ኔልሰን ማንዴላ አረፉ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) እውቁ የአፍሪቃ ልጅ፣ የደቡብ አፍሪካ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ፤ በተወለዱ በ95 አመታቸው በዛሬው እለት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። ይህን በተመለከተ በርካታ የዜና አውታሮች ዘገባ እያቀረቡ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማም ከኋይት ሃውስ፤ የሃዘን መግለጫ ንግግር አድርገዋል።

Nelson Mandela passed away at 95

Nelson Mandela passed away at 95

ለደቡብ አፍሪካውያኑ እንደ አባት ይቆጠራሉ፡፡ የዲሞክራሲ አባት ተብለውም ይጠራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1918 በደቡብ አፍሪካ በኬፕ አካባቢ የተወለዱትና በጐሳቸው አባላት “ማዲባ” በመባል የሚጠሩት ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካውያን ነፃ አውጪና አዳኝም ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ክብርም ይሰጣቸዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ለማላቀቅ ባደረጉት ትግል 27 ዓመታትን በእስር ያሳለፉት ኔልሰን ማንዴላ፣ እ.ኤ.አ. ከ1994 እስከ 1999 የመጀመርያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካውያን ነፃነት ሲነሳ በመላ ደቡብ አፍሪካውያን በታላቅ ክብር የሚጠሩት የ95 ዓመቱ ማንዴላ በመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን ምክንያት ሆስፒታል መመላለስ ከጀመሩ ሶስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ሊተርፉ አልቻሉም – ዲሴምበር 5 ቀን 2013 ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የቢቢሲው አንድሪው ሃርዲንግ ከፕሪቶሪያ እንደዘገበው “የማንዴላ የመኖር ተስፋ የመነመነ ይመስላል፤ የማንዴላ ቤተሰቦች በሙሉ መሰባሰብ ጀምረዋል፡፡” ብሎ ነበር።

የማንዴላ የቅርብ ጓደኞች ከሆኑት አንዱ፣ ‹‹ማንዴላ በሰላም እንዲያርፍ ለቤተሰቦቹና ለሕዝቡ የሚነገርበት ሰዓት ነው፤›› ማለታቸውንም ዘግቧል፡፡  ሕዝቡ ሞት ስለሚባለው ነገር መስማት አይፈልግም፡፡ ሕዝቡ ላለፉት ዓመታትም ቢሆን ስለ ኔልሰን ማንዴላ ሕይወት እንጂ ሞት ማውራት እንደማይፈልግ ይነገራል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ግን ስለ ኔልሰን ማንዴላ መጥፎ ዜና የሚሰሙበት ቀረበና መርዶውን ተረድተዋል፡፡

የኔልሰን ማንዴላ ሕይወት በሞት አፋፍ በነበረበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ‹‹የደቡብ አፍሪካውያን ስጦታ ለሆነው ሚስተር ማንዴላ ፀሎት የምናደርግበት ወቅት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም የማንዴላ የሕልፈት ጊዜ መቃረቡን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጤንነት መታወክ መሰቃየት የጀመሩት ዝነኛው ታጋይ ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ1999 የፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በታላቅ ልዑክ አምባሳደርነት ማዕረግ በፀረ ኤድስ ዘመቻ ተሳትፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የተከናወነው 29ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ እንዲካሄድም ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ በኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ በብሩንዲና በሌሎች አገሮች የሰላም ስምምነት ውስጥም ተሳትፈዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ2004 በ85 ዓመታቸው ግን ለሕዝብ ከሚሰጡት አገልግሎት መራቅ ጀመሩ፡፡ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ማሳለፍንም መረጡ፡፡

“አትደውሉልኝ እኔ እደውላለሁ” በማለትም ማንኛውም አካል እሳቸውን እንዳይጋብዝ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2004 በኋላም መድረክ ላይ ብዙም አልታዩም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የተሳተፉትን ከአሜሪካና ከደቡብ አፍሪካ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ጋር ውይይት ሲያደርጉ የተነሱት ፎቶ በቢሮዋቸው በኩል ቢለቀቅም፣ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ታዳሚ ግን አልሆኑም፡፡

ላለፉት ሶስት ዓመታት ሆስፒታል ሲመላለሱ የከረሙት ኔልሰን ማንዴላ በሳንባቸው ላይ ጉዳት የደረሰው በእስር በቆዩባቸው ዓመታት ነበር፡፡ በወቅቱም የቲቢ ሕክምና ተደርጎላቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዛሬው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን መነሻ የእስር ቤቱ ሕመማቸው ቢጠቀስም፣ እ.ኤ.አ. በ2012 ለረዥም ጊዜ የቆየ የሆድ ዕቃ ሕመምም አጋጥሟቸው እንደነበር ተገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ “ማዲባ” በመባል የሚጠሩት ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ የመጀመርያውን የጥቁር የሕግ ተቋም ከኦሊቨር ታምቦ ጋር በመሆን ያቋቋሙ ናቸው፡፡

ትምህርት በጀመሩበት የልጅነት ዕድሜያቸው ኔልሰን የሚለው የእንግሊዝ ስያሜ በመምህራቸው የተሰጣቸው ማንዴላ፣ የ23 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር የታቀደላቸውን ትዳር ሸሽተው ከትውልድ ስፍራቸው ወደ ጆሃንስበርግ የሄዱት፡፡

ከሁለት ዓመት የጆሃንስበርግ ቆይታቸው በኋላ የሕግ ትምህርት ለመማር የተቀላቀሉት የዊትወተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለማየት ያስቻላቸው ነበር፡፡ በነበሩበት ፋኩልቲ ከእሳቸው በቀር አንድም አፍሪካዊ ባለመኖሩ በዘር የመገለል ዕጣ ፈንታን የቀመሱት ማንዴላ የአውሮፓ፣ የአይሁድ፣ የህንድና የሌሎች አገሮች ኮሙዩኒስትና ሊበራል ተማሪዎች ጋር መልካም ጓደኝነትን ለመፍጠርም አስችሏቸዋል፡፡ በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጐታቸውም የዳበረው እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ነው፡፡

በትምህርት ላይ እያሉ እ.ኤ.አ. በ1944 የተመሠረተው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ዩዝ ሊግ (ኤኤንሲዋይኤል) የወቅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ማንዴላ የፖለቲካ አቀንቃኝነታቸው በማየሉ የትምህርታቸውን የመጨረሻ ዓመት ሦስት ጊዜ መውደቃቸውንና እ.ኤ.አ. በ1949 ዲግሪያቸውን መከልከላቸው ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱት ኔልሰን ማንዴላ በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ቆይታቸውንና ሥልጠናቸውን ተርከዋል፡፡ ለኢትዮጵያም ልዩ ቦታ እንዳላቸው በግልጽ አስፍረዋል፡፡

ትምህርታቸውን ከማደናቀፍ ጀምሮ 27 ዓመታትን ለእስር የዳረጋቸው ደቡብ አፍሪካውያንን ከባርነት የማውጣት ወኔ ግን ወድቆ አልቀረም፡፡ በእሳቸው መሪነት በተከታዮቻቸው መስዋዕትነት ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ አገዛዝ ከተላቀቀችና ደቡብ አፍሪካውያን በዜጋቸው መመራት ከጀመሩ 19 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን በአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን የደረሰባቸውን በደል፣ ግፍና ግድያ ኔልሰን ማንዴላም በእስር ቤት ስላሳለፉት ስቃይ ይቅር በማለት በነጮችና በጥቁሮች መካከል የበላይና የበታች ሳይኖር ሰላምን በዘዴ ያሰረፁ መሪ ናቸው፡፡ ቀድሞ በበደል ሥር የነበሩ አፍሪካውያን ነጮችን እንዳያጠቁ በስምምነት መኖር የሚያስችል ሥርዓትን ያመቻቹም ናቸው፡፡ ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግም ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በፍሪደም ቻርተር መክፈቻ ንግግራቸውም ላይ፣ ‹‹እኛ የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች የአገራችንና የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው የምንፈልገው ደቡብ አፍሪካ በአገሪቷ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ጥቁሮችና ነጮች የሚኖሩባት አገር መሆኗን ነው፡፡ የትኛውም መንግሥት ቢሆን በሕዝቡ ፈቃድ ካልሆነ ሊገዛት አይችልም፤›› በማለት በጥቁርና በነጭ መካከል የነበረውን ልዩነት ያረገቡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1918 የተወለዱት ማንዴላ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን (ኤኤንሲ) የተቀላቀሉት በ1943 ሲሆን፣ በ1956 በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ክሱ ውድቅ ሆኗል፡፡ በ1962 በአሻጥር ተወንጅለው የአምስት ዓመታት እስራት የተፈረደባቸው ማንዴላ በ1964 እስራቱ ወደ ዕድሜ ልክ ተቀይሮላቸዋል፡፡

አፍሪካውያን ብሎም ዓለም ድምፁን ለማንዴላ ሲያሰማ ቢከርምም ማንዴላ በእስር ቤት 27 ዓመታትን አስቆጥረው የተፈቱት እ.ኤ.አ. በ1990 ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1993 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙት ማንዴላ፣ የመጀመርያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት እ.ኤ.አ. በ1994 ነው፡፡ በ1999 ከሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው የወረዱት ማንዴላ፣ ማንዴላ ፋውንዴሽንን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በስማቸው ሐውልቶች፣ አደባባዮች፣ ፓርኮች፣ ቦታዎች የተሰየሙላቸው ማንዴላ ጁላይ 18 ደግሞ የማንዴላ ቀን ተብሎ ይከበርላቸዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ሦስት ጊዜ ያገቡ ሲሆን የስድስት ልጆች አባትና የ17 ልጆች አያት ናቸው፡፡ ከመጀመርያ ሚስታቸው ኢቪሊያ ማሲ ጋር 13 ዓመታትን ሲየሳልፉ ሁለት ወንድና ሁለት ሴቶችን ወልደዋል፡፡ ከሁለተኛ ሚስታቸው ዊኒ ማንዴላ ሁለት ሴቶችን የወለዱ ሲሆን ሁለተኛ ልጃቸውን በወለዱ በ18 ወሯ ነበር ማንዴላ ወደ እስር የወረዱት፡፡ ከዊኒ ማንዴላ ጋር እ.ኤ.አ. በ1992 የተፋቱት ማንዴላ የቀድሞውን የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት የሟቹ ሳሞራ ማሼል ባለቤት ግራሻ ማሼል ያገቡት እ.ኤ.አ. በ1998 80ኛ ልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ነው፡፡

የቀብር ስነ ስር አታቸው ከአስር ቀናት በኋላ ይከናወናል። እስከዚያው አስከሬናቸው በደቡብ አፍሪካ የ2010 አለም ዋንጫ ተካሂዶ በነበረበት ስቴዲየም ውስጥ ቆይቶ፤ ስንብት ይደረግለታል።

ምንጭ፡ ከመጀመሪያ እና መጨረሻው አንቀጽ እንዲሁም አንዳንድ ማስታወሻዎች በቀር ቀሪውን ያገኘነው ከዚህ በፊት ከታተመ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 5, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

2 Responses to ኔልሰን ማንዴላ አረፉ

 1. andnet berhane

  December 6, 2013 at 9:04 AM

  ታላቁ አፍሪካዊ መሪ ኒልስን ሞንዴላ አረፈ
  ባጣም አስደንጋጭ ዜና ብሰማም ቅሉ ይህ ሰው የተሰጠውን ተፈጥራዊ መብት ለራሱ ብቻ ሳይሆን በጭቆናና በገዛ ሃገራቸው ባይታወር ለሆኑ ዜጎች በመቆም ለሃያ ሰባት አመታት በእስር ማቆ በጽናት የታገለው ሰላማዊ ትግል አለምን በማስደመም ከጨላማ ወደብርሃን ለመምጣት የበቃው ታላቁ የሰላም የቢሄራዊ እርቅ አባት የአፍሪካ ምሳሌ ኣውሮፓውያን የምእራባውያን የሰሩትን አላቅ ስህተት ያስተማረ ሰላማዊ ትግል ብርሃን ሆኖ ለዓልም ያበሰረ ዛሬ ባካል ቢለይም ዘላላእማዊ ታሪክ አስመዝግቦ አርፋል፡
  ጽናት ለመላው ቤተሰቡ ለመላው የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች እየተመኘሁ
  ህይህ ነው መሪ ማለት በገባበት ቃል በተግባር በመተርጎም በሕዝብ የተሰጠውን ሃገራዊ አመራር ያላ ምንም አይነት ንትርክ ኃላፊነቱን ለሰጠው ሕዝብ አስረክቦ ተተኪውን በማሸጋገር ሃገሪቱን የኁሉም ደብቡብ አፍሪካውያን መሆናን አንድነትና መረጋጋትን በመፍጠር የሃገሪቱ ልጅ የህዝብ አባት በመሆን እስካለፈበት ቀን ድረስ ሲያገለግል የቆየ የማይረሳና የማይበረዝ ታሪክ ትውስታና ትምህርት አስንቆ ወደመጨረሻው አለምተሰናብቷል፡
  ማንዴላ አልሞተም ተፈትሮ አካላዊ መለየት አድርጓል ይህም አምላካዊ ስጦታ በመሆኑ ሰው እንድመሆናችን ለቅሶና ሃዘን ቢሰማንም ለተለየው ያለን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ለራሳችን የምናዝንበት እኛም ሟቾች እንድሆንን እምንረዳበት ወቅት በመሆኑ ያስለቅሰናል፡
  ማንዴላ ትልቅ ተመስጦ ያለው የነበረበትንና የደረስበትን ሁሉ የማይረሳ ታላቅ የአፍሪካ መሪዎች አስተማሪ የቢሄራዊ እርቀ ሰላም የሃገርና የሕዝብን አንድነት አጥብቆ የሚሰብክ የሃያኛው ክፍለዘመን ነብይ ነበር ብዮ ለመናገር እደፍራለሁ፡
  ነገርግን ማንዴላ በትክክል የተሰጠውን ተፈጥራዊ ኃላፊነት በመወያት ለዓልም ባጠቃላይ ተመስጦ እንዳደረገ ዛሬ የምናየው የሃዘንና መግለጫዎች ምስክሮች ናቸው፡ በመላው ዓለም ያሉ ህዝቦች ያላቸውን አክብሮት ሃዘናቸውን በመግለጽ እያሳዩ የምናየው ለሌሎች በሕየውት ያሉ ከዚህ ታላቅ መሪ መማር ያልቻሉ የስልጣን ነቀርሳዎች በሕይወት ያሉ ለመማር ባለመቻላቸው የሕዝብ ፍቅር የሃገር ኃላፊነት ሳይሆን ለግል ለሚኖሩት ወራዳዎች ምን ይሰማቸዋል ምንስ ይሉ ይሆን ?
  ይህ ነው ለነጻነት ትግል የታገለው ለብሄራዊ እርቅ ለሰውልጅ መብትና እኩልነት ለፍቅር ለአንድነት ለሰላም በማለት ለመከራ ለእስራት የተጋለጠ፡ በዚህ ሳይገታ ለዓለም ምሳሌ ለመሆን የበቃው ፡

 2. andnet berhane

  December 6, 2013 at 11:01 AM

  ታላቁ አፍሪካዊ መሪ ኒልስን ሞንዴላ አረፈ
  ባጣም አስደንጋጭ ዜና ብሰማም ቅሉ ይህ ሰው የተሰጠውን ተፈጥራዊ መብት ለራሱ ብቻ ሳይሆን በጭቆናና በገዛ ሃገራቸው ባይታወር ለሆኑ ዜጎች በመቆም ለሃያ ሰባት አመታት በእስር ማቆ በጽናት የታገለው ሰላማዊ ትግል አለምን በማስደመም ከጨላማ ወደብርሃን ለመምጣት የበቃው ታላቁ የሰላም የቢሄራዊ እርቅ አባት የአፍሪካ ምሳሌ ኣውሮፓውያን የምእራባውያን የሰሩትን አላቅ ስህተት ያስተማረ ሰላማዊ ትግል ብርሃን ሆኖ ለዓልም ያበሰረ ዛሬ ባካል ቢለይም ዘላላእማዊ ታሪክ አስመዝግቦ አርፋል፡
  ጽናት ለመላው ቤተሰቡ ለመላው የደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች እየተመኘሁ
  ህይህ ነው መሪ ማለት በገባበት ቃል በተግባር በመተርጎም በሕዝብ የተሰጠውን ሃገራዊ አመራር ያላ ምንም አይነት ንትርክ ኃላፊነቱን ለሰጠው ሕዝብ አስረክቦ ተተኪውን በማሸጋገር ሃገሪቱን የሁሉም ደብቡብ አፍሪካውያን መሆናን አንድነትና መረጋጋትን በመፍጠር የሃገሪቱ ልጅ የህዝብ አባት በመሆን እስካለፈበት ቀን ድረስ ሲያገለግል የቆየ የማይረሳና የማይበረዝ ታሪክ ትውስታና ትምህርት አስንቆ ወደመጨረሻው ዓለምተሰናብቷል፡
  ማንዴላ አልሞተም ተፈጥሮ አካላዊ መለየት አድርጓል ይህም አምላካዊ ስጦታ በመሆኑ ሰው እንድመሆናችን ለቅሶና ሃዘን ቢሰማንም ለተለየው ያለን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ለራሳችን የምናዝንበት እኛም ሟቾች እንድሆንን እምንረዳበት ወቅት በመሆኑ ያስለቅሰናል፡
  ማንዴላ ትልቅ ተመስጦ ያለው የነበረበትንና የደረስበትን ሁሉ የማይረሳ ታላቅ የአፍሪካ መሪዎች አስተማሪ የቢሄራዊ እርቀ ሰላም የሃገርና የሕዝብን አንድነት አጥብቆ የሚሰብክ የሃያኛው ክፍለዘመን ነብይ ነበር ብዮ ለመናገር እደፍራለሁ፡
  ነገርግን ማንዴላ በትክክል የተሰጠውን ተፈጥራዊ ኃላፊነት በመወያት ለዓልም ባጠቃላይ ተመስጦ እንዳደረገ ዛሬ የምናየው የሃዘንና መግለጫዎች ምስክሮች ናቸው፡ በመላው ዓለም ያሉ ህዝቦች ያላቸውን አክብሮት ሃዘናቸውን በመግለጽ እያሳዩ የምናየው ለሌሎች በሕየውት ያሉ ከዚህ ታላቅ መሪ መማር ያልቻሉ የስልጣን ነቀርሳዎች በሕይወት ያሉ ለመማር ባለመቻላቸው የሕዝብ ፍቅር የሃገር ኃላፊነት ሳይሆን ለግል ለሚኖሩት ወራዳዎች ምን ይሰማቸዋል ምንስ ይሉ ይሆን ?
  ይህ ነው ለነጻነት ትግል የታገለው ለብሄራዊ እርቅ ለሰውልጅ መብትና እኩልነት ለፍቅር ለአንድነት ለሰላም በማለት ለመከራ ለእስራት የተጋለጠ፡ በዚህ ሳይገታ ለዓለም ምሳሌ ለመሆን የበቃው ፡