ተቃዋሚዎች በቂ የፖለቲካ መድረክ (political space) የለም ይላሉ

Also Today:
» Message to Ethiopian Muslim leaders – Mr. Obang Metho »
» Between a Rock and a Hard Place – By Tesfaye Maru »

ሪፖርተር 27 July 2008 – ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ በቂ የፖለቲካ መድረክ (political space) የለም ይላሉ፡፡ መንግሥት ደግሞ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚያስችል በቂ የሆነ የፖለቲካ መድረክና የመጫወቻ ስፍራ አለ ይላል፡፡ ይህ የመንግሥትና የተቃዋሚዎች ልዩነት የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ትኩረት የሳበ ሲሆን አምኒስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ወች በኢትዮጵያ ያለው አሳታፊ የፖለቲካ መድረክ እየጠፋና እየተሸረሸረ ነው ይላሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብና ልዩነት በቅርቡ የፀደቁት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት፣ የፓርቲዎች ምዝገባ ሕግና ረቂቁን የበጎ አድራጎት ማኅበራትና ድርጅቶች አዋጅ ተከትሎ እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የፖለቲካ መድረኩ ምን ይመስላል? ወዴትስ እየሄደ ነው? የሚለው ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች የማይጣጣሙት አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ወች ከሳምንት በፊት ባወጡት ሪፖርት “በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እጅግ እየጠበበና የማያፈናፍን እየሆነ መጥቷል” ብለዋል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት አያያዝን ሲተች የቆየ ሲሆን ከምርጫ 97 ወዲህ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በሙሉ ተቀባይነት ሲያጡ ቆይተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር በሶማሊያ የግፍ እርምጃ እየወሰደ ነው” የሚለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አሁን ደግሞ “በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብትና ዴሞክራሲን ማስፈን የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችን በነፃነት ማንሸራሸር የማይታሰብ ነው” በማለት ገልጿል፡፡ ከምርጫ 97 ወዲህም የፖለቲካ መድረኮች እየተሸረሸሩ፣ ሠብዓዊ መብቶች እየተደፈሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ወችም የአምኒስቲ ኢንተርናሽናልን ሃሳብ የሚጋራ ሲሆን በኢትዮጵያ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦችን ማራመድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ያመለክታል፡፡ “በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሂደት ከምርጫ 97 ወዲህ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ከምርጫው በኋላ የወጡ ሕጐችም የፖለቲካ ተሳትፎውን የሚጐዱና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማያበረታቱ ናቸው” ይላል፡፡ በተጨማሪም የሠብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የሚያመለክተው ሂዩማን ራይትስ ወች ያሉት ሁኔታዎች የፖለቲካ መድረኩን የሚያጠቡ መሆናቸውን የሚዲያ ሕጉ መፅደቁን ተከትሎ የወጣው መግለጫው ያመለክታል፡፡

ይህንን አስመልክተን ያነጋገርናቸው ተቃዋሚዎችም የሁለቱን ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ድርጅቶች ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተስፋ እንዳስቆረጣቸውም የሚገልፁ አሉ፡፡

በግል የፓርላማ ተመራጭ የሆኑትና የቀድሞው የኢፌዴሪ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚናገሩት “እስካሁን ድረስ የሚታየው የፖለቲካ መድረክ ተዘግቷል፡፡ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል የመወዳደሪያ ቦታ የለም፡፡ ይህ ደግሞ የመነጨው ከኢሕአዴግ ፖሊሲ ነው”፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ይህ የፖለቲካ መድረክ መጥበብ የጀመረው በ1993 ዓ.ም. መሆኑንና ኢሕአዴግ በጥቅምት 1999 ዓ.ም. ላይ ያወጣው “ልማት፣ ዴሞክራሲና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው ፖሊሲውና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራሮችና ታክቲኮች ያለውን የፖለቲካ መድረክ ለማጥበብ የተዘጋጁ እንደሆኑ የሚያስረዱት ዶ/ር ነጋሶ “ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በ2ዐ ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ አስገባለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋል፡፡ ጠንካራ መንግሥት ደግሞ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴያቸው የተገደበ መሆን አለበት የሚል ስሌት አለው” ይላሉ፡፡

ዶ/ር ነጋሶ “ኢሕአዴግ ለተቃዋሚ ኃይሎች ጥሩ ስሜት የለውም፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የኪራይ ሰብሳቢዎች ተወካይ ናቸው፡፡ መኖር የለባቸውም ብሎ ያምናል” በመሆኑም የፖለቲካ መድረኩ እየጠበበ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ “ኢሕአዴግ በስትራቴጂው መሠረት በአካባቢ ምርጫ የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት መፈጠር ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ ሕዝቡን፣ ሠራዊቱን፣ የመንግሥት መዋቅሮችንና ሚዲያን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር አውሏል” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ በቅርቡ የወጡት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ሕግ፣ የፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ እና ሌሎችም የፀደቁና ይፀድቃሉ ተብለው የሚታሰቡ ሕጐች አፋኝ እና ሕገ መንግሥቱን ያላከበሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ የፖለቲካ መድረኩ መጥበቡ በፓርላማም ጭምር እየጠበበና እየጠፋ መምጣቱን የሚያስረዱት ዶ/ር ነጋሶ የራሳቸውን ጉዳይ እንደማሳያ ያቀርባሉ፡፡ “እኔ ከ140 ሺህ በላይ ሕዝብ መርጦኝ ፓርላማ ገባሁ፡፡ በፓርላማ ግን ተሳትፎዬ ተገድቧል፡፡ ለወከልኩት ሕዝብ መናገር አልቻልኩም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ተመርጬ፤ በፓርላማው የአሠራር ሕግ መብቴ ተነሥቷል” ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የተቃውሞ ፖለቲካ ረጅም ዓመታትን ያሳለፉት ኘ/ር በየነ ጴጥሮስም ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት ያላቸው ሲሆን በሚያዚያ ወር ከተካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫም ፓርቲያቸው ራሱን ያገለለው የፖለቲካ መድረኩ በመጥፋቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የፖለቲካ መድረክ እየጠፋ ነው ወደሚለው እየተቃረብን ነው፡፡ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችለን መድረክ የለም፡፡ አሁን ያለው ተቃዋሚ ቢኖርም ባይኖርም ለውጥ የማያመጣና ተፅእኖ የማያሳርፍ ነው፡፡ ፉክክር ያለበት መድረክ መጥፋቱም በማሟያና የአካባቢ ምርጫ ወቅት ታይቷል፡፡ የፖለቲካ መድረክ አለ ለማለት የፓርቲ ቁጥር መብዛት ሳይሆን ተፅእኖ መፍጠር የሚችል ኃይል መፈጠሩ ነው” የሚሉት ኘሮፌሰር በየነ የፖለቲካ ሥራ መስራት የሚቻለው በሕዝብ ውስጥ (grass root level) መሆኑንና ሕዝቡን ማግኘት ግን በፍፁም የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ይገልፃሉ፡፡ “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መቀበሪያው ተቆፍሯል፤ መገነዣው ተመቻችቷል፡፡ ግብዓተ መሬቱም እየተፈፀመ ነው” ያሉት ኘ/ር በየነ ከአሁን በኋላ ምንም የቀረ የፖለቲካ መድረክ አለመኖሩን፤ ኢሕአዴግም ይህንን እንደሚፈልገው ይናገራሉ፡፡ “ኢሕአዴግ በአካባቢና ማሟያ ምርጫ የወደፊት አካሄዱን አሳይቶናል፡፡ እየወጡ ያሉት ሕጐችም የሚያመላክቱት ይህንን ነው፡፡ አሁን አንድ የጋራ መድረክ ለመፍጠር የተነሳሳነውም የመደራደር አቅማችንን ለማጐልበትና ይህንን የአንድ ፓርቲ ስርዓት ምሥረታ ለመስበር ጥረት ለማድረግ ነው” ይላሉ፡፡

አቶ ልደቱ አያሌውም የሁለቱን ሰዎች ሃሳብ የሚጋሩ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ ያሉ ሕጐች በቂ የፖለቲካ ተሳትፎ መድረክ ለመክፈት የሚያስችሉ ሲሆን አፈፃፀማቸው ግን ችግር እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡ “የፖለቲካ መድረኩ በተወሰነ ደረጃ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በቂ አይደለም፡፡ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩልነት የሚያስተናግድ መድረክ የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶችም ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ችግር ስላለባቸው መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ሆነዋል” የሚሉት አቶ ልደቱ፣ “በተዋረድ ያለ የመንግሥት መስተዳድሮች ተቃዋሚዎችን እንደ ጠላት መቁጠራቸው ተቃዋሚዎች ወደ ሕዝቡ ቀርበው እንዳይሠሩ አግዷቸዋል” ይላሉ፡፡ መንግሥትም የአካባቢ መስተዳድሮች የሚሰሩትን ስህተት ለማረም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን አቶ ልደቱ ያስረዳሉ፡፡

“በመገናኛ ብዙሃን አፈፃፀም ምንም ዓይነት ክፍት መድረክ የለም፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ለተቃዋሚዎች ዝግ ነው፡፡ እንደ አገር ሃብት ለዴሞክራሰያዊ ስርዓት ግንባታው ማበርከት ያለባቸውን አስተዋፅኦ የመንግሥት ሚዲያዎች እየተወጡ አይደለም” ያሉት አቶ ልደቱ ሌላው የፖለቲካ መድረኩን እያጠበበው የመጣው የመንግሥት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸውና ጠንካራ መዋቅር የሌላቸው በመሆኑም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ተቋማቱ የአገርንና የፓርቲን ጉዳይ ለይቶ የማየት ችግር ያለባቸው በመሆኑም ተፈጥሮ የነበረውን መድረክ በማጥበብ ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እየተወጡ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “በሕግ ደረጃ ሊያሰራ የሚችል የፖለቲካ መድረክ አለ፡፡ ተግባር ላይ ሲመጣ ግን እየጠበበና የማያሰራ እየሆነ ይመጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱና በሕግ የተፈቀዱ መድረኮች አበረታች ናቸው፡፡ በሕግ ደረጃ መቀመጡ ግን ተግባር ላይ ካልዋለ ምንም ፋይዳ አይኖረውም” የሚሉት አቶ ልደቱ የፖለቲካ መድረኩ እየጠበበ መምጣቱንና መስተካከል ያለባቸው ሁኔታዎች እንዳለባቸው ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶቹንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የፖለቲካ መድረክና መንቀሳቀስ ጠፋ አቤቱታ ግን አይቀበለውም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መፈጠሩንና ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን መንግሥት ይገልፃል፡፡ ከ1997ቱ ምርጫ በፊት በነበረው ፓርላማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወደ ፓርላማ መግባት መቻላቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና የሂዩማን ራይትስ ወችን ሪፖርት ተቃውሞ ያወጣው መግለጫ ሲጠቀም ይህንን የሚያክል ስኬት በመጣበት አገር የፖለቲካ መድረክ እየጠፋ ነው ብሎ መናገር ተቀባይነት እንደሌለው አመልክቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርስ ባለመስማማት የራሳቸውን ጥንካሬ እያጡ ባለበት ሁኔታ ለእነሱ እንቅስቃሴ መዳከምም መንግሥትም ሆነ ሌላ አካል ሳይሆን ራሳቸው መሆናቸውን የሚገልፀው መግለጫ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና የሂዩማን ራይትስ ወች ሪፖርት ተቀባይነት እንደሌለው አመልክቷል፡፡

ሁለቱም ድርጅቶች በቅርቡ የወጣው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ መድረክ የሚያጠፋና ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁ ሲሆን መንግሥት ለዚህ በሰጠው መልስ አዲስ የወጣው ሕግ ላለፉት ስድስት ዓመታት ውይይት የተደረገበት፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት አስተያየት የሰጡበት መሆኑን ገልፆ በመንግሥት እምነት አዲሱ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ ልማታዊ ጋዜጠኛ (developmental journalist) የሚያፈራና የኘሬስ ነፃነትንም የሚያስከብር መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ወች ረቂቁን የሲቪል ማኅበራት ሕግ ተቃውመውም መግለጫ ያወጡ ሲሆን ድርጅቶች መግለጫ መሠረተ ቢስ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ድርጅቶቹ መንግሥት ያወጣው ረቂቅ ሕግ በሥነ-ዜጋ፣ በሠብዓዊ መብቶች፣ በግጭት ማስወገድና ፍትህ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ በመሆኑ እንዳይፀድቅ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የወጣው ሕግ ሕጉ የሠብዓዊና ዕርዳታ ድርጅቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የሚረዳና ስራቸውን በተለየ ሁኔታ የሚቆጣጠርና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ግን መንግሥት ማንኛውንም ድርጅት እንዳይቆጣጠር የሚፈልጉ መሆኑ የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡ ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአገሪቱን ሕግ ሳያከብሩ እንደሚገኙና ታክስ ባለመክፈል እንዲሁም የተለያዩ ሕገ ወጥ ሥራ ሲሰሩ ሲያዙ ፈቃዳቸውን እንደሚሰረዝና እስካሁንም 17 ያህል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሕገ ወጥ ተግባር በመያዛቸው ፈቃዳቸው ባለፈው ዓመት መሰረዙን መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ላይ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ የተቃዋሚዎቹና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ ወቀሳም መሠረተ ቢስ መሆኑን መንግሥት ገልጿል፡፡

በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ይደረጉ የነበሩ ክርክሮችና የድርድር መድረኮች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተቋረጠ መሆኑንና ባለፈው የማሟያና የአካባቢ ምርጫ የታየው ደካማ የተቃዋሚዎች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ያልጠነከረው ዴሞክራሲ ጭራሹን ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ብዙ ተቃዋሚዎች ያስረዳሉ፡፡ ሕዝቡ በፖለቲካ ያለው ንቁ ተሳትፎ መቀነሱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውጫዊና በውስጣዊ ችግሮች መታመሳቸው የተቃዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንዳዳከመው ይገልፃል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 27, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.