ታዋቂው ደራሲ እና ተርጓሚ አቶ ማሞ ውድነህ ህይወታቸው አለፈ

ታዋቂው ደራሲ እና ተርጓሚ አቶ ማሞ ውድነህ፤ በተወለዱ በ81 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈ መሆኑ ታወቀ። አቶ ማሞ ውድነህ በዳግማዊ ምኒልክ፣ በጥቁር አንበሳ እና በኢንተርናሽል የልብና ልብ ነክ ደዌዎች ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን፤ በዛሬው እለት ግን ህይወታቸው ያለፈ መሆኑ ተገልጿል።

የአቶ ማሞ ውድነህ የቀብር ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር የካቲት 24 ቀን፣ 2004፤ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም መሆኑ ተያይዞ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

አቶ ማሞ ውድነህ ከመሞታቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ተናግረው የነበረውን የሪፖርተር ቃል ከዚህ ቀጥሎ አቀናብረን አቅርበነዋል።

“- ሕመሜ ከልብ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ቀደም ብዬ በውጭም ታክሜያለሁ፡፡ እግሬ እብጠት አሳይቷል፤ ሰውነቴ ውኃ ቋጥሯል፤ ሐኪሞች እርሱን ለማስወጣት ትንሽ ጊዜ ይጠይቀናል ብለዋል፡፡ ስኳሩም ሳስታምመው 24 ዓመት ሆኗል፡፡ የደም ዙረቱም ችግር አለበት፡፡

“መጀመርያ የታከምሁት ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ነው፡፡ የእግሬን ቁስል አዩና የሚችሉትን አደረጉና ወደ ጥቁር አንበሳ በሪፈራል ሄድኩ፡፡ ጥቁር አንበሳ በስንት መከራ ነው አልጋ ያገኘሁት፡፡ የመጀመርያው ቀን ድንገተኛ ክፍል ወደቅሁ፤ መከራዬን አየሁ፤ ያን ቀን ለመሞት ተመኝቼ ነበር፤ ሲዖል ነበር፡፡ በማግሥቱ ሁለተኛ ማዕረግ አልጋ ተገኝቶ ሜዲካል ገባሁ፤ የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፤ ከ5ኛ ፎቅ ወደ 8ኛ ፎቅ ወሰዱኝ፤ ብዙ ምርመራ በያይነቱ ተካሔዶ ውጤቱ ደህና ነው፤ ያለው ችግር ቀስ በቀስ ይወጣል አሉኝ፤ ይሁን እንጂ አራት ቀን ተሰቃየሁና ዲስቻርጅ አድርጉኝ አልኩኝ፡፡

ያ ክፍል ለእኔ እስር ቤት ነበር፡፡ አልጋው ላይ እንደዚህ መተኛት አይቻልም፡፡ የረገበ ሽቦ ነው፤ ከሆስፒታሉ ጋራ አብሮ የተሠራ ይመስላል፡፡ ለመነሣትም፣ ለመተኛትም ሰው ያስፈልጋል፡፡ ክፍሉ 1ኛ ማዕረግ ተባለ እንጂ ውኃም መብራትም የለውም፡፡ ጭልጭል የምትል የራስጌ መብራት አለው፡፡ በረሮ ስገል ነው የምውለው፡፡ ምግብ ሲሸታቸው ይወጣሉ፡፡ ረጨን ብለውን ነበር፤ ተላምደውታል መሰለኝ፡፡ ውኃ በባልዲ እየተቀዳ ወደ በሽተኛ የሚገባበት ነውና ወጣሁ፡፡ እዚህ ሰው የሚተኛበት አልጋ አገኘሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ምርመራቸውን ፈልጌ ነበር ውጤቱን አልሰጡኝም፤ እንደገና ልመረመር ነው፡፡” ብለው ነበር። ሆኖም ሞት ቀደማቸውና በተወለዱ በ75 አመታችው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ከላይ የተገለጸውን አስተያየት ከተናገሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው የአቶ ማሞ ውድነህ ህይወት ያለፈው። ኢ.ኤም.ኤፍ. በዚህ አጋጣሚ ለአቶ ማሞ ውድነህ ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናቱን ይመኛል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 2, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.