አቡነ ጳውሎስ ሐገረ ስብከቱን እያመሱት ነው

Abune Samuel

  • ፓትርያርኩ በቅ/ሲኖዶስ የተሠየመውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አገዱ (አዲስ ነገር ጋዜጣ)
  • የሐገረ ስብከቱ የባንክ ሒሳብ ታግዷል (ሪፖርተር ጋዜጣ)

(አዲስ ነገር ጋዜጣ፤ አብርሃም በጊዜው):- [PDF] ግንቦት 26/2001 ዓ.ም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የተቋቋመውና ሰባት ሊቃ ነጳጳሳት የሚገኙበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በብፁዕወቅዱስ ቡነ ጳውሎስ በተጻፈ ደብዳቤ ታገደ።

ፓትርያርኩ በፊርማቸው ሐሙስ ዕለት (June 25/2009) ያወጡት የእግድ ደብዳቤ በአድራሻ ለኮሚቴው ሰብሳቢ ለብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የተጻፈ ቢሆንም የኮሚቴው አባላት ለሆኑት ጳጳሳት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር፣ ለብሔራዊ ደህንነት መረጃ አገልግሎት፣ ለፌዴራል እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በግልባጭ እንዲደርሳቸው መደረጉን የአዲስ ነገር ምንኞች አረጋግጠዋል። ፓትርያርኩበዚህ ደብዳቤ “ግንቦት 26 ቀን 2001 ዓ.ም የተሰየመው ኮሚቴ ከዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ አስፈጻሚነቱ ተግባር ታግዷል” ሲሉ አሳውቀዋል።

በደብዳበኔ ቁጥር ል/ጽ/637/2001 የተበተነው የፓትርያርኩ የእግድ ትእዛዝ ውሳኔው የተላለፈው ረቡዕ ዕለት በተካሄደው “የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ” መሆኑን ይገልጻል። በዚህ ጉባኤ ላይ ውሳኔ የተላለፈባቸው የኮሚቴው አባላትም ሆኑ በርካቶች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አለመገኘታቸውን በስብሰባ የተሳተፉ ታዛቢዎች ለአዲስ ነገር ገልጸዋል። በጉባኤው የተሳተፉት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መሆናቸው ቢታወቅም ትክክለኛ ቁጥራቸውን ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ኮሚቴው የተቋቋመው “የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊ አስተዳደር የማስፈጸም አቅም ለማጎለበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲሠራ” እና እስከ ሐምሌ ወር ውስጠ ደንብ እንዲዘጋጅለት፤ እስከዚያው ግን “በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ ደንብ እንዲዘጋጅለት፤ እስከዚያው ግን “በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ ተወስነው የተጓተቱ ጉዳዮችን እየተከታተለ” እንዲያስፈጽም እንደነበር ይገልጻል። ይሁንና ኮሚቴው “ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትደዳርባቸው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ ከቃለ ዓዋዲውና ከሠራተኞች አስተዳደር ሕጎች ውጭ የሆነ አሠራር በመፈጸም ያልተጠበቀ ችግር በመፍጠር አላስፈላጊ ጽሑፎችን ያስተላልፋል ብለን አልገመትንም ነበር” ሲል ለእግዱ ምክንያት የሆኑተርን ችግሮች ይዘረዝራል።

ለዚህም በቀዳሚነት የሚነሣው ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት የፓትርያርኩን የጣልያን ጉዞ፣ የሠራተኞች ዝውውርና ድልድል እንዲሁም አዲስ ሹመት በተመለከተ ማብራሪያዎች እንዲሰጡትና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ያጻፋቸውን ደብዳቤዎች ነው። ይኸው ደብዳቤ የሥራ አስፈጻሚውን ተግባር “የሥልጣን ተዋረዱን ያልጠበቀ” ነው ብሎታል። “የሥራ አስፈጻሚው ተግባር የተጓተቱ ጉዳዮችን እንዲያስፈጽም እንጂ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላኢ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውን ሐላፊነት ድርሻ በመጋፋት ወይም የበላይነቱን ሥልጣን በመያዝ ቤተ ክህነቱን ተክቶ እንዲሠራ ኤኢደለም” ሲል ከሷል።

በዚህ ተግባሩ “የአስተዳደር ጉባኤው” ስድስት ውሳኔዎችን በማስተላለፍ እንዲፈጸሙ አዟል። በውሳኔው መሠረትም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የከፈተው ጽሕፈት ቤት በአስቸኳይ እንዲዘጋ፣ ኮሚቴው ያሳተማቸው ክብ ማህተም፣ ቴተርና ሄዲንግ ማዘዣ ወረቀቶች የቤተ ክርስቲያኒቱን ቃለ ዓዋዲ እና ሕገ ቤተ ክርሲያኑን የጣሱ በመሆኑ በሥራ ላይ እንዳይውሉ ይላል።

በተጨማሪም ሥራ አስፈጻሚው “በሚያከናውነው ሕገ ወጥ ተግባር” ከጀርባው “የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ደንብ መዋቅርንም ጭምር ለማፍረስ የተዘጋጀ አካል እንዳለ ስለሚያመለክት አስፈላጊ ክትትል እንዲደረግበት” ይላል። በአራተኛው ውሣኔው ላይ በሥራ አስፈጻሚው የተላለፉት “ሕገ ወጥና ፀረ ሰላም ጽሑፎች” በኢንተርኔት እና በአዲስ ነገር ጋዜጣ በመውጣታቸው የኮሚቴው አባላት እንዲጠየቁ እና የአዲስ ነገር አዘጋጅም በሕግ እንዲጠየው ሲል ጠይቋል።

በማያያዝም ሥራ አስፈጻሚው ባለፈው ሳምንት ማብራሪያ የጠየቀበትና ከሕግ ውጭ ተካሄደ ያለው የፓትርያርኩ የውጭ አገር ጉዞ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና የሚጠቅም በመሆኑ “ቀጣይነት እንዲኖረው የአስተዳደር ጉባኤው አምኖበታል” ሲል የኮሚቴውን ውሳኔ ተቃውሟል። በመጨረሻም የኮሚቴው አባላት ላሳዩት እንቅስቃሴና ለፈጠሩት ውዥንብር “በሕግ ፊት እንዲቀርቡና እንዲጠየቁ” መወሰኑን አስታውቋል። የኮሚቴው አባላት የሆኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይህንኑ በመረዳት በአስቸኳይ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሲል ደብዳቤው ትእዛዝ አስተላልፏል።

እርምጃው በፓትርያርኩ እና በኮሚቴው መካከል ሲብላላ የቆየው ሽኩቻ ከፍተኛ መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል። ቀደም ሲል ባቀረብናቸው ተከታታይ ዘገባዎች ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው አዲስ የ ራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፓትርያርኩን በአስተዳደራዊ ሥራዎች የሚኖራቸውን ሥልጣን ይገድባል የሚል ግምት መኖሩን መግለጻችን ይታወሳል።


የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ አቡነ ሣሙኤል እና አቡነ ጢሞቲዎስ ከኃላፊነታቸው ታገዱየሐገረ ስብከቱ የባንክ ሒሳብ ታግዷልበታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር ጋዜጣ —በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀጳጳስ አቡነ ሣሙኤል እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ጢሞቲዎስ ከሰኔ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸውና ከሥራቸው መታገዳቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና ከሊቃውንት ጉባኤ ዕውቅና ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎትን ስለማስተላለፍ የተሰራጨው ትምህርተ ቀኖና፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚያፋልስና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሰነዘረ የድፍረት ድርጊት መፈፀማቸውን በመግለፅ፣ ጉባኤው ተጠንቶ በቅዱስ ሲኖዶስ እርማት እስከሚሰጥበት ድረስ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ከኃላፊነታቸውና ከሥራቸው ታግደው እንዲቆዩ በሚል ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት መታገዳቸውን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡በብፅዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፀሐፊዎች ለአንድ ቀን ባደረጉት ስብሰባ፣ ለቤተ ክርስቲያኗ ሠራተኞች እየተላለፈ ያለ ህገወጥ ደብዳቤ በመኖሩ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን፣ በሐገረ ስብከቱ በኩል ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የእምቢተኛነት መንፈስ ከመታየቱም በተጨማሪ፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሚተላለፉ መመሪያዎችም ሆኑ ውሳኔዎች ምላሽ በማይሰጥባቸው ደረጃ ላይ መደረሱን መግለፃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ ተወስነው ያልተፈፀሙ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚያስፈፅም አንድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቢቋቋምም የሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኮሚቴው ስም ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ለመምሪያዎች፣ ድርጅቶችና ለሠራተኞች ባስተላለፏቸው ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዓዋዲ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑና የመሥሪያ ቤቱ መዋቅር እንዲጣስ መደረጉን በስብሰባው ወቅት ትኩረት የተሰጣቸው ነጥቦች መሆናቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ በኩል እየታየ ያለው ችግር በቅርብ የተከሰተ አለመሆኑን የገለፁት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ድርጊቱ የቆየና የኖረ መሆኑን፣ ከላይ የመጣ መመሪያን ያለመቀበል ብቻ ሳይሆን ከታችም መመሪያን ተቀብሎ ማስተናገድ ባለመቻሉ፤ የአብያተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮች ኑሮአቸው የሰቀቀንና “ነገ ምን ይገጥመን ይሆን?” የሚል የሥጋት ኑሮ መሆኑ በምሬት መወሳቱን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች ጨምረው እንዳስረዱት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት መሆኑ በሕግ መደንገጉን አስታውሰው “ፓትርያርኩም ሆኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቢጠሯችሁ፣ መመሪያ ቢሰጣችሁም እንዳትቀበሉ” በማለት ከሐገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሕገ ወጥ ደብዳቤ ቢተላለፍላቸውም፤ ትዕዛዙን ጥሰው በጉባኤው ላይ ሊገኙ መቻላቸውን መግለፃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ በየአብያተ ቤተ ክርስቲያናቱ የተመደቡ ሠራተኞች፤ ለመዳቢዎቻቸው ጥቅም አሰባሳቢ ሆነው ካልተገኙ አኗኗራቸው አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን እንደሚገለፅላቸው የተናገሩት የስብሰባው ተሳታዎች፣ በሀገረ ስብከቱ የሕንፃ ግንባታና በሌሎችም ሙስና በተካሄደባቸው ዘርፎች ጥያቄ እንዳላቸው በመግለፅ ቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሀገረ ስብከቱ እየተከናወነ ያለውንና የእምነቱ ተከታዮች ምዕመናንን ያሳዘነ በርካታ አሳፋሪ ተግባራትና የስነ ምግባር ጉድለት በተለይም የጥንታዊ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በሚቃረን መልኩ ቅዳሴን፣ ፀሎትና ትምህርት በኢንተርኔት መረብ መከታተልና መፈጸም እንደሚቻል ያስተላለፉትን መልዕክት አበክረው እንደሚቃወሙት መግለፃቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ በብፁዕ አቡነ ይስሐቅ እና ንቡረዕድ አብርሃ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የአንድ ቀን ውይይት ሰባት ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁን ምንጮች ገልፀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ጋር የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ጢሞቲዎስም የታገዱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ሰኔ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ በመመለስ ይቅርታ ጠይቀው በመታረቃቸው ምናልባት እግዱ ሊነሳላቸው እንደሚችል ምንጮቹ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሣሙኤልን አግኝተን ለማነጋገር በተደጋጋሚ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 30, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.