነት ነበር። ስብሰባው የተጀመረው ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ የህሊና ጸሎት በማድረግ ሲሆን፤ በመቀጠልም ኢህአዴግ በፓርላማው አብላጫ አባላት ያሉት በመሆኑ፤ ጠቅላይ ሚንስትር የሚሆነውን ሰው ለፓርላማው እንዲያስተዋውቅ በተባለው መሰረት፤ የትምህርት ሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን… አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን አስተዋውቋል። ከዚያም የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተገኔ ጌታሁን ቃለ መሃላ አስፈጽሟል።

በመቀጠል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አጭር መልዕክት እንዲያስተላልፉ ተጠይቆ፤ ከዚህ በፊት የምንሰማቸው አይነት ተመሳሳይ ንግግር አድርጓል። ሆኖም ገና ከመጀመሪያው በየትኛውም የክርስትና እምነት በኦርቶዶክስም ሆነ፣ ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት ዘላለማዊ ክብር መስጠት የሚገባው ለአንድ አምላክ ሆኖ ሳለ… “ዘላለማዊ ክብር ለመለስ ዜናዊ ይሁን” የሚለው አባባል ሌላውን ለማስደሰት ሲባል እና ከበታችነት ስሜት የሚመነጭ፤  ለሰሚውም የሚያሸማቅቅ አይነት ነበር። ብዙውን ጊዜ በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች፤ የራሳቸውን እቅድ ያቀርባሉ እንጂ… “ዘላለማዊ ክብር ለርሱ ይሁን” በማለት የአምልኮ የሚመስል ቃል አያነበንቡም። ይህ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘንድ የሚታየው በራስ አለመተማመን ስሜት የመነጨው በህወሃት ላይ ካለው ፍራቻ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ መልካም አስተዳደርን በሚመለከት… በተለይ የፖሊስ እና የአቃቤ ህጉ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑና “በሙስና የተለከፉ ግለሰቦች የሚወገዱበትን ሁኔታ ሊሰመርበት ይገባል” የሚለው አባባል በሙስና ለተዘፈቁት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከማስፈራሪያነት አልፎ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

“የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የምርጫ ቦርድ፣ ነጻ ሚዲያ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማህበራት ጋር ተባብረን ለመስራት ዝግጁ ነን።” የሚለው አባባል ከየትኞቹ ነጻ ሚዲያዎች ወይም ተቃዋሚዎች ጋር አብረው ለመስራት እንደታሰበ ግልጽ ባይሆንም ለማለት ያህል ግን ተብሏል። “የሃይማኖት ነጻነታችንን እንደምናስከብር ሁሉ በሃይማኖት ሽፋን በሚደረግ ሽብር ስራ ላይ በሚሰማሩት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” የሚለው ማስፈራሪያ አዘል ንግግር ብዙም ደስ የሚያሰኝ አልነበረም።

በውጭ አገር ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወይም በአገር ውስጥ ያለአግባብ ስለታሰሩ ነጻ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ምንም ያለው ነገር ባለመኖሩ፤ በ’ርግጥም ተቃዋሚዎችን በማሰር እና በማንገላታት የሚታወቀውን የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ሊቀጥልበት ማሰቡን አመላካች በመሆኑ በዚህ አቋሙ ቅር የሚሰኙ የአገር ውስጥ እና የውጭ ሰዎች መኖራቸው ግልጽ ነው።

በመቀጠል የአገሪቱን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር በእጩነት እንዲያሳውቁ በተባለው መሰረት፤ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀ መንበር እና የትምህርት ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ፤ በእጩነት ቀርበው በሙሉ ድምጽ ምክትልነታቸው ጸድቋል። አቶ ደመቀ መኮንን በተመሳሳይ ሁኔታ ቃለ መሃላ ከፈጸመ በኋላ፤ ፓርላማው ባንዲራ ፕሮጀክት ባለው ጉዳይ ላይ ተነጋግሮ የእለቱ አስቸኳይ ስብሰባ ተበትኗል። ከአንድ ተቃዋሚ በቀር ሙሉ ለሙሉ በኢህአዴግ አባላት የተሞላው ፓርላማ፤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በኦፊሴል እንደገና ተከፍቶ ስራውን ይጀምራል፤ ድራማውንም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 21, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.