ትንሿ ልጅ – በሞገስ ተፈራ

 “የቤተሰቦቼ ጀግና ነኝ“…የትንሿ ልጅ ለማመን የሚያስቸግር አንደበት! መግለጥ የጀመርኩት ማስታወሻዪ የዛሬዋን ተረኛ ጠቆመኝ ። የ15 ዐመት ታዳጊ ወጣት ነቸ፣ መኖሪያዋም ፣ የስራ ምድቧም መተሀራ ከተማ ነው።መተሀራ ስኳር ፋብሪካ ገጀራ ይዘው ፣ገጀራ ተደግፍው፣ ገጀራ አቅፍው የሚኖሩ የቀን ሰራተኞቸ ዘግናኝ ኑሮ ለመታዘብ በተጓዝኩበት ወቅት ያገኘዃት ልጅ “የቤተሰቦቼ ጀግና ነኝ“ስትል ያጫወተቺኝ ታሪክ ፉከራ አልነበረም።

መተሀራ ስኳር ፋብሪካ ሃ.ያ ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች አሉ፤ከ15ሺህ በላይ የሚሆኑት ከገጀራ ጋር የሚሰሩ ሰራተኞች ናቸው፤ በገጀራ ይሰራሉ፤.ገጀራ ይደገፋሉ፤ በገጀራ ራሳቸውን ይከላከላሉ ፤በገጀራ ይቀልዳሉ።በቆሎ መሳይ ሲፈጭ ፣በጣም ነጭ የሚሆን የኖራ ይዘት ያለው ዱቄት እያቦኩ ጋግረው ይመገባሉ ፤.ማባያቸው አረም ነው። በዚህ ላይ ሁሉም የመገጣጠሚያ በሸታ አለባቸው ፤.የሚጠጡት ውሀ መርዝ ነው፤ ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ብሶታቸው አየለ፤ ገጀራ አነሱ ፤የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበራቸው በድንገት ተገደለ፤ ይበልጥ ብሶታቸው አየለ፤ያነሱትን ገጀራ ማን ይመልሰው? ነገሩ ተካረረ ፤ከበደለኞቹ መካክል አንዱን በገጀራ ትንንሽ አደረጉት፤ የመተሀራ ስኳር ፋብሪካና ማህበራዊ ቀውሱን በተመለከተ ወደፊት እመለስበታለሁ፤ለዛሬ ወደ ትንሿ ልጅ ልመልሳችሁ።

“ ባድመ የሞቱት ያገር ጀግኖች ይባላሉ፣እኔ ደግሞ የቤተሰቤ ጀግና ነኝ፣”በማለት በቅንድቡዋ ቁጭ ብድግ ስታደርገኝ ከማን ጋር እንደማወራ ተጠራተርኩ፣ጆሮዬን ማመን አቃተኝ፣ ካንደበትዋ የሚወጣው ቃል ጥይት መሰለኝ።እወቅ ያለው በልጅነት ያውቃል እንደሚባለው።

ሚያዚያ 19ቀን 1999 መተሀራ ያገኘዃት አንድ ፍሬ ልጅ የቡና ቤት አስተናጋጅ ናት፣ኑሮ በደንብ አድርጎ የጠበሳት ለመሆንዋ ሁለመናዋ ይመሰክራል፣እኔን ግን ከኑሮዋ በላይ የገረመኝ አንደበቷ ስለነበር ታሪክዋን ቀዳሁት።እንዲህ ነው። አባቴና እናቴ በጠብ ሲለያዩ እኔ ሁለት ወንድሞቼንና እናቴን ትቼ ካባቴ ጋር ወደ መቂ ሄድኩ።መቂ ላስር አመት ያህል ከኖርኩ በዃላ አባቴ ሞተ፣ካባቴ ሁለተኛ ሚስት ጋር መኖር ስላልቻልኩ መተሀራ ተመለስኩ።

በሰዎች እርዳታ መተሀራ ሄጄ እናቴን አገኘዃት፣በተከታታይ የተወለዱት ወንድሞቼና እናቴ ያሉበትን ሁኔታ ስመለከት ደነገጥኩ።ምን እንደማደርግ ጨነቀኝ፣ የናቴ አንጀት ታጥፉዋል፣የወንድሞቼ አይን ጎድጉዱዋል፣ረሀብ እንደጠናባቸው ለመረዳት ጊዜ አላባከንኩም…….

ትንሽዋ ልጅ ብዙ አማራጭ ካሰበች በዃላ በበነጋው ቡና ቤት አሻሻጭ ሆነች፣እንደስዋ ገለጻ በፈንጂ ላይ መራመድ ጀመረች፣ስለ ውሳኔዋ ከባድንት ጠየኩዋት፤የምጸት ሳቅ ሳቀች፤“ምን አማራጭ አለ፣ምን ማድርግ ነበረብጘ?”ጥያቄዋ ነበር፤መልስ አልሰጠሁም። እየደጋገመች ስሙን የምትጠራው የከባድ መኪና ሾፌር የመጀመሪያዋ ወንድ ነበር የሚከፈለውን ከፍሎ በገዛው ወሲብ ለመዝናናት ተኙ፤ትንሽዋ ልጅ በእለቱ ስላጋጠማት ሁኔታ እንዲህ አለቺኝ፤”ክፍል ይዞኝ ሲግባ ፈራሁ፣ ልቤ መታ ፣ተጨነኩ፣ከባድሜ ጦርነት ተርፎ የመጣው የመቂ ጎረብቴ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ ፣እኔ ደግሞ የቤተሰቦቼ ጀግና ነኝ በማለት ራሴን አበርታታሁትና አወላልቄ ተኛሁ፤በጣም ትልቅ ስወ ነው ፣ባስቸኩዋይ ገንዝብ ስለምፈልግ በተሰጠኝ ያንድ ቀን ስልጠና መሰረት አቀፍኩት፣”

እያየሁዋት ገጠመኙዋን በሀሳብ ሳልኩት፣ትልቁ ሰው ለመዝናናት፣ ጡት እንኩዋን የሌላት ትንሽ ልጅ ደግሞ ለችግር ማሳለፊያ ተቃቅፈዋል ፣የሁለት አገር ሰዎች! ዝሆን አይጥ ጠብሶ የተረተው ትዝ አለኝ፤………ልቤ አዘነ፤ሰውየው ወንድ የመጀመሪያዋ እንደሆን ሲረዳ ፣በእቅፉ ውስጥ አድርጎ ሲመለከታት ወደ አእምሮው በመመለስ ታሪክዋን ሲያዳምጥ አደረ፤በጣም አዘነ፣የባድመን ጀግኖች አንስታ ስታወጋው አለቀሰ፤ያካባቢው ተወላጅ መሆኑን ነገራት፣ስለ ባድመ ጦርነትና እልቂት አስረዳት፤ምስክርነቱን ሰጠ።

የባድመ ጦርንት ሲጀመር በፈንጂ ላይ እንዲሮጡ የታዘዙት ባስር ሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ልጆች፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሀኖች ደም ያቶ መለስ ዜናዊ ጆሮ ግንድ ላይ ፣የወያኔ አመራሮችና ባንዳዎች አናት ላይ ይጮሀል፤ ፈንጂ በሰው ልጅ ደምና አጥንት ተጠረገ፤ የሰው ልጅ ግሬደር ሆነ፣ እግር ፣እጅ፣አንገት…………የሰውነት አካላት ተበጣጠሰ፤እነማን ነበሩ ፊትልፊት ተሰልፈው ፈንጂውን የረገጡት?በፈንጂ ወረዳ ላይ እንዲሮጡ የተደረጉት?በጾረና ግንባር ለወሬ ነጋሪ እንዳይመች ሆኖ ያለቀው የ20ኛው ክፍለ ጦር 20ሺህ ሰራዊት፣ …ኧረ ስንቱ! ከጦርነቱ ጀርባ ሆናችሁ በቀረርቶ ፣በፉከራ ሰራዊቱን ስታበረታቱ የነበራችሁ አርቲስቶቻችን ለዚህ ጀግና መቀኘት ያልቻላችሁበት ምክንያት ምንድንው?የዛሬ ትኩርቴ አይደለምና ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፤የወያኔን መታወቂያ የወሰዳችሁ እንዳላችሁ ከነስም ዝርዝራችሁ እንደሚታወቅ ግን ሳልጠቁም አላልፍም።

አንድ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ መንገድ ላይ አትክልት እንዳይሸጥ መከልከሉ ሰበብ ሆነና የቱኒዚያ ህዝብ አመጸ።የኑሮ ውድነት፣ስራ አጥነት፣ሙስና (ጉቦ)፣በፖለቲካው ውስጥ ትክክልኛ ውክልና አለመኖር፣የነጻ ሚዲያና የሲቪል ማህብራት አለመኖር፣በተለይም የዋጋ ንረት ያንገፈገፈው ህዝብ ምክንያት ፈልጎ ተነሳ፤መሪዎቹን ሊበላ ተመመ፤ ህዝብ ከተነሳ ተነሳ ነውና አምባገነኑ መንግስት ወደቀ። የቱኒዚያ ህዝብ የፈጸመው ገድል ያለም አምባገነኖችን ሀሳብ ላይ እንደጣላቸው ያለም መገናኛዎች እየወተወቱ ነው፤አቶ መለስና/ ህወሀት/ም ስራቸውን ስለሚያውቁ፣ ተሸማቀው በችጋር እየጠበሱት ያለውን ህዝብ ቱኒዚያ የተፈጸመው ኢትዮጲያ ውስጥ መደገም የለበትም እያሉ እየሰበኩት ነው።ከ1997ቱ ምርጫ አንድ ሳምንት በፊት ቅንጅትን ለመደገፍ፣በጨዋነት ወያኔን ለመቃወም የጎረፈውን የሰው ጎርፍ አቶ መለስና ባንዳዎቹ ስለሚያውቁ ምልጃና ውትወታ አብዝተዋል።

ባገራችን ያለው ችግር ከቱኒዚያ በላይ ነው፤የኑሮ ውድነት ነጥሎ የሚያጠቃቸው ህዝቦች በችጋር እየተጠበሱ ነው፤የስራ ነገር አይወራ ነው፤ስራ ፍለጋ ከሶማሊያና ጅቡቲ፣ ወደ የመን ለመግባት በጀልባ ሲጉዋዙ አደጋ እየደረሰባቸው ባህር ላይ የሚንሳፈፈው የወገኖቻችን አስከሬን ነው።ከተለያዩ ያረብ አገራት በየጊዜው የሚሰማው አስድንጋጭ ዜና የኛው ጉድ ነው፤የስልጣን ክፍፍልና ውክልና ፍትሃዊ መሆኑ ቀርቶ ጥቂቶች ባፈሙዝ የበላይነት ይዘው እንዳሻቸው የሚሆኑባት አገር ኢትዮጵያ ናት፤ለመብታቸው የሚከራከሩ ሲነሱ ባልሞ ተኩዋሾች የሚገደሉብት ፣ህጻን ፣አዋቂ፣አባት እናት…….ሳይለይ የጥይት ሲሳይ የሆንበት ፣ለመብታቸው የሚከራከሩ እስር ቤት የሚታጎሩበት፣ዜጎች ላይ በእስር ቤት ግፍ የሚፈጸምበት፣ጥቂቶች እየበለጸጉ አብዛኞች የቁም ሞት የሚሞቱባት አገር አሁንም የኛዋ ኢትኦጲያ ናት።

የመናገር መብት የሌለበት ፣ ነጻ ሚዲያ የማይታወቅበት፣ ነጻ የሲቪክ ማህበራትና የፍትህ አካላት ያልተደራጁበት፣በደህንነትና ባፈና መዋቅር ተወጠራ ያለች ፣በየእለቱ የጥላቻ መርዝ እየተረጨባት ዜጎችዋ ከመፋቀር ይልቅ እርስ በርስ እንዲጫረሱ የቁርሾ ጽዋ እየተጋቱ እንዲኖሩ ባንዳ የተቀጠረላቸው ህዝቦች የሚኖሩት አቶ መለስ እየመራሁዋት ነው በሚላት ኢትዮጲያ ውስጥ ነው።

ታዲያ የቱኒዚያ ችግር ይበልጣል ወይስ የትዮጲያ?አድማጮች እናንትው መልሱት፤መተሀራ ስኩዋር ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰራተኞች የሚመገቡትን ደረቅ የበቆሎ ቂጣ ማባያው አገዳ ውስጥ የሚበቅል አረም ነው፤የሚሰራው የህብረተሰብ ክፍል መብላት ካቃተው ሌላው እንዴት ይችለዋል? ጎረቤቱ ወንጂ ስኩዋር ፋብሪካ ለሰራተኞች በያመቱ የሚከፈል ቦነስ ተከለከለና ሰራተኞች ያምጻሉ፤ ተፈራ ዋልዋ ያመጸውን ሰራተኛ ለማነጋገር እፊታቸው ሲቀርብ “ከኛ ይልቅ እንቁራሪት ትሻላለች፣ አገዳ ውስጥ ውላ፣ አገዳ በልታ፣ አገዳ ጠጥታ፣ አገዳ ውስጥ ታድራለች፤አሁን እኛ ከንቁራሪት እንሻላለን?አገዳ ውስጥ ውልን ቤት ስንገባ ልጆች ዳቦ፣ደብተር፣እርሳስ፣…..ይጠይቃሉ፤”በማለት አልቅሰው እንደነበር አስታውሳልሁ፤ራስን ከእንቁራሪት ጋር በማውዳደር ማጣትን ከመግለጽ በላይ ድህነት አለ?ከ23 አመት በሁዋላ መንግስት ላይ ያመጸው የቱኒዚያ ህዝብ አረም እመብላት ደረጃ ደርሱዋል?መንግስት ወደ ሌለበት ሶማሊያ ከመሰደድ በላይ ምን ይመጣ ይሆን?

ትንሿ ልጅ ላቅመ አዳም ሳትደርስ ቤትስቦችዋን ለመታደግ ስትል ለኤችአይቪ ኤድስ ደረትዋን ሰጠች፤እስዋ የረገጠችው የፈንጂ ወርዳ ይህ ነበር፤በፈንጂ በታጠርው ሜዳ ላይ እየሮጡ ለሌሎች መንገድ የከፈቱት ወታደሮች ያገር ጀግኖች ናቸው፤ይህችም ልጅ ቤተሰቦቿ ቀን እንዲገፉ ራሷን በመስዋእትነት አቀረበች፤ታዲያ ይህቺ ልጅ የቤተሰቦቿ ፍቅርና ረሀብ ያቃጠላት ጀግና አይደለችም?

የትግራዩ ተወላጅ ሾፌር 500 ብር ጨመረላት፤ከሚያሽከረክረው መኪና ላይ ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት ሰጣት፤አንድ ኩንታል ጤፍ ጨመረላት፤ለወደፊቱም እንደሚረዳትና እንደሚጠይቃት ቃል ገብቶ ተለያት።

ያገኘችውን ይዛ ወደ ቤትዋ ሄደች፤እናት ወደ ወፍጮ ቤት በረሩ፤ስራ አቁመው የነበሩ የቤቱ ቁሳቁሶች ስራ ጀመሩ፤ተፈጨ፣ ተቦካ፣ተጋገረ፣ጭስ ጨሰ፤ያንድ ትንሽ ልጅ የህይወት ዋጋ፣ የጠወለገውን ቤት ተስፋ ሞላው፤ወግ ረስቶ የነበረውን ትሪ ከበው ተመገቡ።

ታሪኳን እንደፊልም ያወጋቺኝ ማአተኛ “በችጋር ከሚሞቱ የተወሰነ መንገድ አድርሼያቸው እኔ ብሞት ምን አለበት?ስህተት ሰርቻለሁ?”አለችና ጀግና ነኝ ብላ አውራ ጣቷን አሳየችኝ። ሳላስበው ”ኧረ ነሽ”አልኳትና እቅፍ አደርኳት። ስንቶች ፖለቲካ፣ኑሮ፣ጉልብተኛ፣አድልዎ፣ባለጊዜ …..ከቤታቸው ገፍትሮ እንዳስወጣቸው ቤት ይቁጠረው።ያቶ መለስ ቅምጦች ለዚህ ሁሉ ግፍ እስከመቼ “ጥሪ አይቀበልም ”የሚል መልስ ትሰጣላችሁ? ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ፣ጠባብ ….እያላችሁ እንደ በቀቀን “ካልተመቸኝ አርነት እወጣለሁ”ለሚለው የእባብ ፖለቲካ ትገዛላችሁ? አብዛኞች በሚሰቃዩባት ኢትዮጲያ ጥቂቶች እየተደጎሙ ይማራሉ፣ይነግዳሉ፣ያስራሉ፣ይፈታሉ፣ጮማ ይቆርጣሉ፣የታላላቅ የንግድ ተቋማትና ኢንቨስትመንት ባለሽርካ ሆነው ኑሮና ህይወት ይከናወንላቸዋል።የዘመን ቅራሪ ባንዳዎች በሃፍርታቸው ያሽካካሉ፤ ወገናቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፣ወንድሞቻቸውን፣እህቶቻቸውን አስረው ይገርፋሉ፣የወገናቸውን ሀብትና ንብረት ያሻሽጣሉ፣የራሳቸውን ሰጥተው ትራፊ ይለምናሉ፤ልመናው እንዳይቆምባቸው ዘመናዊ አሽከርነትን በየእለቱ ይለማመዳሉ፣ዘር ማንዘራቸውን ለኢኮኖሚ ጥገኝነት አሳልፍው ይሰጣሉ፣ልጆቻቸው በድህንት የተጠፈሩ ባሮች ሆነው በግዞት እንዲኖሩ ይማማሉባቸዋል።

የህወሐት ወያኔ የእጅ ስራ ውጤት የሆኑት ፓርቲዎችና ተጠፍጥፈው የተሰሩት መሪዎቻቸው አልጠግብ ባይ ሀነዋል፣እርግማን ያወዛው ፊታቸው፣በግፍ ያጋተው ቦርጫቸውና በርም የሰበሰቡት ሀብታቸው ትምክህት ሆኖባቸዋል፤የቱኒዚያ ህዝብ ከ23 አመታት የግፍ አገዛዝ በሗላ የወሰደው አይነት እርምጃ የማይመለከታቸው መስለው የጣር ሳቅ እየሳቁ መሽቶ ስለሚነጋ የፍርድ ቀን የሚመጣ አይመስላቸውም፤ያ ቀን ግን ከፊትለፊት ነው፣ያ ቀን ሲመጣ ማጣፊያው ያጥራል፣የቱኒዘዚያን ህዝብ አመጽ የፖለቲካ መሪ አልመራውም፣እንደውም ይሄ ነው የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ የለም፤ህዝብ በቃኝ አለ፤ህዝብ ነጻነቱን አወጀ፤ይህ እውነት ነው የቱኒዚያን ለውጥ ልዩ ያደረገው ። የትንሿ ልጅ አይነት ጀግኖች ታሪክ ይሰራሉ፤በነገራችን ላይ ትንሿ ልጅ እንዴት ሆንች? መጨርሻዋ ምን ሆነ?ለምትሉ የአድዋው ሰውዩ ከነቤተሰቦቿ መላ ፈልጎላት እየኖረች ነው፤አቶ መለስና ቱባ ባልስልጣኖቻቸውም አድዋ ናቸው።አስገራሚ መገጣጠም! በ1997 ዓ.ም የምርጫ ክርክር “ጅኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል ፣”በማለት ዶክትር ብርሀኑ የህዝብን ለውጥ ፈላጊነት መገደብ እንደማይቻል ሲናገሩ አቶ በረከት ስምኦን “ከጠርሙሱ የወጣው ጅኒ ቦዘኔው ነው፣ቦዘኔ በየትኛውም ዓለም ለውጥ አምጥቶ አያውቅም” የሚል መልስ ሰጥተው ነበር፤እንዲህ ያለ መሪ 20 ዓመት ከኛ ጋር አለ።እኛም አለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 31, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.