“ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ”ግፈኞችና ግምኛ አፋቸው – በክፍሉ ሁሴን

የአገሬ ሰው “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም”የምትል አባባል ነበረችው።ግፍ በተለያየ ምክንያት ሊውልብህ ቢችልም የግፉ ደራሲ ግፉን ሲፈጽምብህ ወይም እየፈጸመብህ መርዘኛ በሆነ ፀያፍ አነጋገር በሕሊናህም ላይ ጠባሳ ካልተወ በጊዜ ብዛት የደረሰብህን ግፍ ችላ ልትል፤ ከቶውንም ግፈኛውንም ይቅር ልትል እንደምትችል ለማመላከት ይመስለኛል።

“ስልጣን ያባልጋል፤ፍፁም ስልጣን ደግሞ ፍፁም ያባልጋል” የሚለው አባባል ደጋግሞ በታሪክ እንዳሳየን አምባገነኖችና ጀሌዎቻቸው ግፍ ሲውሉ ጨካኝና ነውረኛ ድርጊታቸውንም በመርዘኛና ፀያፍ ባህሪም ጭምር እያጀቡ ነው።ይህ ታዲያ ከሚፈጽሙት ግፍ በላይ ማንነታቸውን አጎልቶ በማሳየት የማይቀረው የተጠያቂነት ዘመን ሲመጣ ከሰሩት ግፍ ይልቅ በሕግም ሆነ በታሪክ መድረክ ይበልጥ የሚወሳ ይሆናል።በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነመንግስት የትግራይና የወሎ ሕዝብ በረሃብ ቸነፈር የተነሳ ከቀዬው እየተሰደደ ወደአዲስ አበባ እየጎረፈ መሆኑ ሲነገራቸው “ወሎ መሰደድ ልማዱ ነው”ብለው የተሳለቁ ባለስልጣን በለውጡ ጊዜ ያቺ ንግግር ብቻ ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለቻቸው ይነገራል።

የሊቢያው ኮሎኔል ጋዳፊ ሕዝቡን ከበረሮ ጋር አመሳስሎ ባናናቀ ማግስት የደረሰበትን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሁላችንም የምናስታውስ ይመስለኛል።በወያኔ ዘመን መዝግበን ከያዝናቸው የግፍ አነጋገሮች በጥቂቱ፤

ሟቹ ባለ”ራዕይ”በ1984-85 ገደማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ደም በጥይት ካፈሰሰ በኋላ ለምን የአስለቃሽ ጢስ እንዳልተጠቀመ ሲጠየቅ “ከተረከብነው የደርግ ኢሠፓ መንግስት ግምጃ ቤት እንደዚያ አይነት መሳሪያ ባለማግኘታችን ነው”ሲል ሥርዓተ አገዛዙን በሕዝብ በመሳለቅ ጀምሮ አድልዎ የማያውቀው መልዓከ ሞት እስቲቀላው ድረስ በዚያው ጥጋብ እንደዘለቀበት የሚዘነጋ አይደለም።

እንደንጉሱ አጎንብሱ ነውና ከጌቶቻቸው በተማሩት መሰረት የወያኔ ሎሌዎችም በየደረጃው ከግፋቸው ጋር እንዳቅሚቲ ጥጋባቸውን አካፍለውናል።አሁን የቅርቡ ከኬንያ አፍነው ወስደው ለረጅም ጊዜ ሰቆቃ ሲፈጽሙበት ስለነበረውና በቃሊቲ ማጎሪያ ካምፕ እንዳለ ሞተ ስለተባለው ተስፋሁን ጨመዳ ሲጠየቁ ያሳዩት ባህሪ ነው።አዲስ ቮይስ ድረ ገፅ ላይ እንዳነበብኩት ከሆነ ኢሳት የተባለው ቴሌቪዥን ስለጉዳዩ የቃሊቲ አስተዳዳሪዎችን ለማነጋገር ስልክ ሲደውል የማጎሪያ ካምፑ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ግዛቸው መንግስቱ የተባለ ሰው በተስፋሁን ጨመዳ ሞት እየተሳለቀ ገልፍጧል።ለእንደዚህ ያሉ ግፋቸውን ከግምኛ ባህሪ ጋር ለሚያጅቡ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ “እስከቀንህ”በሚለው ግጥሙ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ እንደሚከተለው ይላቸዋል።

“የደረሰው ቀንህ፣ዱብ እስከሚልብህ፣
ሰማይ እንቅብ ሆኖ፣ዱብ እስኪደፋብህ፣
ምድሩ አዘቅት ሆኖ፣እስኪሰለጥቅህ፣
ወይ ወህኒ እስኪያተላህ፣እስኪያበሰብስህ፣
ደንስ እስከቀንህ!!!”

Email: kiflukam@yahoo.com
Twitter: @Hussainkiflu

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 27, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.