ኖርዌይ በአቶ መለስ የተጠረነፈች አገር !!

አቶ መለስ የአገር ቤቱን ህዝብ በጉልበት ፣ ፈረንጁን ደግሞ በአፍ ብልጠት መጠርነፉን ያውቁበታል፡፡ማን ነበር ? የአቶ መለስ ምላስ ሶስት ቻናል አለው ፣ ለፈረንጁ በፈረንጅኛ፣ ለትግራዩ ማህበረሰብ በትግርኛ፣ ለአማርኛ ቋንቋ አድማጩ ህዝብ ደግሞ በአማርኛ ቻናል እየለዋወጡ ነው የሚያጭበረብሩት ያለው ? አቶ መለስ በቁጭ በሉነት ቁጭ ካደረጓቸው ሞኝ ባገኝ አገሮች አንዷ የስካንዲኔቪያዋ ትንሿ አገር ኖርዌይ ናት፡፡

አቶ መለስ ፣ October 10, 2011 ኦስሎ በሚዘጋጀው Energy for all ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ መረጃው ኖርዌ ለሚኖርው ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ሲደርሰው ፣ አንድ ግብረ ኃይል ተዋቀረላቸው ፡፡ ግብረ ሃይሉን እንዲመሩ ደግሞ የቀድሞውን የአቶ መለስ አለቃን አቶ ግደይ ዘርአጽዮንን መረጠ ፡፡ምክንያት ! አቶ መለስ ፣ ሙልጭ ልጭ እያለ አሳ እንደላሰው የሚለውን ሙዚቃ እንደሚወዱ አቶ ግደይ ያውቁባቸዋል ብሎ በማመን የተቃውሞውን እንቅስቃሴ ዝግጅት አጧጧፈ ፡፡

አቶ መለስ ፣ ኖርዌይ ሲመጡ የሚገጥማቸውን ተቃውሞ በሚገባ ስለሚያውቁት ፣ በቅድሚያ እሳቸው ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ አንድ አብሪ ጦር ወደ ኦስሎ በአስመጪና ላኪ ስም የሚንቀሳቀሱ አሰማሩ ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ያሰማሯቸው አብሪ ጦሮች ፣ ከዚህ ቀደም በኖርዌ ጥገኝነት ጠይቀው ፣ጥያቄያቸው በኖርዌይ መንግሥት ውድቅ የተደረገባቸውና በፍቃደኝነት IOM በተባለ መልሶ አቋቋሚ ድርጅት ወደ አገር የተመለሱትን ሰዎች እንደገና በንግድ ልኡክ ስም በማሰማራት ነበር ፡፡

የተላኩት አብሪ ጦሮች በኦስሎ ነዋሪ የሆኑትን ሰዎችና የከተማዋንም መግቢያና መውጫ ጭምር መንጥረው የሚያውቁ ስለሆነ ፣አንድም ስነልቦናዊ ጫና ለመፍጠርና ተሰላፊውን ዜጋ ለማስፈራራት ጭምር ነበር፡፡ ግን የአቶ መለስ ሴራ አልሰራላቸውም ፡፡ ሊበሥሱ የመጡትን ሰዎች ፣ ስደተኛው ገልብጦ በሰሳቸው ፡፡

ታላቁ ሰላማዊ ሰልፍ ቀኑ ደረሰ ፡፡ አቶ መለስ ኦስሎ የተመደበላቸው ሆቴል ከስብሰባው ቀን አንድ ቀን ቀደም ብለው ሲደርሱ አድብቶ ይጠብቅ የነበረው ኃይል በአበባ ሳይሆን በደባ ተቀበላቸው፡፡ የኖርዌ መንግሥት ባነነ ፣ ዛሬ እንዲህ የሆነ ፣ ነገ ምን ሊሆን ነው ብሎ መከረ ፡፡
October 10,2011 ደመናማና ቀዝቃዛ ቀን ነበር ፡፡ ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተሰባሰቡ ፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከጎረቤት አገሮች ከሆኑት ፣ ስዊድን ፣ ፊንላንድ ጭምር ነበር የመጡት ፡፡ ሰልፈኛው ጉባኤው ከሚካሄድበት ስፍራ በግምት ከሰላሳ ሜትር ርቀት ላይ ነበር ተቃውሞውን እንዲያሰማ ቦታ የተሰጠው ፡፡ የስብሰባው አዳራሽ ዙርያውን በልዩ ጠንካራ ኮማንዶ ፖሊስ ተከቧል ፡፡

ፖሊስ የሰልፈኛውን መትመም በመመልከት ፣ የተቃውሞውን ሰልፍ ፣ የድምጽ ጩኽት ለማስቀነስ በሚል ምክንያት ፣ የድምጽ ማጉያ ሰልፈኛው እንዳያስገባ ከለከለ፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን አድርገው ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በጋራ በመመካከር አንድ ህብረት የፈጠሩት ፣ የኦነግ ፣ የኦብነግ ሰልፈኞች ኳሷን መለስ ዜናዊ ላይ ብቻ በሚል የህብረት ድምጽ ፣ አንድ ላይ በመጮሃቸው ፣ የስብሰባው አዳርሻ ታወከ ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ በተገኙበት ስብሰባ መለስ ዜናዊ በድንጋጤ ጭብጦ አክለው እጃቸውን ወደ ኋላ አድርጎ ከመቆም አላመለጡም ፡፡

እሳቸው ወደ ኖርዌይ ከመምጣታቸው አንድ ሳምንት አስቀድሞ ፣ የአገሪቱ አንጋፋ ጋዜጣና ዋና ልሳን የሆነው AFTEN POSTEN የተባለው ጋዜጣ ፣ የአቶ መለስ መንግሥት የርዳታ እህሎችን ፥ ማዳበሪያዎችን የመሳሰሉትን ለደጋፊዎቹ ብቻ ነው የሚያከፋፍለው የሚለውን ውንጀላ በሰፊው ለህትመት በማብቃቱ፣ አቶ መለስ በአምባገነንነት አገሪቱን በብረት ክንድ እየገዙ ፣ተቃዋሚ ያሉትን ሃይል ሁሉ ፣ ብሽብርተኝነት ክስ ዘብጥያ እንደሚወረውሩ ጋዜጣው በማጋለጡ ፣ አቶ መለስን የጋበዟቸው የኖርዌው ጠቅላይ ሚንስቴር ዬንስ ስቶልትንበርግና ፣ የውጭ ርዳታ ሚንስቴሩ ኤሪክ ሱልሃይም ዜናው ሳይጎረብጣቸው ባይቀርም ፣ ቀኑ ሲደርስ ግን አቶ መለስን የያዘችው ጢያራ ጉዙዋን አላቋረጠችም ኦስሎ ኖርዌ ደረስች ፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በኦስሎ ከተማ ፣ በየትኛውም ምእራባዊ ዓለም እንደዚህ ያለ ተቃውሞ ያልገጠማቸው አቶ መለስ፣ ተቃውሞውን እያንገሻገሻቸው ተጎነጩት፡፡ የዚህ አይነት ተቃውሞ ፣ከዚህ በፊት ያራ የተባለው ማዳበርያ አምራች ድርጅት ለሽልማት በጋበዛቸው ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የኖርዌ ጠቅላይ ሚንስቴር የነበሩት ሚስተር ቡንድቪክ ጭምር አልቀበላቸውም ብለው በመናገራቸው ፣ በጉቦ መልክ ሽልማት የሰጣቸው ያራ የተባለው ድርጅት ባዘጋጀው የእራት ምሽት ፕሮግራም ላይ ጭምር እንዲገኙ የተጋበዙት የኖርዌ ምርጥ አርቲስቶች አድመው አንገኝም በማለታቸው አቶ መለስ ውስጥ ውስጡን ለህዝብ ሳይታዩ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ያስታውሱታል፡፡

አቶ መለስ ስለገጠማቸው ከፍተኛ ተቃውሞ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲመልሱ ፣ተቃውሞውን በደመና አመሳስለውታል፡፡ዳመናው ሲተን ተቃውሞውም ይጠፋል በሚል አባባል ጥያቄውን ለማዳፈን ሞክረዋል፡፡ አቶ መለስ የቀድሞውን ሸዋ ላይ ዳመነ…ዳመነ የተባለውን ዘፈን አሻሽለው ለኦስሎ ኢትዮጵያውያን ኦስሎ ላይ ዳመነ የሚል ነጠላ ሥራ ለቀዋል፡፡

ጋዜጠኞች ከበድ ከበድ ያሉ ተግዳሮታዊ ጥያቄ ያከታተሉባቸው መለስ፣ ቆጣ ብለው በውስጥ ጉዳያችን አትግቡ ፣ ኢትዮጵያ ቅኝ የተገዛች አገር አይደለችም… ሳንቲሟን ብቻ መወርወር እንጂ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ ብለው በመቆጣት አንበሳው አገሳ የሚለውን ሙዚቃ ፈረንጆቹ እንዲያዳምጡ ለመጋበዝ ልባቸው እንደከጀለ ከሰጡት ቃለ መጠይቅ የድምጻቸው አወራረድ ላይ መረዳት ይቻል ነበር ፡፡
ድሮ ድሮ ! ልጆች ሆነን ፣ መሬት በክብ ሸንቁረን ሳንቲም ጉርጓዷ ውስጥ ያስገባ አይነት ጨዋታ እንጂ ፣ሳንቲሟን ማን በላት አትበሉ ያሉት አባባላቸው ፣ እግራቸው ኦስሎን ከለቀቀ ጀምሮ ፣የአገሪቱን ከፍተኛ ፓርቲዎች በማስቆጣቱ በፓርላማ ክርክሩ ሊጦፍ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ እንዴት እንዲህ ያለ አምባ ገነን መሪ እዚህ ድረስ ተጠርቶ ይሞካሻል ? የኖርዌይ ግብር ከፋይ ህዝብ ገንዘብ የትም አይወረወርም በሚል ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል፡፡

እንደመተሬ የቀረበላቸውን ተቃውሞ ጠረቤዛ እንደ አገር ቤቱ ሳይደልቁ የተጎነጯት መለስ፣ ዶሮ ማታ … ዶሮ ማታ… የተባለላቸውን እራት ሳይበሉ ጢያራቸውን አስነስተው በንዴት እብስ ብለዋል፡፡የእራት ፕሮግራም እንደተያዘላቸው የሚያወቀው ሰላማዊ ሰልፈኛ ፣ ከእራት አዳራሹ እንደገና ማምሻውን በመገኘት እበር ላይ ቢጠባበቅ ፣እነባንኪሞንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወደ ማዕድ እልፍኙ ሲገቡ መለስ የውሃ ሽታ ሆነው በመገኘታቸው ፣ የጸጥታው ሃላፊ ፖሊስ ወደ ሰልፈኛው በመምጣት ፣

መለስ ብለዋል እብስ
እንኳን ሊበሉ ድግስ ፡፡
ብሎ አሰናበተን ፡፡ ፈረንጅ Give me money !! የሚለውን ልጆች ሆነን ፈረንጅ ባየን ቁጥር ሙጭጭ የምንለውን ጥያቄ አቶ መለስ አሻሽለው ንግግር ሲያደርጉ አንጀት በመብላት ኖርዌይ በ-July 22,2011 በገጠማት የሽብርትኝነት አደጋ ልባችን አዝኗል በማለት ዬንስ ስቶልትንበርግ አንጀት ውስጥ ለመዘፍዘፍ ሞክረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ሰልፈኛው ኖርዌይ ውስጥ ኦስሎ ከተማ ላይ በ-July 22 ቱ ሽብር እልቂት የፈጸመውን አንደርሽ ብሬቪክን ስም በመጠቀም መለስ ጥቁሩ ብሬቪክ ፣ በእስክንድር ነጋ ፣አንዷለም አራጌ፣ዉብሸት ታዬ ልጆች ላይ ፣ ሽብር አስፋፊው እያለ መፈክር አውርዶባቸዋል ፡፡በአደጋው ለሞቱት የክብር አበባ ታላቁ ካቴድራል አጠገብ ተጋባዦቹ እንግዶች እነባንኪሙን ጭምር በአደባባይ ተገኝተው አበባ ሲያስቀምጡ ፣ አቶ መለስ ከሆቴላቸው ሳይወጡ ተደብቀው ውለዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ቀድሞ ዲያስፖራዎችን የማይረጥቡ አሳዎች !! እያለ ይሳለቅ የነበረው ሪፖርተር ጋዜጣ ጭምር ይህን ተቃውሞ መዘገቡ ፣ ኸረ ጎበዝ ! እንዴት ነው የአቶ መለስ አገዛዝ በሪፖርተር ሳይቀር ውነቱ ሊወጣ የቻለበት ምክንያት እንድንል እያደረገን ነው፡፡

እንግዳ ታደሰ / ኖርዌይ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 13, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.