አማረ አረጋዊ ክፉኛ መደብደቡ ተሰማ

የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ የሆነው አማረ አረጋዊ ሰሞኑን ቦሌ አካባቢ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታቁ ሰዎች ክፉኛ መደብደቡ ተሰማ። የኢትዮ ፎረም ምንጮች ከስፍራው ያደረሱን ዘገባ እንደሚያረጋግጠው፤ ጭንቅለቀቱ አካባቢ በደረሰበት ከፍ ያለ ድብደባ ብዙ ደም የፈሰሰው አማረ አረጋዊ፤ ራሱን በመሳቱ ሀያት ሆስፒታል ተኝቶ ህክምና እየተከታተለ ይገኛል።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሀት አባል፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ ደግሞ ፤በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ፣ቀጥሎ የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረው አማረ አረጋዊ፤ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት የነበረውን ሀላፊነት በመልቀቅ ሪፖርተር ጋዜጣን መስርቶ በበላይነት ሲያስተዳድር ቆይቷል።

በሚዛናዊነቱና በጠንካራ ዘገባዎቹ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው ሪፖርተር ጋዜጣ፤ በ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ፤ እንዲሁም በህወሀት ክፍፍል ማግስት ከፍተኛ የ አቋም መዋዠቅ በማሳየቱ፤ ጋዜጣው ነፃ ወይም የግል ነው የሚለው አመለካከት ተቀባይነት እያጣ መጣ።

በተለይ ከህወሀት ክፍፍል ማግስት ጀምሮ ፤በወቅቱ የመለስ ቀኝ እጅ ከነበሩት የብአዴን ሹመኞች በተለይም ከበረከት ስምኦን ጋር ከፍ ያለ አለመግባባት ውስጥ የገባው የአቶ አማረ ሪፖርተር፤ይህም አለመግባባት አዲስ ረቂቅ የፕሬስ ህግ መፅደቁን ተከትሎ ወደ ጠላትነት ደረጃ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። አቶ አማረ ፤በፕሬስ ህጉ ሽፋን ከማስታወቂያ ሚኒስትር ባለስልጣናት ጋር በአደባባይ ባሳዩት ግብግብ ቀረሽ ፍጥጫና ወደ ጫፍ በሄደ ተከታታይነት ያለው ጠንካራ ተቃውሞ ፤ ቀደም ሲል ሪፖርተርን አስመልክቶ በህዝብ ዘንድ የነበረውን ጥርጣሬ በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ ችለው እንደነበር ይታወቃል።

ሆኖም፤ በምርጫ 97 የኢህአዴግ ስልጣን ጫፍ ላይ መድረሱ ከፍ ያለ ድንጋጤ ላይ የከተታቸው አቶ አማረ፤ በተለይም ሚዛናዊነት የሚባለውን ዋነኛ የጋዜጠኝነት ሙያዊ መስፈርት ያለ አንዳች ይሉኝታ እንደ እራፊ ጨርቅ በመወርወር፤” አደይ ድርጅቴን” ወደማቀንቀን ወረዱ።

ኢህአዴግ፤የቅንጅት መሪዎችን፣ጋዜጠኞችንና የሲቪክ ማህበራት መሪዎችን ለእስር በመዳረግ፤ በሀገሪቱ ብልጭ ብሎ የነበረውን የዲሞክራሲ ተስፋ ለማጨለም በወሰደው አምባገነናዊ እርምጃ ፤ዋነኛ መንገድ መሪና አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆን አገልግሎት የሰጡት አቶ አማረ፤ “ነኝ” የሚሉትን ማንነታቸውን በመዘንጋት “ የታሰሩትጋዜጠኞች ተገቢውን ቅጣት ያግኙ” ብለው በርዕሰ አንቀፃቸው አቋማቸውን እስከማንፀባረቅ የደረሱ ነበሩ።

ብዙዎች እንደሚስማሙበት፤ አቶ አማረ የታሰሩትና የተደበደቡት አሁን ሳይሆን ፤ያኔ በሌሎቹ ላይ ከአንድ፤ “ጋዜጠኛ ነኝ” ከሚል ግለሰብ የማይጠበቅ ጭፍን ተግባር ሲያከናውኑ ነው።

በምርጫው ቀውስ ጊዜ ከእናት ድርጅታቸው ጋር በመወገን “ የጋራ ጠላታችንን እንምታ “ዓይነት መዝሙር የዘመሩትና፤ ቅንጅትን ለማፍረስ በተያዘው ዘመቻ ከነበረከት ጋር የነበራቸውን ልዩነት እርግፍ አርገው የተውት አማረ፤ኢህአዴግ የምርጫ ውጤቱን በሀይል ቀልብሶ ስልጣኑን ያረጋገጠ ሲመስላቸው፤ እንደገና ነፃ እና የግል ፕሬስ ለመምሰል በተደጋጋሚ የመንግስትን አሰራር የሚተቹ ፤ሆኖም ለኢህአዴግን ስልጣን ዘብ የቆሙ የሚመስሉ ፅሁፎችን ማተም እንደጀመሩ ይታወቃል።

በአሁኑ ጊዜ በተለይ አገር ቤት ውስጥ በህዝብ ተቀበቀይነት ያጣው ሪፖርተር ጋዜጣ፤ የህትመት መጠኑ ከሽቆለቆለበት ደረጃ ፤ሊያገግም እንዳልቻለ ታውቋል።

በነፃ ፕሬስ ስም ድርጅታዊ አገልግሎት እወየሰጡ ያሉት አቶ አማረ፤ በቅርቡ ረቂቅ የፕሬስ ህጉ መፅደቁን ተከትሎ ከአቶ በረከት ጋር የነበራቸው ቁርሾ እንደገና ከማገርሸቱም በላይ፤ አቶ በረከት በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩትን ዳሸን ቢራ ፋብሪካን በጋዜጣቸው በማብጠልጠላቸው፤ ጎንደር ድረስ ተወስደው መታሰራቸው ይታወሳል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለህትመት በሚያበቋቸው ጋዜጣዎች ደግሞ፤ በሸህ መሀመድ አላሙዲን ፕሮጀክቶች ላይ የተቃውሞ ዘመቻ የከፈቱ ሲሆን፤ ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ ደ በሆነው ethiopiafirst.com ድረ ገፅ ላይ በሶስት ተከታታይ ክፍሎች አቶ አማረን የሚቃወሙና የሚያስጠነቅቁ ፅሁፎች ተስተናግደዋል።

አቶ አማረ የተደበደቡት ከድርጅታቸው ከኢህአዴግ ሳይሆን፤ ከገዥው መንግስት ከፍተኛ ሹመኞች ጋር እንዲህ ያለ የጥቅም ግጭት ውስጥ በገቡበት ሰዓት በመሆኑ፤”ደብዳቢዎቹ እነማን ለሆኑ ይችላሉ?” የሚለው ለብዙዎች ምስጢር አይሆንም ይላሉ_ አስተያየት ሰጭዎች።

ሆኖም፣እንደምንጮቻችን ገለፃ አቶ አማረ የተደበደቡት ፤ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ለማምጣት ሲሄዱ ላዳ ታክሲ ውስጥ በነበሩ ሶስት ሰዎች ሲሆን፤ ሁለቱ ተያዘው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።

እርሳቸውም በሀያት ሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 31, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.