በፋሲካ ገበያ በሬ 12 ሺህ፣ ዶሮ 100 ብር እየተሸጡ ነው

18 April 2009 (ብርሃኑ ፈቃደበዘንድሮ የትንሣኤ (ፋሲካ) በዓል የበሬ፣ የበግ፣ የፍየል እና የዶሮ ዋጋ ማሻቀቡን እስካለፈው ሐሙስ ዕለት ድረስ ከአዲስ አበባ ገበያዎች ያሰባሰብነው የዋጋ ዳሰሳ አመለከተ፡፡

ከመርካቶ እና ከሾላ ገበያ ያሰባሰብነው መረጃ እንደሚያሳየው የፍየል ሙክት እስከ ብር 1 ሺ 600 እየተሸጠ ሲሆን በግ ትልቁ (ሙክት) 900 ብር፣ መካከለኛ በግ ከ600 እስከ 700 ብር፣ ዶሮ ከ60 እስከ 100 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እንዲሁም በኪሎ 4 ብር ከ50 ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት ሰሞኑን በኪሎ 10 ብር፣ ቅቤ የሸኖ አንደኛ ደረጃ ከ90 እስከ 100 ብር በኪሎ ተሸጧል፡፡

ኮተቤ በር በሚገኘው በካራ እናበሸጎሌ አዲሱ ገበያ ሠንጋ በሬ ከ10 ሺህ እስከ 12 ሺህ፣ መካከለኛ ከ7 ሺህ እስከ 8 ሺህ፣ ዝቅተኛ ከ3 ሺ 500 እስከ 4 ሺህ፣ ወይፈኖች ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺ 500 ብር በመሸጥ ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የበዓል ገበያ ቅኝት በከፊል

ከፋሲካ በዓል ቀደም ብለው በነበሩ ቀናት ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በጥቂቱ ለማሳያ ይሆን ዘንድ በአንዳንድ ቦታዎች ቅኝት የገበያ አድርገናል፡፡

ሾላ ገበያ ጎጃም በረንዳ መርካቶ መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባዊዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩ በዓላት ይልቅ አብዛኞቹ ዕቃዎች ዋጋቸው ጨምሯል፡፡

በሾላ ገበያ የበግና የፍየል ግብይት በስፋት ይካሄዳል፡፡ መካከለኛ ደረጃ ያላቸው የፍየል ጠቦቶች ከ700 እስከ 900 ብር ይጠየቅባቸዋል፡፡ የሰባ የፍየል ሙክት ከ1 ሺህ 600 መቶ ብር በላይ ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡ ስለሁኔታው አንዳንድ ነጋዴዎችንና በአካባቢው የሚገኙ አሻሻጮች (ደላሎችን) ጠይቀን እንደነገሩን፣ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እየናረ የመጣው የፍየል ዋጋ መንስኤው ልኳንዳና ምግብ ቤቶች እንደሆኑ ነው፡፡

በእነዚህ ንግድ ቤቶች እየተዘወተረ የመጣው የፍየል ሥጋ ሽያጭ የሙክቶችን ተፈላጊነትና እንዲሁም ዋጋ በአዘቦት ቀናትም እንዲጨምር ማድረጉን ይገልፃሉ፡፡

ካለፈው የገና በዓል ጋር ሲነፃፀር የበግ ዋጋም ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶታል፡፡ በ250 እና በ300 ብር ገደማ ሲሸጥ የነበረው የመካከለኛ ደረጃ በግ በፋሲካ በዓል ሰሞን ከ350 እስከ 500 ብር ደርሷል፡፡ ደህና የወለጋ ቅጥቅጥ ሙክት 900 ብርና ከዚያም በላይ እየተሸጠ ነው፡፡

የዋጋው ልዩነት በየቀኑ የሚስተዋል ሲሆን እያቀረብን ያለነው ደግሞ ለሕትመት እስከ ገባንበት እስካለፈው ሐሙስ የነበውን የገበያ ሁኔታ ነው፡፡

ሽንኩርት አሁንም ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ በኪሎ 4 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው የባሮ ሽንኩርት በሰሞኑ ገበያ ከስድስት እስከ ሰባት ብር ከፍ ብሏል፡፡ የአበሻ ሽንኩርት የሚባለው በኪሎ 10 ብር ሲያወጣ ነጭ ሽንኩርትም በመርካቶ ገበያ በተመሳሳይ ዋጋ ተሸጧል፡፡ ዶሮ አነስተኛው ከ 50 እስከ 60 ብር ደህና ብልት ወይም መልክ ያለው እስከ 100 ብር አውጥቷል፡፡ እንቁላል በ1 ብር ከ25 ሳንቲም ሲሸጥ ሴት ዶሮ ከ 50 ብር በላይ ተሸጧል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት ካለፈው የገና በዓልም ሆነ ከሰሞኑ የገበያ ሁኔታ አንፃር የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆኑ ብዙም ለውጥ ያልታየባቸው አንዳንድ እቃዎችም አሉ፡፡

አገር ውስጥ የሚመረተው የኑግ ዘይት በችርቻሮ ለሚገዙ በሊትር 20 ብር ሲሸጥ በበርሜል እስከ 18 ብር ለነጋዴዎች እየቀረበ ነው፡፡ የውጭው ዘይት እንደ ዓይነቱ መጠነኛ ልዩነት ቢኖረውም 20 ሊትር የሚይዘው የሃያት ዘይት 230 ብር ባለ ሦስት ሊትሩ ደግሞ እስከ 51 ብር ተሸጧል፡፡

አንደኛ ደረጃ የዳቦ ዱቄት ኪሎ 8 ብር ሲሆን በኩንታል ከዚህም በታች እየተሸጠ ነው፡፡ በመሳለሚያ የእህል በረንዳ ባደረግነው ቅኝት መንግስት ግዢ ከውጭ የሚያስገባው ስንዴ በነጋዴው እጅ በኩንታል 410 ብር ገደማ ሲሸጥ ነጭ ስንዴ 500 እና 550 ድረስ ተሸጧል፡፡

የጤፍ ዋጋ ካለፈው በዓል ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰሞኑ ገበያም ጋር ሲነፃፀር የ 20 እና የ30 ብር ጭማሪ የታየበት መሆኑን አቶ አሻግሬ የተባሉ የእህል በረንዳ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

“ጤፍ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ዋጋው ጨመረም ቀነሰም ሰው ይገዛል” ያሉት ሌላዋ የእህል ነጋዴ ናቸው፡፡ በመሳለሚያ እህል በረንዳ የኦሎንኮሚ ማኛ ጤፍ በኪሎ ከ10 ብር እስከ 11 ብር በኩንታል ከ1000 እስከ 1100 ብር ተሸጧል፡፡ የአዳኣ ማኛ ጤፍ በኪሎ 11 ብር ከ50 ሳንቲም በኩንታል 1150 ብር አውጥቷል፡፡

ሆኖም ካለፈው አመትም ሆነ ከዘንድሮው የገና በዓል ጋር ሲነፃፀር በሌሎች የጤፍ አይነቶች ላይ መጠነኛ ለውጥ (ቅናሽ) እንደሚታይም ተገልፆልናል፡፡

ሰርገኛ ጤፍ ከ 750 እስከ 800 ብር፣ በተለምዶ አቦልሴ የሚባለው ጤፍ 740፣ ብር ጥቁር ጤፍ 700 ብር ገደማ ሲሸጥ ነጭ ጤፍ 900 ብር አውጥቷል፡፡

የሰሞኑ የበርበሬ ዋጋ መጠነኛ መረጋጋት የታየበት እንደሆነ ገዥና ሻጭ ይስማማሉ፡፡ ከ 300 ብር ጀምሮ እንደ ገበያው ሁኔታ በፈረሱላ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡

በዓል በመጣ ቁጥር ሸማቹ ለበዓል ፍጆታ የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ሲሆን ነጋዴዎችም ከወትሮው በተለየ ትርፍ ለማግኘት ዋጋ የሚሰቅሉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ለበዓል ሲባል ከሚወጡ አላስፈላጊ ወጪዎች ራስን መቆጠብ የመጀመሪያው አማራጭ እንደሆነ በመጠቆም ለውድ አንባቢያን መልካም በዓል እንዲሆን እንመኛለን፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 18, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.