“አሁንም ቀሪ የ90 ደቂቃ ጨዋታ ይቀራል” አሰልልጣኝ ሰውነት ቢሻው

ተሸንፈንም ባልቀዘቀዘው የህዝብ ድጋፍ ተደንቀናል – አሰልጣኝ ሰውነት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋልያዎቹ ደጋፊዎች በትናንቱ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በናይጄሪያ አቻው ተሸንፎም በሰጡት ድጋፍ መደነቃቸውን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ገለፁ ። አሰልጣኙ እስከመጨረሻው ለዘለቀው የህዝቡ ድጋፍ ምስጋናችንና አድናቆታችን ትልቅ ነው ብለዋል ። አዳነ ግርማን በኡመድ ኡክሪ የተካሁት ተጨማሪ ጎሎችን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲያስቆጥር በማሰብ ነው ብለዋል ። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ማምሻውን ለ120 ደቂቃችን እንደተናገሩት ፥ ተጨማሪ ጎል ፈልገው አዳነን ቢተኩም እንዳሰቡት አልሆነም ። ይህም የጨዋታ ባህሪ መሆኑን ነው አሰልጣኙ ያስረዱት ።

” በመልስ ጨዋታው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይጠብቅ ? ” የተባሉት አቶ ሰውነት ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ እግር ኳስ ይወዳል ይህን መውደዱን እንዲቀጥል እንሰራለን ብለዋል በምላሻቸው ።

የምንችለውን ሁሉ ሰርተን የምናገኘውን ውጤት እንይዛለንም ብለዋል ።

የትናንቱ ጨዋታ ሲገመገም

የትናንቱ ጨዋታ ውጤት ለኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ነበር ፤ በአቀያየር ላይ በተፈጠረ የታክቲክ ስህተት እና በካሜሩናዊው ዳኛ ውሳኔ እንጅ በማለት የሱፐር ስፖርቱ ኢዎዲ ኦጂንማህ አስተያየቱን አስፍሯል ። ዋልያዎቹ ጫና በመፍጠር እና ጎሎችን በማስቆጠር በሜዳቸው ያደረጉትን ጨዋታ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ በሚያደርጉት የኳስ ቅብብል እና በሚያሳልፉት ውሳኔ ስህተቶች ይስተዋሉ ነበር።
Goal
በትናንቱ የኢትዮጵያውያን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተደመመው የናይጀሪያው አስልጣኝ ስቴፈን ኬሽ ፥ ኢትዮጵያውያን አስደናቂዎች እንደነበሩ ይናገራል ፤ አሰልጣኙ ቡድኑ ጥሩ እግር ኳስ መጫወቱንም ነው የመሰከረው። ኬሽ ስለጨዋታው ሲናገር ፥ በመጀመሪያው አጋማሽ በራሳቸው ሜዳ ተገድበው ሃይላቸውን ለመቆጠብ መጫወታቸውንና በራሳቸው የጨዋታ እቅድ ወደ ሜዳ እንደገቡም ለፊፋ ሪፖርተሮች በሰጠው አስተያየቱ ገልጿል። ኦጂንማህ ባሰፈረው ጽሁፉ የጎል እድሎች ቢፈጠሩም ከልክ ባለፈ በጓጉት ኢትዮጵያውያን የናይጀሪያው ግብ ጠባቂ ኢንዬማ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብዙም አልተፈተነም ይላል ።

የጨዋታውን ድባብ የመቀየር አቅም የነበራት ሳላሃዲን ሰኢድ ያሰቆጠራት እና መስመሩን አልፋ በዳኛው የተሻረችው ጎል በስቴዲየሙ የነበረውን ተመልካች ስሜት ያቀዘቀዘች እነደበነበረችም አስፍሯል። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጨዋታውን አዲስ አበባ ላይ ከመጨረስ ይልቅ አንጋፋውን አዳነ ግርማን ቀይረው ማስወጣታቸው ትልቁ የጨዋታው ስህተት መሆኑን ነው የሱፐር ስፖርቱ ጸሃፊ የገለፀው።

በአንጻሩ የናይጀሪያው አቻቸው ኬሽ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ያደረጉት የተጫዋች ለውጥ ፥ ለቡድኑ ፍጥነትን እና ለጨዋታ የሚመቻቸውን የአካል ብቃት አቀራረብ በመጨመር ናይጀሪያዎችን የተሻለ አድርጓቸዋል ይላል። ከዚህ በኋላ ነጭ ለባሾቹ ናይጀሪያውያን በሜዳ ላይ ጥሩ ከመንቀሳቀሳቸውም በላይ በ67ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂውን ጀማል እንቅስቃሴ በሚገባ የተረዳው ኢምኒኬ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል ።

ኦጂንማህ በአስተያየቱ ቡድናቸውን ለማበረታታት ስታዲየም የተገኙ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ከአቻነቷ ጎል በኋላ ፥ በዝማሬ ዋልያዎቹን ከማበረታታት ይልቅ በዝምታ መዋጣቸው ተገቢ አይደለም ብሎ ተችቷል። በዝምታ በተዋጠው የአዲስ አበባ ስቴዲየም የናይጀሪያው አጥቂ ኢሚኒኬ በኢትዮጵያውያን የግብ ክልል በተሰራበት ጥፋት ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠር የመልሱን ጨዋታ ከባድ አድርጎታል ።

በተያያዘ ዜና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የካሜሮናዊው አልቢትር የተዛባ ውሳኔ እንዲሁም በሁለተኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የተደረገው የታክቲክና የተጫዋቾች ለውጥ የጨዋታውን ሂደት መቀየሩን ለሱፐር ስፖርት ተናገሩ።

አልቢትሩ በግልፅ መስመር ያለፈንና የተቆጠረን ግብ ከመሻር ባለፈ ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ 5 ተጫዋቾቻችንን የቢጫ ካርድ ሰለባ ማድረጋቸውን አሰልጣኙ ገልፀዋል ። ጎል ባስቆጠርንበት ወቅት ጨዋታውን የተቆጣጠርነው መስሎኝ ነበር የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረኩት ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት ፥ ነገርግን ከቅያሪው በዃላ ጨዋታውን በዚያው ልክ ልንቆጣጠረው አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል።

የሆነ ሆኖ ጨዋታው አልተደመደመም ፥ የመልስ ጨዋታ በናይጄሪያዋ ካላባር ይጠብቀናል ፤ በዚያም ውጤቱን ለመቀየር ጠንክረን እንሰራለን ነው ያሉት ። አሁንም ቀሪ የ90 ደቂቃ ጨዋታ ይቀራሉ ፥ እግር ኳስም በባህሪው ለሁሉም እኩል እድልን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ ይህን እድል ለመጠቀም እንሞክራለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሁሌም ከጎናችን በመሆን ድጋፉን ለሚቸረን ለሚወደው ደጋፊያችንም ታላቅ ምስጋና እና አድናቆት አለኝ ብለዋል።

ምንጭ http://www.supersport.com/

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 15, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.