አቶ ስዬ አብርሃ መኖሪያ ቤታቸውን እንዲያስረክቡ ተባለ

ከወራት በፊት የትምህርት ዕድል አግኝተው በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ኬኔዲ ስኩል ኦፍ ገቨርናንስ ለመማር ወደ አሜሪካ የሄዱት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ስየ አብርሃ፤ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራይተው የሚኖሩበትን ቤት እንዲያስረክቡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ስምንት ቀናት ብቻ ቀርቶታል፡፡ የትምህርት ዕድሉን የሰጣቸው ዩኒቨርስቲ የአቶ ስዬ ባለቤትን ወ/ሮ ሐዳስ ዓለሙን ጨምሮ ሦስት ልጆቻቸው በቅርባቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲማሩ ሁኔታዎችን ስላመቻቸላቸው ለመኖሪያ ቤታቸው ጠባቂ አድርገው ቤተሰባቸውን በመውሰድ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አቶ ስየ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራይተው የሚኖሩበት በወረዳ 17 ቀበሌ 19 የቤት ቁጥር 106 የሆነውና ቦሌ አካባቢ የሚገኘው ቤት ከዐዋጅ ውጭ የተወረሰ በመሆኑ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ቤቱ ለባለመብቱ እንዲመለስ መወሰኑንና ውሳኔውን ተከትሎ ባለመብቶች በኤጀንሲው ላይ የአፈጻጸም ክስ መሥርተው እንደተመለሰላቸው ኤጀንሲው ለአቶ ስየ የጻፈላቸው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡

ኤጀንሲው ውሳኔውን በመቃወም ለፕራይቬታይዜሽን ቦርድ ያቀረበው አቤቱታ ተመርምሮ ተገቢው ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ አፈፃፀሙ ታግዶ መቆየቱን እና ይህንንም አቶ ስየ እንዲያውቁት ማድረጉን ደብዳቤው ይዘረዝራል፡፡ ሆኖም የፕራይቬታይዜሽን ቦርድ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ያቀረበውን ይግባኝ አለመቀበሉን ነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም እንዳሳወቀው በመግለጽ፤ “ኤጀንሲያችን ሲያስተዳድረው የነበረውና እርስዎ በውል ተከራይተው የሚኖሩበት ቁጥሩ ከላይ የተጠቀሰውን ቤት የቀድሞ ባለንብረቶች ቤቱን እንዲረከቡ የመጨረሻ ውሳኔ ያረፈበት በመሆኑ እንደውሳኔው መፈፀም እንዲቻል ይህ ደብዳቤ በደረሰዎት 30 ቀናት ውስጥ የቤቱን የመብራትና የውሃ ፍጆታ በመክፈል፣ ቤቱ ለቀድሞ ባለንብረት ወራሽና ባለቤት ለወ/ሮ ገነት ፍሥሐ እንዲያስረክቡ በማክበር እናሳስባለን” በሚል ለአቶ ስየ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ኤጀንሲው ይህን ደብዳቤ ለአቶ ስየ የጻፈው መስከረም 12 ቀን 2004 ዓ.ም ሲሆን በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ቤቱን ጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ለማስረከብ የስምንት ቀናት ጊዜ ብቻ ቀርተውታል፡፡ የቤቱን ርክክብ ማን እንደሚፈጽም ለማወቅ መኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ፣ አቶ ስየ ቤቱን ለአንድ ዘመዳቸው እና ጠባቂ አደራ ብለው መሄዳቸውንና የሚመጣውን ከመጠበቅ ውጭ ዕቃውን አውጥተው የሚያስቀምጡበት ቦታም ሆነ የሚወስዱት አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ስየ አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው፤ እንዲህ ያለ ችግር ሲገጥም ለሌሎች ግለሰቦች ተለዋጭ ቤት እንደሚሰጠው ሁሉ ለእርሳቸውም ተለዋጭ ቤት እንዲሰጣቸው ጠይቀው እየጠበቁ እንደነበር መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በመኖሪያ ቤቱ ያገኘነው ጥበቃ ለአቶ ስየ ምንም ተለዋጭ ቤት እንዳልተሰጣቸው ገልፆ፤ ቤቱን እንዲያስረክቡ ትእዛዝ የሚሰጠው ደብዳቤ ብቻ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 15, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.