ታላቁ የሚሊኒየም ግድብ – ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተትዋን እማላይ!

ታደሰ ብሩ

“የሚሌኒየሙን ግድብ ሕዝባዊ የልማት ሐውልት እናድርገው !!” የሪፓርተር ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ

ይህ ድንቅ ሃሳብ ነው። ብራቮ ሪፓርተር!!! ግን ለምን እስከነገ እንጠብቃለን? የሚሊኒየሙ ግድብ የልማት ሃውልታችን ነው!!!! ነው!!!! ነው!!!! ነው!!!!

የሪፓርተር ጋዜጣ ታላቁ የሚሊኒየም ግድባችን የልማታችን ሃውልት እናድርገው በማለቱ መፈንጠዜ ያለምክንያት አይደለም። ልማታችን እንደ ሚሊኒየም ግድባችን ሁሉ “ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተትዋን እማላይ” ስለሆነ የግድቡ ሃውልትነት ተገቢም ወቅታሚም በመሆኑ ነው። በበኩሌ ሪፓርተር እንዲህ ዓይነት በሳል ሃሳብ ሲያቀርብ አላጋጠመኝም።

ይህ ዜና ያስደሰተኝ በሁለት አንኳር ምክንያቶች መሆኑ እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ። አንደኛ፤ የሚሊኒየሙ ግድብ የሰማይ ላይ ላሞቻችንን ቁጥር በአንድ አሳድጎልናል። ሁለተኛ፤ ይህች ላም ለሌሎች ላሞቻችን በሃውልትነት የማገልገል ተጨማሪ እገዛ ታደርጋለች። “የሰማይ ላይ ላም እንዴት ሃውልት ይሆናል?” ብላችሁ አትጠይቁ፤ ይሆናል! “የሰማይ ላይ ላሞቻችን ሃውልት ለምን ያስፈልጋቸዋል?” አትበሉ፤ ያስፈልጋቸዋል!

ሌላው አስደሳች ዜና ደግሞ ይህች ውድ ላማችን አንድም ክፉ ነገር እንደማይደርስባት ካሁኑ ማረጋገጫ ማግኘታችን ነው። “ግድቡን ማንም መጥቶ በቦምብ ያፈነዳዋል የሚል ስጋት አይግባችሁ፤ እንደዚህ የሚባል ነገር ቀልድ ነው የሚሆነው ” ብሏል መለስ ዜናዊ። “በሰማይ ላይ ያለን ግድብ ማን ሊያፈነዳው ነበር?” ብላችሁ አትጠይቁ።

ለማንኛውም ይህን የደስታውን ብስራት ተጠቅመን የሰማይ ላይ ላሞቻችንን ለምን አንቆጥራቸውም?

የሰማይ ላይ ላም ቁጥር አንድ: መልካም አስተዳደር

በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን ከሁሉም በላይ የደላት የሰማይ ላይ ላማችን “መልካም አስተዳደር” የተሰኘችው ናት። ስለዚች የሰማይ ላይ ላማችን በየስብሰባው እንሰማለን። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ስለእሷ ተናግረው አይጠግቡም። አቶ መለስም ስለዚች ላም ሳያነሳ የሶስት ደቂቃ ንግግር ማድረግ አይችልም፤ ይናፍቃታል። ታድያ ይህች ላማችን ከ1983 ጀምሮ ለሃያ ዓመታት ወሬዋ ይሰማል እንጂ እግሮቿ የኢትዮጵያን ምድር ረግጠው አያውቅም። ይህች ላም አንድ ቀን እግሯን መሬት ላይ ታሳርፍ ይሆናል የሚለው ተስፋቸው የተሟጠጠባቸው የአንድ ወቅት የፓርላማ አባል “እንኳን መልካም አስተዳደር መጥፎም አስተዳደር አላገኘንም” ሲሉ አማረሩ። እኚህ ሰው ተሳስተዋል “መልካም አስተዳደር” አለች – ሰማይ ላይ!

የሰማይ ላይ ላም ቁጥር ሁለት: የህግ የበላይነት

“በህግ አምላክ” የሚልን ሰው ተስፋ ለማስቆረጥ መለስ “የህግ የበላይነት” የተባለችው ተወዳጅዋ ላማችንን አርቆ ወደ ሰማይ ያመጠቃት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥላዋ እንኳን አይታይም። እስዋም በመለስ ክፋት በመማረሯ እስከ አገዛዙ ፍፃሜ ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ ምላለች። ዛሬ በኢትዮጵያ በምድር ላይ እስዋን ተክታ እየሰራች ያለችው ከቆዳና ጭድ የተሰራችው “የህግ የበታችነት” የተባለችው አሳሳች አምሳያ ነች። ያም ሆኖ ግን ከእይታ አድማስ ስለራቀችው “የህግ የበላይነት” ዘወትር ሲወራ እንሰማለን። ሌላው ቀርቶ “የህግ የበታችነትን” ከቆዳና ጭድ የሰሩት መለስና ጓደኞቹ ሳይቀር ስለህግ የበላይነት አብዝተው ይናገራሉ።

የሰማይ ላይ ላም ቁጥር ሶስት፡ ፈጣን እድገት

ከምርጫ 97 ወዲህ የመጠቀችው ሶስተኛዋ ላማችን “ፈጣን እድገት” ትሰኛለች። በዚህ ላማችን ማረግ ያላዘነ የለም። “ቁርስ”፣ “ምሳ” እና “እራት” በደረሰባቸው ሃዘን ምክንያት “ቁምሳ” ወይም “ቁራት” ወደሚል አንድ ቃል ተጠቃለዋል። ይሁን እንጂ ፒያሳ የሚገኘው የጠቅላይ ስታትስቲክ ጽ/ቤት ስለ ላማችን ደህነት ወቅታዊ መረጃዎችን ይሰጠናል። ቻይናዎች በመሬት ልዋጭ የሰሯቸውን መንገዶችና የመለስ ጓደኞች የሠሯቸው ህንፃዎች ርዝማኔ “ፈጣን እድገት” የተሰኘችው የሰማይ ላይ ላማችን ጤንነት የተሟላ መሆኑ ማረጋገጫዎች ናቸው ተብሏል። ገበሬው ቢፈናቀል፤ ሠራተኛው ከሥራዉ ቢባረር፤ ዘይት ቢጠፋ የፈጣን እድገታችንን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም። እንዲያውም በምድር ችጋር ሲበዛ እሷ በሰማይ ትፋፋለች።

ከላይ እንደተገለጸው በዚህ ሳምንት አንዲት ላም ተጨምራልናለች። የቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ የመንና ሊቢያ ወጣቶች ተጋድሎ ይህችን ድንቅ ላም እንድናገኝ ቁልፍ የሆነ አስተዋጽዖ አድርገዋል ተብሏል፤ እናመሰግናለን። ስለዚች አዲስ ላማችን ትንሽ እናውጋ።

የሰማይ ላይ ላም ቁጥር አራት: ታላቁ የሚሊኒየም ግድብ

“ታላቁ የሚሊኒየም ግድብ” “በትራንስፎርሜሽን” እቅድ ውስጥ እንኳን ያልነበረች፤ ዝርያዋ በውል ያልታወቀ፤ በድንገት ቡልቅ ያለችልን ተዓምራዊ ድንቅ የሰማይ ላይ ላማችን ነች። ለዚህም ነው ዝናዋ ግን ገና ካሁኑ ዓለምን ያዳረሰው። ስለዚች ላም የተነገሩ ነገሮች እርስ በርሳቸው የሚጣሉ ቢሆንም ላሚቷ ሰማይ ላይ አለች።

“የግድቡ ጥናት የት አለ? መቸ ተደረገ?” “ክርክር የሌለባቸው የሌሎች ወንዞች ግንባታ ቢቀድም አይሻልም ነበር ወይ?” “ይሰራስ ቢባል አቅሙ አለን ወይ?” “የተመረተውንስ የኤሌክትሪክ ኃይል ምን ልናደርገው ነው?” … ወዘተ … ጥያቄዎችን ማንሳት አይገባም። መስማት ያለብን የሚከተለውን ነው።

ሚሊኒየም ግድባችን ከሱዳን ድንበር ከ20 አስከ 40ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ ይገነባል። ግንባታው ሲጠናቀቅ 5,250 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል። ይህ ግድብ በኢትዮጵያ እስካሁን ከተገነቡት መካከልል ትልቁ ሲሆን፣ ከ62 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የውሃ መጠን (የጣና ሐይቅ የውሃ መጠንን ሁለት እጥፍ) የመያዝ አቅም ይኖረዋል። ለግድቡ የሚያስፈልገውን ወጪ ከ70 እስከ 80 ቢሊዮን ብር ወጪ ራሳችን እንችላለን። በፕሮጀክቱ ግብጽና ሱዳንንም ተጠቃሚ ናቸው።

ተዓምራዊ የሰማይ ላይ ላም!!!

በሪፓርተር ጋዜጣ በሳል ጥቆማ መሰረት ይህች ላም ለልማታችን ሃውልት ትሁን። እኔ ይህንን ሃሳብ በሙሉ ልብ እደግፋለሁ። የሰማይ ላይ ላም ለሆነው ልማታችን በሰማይ ላይ የተገነባ ግድብ የመታሰቢያ ሃውልት ይሁነው !

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 9, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.