አርቲስቶቹ ወዴት እያመሩ ነው? አንተነህ ዘውዴ (ቶኪዮ)

አንዳንዴ የምናደርገው እና የምንጠይቀው ነገር ተገቢ እና ትዝብት ላይ የማይጥለን መሆኑን ማወቅ ግድ ይለናል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስመ ጥር የሆኑ አርቲስቶች እና ሙዚቀኞች የሚያሳዩት ባህሪ እና መገኛ ቦታቸው አዲስ እና ያልነበረ ስብእናቸውን እየገለጠው ቢገርመኝ ነው ይህን ትዝብቴን እንድሰነዝር ግድ ያለኝ።
ከሰለሞን ተካልኝ እስከ ነዋይ ደበበ የሰሞንኛ አሳዛኝ ትእይንት ድረስ ያለውን አስገራሚ ድራማ እኔም ካለፍኩበት ሁኔታ ጋር አገናኝቼ ወደ ኋላ እንዳይ ግድ ብሎኛል። እርግጥ እኔ ቀድሞ እሰራበት በነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የነበረውን እውነታ ( ዛሬም ድረስ ያለ) ለሚያውቅ የሰሞኑን የነዋይ ደበበን አቤቱታ ስቆ እና ታዝቦ ከማለፍ ሌላ አማራጭ አይኖረውም። እኔን ጨምሮ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው ነዋይ ደበበ “ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙዚቃዬን ያለ እውቅናዬ ተጠቅመውበታል። ፍርድ ቤት እገትራቸዋለሁ ። “ ማለቱን ተከትሎ ስሙ ከፍ ዝቅ ማለት ጀምሯል።

ነዋይ ዛሬ እንዴት እንደተገለጸለት ባይገባኝም ሙዚቃዎቹን ከማጫወት ከከለከሉት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወይም አሽቃባጭ ትንንሽ አነፍናፊዎች ተግባር አንጻር ግን እያደረገ ያለው ነገር ተገቢ አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ይመራኛል። ይህን ያልኩትም ከመሬት ተነስቼ አይደለም። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዋናው ጣቢያ ፣ በኤፍ.ኤም 97.1 እና በኢቲቪም ጭምር ሙዚቃቸው እንዳይጫወት ከተከለከሉት ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ እንደነበር ስለማውቅ ነው። ከሃገር ቤት ከወጣሁ አራት አመታት ቢያልፉኝም ዛሬም አሰራሩ እንዳለ እንደሆነ አውቃለሁ። የቴዎድሮስ ካሳሁንን፡(ካብ ዳህላክ) ፣ የአስቴር አወቀን( አንድ አድርገን) ፣ እና ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሱ እና አንድነትን የሚሰብኩ ዜማዎችን ማጫወት የማሪያም ጠላት ያሰኝ ነበር። ምናልባትም አሁንም ድረስ በሃገር ቤት ሆነው ይህንን እየተገበሩ ያሉ ዲጄዎች እና ጋዜጠኞች ቋሚ ምስክሮች ናቸው። እኔ እስከማውቀው ድረስ የነዋይ ደበበ ሃገሬን አልረሳም ዜማም ከተከልካዮቹ መካከል የገባ ነበር።

እንደውም ነዋይ ቢገባው ተቃዋሚዎች እኮ ቦታ ሰጥተውት እና የዜማዎቹን መልእት ጠንቅቀው ስለተረዱለት ነው ደጋግመው ያጫወቱለት። ሃገሬን አልረሳም ማለቱም ሃገሩን መውደዱን ያሳያል ከሚል እንጂ ነዋይ ይደግፈናል ወይም ይረዳናል በሚል አንደምታ እንዳልተጠቀሙበት ማሰብ የጠፈር ሳይንስ ያህል ከባድ አይደለም። ታዲያ ነዋይን ያዙኝ ልቀቁኝ ያስባለው ምንድነው? ምንን ምን ቢመራው …የሚለውን ተረት እንድናስታውስ ግድ ይለናል። እንኳን ያዜመው ዜማ ቀርቶ ራሱ ነዋይስ የተቃዋሚው መንደርተኛ አልነበር እንዴ? እውነትም አዲስ አበባ ያለው አየር ተበላሽቷል። ስንቶች እንደምታውቁ ባይገባኝም ወደ አድማጭ የሚደርሱ ዘፈኖችን ሳንሱር ማስደረግ የሚወስደውን ጊዜ ያለፉበት ያውቁታል። እንደውም ነዋይ ደበበ እና ዘፈኖቹ ላይ ያለው ፈተና ያስገርማል። እስኪ ይሁን ……እስኪሰለችህ ድረስ እነ ኢቲቪ ዘፈንህን ያስኮመኩሙልሃል ።( ብዙ የሚሰማቸው ባይኖርም) …እርግጠኛ ሆኜ ልናገር የምችለው ጉዳይ ግን የቀድሞዎቹ የበላይ አለቆቼ “ ኢትዮጵያን የሚያወድስ” ዘፈንህን ለማጫወት አሁንም ይጎረብጣቸዋል።
ዛሬ ይህን አስገራሚ አስተያየትህን እንድናደምጥ የገፋፉህ የጊዜው ወዳጆችህ ባስ ካለ ደግሞ ” ማንም ስለ ሃገር ያዜምኩትን ዜማ እንዳያደምጥ ይከልከልልኝ” በል እንዳይሉህ ሰጋሁ። ሙዚቃ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚል መጣጥፍ ከዚህ ቀደም ስሞነጫጭር እንደው ነካ ነካ አድርጌ ያለፍኩትን ጉዳይ እድሜ ለነዋይ ደበበ ተመለስኩበት። በየትኛውም ዘርፍ ላለ ባለሙያ ክብሩ እና ማእረጉ ባለበት ህብረተሰብ ውስጥ ለሙያው የሚሰጠው ቦት እና ተቀባይነት ያልተሸራረፈ መሆኑ ነው። ራሱ ነዋይ የማይክደው እውነታ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘፈኖቹን ሁሉንም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ይወዳቸዋል። በታለይ ስለ ኢትዮጵያ ያዜመው “ ሃገሬን አልረሳም “ ዜማው አያከራክርም ። ይህን ዜማ ደግሞ በሬዲዮም ሆነ በኢቲቪ ማጫወት በተለይ በምርጫ ወቅት በባለስልጣናት ተከልክሏል። የማያጠያይቅ ምክንያቱ ደግሞ የሰዉን ስሜት ኮርኩሮ የተዳፈነ ብሶቱን እንዳያግመው ነው። ተቃዋሚዎች ደግሞ የእናት ሃገር ፍቅርን ይገልጻል ብለው አመኑና ዜማውን ተጠቀሙበት። እንደ እኔ እንደ እኔ ነዋይ ተቃዋሚዎቹን እጅ መንሳት ይጠበቅበት ነበር ። አሳፋሪ አስተያየቱን ከሚያስደምጥ ይልቅ..

መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በተለይ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች እና ዘፋኞች ከወቅታዊው የሃገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ባህሪያቸውም እንዲሁ የሚገለባበጥ ሆኗል። የነዋይ ደበበ አስተያየት አስደምሞን ሳናበቃ ፍቃዱ ተክለማሪያም፣ እመቤት ወልደገብሬል፣ እንዲሁም ሃረገወይን አሰፋ ደግሞ የበረከት ስምኦን ፍብረካ የሆነው (የሁለት ምርጫዎች ወግ) መጥሃፍን አንብበን ተመስጠናል..መመሰጥ ብቻም ሳይሆን ከተመሰጥንበት ጉዳይ ውስጥ እናካፍላችሁ ብለውን በመጽሃፉ ምረቃ እለት መድረክ ላይ ተሰቅለዋል። ማን ያውቃል እንደውም መጽሃፉ ሳይታተም በፊት ረቂቁን እንዲያዩ እና ፍቅራቸውን እያጎለበቱ እስከምርቃቱ ቆይተው ይሆናል ። አልነገሩን ይሆናል እንጂ….እንደውም እኮ ሼኩ ያላነበቡትን መጽሃፍ ለቀጣዩ ትውልድ የዴሞክራሲ ምንነትን የሚያስተምር ማለታቸውን መታዘቡን ረፖርተር አስነብቦናል ። አርቲስቶቹም ሆኖ ሙዚቀኞቹ እንደሌላው የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ የፈለጉትን የመደገፍ እና የመቃወም መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ መንታ ሆነው መታየታቸው አስተዛዛቢ ነው። አንድ የፌስቡክ ወዳጄ ያካፈለኝን አስተያየት እዚህ ጋር መጥቀስ ወደድኩ “ እውነት ይሄ በብሄራዊ ትያትር መድረክ ላይ አጼ ቴዎድሮስን ሆኖ የሰራው ፍቃዱ ተክለማሪያም ነው ወይስ ሌላ ?” ሲል ነበር የሚወደውን አርቲስት ምን እንደነካበት የገለጸልኝ።

ሰለሞን ተካልኝ የቁርጥ ቀን ወንድሙ እና ሚዜው የነበረውን ታማኝ በየነን “ ያልገባው” ሲል የሚገልጽበት ቃል ምናልባት አዲስ አበቤዎቹን አርቲስቶች( እነ ነዋይ እና እመቤትን) ገብቷቸዋል። ስለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት እና እኩልነት ከመጮህ ይልቅ ከገዳዮች ጋር ተሰልፎ ሆድን መሙላት እና በጊዜያዊ ምቾት ራስን ማታለል እና ህሊናን መሸጥ እርኩሰት እና ሌብነት ብሎም ከሃዲነት “የገባቸው” ፍጡራን መገለጫ ነው። በዚህ መልኩ ከታየ እውነትም ታማኝም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት እና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ባለቤትነት የሚጮሁ ሁሉ ባይገባቸው አልገረምም። የገባው ተብሎ ለመፈረጅ ከሃዲ መሆን እና ማጎብደድ ግድ ከሆነ “ ያልገባው “ መባል ጽድቅ ነው።

ቸር እንሰንብት…..

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 29, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.