በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሟች ተማሪ ጉዳይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ማብራሪያ ሰጡ

(በ ዘሪሁን ሙሉጌታ) ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በግምት ሦስት ሰዓት ላይ ለጊዜው ባልታወቁ ሰዎች በጩቤ ተወግቶ ስለተገደለው ሟች ተማሪ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ማብራሪያ ሰጡ።

ፕሬዝደንቱ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ስለ ሁኔታው በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት በዕለቱ ጥቂት ተማሪዎች “ፓርቲ” ብለው ለመዝናናት ወደ ከተማ መውጣታቸውን፣ ተማሪዎቹም መጠኑ በርከት ያለ የአልኮል መጠጥ መውሰዳቸውንና ወደ ዩኒቨርሲቲው በመመለስ ላይ ሳሉ አለመግባባት መፈጠሩን አስረድተዋል።

አለመግባባቱንም ተከትሎ በተፈጠረ መረበሽና ጩኸት የአካባቢው ነዋሪዎች በቦታው ደርሰው ተማሪዎችን ወደዩኒቨርሲቲው በማምጣት የዩኒቨርሲቲውም ጥበቃዎች መታወቂያቸውን በማየት ካስገቧቸው በኋላ ጠዋት ሌሎች ተማሪዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ማታ ጩኸት በነበረበት ቦታ ፖሊስ አስከሬን ሲያነሳ ተመልክተው መረበሻቸውን ገልፀዋል።

የተማሪው አስከሬን በፖሊስ ከተነሳ በኋላ በተደረገለት ምርመራ በግራ ጎኑ በኩል በጩቤ እንደተወጋና ሳንባው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ለህልፈት እንደበቃ መረጋገጡን ገልፀዋል።

ሟቹ ተማሪ የሦስተኛ ዓመት የማርኬቲንግ ተማሪ ሲሆን ስሙ አንተነህ አስፋው የሚባል መሆኑን ፕሮዚደንቱ የጠቀሱ ሲሆን፤ አደጋው በደረሰበት ወቅት የነበሩ ተማሪዎች ስለሁኔታው ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠታቸውን የአልኮል መጠጥ እየወሰዱ በነበረበትም ወቅት በመካከላቸው ተማሪ ያልሆነ ሰው ጋር ጠብ እንደተፈጠረም ለፖሊስ ቃላቸውን እንደሰጡም ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲውም አደጋው መድረሱን ካረጋገጠ በኋላ አስከሬኑ ወደ ወላጆቹ እንዲሄድ ማድረጉን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መንገሻ፣ ነገር ግን በመሀሉ አደጋው በደረሰበት ወቅት ጥይት ተተኩሶ ነበር የሚል መረጃ በመምጣቱ የሟቹ አስከሬን መመርመር አለበት በመባሉ እንደገና በአዲስ አበባ ምኒልክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ መደረጉን ገልፀዋል። ነገር ግን አስከሬኑ ከተሸኘ በኋላ ቁጥራቸው አራት መቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በሟቹ ተማሪ አሟሟት ላይ ቅሬታቸውን ለመግለፅ በማሰብ ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ ዩኒቨርሲቲው መከልከሉን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ የተቃውሞ ጩኸት እያሰሙ ከግቢው እንዳይወጡ የከለከለው ለተማሪዎቹ ጥሩ ባለመሆኑና ሌላም አካል ሊቀላቀላቸው ይችላል በሚልና ለተማሪዎቹ ደህንነት ጥሩ ስለማይሆን እንደምንም ተብሎ ለማስቆም ጥረት መደረጉን ገልፀዋል። ተማሪዎቹ ማንኛውንም ጥያቄ የማቅረብ መብት ቢኖራቸውም ከዩኒቨርስቲው መውጣታቸው ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ ምክር ሊሰጣቸው መሞከሩን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ደህንነት በመጠበቅና የዲስፒሊን ቁጥጥር በማድረግ ረገድ ያሉበትን ጉደለቶች በተመለከተም ፕሬዚደንቱ ተጠይቀው ዩኒቨርስቲው በተማሪዎቹ የተሟላ ተሳትፎ የተማሪዎች የዲስፕሊን ቁጥጥር መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉን ገልፀዋል። ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በፈለጉበት ጊዜና ሰዓት መውጣትና መግባታቸው ቀርቶ በዚህ ዓመት ማንኛውም ተማሪ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ እንዳይገባና ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት በፊት እንዳይወጣ የሚል መመሪያ ተግባራዊ ሆኗል ብለዋል።

የተማሪዎቹ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ የመጠቀም ሁኔታ በተመለከተም የዩኒቨርሲቲውን የዲስፕሊን መመሪያ መጣስ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን በተለምዶ “ፓርቲ” በሚል ነገር ተማሪዎች ከመጠን ያለፈ የአልኮል መጠጥ በመውሰድ ዩኒቨርሲቲውም ላይ ችግር በመፍጠሩ፣ ተደጋጋሚ ምክር መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ከተማሪው አሟሟት ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ የታሰሩ ተማሪዎች መኖራቸውንም በተመለከተ ለፕሮፌሰር መንገሻ ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ በወቅቱ የታሰሩ ተማሪዎች መኖራቸውን አረጋግጠው፣ ነገር ግን ማረሚያ ቤት መቆየት የለባቸውም በሚል እምነት የተወሰኑ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ተናግረዋል። በተፈጠረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተወሰነ የዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱ የማጣራት ሥራ እንደሚደረግ አያይዘው ገለፀዋል።

የሟቹ ተማሪ አሟሟት እስካሁንም አለመታወቁን የገለፁት ፕሬዚደንቱ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረ ስለሆነ ገዳዩ ማን እንደሆነ በሂደት ተጣርቶ የሚረጋገጥ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከተማሪው ህይወት በኋላ በስልክ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች በተማሪው ድንገተኛ መሞት መደናገጣቸውን ገልፀዋል። ከዚህ በፊት በጩቤ መውጋት ሙከራ በተማሪዎች ላይ ሲፈፀም እንደነበር፣ በሴት ተማሪዎች ላይ የመደፈር ወንጀል እያጋጠመ መሆኑን ተናግረዋል። ተማሪዎቹም የልጁ አሟሟት ጥያቄ ሲያነሱና የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ከግቢው እንዳይወጡ ሲደረግ ረብሻ መነሳቱን አረጋግጠዋል።

በወቅቱ ተማሪዎቹ ደህንነታችን ይጠበቅ፣ የተማሪው ገዳዮች ታውቀው ለፍርድ ይቅረቡ በሚል የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸውን ገልፀዋል። በተቃውሞ ወቅት ከሁለት መቶ በላይ ተማሪዎች መታሰራቸውን አስረድተዋል። በረብሻው ተደናግጠው ከግቢ የወጡ ተማሪዎችም መታወቂያቸው እየተያዘ መመለሳቸውንና በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ መስፈኑን ተናግረዋል። ሟቹ ተማሪ የሐዋሳ ልጅ መሆኑን የጠቀሱት ተማሪዎቹ አስከሬኑም ወደዚያው መላኩን ከተማሪዎቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

Source: ሰንደቅ ጋዜጣ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 27, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.