ተጠለፉ የተባሉት የስልክ ንግግሮች በፍርድ ቤት ተሰሙ

(ኤፍሬም ካሳ)

ህዳር 7 ቀን 2004 ዓ.ም፡- በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በኤሊያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል “በመረጃና በደኅንነት ኀይሎች ሥልካቸው ተጠልፎ የተያዘ ነው” የተባለ የድምጽ ማስረጃ በዐቃቤ ሕግ ቀረበባቸው፤ የተከላካይ ጠበቆች በማስረጃው ላይ ያላቸውን አስተያየት ከህዳር 18 ቀን 2004 ዓ.ም በፊት እንዲያቀርቡ ታዘዙ፡፡

የዐቃቤ ሕግን የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን ትናንት ከሰዓት በኋላ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ- ሕግ እና የተከላካይ ጠበቆች የማስረጃ አስተያየትን መርምሮ ህዳር 18 ቀን ማስረጃዎቹ በጥፋተኝነት ሊያስከስሱ ይችሉ ወይም አይችሉ እንደሆነ ውሳኔውን እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡

ማስረጃው ዐቃቤ ሕግ በመረጃና በደኅንነት ኃይሎች ሥልካቸው ተጠልፎ ማስረጃ ተይዞባቸዋል ያላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀ መንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚያአብሔር፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ም/ል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ እና የፍትሕ ጋዜጣ ዓምደኛና መምህርት ርዮት ዓለሙ በአሜሪካን አገር ከሚኖረው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ክፍሌ ጋር መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ ያደረጉትን ንግግር ነው ተብሏል፡፡

ዐቃቤ ሕግ እንዳስረዳው በቀረበው የድምጽ ማስረጃ ላይ ተከሳሾች ከኤሊያስ ክፍሌ ጋር ያደረጉትን የቀን ተቀን የስልክ ግንኙነት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አብዴፓ) ሊቀ መንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግያአብሔር በአብቶቡስ ተራ አካባቢ በሊስትሮ ሥራ ከሚተዳደረው እና “በቃ” እያለ ከጻፈው ቦና ታከለ ጋር ያደረጉትን ንግግር ነው፡፡

በችሎቱ ላይ ከቀረቡት 16 የተለያዩ የሥልክ ንግግር ልውውጦች ዐቃቤ ሕግ “የኤሊያስ ድምጽ ነው” ካለው ጋር በተለያየ ጊዜና ቦታ ሲነጋገሩ የተሰሙት ድምጾች የአቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር ፣ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና የጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ ድምጾች መሆናቸው በፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲስ ዲፓርትመንት ተረጋግጧል በማለት ዐቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ባሰማው የድምጽ ማስረጃ ላይ አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር ለኤሊያስ ክፍሌ “…ይኸውልህ በስልክ አላወራም ግን እንደሚሆን እናደርጋለን” ብሎ ሲናገር በሌላ የሥልክ የመልዕክት ልውውወጥ ላይ ደግሞ ለውብሸት ደውሎ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ “ሰውየውን አናገርኩት እኮ ወደ በኋላ ላይ ቁጥሮቹን እሰጥሃለው ብሎኛል-አብረን የምንሰራው ሥራ ይኖራል” ብሎ ሲናገር ይደመጣል፡፡

ቀጥሎም ጋዜጠኛ ኤሊያስ ክፍሌ ለጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ደውሎለት “በቃ” ተብሎ የተጻፈባቸውን ቦታዎች ተመልክቶ ዘገባውን ቶሎ ሰርቶ እንዲልክለት የሚጠይቅ ሲሆን ለጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ በመደወል ደግሞ መርካቶ አብቶቡስ ተራ አካባቢ “በቃ” የሚለውን ጽሑፍ ያለበትን ቦታ ፎቶ አንስታ እንድትልክለት ሲጠይቃት እርሷ ካሜራ እንደሌላት ከቻለች ተውሳ ፎቶውን እንደምታነሳ የተናገረችው ተደምጧል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት ዐቃቤ- ሕግ ያቀረበው የድምጽ ማስረጃ ማን ከማን ጋር በምን ሁኔታ እንደተነጋገረ ያልተብራራና ድምጹም የእነርሱ ነው ወይ፣ ጽሑፎን የገለበጠው ሰው የራሱን ሃሳብና ትችት እንዳላካተተበት ማስተማመኛ የለም በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ “ይህ ብቻ ሳይሆን ከብዙ ነገር ጋር ተመሳክሮ የሚታይ ነው፣ እነርሱ ያሉት የፎረንሲክ ዲፓርትመንት ተከታትሎ የያዘው ነው፣ ይህ ምስክሮች ከሰጡት ቃል ጋር ተገናዝቦ የሚታይ ነው” ብሏል፡፡

Source: Addis Neger online

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 18, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.