አምባገነን መሪዎች የሚያሳድሩብንን ፍርሃት እንዴት መቋቋም እንችላለን?

የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች ፍርሃት አንድ ነገር አደጋ ሊያደርስብን ይችል ይሆናል፤ ከሚል ግምት የተነሳ የድንጋጤ መንፈስ ስያድርብን የሚሰማን ስሜት ነው ይላሉ። ብዙ ጊዜ ፍርሃት የሚነሳው ከተለያዩ ውጭያዊ ክስተቶችና በተፈጥሮ ካለብን የዝርያ ጸባይ (external traumatic events and internal predisposition such as heredity and genetics) ጋር የተያያዘ ነውም ይላሉ። የፍርሃት ስሜትን ሊያስነሱ የሚችሉ ምክንያቶች እጅግ ብዙ ከመሆናቸውም በላይ አሁንም በየወቅቱ ይተለያዩ
መንስኤዎች እየተገኙ ነው።

የተለያዩ የፍርሃት አይነቶች ቢኖሩም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ግን በአገራችን በጣም የተንሰራፋውን የአምባገነን መንግስትን እጅግ አድርጎ የመፍራት ስሜት ከምን ሊመጣ እንደቻለና እንዴትስ ሊወገድ እንደሚችል በአጭሩ ለመግለጽና እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸውን በጉዳዩ ሰፋ ያለ መረጃ እንዲያቀርቡ ለመጋበዝ ነው። ይህ ጽሁፍ ቤን ፍሪት The subjugation of the people of Zimbabwe for the sake of political power by Ben Freeth ከሚለው የድረ-ገፅ አንቀጽ በአብዛኛው የተቀዳ ነው (1)።

እንደ ሚስተር ፍሪት ከሆነ በአለም ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ሶስት ነገሮችን ይፈራል። በመጀመርያ የሰው ልጆች የራሳቸውን ወይም የቅርብ ዘመዶቻቸውን ህይወት ሊያጠፋ ወይም የአካል ጉዳት ልያደርስ የሚችል ነገር ነው ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ነገር ይፈራሉ። እንዲህ ያለው ፍርሃት በህዝብ ማህከል ከተንሰራፋ ሰዎች የሚውስዱት እርምጃ፤ ሲሆን ከአደጋው መሸሽና መጥፋት አለበለዚያም ሥርዓቱን የተቀበሉ መስሎ ማደርን ይመርጣሉ። ይህም ሁኔታ ሥርዓቱ ያለምንም ተሃቅቦ እንዲቀጥል ያደርገዋል። በአገራችን እንደታየው በደርግ ጊዜም ይሁን በወያኔ ሥርዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አምባገነኖችን ከመጋፈጥ ይልቅ አገርን
ጥሎ መሰደድን መርጠዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ሰዎች የስራ ወይም የንግድ ተቋሟቸው እንዲሁም ሠርተው ያፈሩት ንብረታቸው ሊገታባቸው ወይም ሊወሰድባቸው እንድሚችል ሲያውቁ ፍርሃት ያድርባቸዋል። በአገራችን እንደሚታየው ብዙዎች የንግዱ ማህረሰብ አባላት ወያኔን ከመጋፈጥ ይልቅ መንግስት በየውቅቱ የሚጠይቀውን የተለያየ የገንዘብ እርዳታ
ጥያቄ እየከፈሉ መኖርን መርጠዋል።

ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የንግዱ ማህረሰብ በእናት አገር ጥሪ መፈክር ስር ለተደረገው የገንዘብ ስብሰባ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በቅርቡም ለህዳሴ ግድብ በሚል አዲስ መፈክር ስር ተመሳሳይ አስተዋጽኦ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው እያደረገም ነው። እንደዚህ ያለው ሁኔታ የአምባገነኖችን ክንድ ያጠነክራል፤ ጭቆናውም እንዲቀጥል አምባገነኖችን ያበረታታል። መጨረሻው ግን እራሱን ለጋሺውን ጭምር የሚያጠፋ ይሆናል። ዊኒስተን ቸርችል የተባሉት የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ይህን በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡ “እኔን በመጨረሻ ቢበላኝ ይሻላል ከሚል አጉል ተስፋ የተነሳ ሊሎችን ለአዞ ቀለብ ማድረግን መምረጥ ነው” “feeding the crocodile and hoping you would be the last to be eaten.”

በሶስተኛ ደረጃ ሰዎች ማንኛውንም በሃይል ነጻነታቸውንና መብታቸውን የሚገድብን ኃይል በእጅጉ የፈራሉ። የሚገደበው መብት በሰላም ሰርቶ መግባትን፤ በልቶ ማደርን እንዲሁም በነጻ የመንቀሳቀስን መብትን ሁሉ ያካትታል። እንደሚታወቀው በአገራችን የተንሰራፋው ያአንድ ግለሰብ አገዛዝ የዜጎችን ነጻነት በእሥር በመገበድ የታወቀ ነው። በተለይም አስከፊ የሆነው የወያኔ እስር ቤት የዜጎችን ጤንነት በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ህመም መሸመቻ ቤት (ፕሮፌሰር አሥራትን ያስታውሷል) በመሆኑ ዜጎች በእጅጉ እንደሚፈሩት የታወቀ ነው።

የወያኔ መንግስት በራሱ ህገመንግስት ላይ የሰፈረውን የዜጎች መብት እንኳን ሳይቀር ባለማክበር ብዙሃን ጋዜጠኞችን፤ የሰባዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦችን እንዲሁም በንግዱ መስመር እንኳን የተፎካከሩትን ነጋዴዎች ሁሉ ሳይቀር ወህኒ እያወረደ ህዝብን በማስፈራራት ያለገደብ ለመግዛት አልሞ የተነሳ ሥርዓት ነው። እንግዲህ አምባገነኖች ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት የፍርሃት መንስኤዎች በመጠቀም በስፋት በዜጎች ላይ ተጸኖ እንዲአሳድሩ ካደረጉ፤ ህዝብን ጨቁኖ የመግዛት እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍርሃት ውስጥ ያለ ዜጋ ከታዘዘው ውጭ ምንም ነገር ለማድረግ አይሻም። ነገር ግን ህዝብን እንዲህ ባለ የፍርሃት ውጥመድ ለማስገባት አምባገነኖች ህሊናቸውን የሸጡና ሆዳም፤ ታማኝነታቸው የተረጋገጠ አባሪ ተባባሪ ይሻሉ (እነበረከት ሥመኦንን አነሽመልስ ከማልን እነሳሞራን ልብ ይሏል)

አምባገነኖች የሚከተሉት አሰራር ስህተት መሆኑን እያወቁ ተበባሪዎቻቸው በዜጎች ላይ በደል እንድያደርሱ አራት መሰረታዊ መንገዶችን የጠቀማሉ፡፡ የመጀመርያው መንገድ ተባባሪዎቻቸውን በአጉል ፍልስፍና ወይም ረእዮተ ዓለም ፕሮፓጋንዳ በመሙላት የሚያደርጉት እኩይ ተግባር ሁሉ “ታላቅ” የሆነውን ይህን ፍልስፍና ግቡን እንዲመታ እንደሚረዳ በማሳመን ነው። ስለሆነም ይህንን ፍልስፍና የማይደግፍ ዜጋ ሁሉ የጥቃት እርምጃ እንዲወሰድበት የገፋፋሉ። አሁን ባለንበት የአምባገነን ሥርዓት አቶ መለስ ወደ አትዮጵያ የከለሱት አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተባለው ጉልድፍ ፍልስፍና በጭቆና መሳርያነት ያገለግላል።

የናዚ ፓርቲ በጀርመን ውስጥ ከፍተኛ ስኬት ያገኘው የጀርመንን ህዝብ ከሌሎች ይተሻለ ገዢ ዘር እንደሆነና ሌሎችን በተገዢነት በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ለተገዢው ህዝብ ደህንነትን ሊያመጣ እንደሚችል ጀርመኖችን በማሳመኑ ነው። (አንባቢ ይህን የናዚ ፍልስፍና ከTPLF የትግራይ የበላይነት ከሚለው ያልታወጀ ነገር ግን በሥራ ላይ በግልጽ እየተገበረ ያለውን ሁኔታ ያገናዝብ። ለምሳሌ ያህል የደህንነት ሥራ፤ የመከላከያ ሥራ አንዲሁም ሌሎች ቁልፍ የፖለቲካና የንዋይ መገኛ ቦታዎች በአንድ ዘር ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መጥቀስ ይቻላል)።

ለዚህ ፕሮፓጋንዳና የውሸት ሥራ እንዲጠቅም አምባገነኖች መገናኛ ብዙሃንን በቆጥጥር ሥር በማዋል
ነጻ ሚዲያዎችን ጨርሰው ያጠፋሉ። ሂትለር “ውሸት በበዛ ቁጥር ታአማኒነቱ ይጨምራል” ይል ነበር። በተጨማሪም አባላቶቻቸውን የሌለ ጠላት በመፍጠር ሁል ጊዜም ቢሆን በግልና በነጻነት እንዳያስቡ ያደርጋሉ። ለሂትለር ዋነኛው የጀርመን ጠላት የአይሁድ ዘር ነበር፤ ለዚምባብዌ የነጭ ዘር ሁሉ እንደጠላት የተወሰደበት ሁኔታ ነበር። በአገራችን ደግሞ በመጀመርያ ያአማራው ዘር ለኢትዮጵያ ጠር እንደነበር ሲነገር ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ የአሮሞ ህብረተሰብ በዋነኛ ጠላትነት እይተፈረጀ ነው።

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የሰውን ለራስ የማድላት ጸባይን በመጠቀም መደለል ነው። ይህም የሚሆነው በግፍ አሰራር ከተዘረፈው ሐብትና ንብረት ላይ ለዋነኛ አባላቱ በማካፈል ነው። ማንኛውም አይነት የመበልጸግያ መንገድ ህጋዊም ሆነ ህገወጥ ለሥርዓቱ አራማጆች ክፍት ነው። በበረባርሶ ጫማ አዲስ አበባ የገቡት የነጻ አውጭዎች ዛሬ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ንብረት ባለቤት ሆነዋል። ይህንን የእነሱን መክበር ከዳር ሆነው የተመለከቱ ሆድ አደሮች ደግሞ እራሳቸውን በፈቃደኝነት ለሥርዓቱ አስገዝተዋል። እንደነዚህ ያሉ ሆዳሞች አንድ ጊዜ በግፍ ከተዘፈቁ ቦሃላ ያላቸው ምርጫ የአምባገነኑ ሥርዓት እንዲቀጥል ዘወትር መታተር ይሆናል።

ሦስትኛውና መንገድ በአገራችን በሰፊው እየተስራበት ያለው ህዝብን ዘወትር ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ ጨቁኖ መያዝ ነው። የራበው ህዝብ የመጀመርያ ጥያቄው የሚቀጥለው ምሳ ከየት ይገኛል ነው እንጂ ሥርዓቱን መዋጋት አይደለም። በተጨማሪም ህዝብን በረሃብ በማሰቃይት እንዲዳከምና ስርአቱን የመዋጋት አቅሙን መስበር የአምባገነኖች ዓይነተኛ መሳርያ ነው። የኦጋዴንን ህዝብ ወያኔ እንዴት አድርጎ በረሃብ እየቀጣው መሆኑን ለአንባብያን ማስረዳት ቀባሪን እንዳማርዳት ይቆጠራል።

አራተኛው የጭቆና ማስፈኛ መንገድ ደግሞ ታዳጊ ዜጎችን የውሸት ፍልስፍናን መከተብና ወጣቱ ለአገሩና ለፍትህ እንዳያስብ ማድረግ ነው (damning down the youth). ይህ መንገድ በአገራችን በሰፊው እየተሰራበት ነው። ወጣቱን ጎጠኛ እንዲሆንና በሰፊው እንዳያሳብ ተደርጎ በተዘጋጀ የትምህርት ካሪኩለም ተወጥሮአል። ትምህርቱንም ቢጨርስ እንኳን በስራ ሊተገብረው የማችልበት ሥርዓት ውስጥ ስለሚገኝ ከድህነት ዓለም መውጣት አይችልም። ይህም ሁኔታ ወጣቱን በሆዱ ለመግዛት እንዲቻል ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።

አምባገነኖችን እንዴት ልንዋጋ እንችላለን?
አምባገነኖች ሀዝብን በፍርሃት ወጥመድ ውስጥ ማስገባት የሚፈልጉበት ዋነኛው ምክንያት እራሳቸው ፈሪ ስለሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ አጥብቀው የሚፈሩት ነገር ደግም እውነትን ነው። ሀዝብ ከፍተኛ የሆነና አምባገነኖችን ገርስሶ መጣል የሚችል አቅም እንዳለው እውነት ነው። አምባገነኖች ይህን ሀቅ አጥብቀው ይፈራሉ።
የሰሩትና እየሰሩ ያሉት የህዝብ ማጥፋት ወንጀልና የዘረፋ ታሪክ እውነቱ እንዳይውጣ ይፈራሉ። ይህን ማስተዋል ከባድ አይደለም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ መንግስት የነጻ ሚዲያ በሃገሪቷ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ወደ አገር ቤት የሚተላልፉ የነጻ ሚዲያዎችን (የአሜሪካንና የጀርመንን ድምጽ ሳይቀር) አጥብቆ
የሚዋጋው።

ስለዚህ በተቃዋሚነት የተሰለፈ ማንኛውም ድርጅት ወያኔን እጅግ መጉዳት ከፈለገ ነጻና እውነተኛ ኢንፎርሜሽን በህዝብ መሃል እንዳይታወቅ በሰፊው መስራት ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን ይገባዋል። በነጻው ዓለም የሚኖር የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ግለሰብ ደግሞ ለነጻ ሚድያ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በተቻለ አቅም በገንዘብና በሀሳብ መደገፍ ግዴታው ነው።

ከዚህ በመቀጠል ሊሰራ የሚገባው ስራ ደግሞ የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶችን በአንድ የጋራ ዓላማ ስር በመስተባበር ሃይልን ማጠንከር ነው። የአምባገነኖች አንድ የጭቆና መሳርያ “ከፈፍለህ ግዛ” የሚለው ፖሊሲ መሆኑ እየታወቀ የኔ ድርጅት ከእገሌ ድርጅት የተሻለ ስልሆነ ብቻዬን ታግዬ አቸንፋለሁ የሚል ዓላማ ከአላቸው
እንደንዚህ ያሉ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ቢይዙም እንኳን እራሳቸው አምባገነን ከመሆን አይመለሱም። የድርጅት አባላት ድርጅቶቻቸውን ወደ አንድ የጋራ መድረክ እንዲደርሱ መገፋፋት ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል።

ስለድርጅት ስናወራ መርሳት የሌለብን ጉዳይ ቢኖር የሃይማኖት ድርጅቶችን ነው። የሃይማኖት ድርጅቶች ከየትኛውም ድርጅት የበለጠ አባላት አሏቸው። የሃይማኖት ድርጅቶችን ወደተቃዋሚው ጎራ ማስገባት መቻል የትግሉን ውጤት ያፋጥነዋል። ነገር ግን ብዙ የዘመናችን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች የሃይማኖት ድርጅቶችን ሚና አጥብቀው ለመጠቀም አይሞክሩም። ይህም ደግሞ የሃይማኖት ተከታዮች በዚህ አለም ላይ ለሚደረገው ቀውስ ፈጣሪ ብቻ መፍትሄ እንደሚሰጠው አድርገው ስለሚቆጥሩ ተደራጅቶ መታገልን አይፈቅዱም ከሚል የተሳሳተ እምነት የተነሳ ነው። ነገር ግን የእስልምናም ሆነ የ ክርስትና ህይማኖት ግፍን አጥብቀው ይጠላሉ።

ለምሳሌ ቁራን ስለ መጥፎዎች ሲናገር ፡ “እግዚአብሄር ሰዎችን ተጠቅሞ መጥፎዎችን ባያጠፋ ኖሮ ምድር በክፋት ትሞላ ነበር” ይላል (2)። ይህ የሚይስረዳው እግዚአብሄር ግፍን ለማስወገድ ሰዎችን እንደሚጠቀም ነው። “ሰዎች” የሚለው ቃል የሃይማኖት ተከታዮችንም የጨምራል።

ሌላው መረሳት የሌለበት ትልቅ ጉዳይ ደግሞ የአምባገነኖች ድርጅቶችን ነው። ተቃዋሚ ድርጅቶች አባላቶቻቸውን በአምባገነኑ ድርጅቶችና ተቋሞች ውስጥ መሰግሰግ መቻል አለባቸው። ይህም ሁኔታ የራሱን የአምባገነኑን መዋቅሮች ለትግሉ መጠቀሚያ ለማድረግ ያስችላል። አልፎም የአምባገነኑን ታክቲኮች ገልብጦ አስፈላጊ በሆነው ቦታና ጊዜ መጠቅም መቻል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንደኛው የወያኔ ታክቲክ ተቃዋሚዎች ድርጅት ሲመሰርቱ ወያኔም ያንኑ የመሰለ ድርጅት አቋቁሞ እውነተኛ ታቃዋሚ የሆነውን ድርጅት ማዳከም ነው። በቅርቡ
እንደሰማነው የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ድርጅትም በወያኔዎች መጠቀሚያ እየተደረገ መሆኑን ነው። ይህን ለመዋጋት አንደኛው ዘዴ ተጠሪነቱ በሰሜን አሜሪካ ላሉ ኢትዮጵያኖች የሆነ ሌላ ተመሳሳይ ድርጅት ማቋቋም ነው።

እንዲያውም ይህንን የእግር ኳስ በዓል በቅርቡ ከተቋቋመው የኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርስ በዓል (Ethiopian Heritage Festival in North America) ጋር በማጣመድ ትልቅ የሆነ ኢትዮጵያዊነትን የሚአንጸባርቅ ዝግጅት እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

ከዚህ በመቀጠል የተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝብን ማደራጀት ይኖርባቸዋል። እውነትን በተገኘው ሚዲያ ለህዝብ ካስጨበጥን ሕዝብን ለማደራጅት ከባድ አይሆንም። በመጨረሻም መደረግ የሚገባው ነገር ቢኖር የዲፕሎማሲያዊ ስራ ነው። ምንም እንኳን የዚህ ስራ ውጤት አድካሚና ውስብስብ ቢሆንም የተቃዋሚ ድርጅቶች ቢያንስ ቢያንስ በህዝብ ላይ የሚደረገውን ግፍ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ማሳወቅ ይገባቸዋል።

ፍርሀትን እንዴት ልናስወግድ እንችላለን?
መጽሀፍ ቅዱስ ሁለት አይነት ፍርሀት እንዳለ ይናገራል። የመጀመርያው ፈጣሪን መፍራት ሲሆን ይህም የአምላክን ታላቅነት ብቻ ሳይሆን የሀጢያት ጥላቻው ሊቋቋሙት የማይቻለውን ቁጣውን እንደሚያመጣ አውቆ በቅንነት መኖርን መምረጥን ጭምር ነው። እግዚአብሄርን መፍራት የጥበብ ሁሉ መጀመርያ ናት።

ይህ ማለት አንድ ስው ከራሱ በላይ የሆነ የሚፈርድ አካል እንዳለ በማወቅ በሌሎች ላይ የግፍ ቀምበርን ከመጫን መቆጠብን ያስተምራል። የዚህ ዓይነቱ ፍርሀት በቅንነት ላይ የተመሰረት ስለሆነ በእጅጉ ሊበረታታ ይገባል። ሁለተኛው ፍርሃት ደግሞ “የፍርሐት መንፈስ” የተባለው የፍርሐት ዓይነት ሲሆን ይህም ደግም ሊወገድ የሚገባው መሆኑን ያስተምራል።

የፍርሐት መንፈስ ከእግዚያብሄር የተሰጠ ሳይሆን የሰይጣን መጠቀሚያ መሳርያ ነው። ስይጣንም “ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣምና” ዮሐ 10:10።

ነገር ግን የእግዚአብሄር ስጦታ “የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም” 2 ጢሞ. 1:7። በመሆኑም መጽሀፍ ቅዱስ ስለፍርሐት የሚከተለውን ያስተምራል።

1. ፍርሐት መንፈስ ነው
2. ፍርሐት ከእግዚአብሄር የተሰጠ አይደለም
3. ፍርሐትን ለመዋጋት በጽድቅ መመላለስንና በእግዚአብሄር መተማመንን ተገን ማድረግ ይስፈልጋል።

በጽድቅ መመላለስ ማለት ለእውነት መዋጋትን፡ ለፍትህ መቆምን፡ ረዳት የሌለውን መርዳትን ሁሉ ይጨምራል። በእግዚአብሄር መተማመን ደግሞ ሰው ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጭ ምንም አይነት ጉዳት ሊያደርስብን እንደማይችል ያስተምረናል።

ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፡ “በእግዚአብሔር ስለታመንሁ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?” ዳዊት 56:10። ራሱ እግዚአብሄርም ከፍርሕት እንድንርቅ አጥብቆ እንዲህ በማለት ይመክረናል፡ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል። የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ እግዚአብሔር።
አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና።” ኢሳ 41:10-13

ኢትዮጵያን በመግዛት ላይ ያለው አገዛዝ ይህንን ሀቅ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ህዝቡ በአምላኩ ላይ እንዳይተማመን የተለያዩ ዘዴውችን ይጠቀማል። በመጀመርያ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማትን በበላይነት በመቆጣጠር የውሸት ትምህርት ማስፋፋት ነው። ለዚህም በስልጣን ላይ ያሉትን የእስልምናም ሆነ የክርስትና ሃይማኖት መሪዎችን ሥራ መታዘብ ይቻላል። በተጨማሪም እንደ ማህበረ ቅዱሳን ያሉ የስራአቱ ደጋፊዎች ምን ያህል ምእመናኑን እይከፋፈሉት መሆኑን ማስረዳት ቀባሪን ማርዳት ነው። ሁለተኛው ዘዴ ደግም የባእድ አምልኮን ማስፋፋት ሲሆን የዚህም አምልኮ ተቀዳሚ ተዋናይ ብዙ የጠንቋይ አማካሪ እንዳላችው የሚታሙት የስርአቱ ቁንጮ የሆነው እራሱ መለሰ ዜናዊና ባለቤቱ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ የጠንቋይ መጫወቻ ከሆነ ውሎ አድሯል። አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ጠንቋዮች እንደ ዳኛና ፍርድ ቤት ሆነውም እያገለገሉ ነው። በእነዚ ቦታዎች
ባለጋራዎ ከጠንቋይ ቤት አጽፎ ለፍርድ ጠንቋዩ ጋር እንዲቀርቡ የክስ ወረቀት ቢያመጣልዎ የሚገርም አይደለም። ይህ የሚያሳየው በሃገራችን ምን ያህል ስርአተ አልበኝነት እንደነገስ ነው።

ይህን ሁሉ ስርአተ አልበኝነትና የፍትህ መዛባትን ለመዋጋት በመጀመርያ በራሳችን መረዳት ሳይሆን እግዚአብሄርን በመተማመን፤ በእኛ ጥበብ ሳይሆን በእግዚያብሄር እውቀት ላይ በመንተራስ ከተጓዝን ምን ጊዜም እናቸንፋለን ምክንያቱም ሰውን አንፈራምና።

በፈረንጆች አቆጣጠር 2005 ላይ ተደርጎ በነበረው ምርጫ ተከትሎ የተነሳውን ግርግር በሰላም እንዲፈታ የሃይማኖት ተከታዮች ያቀረቡትን የፀሎት ጥያቄ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንዴት እንዳስቆመው የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ እራሱ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው። በዚያን ወቅት ከአባ ጳውሎስ ጽህፈት ቤት የወጣ ፀሎት እንዳይደረግ የሚያትት ትእዛዝ በየቤተክርስትያኑ የአጥር በር ላይ ተለጥፎ ነበር።

ከፍርሀት ለመላቀቅ በእግዚአብሄር ይተማመኑ።
አቶ እሥክንድር ነጋ “አምባገነንነትን ከኮምፒውተርዎ ላይ ሆነው ይዋጉ!”
እንደሚሉት፡ እኔ ደግሞ “አምባገነንነትን ዘወትር በፀሎትም ይዋጉት!” እላለሁ።
ውጤቱ ያስገርምዎታል።
_______________
ምንጭ፡
1. http://www.swradioafrica.com/pages/subjugation100310.htm ይህ
ጽሁፍ አምባገነኖች ምን ያህል ተመሳሳይ ታክቲክ እንደሚጠቀሙ በግልጽ ያሳያል።
2. The Quran, English Translation: Maulana Wahiduddin Khan 2009: The Heifer 2:251, Pg. 30__

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 20, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.