ብርቱካን የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብላ ልትሸለም ነው

Birtukan Mideksa - Person Of The Yearቫንኩቨር (1 Sept. ’09) በቃሊቲ እስር ቤት በፖለቲካ እስረኝነት የምትገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓረቲ ፕሬዚዳንት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የዓመቱ ታላቅ ሰው ተብላ ለሽልማት እንደታጨች ተገለጸ። ከተለያዩ የካናዳ ከተሞች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያንና የሲቪክ ማህበራት የተሳተፉበት ምርጫ ኮሚቴ፡ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የዓመቱ ታላቅ ሰው ብሎ በብቸኛ እጩነት ያቀረባት ሲሆን፡ የሽልማት አሰጣጥ ስርአቱ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 5 ቀን በውቧ የምእራብ ካናዳ ከተማ፡ ቫንኩቨር፡ እንደሚካሄድ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ ከተመረቀችበት ግዜ አንስቶ ከስድስት አመታት በላይ በመጀመሪያና ከፍተኛ ፍ/ቤት ደረጃ በሰራችበት ጊዜ ሁሉ የቀድሞውን የሕወሀት መከላከያ ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎች ያለአግባብ የታሰሩና ህገ መንግስታዊ መብታቸው የተጣሰ ሰዎችን መብት በማስከበር ረገድ ላሳየችው ሐቀንነት፤ እንዲሁም ከዳኝነት ሙያዋ ስትነሳም፡ ወደ ፖለቲካው መስክ ገብታ በኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ እየከፈለች ላለቸው መስዋእትነት ለዚህ ሽልማት እንደበቃች ኮሚቴው ገልጿል።

ወ/ት ብርቱካን ለሰላማዊ ትግል ያላትን ታማኝነት በየግዜው ብትገልጽምና ብታሳይም፡ ቀደም ሲል በቅንጅት ም/ሊ/መት በነበረችበት ግዜ ምርጫ 2005ን ተከትሎ በሕወሀት አገዛዝ ታስራ በቃሊቲ ከ18 ወራት በላይ መስዋእትነት ከፍላለች። ከእስር ከተፈታች በኋላም በየጊዜው የሚደርስባትን ወከባና አፈና ተቋቁማ በአገዛዙ እርምጃ የፈረሰውን ቅንጅትን እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ ባዲስ መልኩ አዋቅራ፡ የአንድነት ፓርቲን በተሳካ ሁኔታ ከትግል አጋሮቿ ጋር በመሆን መስርታ በሊቀ መንበርነት ተመርጣ ነበር። ይሁን እንጂ የብርቱካንን ጽናትና እየገነነ መምጣት የተመለከተው አገዛዝ በተለያየ ግዜ ቅስሟን ለመስበር ያጠመደው ወጥመድ አልሳካ ቢለው፡ ወ/ት ብርቱካን በድጋሜ ወደ ቃሊቲ በእስር ከተወረወረች እነሆ 240 ቀናት አለፏት። በነጻነት ትንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት ሁሉ ብርቱካን ሰላምን አጥብቃ የምትሰብክ፡ ከበቀልና ጥላቻ የራቀች የፍቅር ሰው ነበረች። በእስር ባለችበት ሰዓትም ብርቱካን የጽናትና የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ነች። ስለዚህም በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵአዊያን ይሄንን የዓመቱን ታላቅ ሰው ሽልማት በታላቅ ደስታና ኩራት አበርክተውላታል።

በዚህ የሽልማት ስነስርአት ላይ መቀመጫው ሲያትል የሆነውና ብርቱካንን በቅርበት የሚያውቃት የህግ ባለሙያ አቶ ሼክስፒር ፈይሳ ይገኛል። ይሄንን ሽልማትም የኢትዮጵያ ካናዲያዊያን ዜጎች ሊግ፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ፡ ኤ.ቲ. ኢንተርቴይንመንት፡ አንድነት ቫንኩቨርና፡ በአቶ ኦባንግ የሚመራው የጋራ እንቅስቃሴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ያጸደቁትና የሚደግፉት ሲሆን፡ ከሽልማት ሽነስርአቱ በኋላ፡ ገቢው ለብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰቦች መርጃ የሚሆን የባህል ምሽት በቫንኩቨር በሚገኘው የፋሲል ሬስቶራንት ውስጥ እንደሚካሄድም አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ቫንኩቨር የ2010ን የበጋ ኦሊምፒክ የምታዘጋጅ ሸጋ ከተማ ስትሆን፡ ከመስከረም አምስት እስከ መስከረም ስድስት ቀንም በካልጋሪ፡ ኤድመንተን፡ ቫንኩቨር፡ ሲያትል፡ ፖርትላንድና ቪክቶሪያ መካከል የሚካሄደውን የኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ውድድርም እንደምታስተናግድ ታውቋል። የዓመቱ ታላቅ ሰው ሽልማትም የሚካሄደው በዚሁ የስፖርት ውድድር ማካሄጃ ሜዳ አጠገብ በሚገኘው ኬንሲንግተን ፓርክ ውስጥ ነው። በሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን ባቅራቢያው ከሚገኙ ከተሞች ውድድሩን ለመመልከት ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፡ ታዋቂው ድምጻዊ አብዱ ኪያርም ዝግጅቱን ንደሚያቀርብ የኮንሰርቱ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ዛሬው አትክልት አሰፋ አስታወቋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 1, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.