አሰባብሮ ወደ ፖለቲካ፤

ለአማተር ፖለቲከኞች፣ ስድስቱ አቋራጭ ነጥቦች፣….

 (ሰለሞን ተሰማ ጂ. ከአ.አ.)                 semnaworeq.blogspot.com
ዛሬ ስምስት አመት ገደማ፣ ዝነኛ የሩጫ ባለሙያ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ፖለቲከኛነት እቀየሳለሁ ሲል ተደምጧል፡፡ ኃይሌ ብቻም ሳይሆን ታዋቂው የኢትዮ ሳውዲ ቱጃር ሼክ ሙሐመድ አላሙዲን በ1997 ዓ.ም ከመቅጽፈት ወደ ፖለቲከኛነት ተቀይረው ነበር፡፡
ከተዋንያኑና ከመድረክ ሙያተኞቹ እነ ደበበ እሸቱ፣  ሰለሞን ተካልኝ፣ ነዋይ ደበበና ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዴ አፍሮ) ከመቅጽፈት ከተዋቂዎቹ አደባባይ ወደ ፖለቲካ መድረክ ላይ ሊገቡ ሲሞክሩ አይተናል፤ ታዝበናል፡፡  ከኃይሌ ገ/ሥላሴ በስተቀር ሌሎቹ ተዋቂዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአንድ የፖለቲካ ቡድን ወይ ፓርቲ ደጋፊ ወይም ቲፎዞ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ መሆን መብታቸው ነው፤ ቢባልም እንኳ የተሰማሩባቸው የሙያ መስኮች  ግን የሁሉም ሕዝብ የጋራ ንብረቶች ስለሆኑ እንደ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ (ቢያንስ በመርህ ደረጃ) ነፃና ገለልተኛ ቢሆኑ ይመከራል፡፡ እንኳን እንደኢትዮጵያ ባሉ ከመሳፍንትና ከመኳንንት አገዛዝ ወደ ብልጣብልጦቹ የፖለቲካ ስልጣን ቁማር የተሸጋገረችውን ቀርቶ፣ በፖለቲካው መስክ ረጅም ታሪክ ባሳለፉት የምዕራብ አውሮፓ ሀገራትም ቢሆን ዝነኞቹ የፖለቲካውን መስመር በጥንቃቅ ነው የሚያዩት፡፡ ተጠንቅቀው፣ ተቆጥበው፣ ለረጅም ጊዜ አማራጮቻቸውን ሁሉ መርምረውና አስልተው ነው የሚቀላቀሉት፡፡ (አለበለዚያ ግን እንደ ዶሚኒክ እስትራውስ ቅሌት ላይ የወድቃሉ፡፡ ሊያውም በአፀያፊ – የአስገድዶ መድፈር ጉዳይ ተጠርጥረው ዘብጥያ መውረዳቸው አይቀርላቸውም፡፡….ሰዓሊነነ-ቅድስት እንበል ሦስት ጊዜ!!!)
በእኛም ሆነ በአንዳንድ ታዳጊ ሃገራት ያሉ ዝነኛ ሰዎች፣ በመገናኛ ብዙሃኑና በዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲው አካባቢው ባሉ ሰዎች ስለታወቁ ያንን እንደፖለቲካ ቀብድ (መለኪያ መስፈርት) ወስደው ሊጠቀሙ ሲሞክሩ አስተውለናል፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑም ሆነ ሌሎቹም ግብአቶች ፋይዳ የላቸውም ማለታችን ሳይሆን ግማሽ ጌጥ ናቸው፡፡ ስለሆነም  በአቋራጭ ፖለቲከኛ ለመሆን ለሚሹትና በየአደባባዩ ላይ ላሉት ዝነኞች (ለዩኒቨርስቲ ፕሮፈሰሮችም ጭምር ድፍረት ካልሆነብኝ) ለዝነኛ ሐኪሞች፣ ለዘፋኞች፣ ለአትሌቶች፣ ለተዋንያን፣ ለጦር ሜዳ ጀግኖች፣ ለወሬ አሩጥ ጋዜጠኞችም ቢሆን የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች እንዲያጤኗቸው እንሆኝ ብያለሁ፡፡
1.  ራስዎን አይመርጡም/ ማነው የሚመርጦት?
ወደ ፖለቲከኛነት ሲያሳብሩ ሁነኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ያስፈልጎታል፡፡ ፖለቲከኛነት ያሰኘው ግለሰብ አሉ የተባትን የአካባቢው ነዋሪዎች ሊያውቅ ቢችል፤ እና በይበልጥም በየመንገዱ ጥግና ዳርቻ በየግል ኪራይ ቤት ስርቻ ያሉት መራጮች ናቸው እና እንዲመረጥ ወይም እንዲወድቅ የሚወስኑት ጠንቅቆ ወዳጅነቱን ቢያጠናክር ይጠቅመዋል፡፡ (ይህ የእኛ ዘመን የንጉሱ “ የእንደራሴ” ምርጫ ጊዜ አይደለምና)፡፡ የመጀመሪያው የፖለቲካ ህግ መራጮች የት እንደሚገኙ ማወቅና የሚያስመርጠውን የፖለቲካ አጀንዳ በቅጡ ማሰናዳት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲውም የምርጫ ማኒፌስቶ(የምረጡኝ ቃልኪዳን ሰነድ) የተመራጩን የቅስቀሳ አጀንዳ እንዲያንፀባርቅ ሆኖ ወረዳ ውስጥ ያሉትን የተለያየ አመለካከትና አቋም ያላቸው ወገኖች ፍላጎት የሚስብ ሆኖ መረቀቅ አለበት፡፡ ተወዳዳሪ ፖለቲከኛ ያለፓርቲ ደጀንነት ወደ ምክር ቤት ከሚገባ ይልቅ ሹራቡንና ሰደርያውን አውልቆ ወደ ንግድ ምክር ቤት ክበብ ቢገባ ይቀለዋል፡፡
አስረግጦ ለመናገር ያህል የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለግለሰቡ፣ ከተናዳፊ የአርበኞች፣ ካሽሟጣጭ ሴቶች፣ ከመሰሪ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና ማህበራት ይጠብቀዋል፡፡ ተወዳዳሪው ለክልል ፕሬዝዳንትነት ወይም አፈ ጉባኤነት አልያም ለሚቋቋመው መንግስት የካቢኔ አባልነት እስካልቋመጠ ድረስ የግል አመለካከቱም ሆነ የግል ፍልስፍና የፈለገው ቢሆን ፓርቲው “ጥላ ከለላ” ይሆነዋል፡፡
አሁንም ለማስረገጥ ያህል የፖለቲካ ፓርቲ የብዙሀኑን መራጭ ምኞትና ተምኔት የሚፃረር ሁኔታ የግል አቋሞች ያሉትን ተመራጭ አይታገስም፡፡ ለምሳሌ ያህል የአሰሪና ሰራተኛ ህግን ፈፅሞ የሚቃወምን ተመራጭ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚው ባይፈልገው ለብዙሃኑ መራጮች ዋስትና ነው እንጂ የግለሰቡ ኃሳብ ስህተት ነው ማለት አይደለም፡፡ ከአንዳንድ ጀማሪ ፖለቲከኞች ከላይ የጠቀስነው መሰል እንግዳ ሃሳቦችን ማዳመጥ የተለመደ ነው፡፡ ሕዝቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች አወዛጋቢ መልሶችን መስጠት ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን ፓርቲውንም ስንኩል ያደርገዋል፡፡
ተመራጩ በምርጫው ውድድር መቀጣትን ካልፈለገ በስተቀር መራጮቹ በብዛት ወደሚደግፉት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መቀላቀል አለበት፡፡ ይህ አይነቱ አስተውሎት ማኬቪያላዊ የፍልስፍና ድምጸት ሊሰጠው አይገባም፡፡ ግለሰቡ የለውጥ ሐዋርያ ወይም ወግ አጥባቂና ጽንፈኛ(ወይም ለእኛ ሀገር አሰላለፍ – ብሔርተኛ ወይም ሕብረብሔራዊ) የመራጮቹን አመኔታ የሚያገኝበትን የምርጫ ወረዳና እዛ የሚያደርሰውን ፓርቲ ማወቅ አለበት፡፡ እንበልና ተወዳዳሪው የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ፈልጎ የፓርቲዎቹን የድርጅት ጉዳይ መዋቅር ተከትሎ መረጃ ለመጠየቅ ወደ መረጠው የፓርቲው ጽ/ቤት አመራ፡፡ የፓርቲው ተወካዩ በግብር ስርዓት ስለመሬት ይዞታ መብት፣ ስለሲቪል ሰርቪስ ተሐድሶ ሂደት ላይ ያሎትን አቋም ሳይሆን ወይ የሚናገሩትን ቋንቋና ብሔሮን ወይም የሚከተሉትን ሐይማኖትን ይጠይቆታል፡፡ የመጀመሪያውን ጥያቄ የሚጠይቆት ከሆነ ፓርቲው የብሔር ፓርቲ ለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የሚከተሉትን የሐይማኖት ተቋም የጠየቆት ፓርቲ ህብረ ብሔራዊ ነው፡፡
ልዩነቱ ቋንቋዎትንና የመጡበትን ብሔር ብሔረሰብ የጠየቆት የፓርቲ ተወካይና የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ የመደራጃ ስልቶች ስለሆኑ በየስብሰባውና በየመድረኩ መነሳታቸው አይቀርም፡፡ ሐይማኖቶን የጠየቆት ፓርቲ ግን ከዚያ በኋላ ስለሐይማኖት ጉዳይ አያነሳብዎትም፡፡ ሆኖም ብልሁ የፖለቲካው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ በስፋት እርስዎ የሚከተሉትን ሐይማኖት ተከታዮች ባሉበት የምርጫ ወረዳ ይመድብዎታል፡፡ ጀማሪው ፓለቲከኛ አወዛጋቢ የምረጡኝ ቅስቀሳዎችን በማድረግ የመውደቅ እና ያለመውደቅ እጣ ፈንታው በመራጮቹ ይወሰናል፡፡
እጩ ተመራጩ በተለያዩ እድሮች፣ እቁቦችና የሰንበቴ ወይም የአምቻ-ጋብቻ ማህበራት አባል ቢሆን ይጠቅመዋል ! የግድ መሆን ግን የለበትም፡፡ እጩው የመከላከያ ሰራዊቱ ባልደረባ የነበረ ቢሆን፣ በተለይም የሰራዊቱን መለዮና ቅጠልያ (ዥንጉርጉር) የለበሰ ቢሆን የተሻለ እድል አለው፡፡ ምክንያቱም፣ ብዙዎቹ የመከላከያ ሰራዊቱ መለዮ ለባሾችም ሆኑ የሲቪል ባልደረቦች አዕምሮአቸው በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ትብ ነው፡፡ በየትኛውም የጦር ዓውደ ግንባር ላይ ያልተሳተፉት አባላት እንኳ በረጋ ኩሬ አጠገብ ከተራቡ የወባ አማጭ ትንኞች የባሰ አንዘፍዛፊ ናቸው፡፡ የገዢው ፓርቲ ተዋጊ ሰራዊት አባላት የነበሩና በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከሰራዊቱ ተቀንሰው የቀበሌ ወይም የወረዳ፣ ወይም የዞን ስራ አስፈፃሚ የሆኑ ታጋዮችን ማማለል ባይችልና ባይመረጥ እድሉን ማማረር የለበትም፡፡ እነዚህ ወገኖች እንዲሰፍን የሚሹት ስርዓት አገልግሎታቸውንና እንግልታቸውን ከውስጥ ሆኖ የሚያውቅላቸውን እጬ እንጂ ከዳር ቆሞ የሚያጋፍር ብልጣ ብልጥን አይደለም፡፡ በአጠቃላይ፣ እጩ ተመራጩ ምርጫውን በድል እንዲወጣ የሚያደርጉትን መራጮች ማንነትና ፍላጎታቸውን ጠልቆ ማጤን አለበት፡፡
2.  የተረጋጋ ጥሞና አለዎት እንዴ?
ብዙ ጀማሪ ወጣቶችን ወደፖለቲካው መድረክ ሊቀላቀሉ ሲያስቡ፣ በጣም የሚያሰጋቸው ነገር እንዴት አድርገው ከአንጋፋ ፖለቲከኞች ጋር መስተካከል እንደሚችሉ አለማወቃቸው ነው፡፡ ወደድንም ጣለንም “ፖለቲከኞች” ማለት “ምንም ትዕግስት በሌለባት ዓለም ላይ በጣም ታጋሽ” የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ የሃይማኖት ልዩነቱ፣ ደሃውና ሀብታሙ፣ የተማረውና ማህይማኑ፣ ዘመናዊውና ኋላቀሩ፣ ከተሜውና ባላገሩ፡- ሁሉም መራጭ በመሆናቸው የፓርቲውን እጩ እጣፈንታ ይወስኑታል፡፡ ፖለቲከኞች ታጋሽና የተረጋጉ መሆን አለባቸው፡፡ እንደነሱ ያለ ታግሶ እድሉን በምላሱ ልሶ የሚያጣጥም አይገኝም ይሆናል፡፡
ፖለቲከኛ መሆን መቻል ወይም አለመቻልን ፈጥኖ ለማወቅ የፈለገ ካለ፣ ከድራፍት ወይም ከፉት ቤት ቀርቶ የድርጀት አባላት ስብሰባ ላይ አንድ ምሽት ይሰዋ፡፡ ያንን የታፈነ አየር ችሎ፣ ጫጫታውንና ንትርኩን ችሎ፣ ተጣቦ መቀመጡንና ተጋፍቶ መቆሙን ተቋቁሞ ለሶስት ወይም ለአራት ሰዓት ከቆየና በሌላ የስብሰባ ቀን ተመልሶ ለመሄድ ከዳዳው – ማለትም – ፍቃደኝነቱና ጉጉቱ ካደረበት እርሱ ፖለቲከኛ ለመሆን ስጦታው አለው፡፡ (በሌላ ፓርቲ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀስ – ሰርጎ ገብ – እንኳ ቢሆን ፖለቲካ – “እንጀራው ነው!” እንላለን፡፡)
መራጮች መቼም ቢሆን ወደ ተመራጩ/ ወደ ፖለቲከኛው አይሄዱም፡፡ እርስ ወደ እነርሱ ይሄዳል እንጂ፡፡ ያኔ፣ ታዋቂ አትሌት፣ ተዋናይ፣ ድምፃዊ ወይም የጦር ሜዳ ጀግና እያለ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው አድናቆታቸው ይገልጹለት እንዳልነበረ ሁሉ፣ ዛሬ ግን እርሱ እንዲያደንቃቸው ይሻሉ፡፡ ያሉበት ድረስ ሄዶ እንዲያነጋግራቸው ይፈልጋሉ፡፡ በእቁብ፣ በእድር፣ በሰንበቴ፣ በጁምዓ፣ በማህበር እና በተለያዩ ግብዣዎች ላይ እንዲገኝ ይጠብቃሉ፡፡ የአርበኞች ማህበራት በድል በዓል ወይም በሰማዕታት መታሰቢያ በዓላት ላይ እንዲገኝ ይፈልጋሉ፡፡ ብዙ ጠጅና ቢራ፣ ጥብስና ጥሬ ስጋ ከዳጣ ጋር እየሰነፈጠው የመክፈቻ ወይም የመዝጊያ ንግግር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
እጩው የተለያዩ የምግብ ጠረኖች በሸተቱት ቁጥር የሚያቅለሸልሸውና ወደላይ ወደላይ የሚለው ከሆነ፣ ጨጓራውን ሰፋ አርጎ መገኘት አለበት፡፡ ቢራና የፖለቲካ ስብሰባዎች ልክ እንደ በርና መቃን አይለያዩም፡፡ እጩውም በቢራው ስካር ሳይረታ የብዙ ሰዎችን ስምና መልክ የማስታወስ ችሎታ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ከጠጪዎቹ ጋር ፈለገም አልፈለገም ለምርጫው ቅስቀሳ እስከሆነ ድረስ መጠጣት አለበት፡፡ ሚዛኑን ስቶ እስከሚንገዳገድ ድረስ ቢጠጣ የነገዎቹ መራጮች አይታዘቡትም፡፡ “ከሮማውያን ጋር ስትሆን እንደሮማውያን ሁን” ነውና፡፡
ማንም ሆነ የትኛውም እጩ የግብዣና የመጠጥ ሰዓታት ዋጋ የላቸውም የሚል ከሆነ-ፖለቲከኛ አለመሆኑን ይመን፡፡ እንኳን ለሚፈልገው የኃላፊነት ቢሮና ቦታ ቀርቶ፣ እጩው ለማይፈልገውም የኃላፊነት ቢሮና ኃላፊነት ተራው ሰው ከሚያስበው በላይ ሰዓታትን ይበላል፡፡ ተቀናቃኙ የፖለቲካ ፓርቲ ጠንካራ በሆነበት የምርጫ ወረዳ ላይ ከምርጫ አስተባባሪዎችና ከደጋፊዎች ጋር ከሶስት እስከ አምስት አስቸኳይ ስብሰባዎችን ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ብዙዎቹ ስብሰባዎች የሚጀመሩት አርፍደው ነው፡፡ ከ12፡30 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን ሰዓት ባለማክበር ደግሞ የሚስተካከለን ያለ አይመስለኝም፡፡ ዘግይቶ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ የጀመረ ስብሰባ ደግሞ ከሌሊቱ ሰባት(7፡00) በፊት ያልቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የምርጫው ወቅት ሲቃረብና  እጩው ተመራጭም ሆነ የፖርቲው የአመራር አባላት አይናቸው እንደጎሽ ግት ቀልቶ፣ በእንቅልፍ እጦት ስካር ይዟቸው ረጋ ብለው መነጋገር ሲያቅታቸው ላየ ፓርቲው የሚከፈል (የሚሰነጠቅ) ሊመስል ይችላል፡፡
3.  ዝናን ማትረፍና እድለኝነት
አሁን ደግሞ፣ አንድ የምርጫ ዘመቻ ምን ያህል እንደሚያስወጣ እናያለን፡፡ መልሱም ከዜሮ እስከ ሚሊዮኖች ሊፈጅ ይችላል፡፡ በአንድ መለስተኛ የምርጫ ወረዳ ላይ ተወዳድረው ቢያሸንፉ የሚያገኙትን የአመት ደመወዝዎን ድምር ለምርጫ ቅስቀሳው ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ለእጩነት ያቀረበዎት የፖለቲካ ፓርቲም የአንድ አመት ደሞዝዎን ለምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እንዲያዋጡ ይጠይቅዎታል፡፡ ይህም ገንዘብ ፓርቲዎ ለማስታወቂያ፣ ለሕግ ጠበቃና ለመገናኛ ብዙሃን የሕትመትና የአየር ሰዓት መግዣ ፈጽሞ እንደማይበቃ ይነግርዎታል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎ የፖለቲካ ግብ ተሃድሶ አራማጅ ወይም የጥገና ለውጥ ማምጣት ቢሆን፣ ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ የትየሌሌ ገንዘብ የማሰባሰብ አቅም ያለው መሆን አለበት፡፡ ለማዕከል፣ ለክልል፣ ለዞንና ለወረዳ ጽ/ቤቶች ኪራይ፣ ለስብሰባ አዳራሾች መከራያ፣ በጋዜጦች፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በጎዳና ላይ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎችን መግዣ ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የአንድ ፓርቲ ትልቁ (ግዙፉ) ወጭ የሚሆነው፣ በምርጫው ዕለት ምርጫውን በሁሉም የምርጫው ጣቢያዎች ለሚታዘዙ የምርጫ ታዛቢዎች ክፍያ ነው፡፡ ከሶስት እስከ አምስት ታዛቢዎችን በእያንዳንዱ ፓርቲው በሚወዳደርበት የምርጫ ጣቢያ ላይ ከአንድ መቶ እስከ ሃምሳ ብር ከፍሎ የማዋል ግዴታ አለበት፡፡ ከ47 ሺህ እስከ 50 ሺህ ለሚደርሱ የምርጫ ጣቢያዎች ሶስት ሰዎች ቢኖሩ፣ ለእያንዳንዳቸውም አንድ መቶ ብር ቢከፈላቸው በ50ሺህ ጣቢያዎች ውስጥ (3 C 100 C 50,000 = 15,000,000) አስራ አምስት ሚሊዮን ብር ለምርጫው ዕለት ብቻ ፓርቲው ወጪ ያደርጋል፡፡ ይህም ወጪ የተቆጣጣሪዎችን የመጓጓዣና የፓርቲውን የጽህፈት ቤት የስልክና የተሽከርካሪዎች ኪራይ ወጪ ሳይጨምር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን ያህል ወጪ የወጣበት ምርጫም በተለያዩ እንከኖች ሳቢያ ሊሳካም ላይሳካም ይችላል ፡፡ ላለመሳካቱ ዋነኛ ምክንያቶች ሊሆኑ ከሚችሉት አንደኛው የእጩው እድለ ቢስነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእጩው ዝነኛ አለመሆን ናቸው፡፡
4.  የማስፈራሪያና የማጭበርበርያ ምልዕክቶች ወርጅብኝ
የውጭ አገር ጋዜጣ አዘጋጆች ለእጩው አስቸጋሪ ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ጋዜጣ አዘጋጆች ደግሞ የበለጡ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ አንድ የአስር ወይም የሃያ ሺህ ሳምንታዊ ሥርጭት ያለው የጋዜጣ አዘጋጅ ወኪል ወደ እጩው መጥቶ የሁለት ሺህ ወይም የአምስት ሺ ብር ግምት ያው ማስታወቂ በጋዜጣቸው ላይ እንዲያስተዋውቅ ሊይጠይቀው ይችላል፡፡ እጩው ካልተስማማ ግን በጋዜጣው የርዕስ አንቀጽ ላይ አጉዳፊ የሆነ ጽሑፍ እንደሚያትም ሊያስፈራራው ይችላሌ፡፡ በማስፈራሪው ተደናግጦ ለእሁድ እትም ጋዜጣ ማስታወቂያውን የውል ስምምነት ደብዳቤ  ወደ ፈቀደው ፖለቲከኛ ቢሮ ሸንቃጣ የሆኑ መልከኛ ሴቶችን ወይም ከረቫታቸውን አንገታቸው ላይ ያጠለቁ እሳት የላሱ ወንድ ማርኬተሮችን ይልካሉ፡፡ ሁሉም ማስታወቂያውን ከተከለከሉ በርዕስ አንቀፆቻቸው የእጩውን ሥምና ክብር የሚያጎድፍ ይዘት ያለው ዘገባ እንደሚያወጡ ይዝታሉ፡፡ እጩውን ይቀርባሉ ያሏቸውን ሰዎችም አማላጅ ይልካሉ፡፡ በመልዕክቶች የሚበረግግ እጩ ከሆኑ ለሁሉም ህትመቶች በርግጎ ወይም ተጭበርብሮ ለማስታወቂያ ይከፍላል፡፡ እነዚህ ይሉኝታ ቢስና ሀፍረተቢስ የግል ጋዜጣ አሳታሚዎችም ለፖለቲካ ቀመስ ማስታዊያዎች በእጥፍ ወይም በሦስት እጥፍ አድርገው ይቸበችቡታል፡፡ በመጨረሻም የተሻለ የከፈላቸውን እጩ ደግፈው የድጋፍ አቋማቸውን የሚንፀባርቅ (endorsement) ርዕሰ አንቀጽ ሊፅፉ ይችላል፡፡
ቆዳው ስስ የሆነ ሰው ወደ ፖለቲካው ጉራ ፈፅሞ ሊገባ አይችልም ፖለቲካ ሞት ፍቅርና ጦርነት መሳ ለመሳ የሚተያዩበት የጨዋታ ሜዳ ነው፡፡ እጩው እንኳን በእውነት ቀርቶ በሕልሙም ሊያልሟቸው የማይችላቸው ቅጥፈቶችና አስመሳይ ውሸቶች ከመዳፎቹ ወይም ከጠላቶቹ ሊሰነዝሩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እጩ ተመራጩ ከቀድሞ ሚስቱ ጋር ያለውን ሰማኒያ ሳይቀድ በመዘጋጃ ቤት ሌላ ሚስት ማግባቱን አትተው ፣ ይህም በጋብቻ ላይ ጋብቻ የመፈጸም ወንጀል መሆኑን ሊዘረዝሩ ይችላሌ፡፡ ወዲያውም ደግሞ ፣ እጩው ከትዳሩ ውጭ ሁለት የብቻ ልጆ እንዳለው ወይም እንዳላት የሚገልፅ ዜና ይፃፋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሽርጉድም ፣ ምናልባትም ፣ እጩ ተመራጩ ኃላፊነትን ለመረከብ ብቃት የለውም የሚል ትርጉም እንዲኖረው ተደርጎ በርዕሱ አንቀፆች ውስጥ ሽፋን ይሰጠዋል ፡፡ አንድ ፖለቲከኛ ለመሆንና ሕዝባዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚፈልግ ሰው ከላይ ለተጠቀሱት ማስፈራሪያዎችና ቅጥፈቶች ሊሰጥ የሚገባው መልሱ ንቆ መተው ብቻ ነው፡፡ በእጩው የወደፊት ስኬትም ሆነ ሥልጣን አይናቸውን የቆጦቆጣቸው ያቀነባበሩት ፍሬ ቢስ መሆኑን ተረድቶ ችላ ማለት ይጠቅመዋል፡፡ ወደ ፖለቲካው መድረክ የሚገሰግስ እጩ ተመራጭ አሉባልታዎችና ተራ የሥም ማጥፋት ዘገባዎች ሲያነብም ሆነ በሬድዮና በቴሌቪዡን ሲሰማ ፈፅሞ መደናገጥ የለበትም፡፡ የፖለቲከኛ ቆዳውም ሆነ ልቡ ድርብርብ ነው እንደተራው ሰው አይደለምና፡፡
5.  የፀጉር ሥንጠቃ እስከ ከቁንጫ መላላጫ
በፖለቲካው ዓለም ሙስና ፣ ጉቦ ፣ ታማኝነትም ሆነ ቃል አባይነት ያሉና የሚኖሩ ክስተቶች ናቸወ እነዚህ ኩነቶች ደግሞ በንግድ ሥራ ውስጥ የዕለት ተዕለት ገጠመኞች ናቸወ፡፡ የፖለቲካው ዓለም አደገኛ ጨረታዎችና ግብርገብነት የጎደለው ሥግብግብነቶች ይታዩበታል፡፡ አቶ ተካልኝ በሺዎች የሚቆጠር ብር ለእጩው የምርጫ ቅስቀሳ እንዲሆን ቢያዋጣ ፣ አቶ ገብሬ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚሆን ብር ሊያዋጣና የወረዳው ወይም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መሆንን ሊማፀን ይችላል፡፡ አቶ አብዱላኢ ደግሞ በመቶ ሺህዎች ብር ለምርጫው ቅስቀሳ አዋጥቶ ፣ ፖለቲካ ሳይንስ ያጠናው ልጁን ለኩዌት ወይም ለኳታር አምባሳደር ሆኖ እንዲሾምለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
በአጠቃላይ መልኩ በጣም ንቁና ፈጣን አይምሮ ያለው እጩ ፖለቲከኛ ለመዋጮዎቹና በእጁ መንሻዎቹ ሳይደናገጥና ሳይፈነድቅም ልክ እንደ ብልህ ነጋዴ ትርፍና ኪሳራውን ማስላት አለበት፡፡ እርግጥ ነው  ፖለቲከኛው ጥቂት እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ትርፍና ኪሳራው ሲያመዛዝን ይቆያል – እንደ ነጋዴውም ባይሆን ማለቴ ነው፡፡ መቼም ንቅዘት በንግድ ውስጥ የተንሰራፈውን ያህል በፖለቲካ ውስጥ አይኖርም፡፡ ለአብነትም ያህል ፣ አንድ የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ የተመረጠ ባለሥልጣን በመሥሪያ ቤት ውስጥ ያያትን ነባርና አዲስ ቅጥሮች ሁሉ ለዘመዶቹ ሲሰጥ ፓርቲው በዝምታ አያየውም፡፡ አንድ የዲሬክተሮች ቦርድ ግን የቀጠረውን ሥራ አስኪያጅ መላ ቤተሰቡን ቢሰገሥጋቸው አይቶ እንዳላየ ሊያልፈው ይችላል ፡፡ (ይህቺ ናት ንቅዘት ማለት) ነገሮችን አቻችሎ ፣ ነፍሱ በሙሉ ሳትሞስን ወይም በከፊል ሞስና ኃላፊነቱን አለመቻሉ  ብዙ ትችቶች ሊራገቡ ይችላሉ ፡፡
እጩ ተመራጩ የመጫወቻ ሜዳውን በቅጡ ለክቶና ግራ አጋቢ ያልሆነ መልሶችንና ቅሥቀሳዎችን ማድረግ አለበት፡፡ የከተማው ወይም የአገሪቱ ህዝቦች ከኑሮ ውድነትና ከዋጋ  ግሽበት  ጣጣ እንዲወጡ ፣ የዋጋ ጭማሪውን እንደሚደግፉ ወይም የውጭ ምንዛሬ ማስተካካያ ቢደረግ እንደሚደግፉ መግለፅ እና የተሻለ መንገድ መፈለግና ማመላከቱ ይሻለዋል፡፡ መቻቻል ሊያመጣ የሚችል የታወቀ ቀመር ሥላሌለ እጩው ቃልንና በተግባር ሊተረጉመው የሚያቅደውን ተግባሩን በምጥን ወይም በብዕር ስማቸው ለሚፅፉ ተናዳፊዎች በሳምንታዊ ጋዜጦች ላይ ቁርስ ምሳና እራት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
6. ከጋዜጠኞች ራስን የመጠበቅ ፋይዳ
ጋዜጦች በነፃ መንፈስ ስለፖለተከኛው ሃሳባቸውን የመግለፅ ሙሉ መብት እንዳላቸው አንድ እጩ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ መረጃዎችን ከየት እያመጡ ነው የሚፅፉት ሌላ የሚነሳ ጉዳይ ቢሆንም ከየትም ያምጡት ያፃፉት ነገር እውነት ከሆነ መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ሚድያ በብዛት የሚፈልገው መረጃ ተነባቢነቱን ሊጨምርለት የሚችል ወይም ተመልካቹን ሊጨምርለት የሚችል አነጋጋሪ የሆነ ነገር በጎም ሊሆን ይችላል መጥፎ (በብዛት ወደዚኛው ማድላታቸው ዓለም አቀፋዊ ባህሬያቸው እየሆነ በመምጣቱ) ማነፍነፋቸው አይቀርም፡፡ አንድ የማውቀው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በአንድ ወቅት ፣ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለና ጋዜጠኞች ለይተው ሳያውቁት የሚኖር ሰው ስመለከት እንዴት እንደምቀናበት ልንገርህ አልችልም ብሎኝ ነበር፡፡ ከጋዜጠኞች ጋር ቁርኝት ሳይፈጥሩ የፖለቲካ ህይወት የአደባባይ ዝና አተርፈላሁ ብሎ የሚያስብ ፖለተከኛ ካለ እርሱ የሕይወት ጥሪው ሌላ መሆኑን በግዜ ማወቅ አለበት፡፡
ለአንድ ፖለቲከኛ በአደባባይ ሕይወቱና በግል ሕይወቱ ያለውን ድንበር ማንም ሊያከብረው አይፈልግም – በተለይም ጋዜጠኞች ፡፡ የአቶ ማንትሴን የ17ዓመት ልጅ አንድ የአረብ ቱጃር ሊያገባት መሆኑ እና አባትየው አቶ ማንትሴም ተስማምተዋል፡፡ የሚል ዜና በቅዳሜ ጠዋት ዕትም ላይ ቢያነቡ አያስደንቅም፡፡ ልጅዎን መዳርም ሆነ አለመዳር የግል ሕይወትዎ ቢሆንም፤ እርስዎ የ 17 ዓመት ልጅ የመዳር መብት የለዎትምና አስራ ስምንት ዓመት እስኪሞላት ጊዜ መጠበቅ አለብዎት፡፡ እዚህ ላይ ስም ይወጣል ከቤት ይከተላል ጎረቤት የምትባል ምርጥ አባባል አይርሱ፡፡ በጋዜጣውና በጋዜጠኞቹ ላይ ሳይሆን ፣ ወደቤተሰብዎ ወይም ወደ ቅርብ ጓደኞችዎ በአንክሮ ይመልከቱ ፡፡ የወሬው ምንጮች እነርሱ ናቸው እና፡፡
የጋዜጣ አዘጋጅ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ አንድን የአደባባይ ሰው (public man) ሊጣላው ይችላል፡፡ ስለዚህም የሆነ የማጭበርበሪያ የተቀላቀለበት የግላዊ ህይወቱን የሚመለከት ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ ከዚያም በትክክል የመለሰውን ሳይሆን ያስተባበለውን ወይም የካደውን ብቻ መርጦ ሊያትም ይችላል፡፡ ከዚያም ፣ አንድ ቀን የአዘጋጁ ጋዜጣ የሚከተለውን የፊት ለፊት ዜና ይዞ ሊወጣ ይችላል፡፡ እርሶ ለገበያ ቀርበዋልና፡፡
ለምሳሌ፡ ‘የእከሌ ድርጅት ሊቀመንበር ከባለቤታቸው ጋር ሊፋቱ እንደሚችሉ ገለፁ፡፡’ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ሌላው ጋዜጣ ‘የእከሌ ድርጅት ሊቀመንበር የመጨረሻ ልጅ ከአንዲት የ40 ዓመት ባልቴት ጋር ፍቅር ይዞታል ተባለ፡፡’ በሌላኛው ቀን ደግሞ ‘አንዲት የኮሌጅ ተማሪ የፍቅር ደብዳቤ ፃፈችልኝ ሲሊ ለቅርብ ሰዎቻቸው የእከሌ ድርጅት ሊቀመንበር ተናገሩ’ ተብሎ ቢወጣ፣ ፈፅሞ መርበድበድ ወይም ማስተባበያም መስጠት አይገባም፡፡ ትክክለኛው መልስ ሆድ ይፍጀው ነው፡፡ (ልክ እንደጥላሁን! አንገቱን አሳርዶ ሆድ ይፈጀው ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ የምን ጨሰ-አቧራው ጨሰ ነው ደግሞ!)
Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 20, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.