“ናሽናል ፕሬስ ክለብ” ፤ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎችን ክስ ውድቅ እንዳደረገው

ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  የተባለው የገዥው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ አውታር አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስን  በማነጋገር ትናንት ባሰራጨው ቪዲዮ፤ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በቡድን 8 አገሮች ስብሰባ ላይ በፈፀመው ተግባር፤ ከእንግዲህ የአሜሪካ መንግስት በሚያዘጋጃቸው ማናቸውም ስብሰባዎች ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ እንደተጣለበትና  የፕሬስ ፈቃዱን  እንደተነጠቀ  አውጇል።

ከአሜሪካ  የጋዜጠኞች ማህበር የተገኙት መረጃዎች  ግን፤ ይህ የአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ቃለ-ምልልስ  ስህተት መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው።

ታላቁ የአሜሪካ ናሽናል ፕሬስ ክለብ እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት  ጋዜጠኛ አበበ ገላውን አስመልክቶ ያቀረበው ክስ ውድቅ ሆኗል።

በካምፕ ዴቪድ በተካሄደው የቡድን 8 አገሮች ስብሰባ ላይ ፤ጋዜጠኛ አበበ ገላው – በአቶ መለስ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ተከትሎ ከፍተኛ ብስጭት ያደረባቸው  የአቶ መለስ ሥርዓት  ደጋፊዎች ፤ አበበ  ከናሽናል ፕሬስ ክለብ አባልነቱ እንዲታገድና  የጋዜጠኝነት ፈቃዱ እንዲነጠቅ በሚጠይቅ ደብዳቤ ላይ ፒቲሺን በመፈራረም  ለፕሬስ ክለቡ  አመልክተዋል።

ሆኖም  ከሥርዓቱ ደጋፊዎች  የቀረበው ክስና አቤቱታ   ተቀባይነት እንዳላገኘና ውድቅ እንደሆነ ነው የናሺናል ፕሬስ ክለብ ያረጋገጠው።

የናሽናል ፕሬስ ክለብ  ፕሬዚዳንት ቴሬሳ ዌርነር ለኢሳት እንዳሉት፤ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን በተመለከተ የተወሰደ እርምጃም ሆነ የተለወጠ አዲስ ነገር የለም።

አምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ፦”እኔ እንደሚገባኝ…”በሚል መላ ምት ተነስተው እርግጠኛ ስላልሆኑበት ነገር የሰጡት መግለጫ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁትን ፈገግ ያሰኘ ሆኗል።

እነዚሁ ወገኖች በሰጡት አስተያዬት፦“የአምባሳደሩ ቃለ-ምልልስ ምናልባትም ለገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች እንደማጽናኛ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጋዜጠኛ አበበ ገላውን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ከተሰራጩት አስገራሚ ዜናዎች መካከል ሌለኛው ደግሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የታተመው ነው።

ጋዜጠኛ አበበ  በአቶ መለስ ላይ ተቃውሞ ካሰማ በሁዋላ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ላይ እንዳለ፣ሁለት የቀድሞ ጦር አየር ወለዶች በፈቃደኝነት የሚኖርበትን አፓርትመንት እየጠበቁ እንደሆነ፣ ከደጋፊዎቹ በመቶ ሺህ ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እየተዋጣለት እንደሚገኝ  የሚያትተው አዲስ አድማስ፤ አበበ ካደረበት ስጋት አኳያ ተቃውሞውን ካሰማበት ዕለት አንስቶ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ሄዶ እንደማያውቅ ዘግቧል።

ኢሳት እንዳረጋገጠው፤ጋዜጠኛ አበበ ገላውን አስመልክቶ አዲስ አድማስ ፦”ከምንጮቼ  ያገኘሁት ነው”በማለት ካተመው  ከዚህ ዜና ውስጥ አንድም  እውነት የለም።

እንደወትሮው ሁሉ  እዛው ዲሲ ውስጥ በመደበኛ ሥራቸው ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ አበበና የሥራ ባልደረቦቹ፤  ይህን የአዲስ አድማስ ዜና  ሲያነቡ መገረማቸውና ፈገግ መሰኘታቸው ታውቋል።

ጋዜጠኝነት ከሚጠይቃቸው ሥነ ምግባሮች አንዱ እና ዋነኛው ድፍረት እና ለእውነት መሰጠት መሆኑን የሚያወሱ በርካታ  የዘርፉ ባለሙያዎች፤ጋዜጠኛ አበበ ገላው የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ በዓለም መሪዎች  ፊት በማሰማት ባሳየው ሥርዓትን የጠበቀ ደፋር ተቃውሞ የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ደረጃ ልዩ ክብር እንዲላበስ አድርጎታል ይላሉ።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 13, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.