በየመን የኤምባሲ ተወካዮች ተዋርደው ከቤተክርስቲያን ወጡ… [ ሀበሻ በየመን ክፍል 10]

(በግሩም ተ/ሀይማኖት)

        የምጀምረው በሁለት አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ የመን ውስጥ ከሚታተሙት የግል ጋዜጣዎች አንዱ የሆነው አል-ሻራዕ የተባለው በ21/1 2012 ዕትሙ “ሶስት ኢትዮጵያዊያን ተገደሉ”  በሚል የያዘውን ዘገባ ተርጉሜ እንደሚከተለው አስነብባለሁ፡፡

   በዚህ ሰሞን በባህር ወደ የመን ከገቡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መካከል ሰላሳ የሚሆኑትን ወደ ሳዑዲ ለመውሰድ የጫናቸው መኪና ላይ በተከፈተ ተኩስ ሶስቱ ሲሞቱ የመናዊ ሾፌሩን ጨምሮ የቆሰሉም መኖሩ ተረጋገጠ፡፡ ማንነታቸውን የሚገልፅ ምንም አይነት መረጃ ካልተገኘላቸው ሟቾች ጋር ከነበሩት መካከል አምስት የሚሆኑትን ደግሞ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡ የሟቾቹ ኢትዮጵያዊነትም የተረጋገጠው አብረዋቸው ካሉት ተጓዦች ነው፡፡ ችግሩ የተከሰተው ሰላሳ ኢትዮጵያዊ እና ሁለት የመናዊ ሴቶችን ጭኖ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሲያመራ በነበረ መኪና ላይ ትንሽ ፀብ ተነሳ፡፡ በሀበሻዎቹ እና በየመናዊዋ መካከል ነበር አለመግባባቱ፡፡ መኪናውን አስቁማ ከወረደች በኋላ በያዘችው መሳሪያ ተኩስ ከፍታ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ሲሞቱ ከነሾፌሩ በርካታ ሰዎች ተጎዱ፡፡ አምስት ኢትዮጵያዊያን ተይዘዋል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ ይህ ድርጊት የተፈፀመበት ሩባዕያ የምትባል ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህች ቦታ ደግሞ ስጠይቅ እንደተነገረኝ ሞካ ከምትባለው ጠረፍ የወደብ ከተማ በቅርብ ርቀት ያለች ስትሆን ወደ ሳዑዲ ለመሄድ የሚጠቀሙባት ነች ብለውኛል፡፡

    ይሄው አል-ሻራዕ የተባለው ጋዜጣ በአሁኑ ቅዳሜ 4/2/2012 ዕትሙ ደግሞ ‹‹የክሪስመርስን በዓል ሲያከብሩ የነበሩ 35 ኢትዮጵያዊያን ሳዑዲ ውስጥ ተያዙ ሀያ ዘጠኙ ሴቶች ናቸው›› በሚል ርዕስ የሁማን ራይትን መግለጫ መሰረት አድርጎ ሌላ ዘገባ አቅርቧል፡፡

      እንደጋዜጣው ዘገባ ከሆነ የክሪስመርስ ዋዜማ ዕለት 35 ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ውስጥ በዓሉን ሲያከብሩ ያሉበት ቤት ተሰብሮ ተያዙ፡፡ 29 ሴቶች እና 6 ወንዶች ናቸው፡፡ ነገሩ የሸሪዓውን ህግ በመጣስ ተብሎ በሌላ ተተርጉሞባቸዋል፡፡ ሁማን ራይት ባወጣው መግለጫ መሰረት ሴቶቹ ኢሰብዓዊ ባልሆነ መልኩ ሲፈተሹ ወንዶቹ ሙስሊም ባለመሆናቸው ተደብድበዋል ብሏል ጋዜጣው፡፡

Habeshas in Yemen

    ከጋዜጣው ዘገባ ውጭ በዚህ መረጃ መሰረት ስልክ ወደ ጅዳ መትቼ ለማጣራት ሞክርኩኝ፡፡ እውነታው እውነትነቱን ብቻ ሳይሆን ሴቶቹ ላይ የተደረገው ምርመራ በአንድ ጓንት አስራ አምስት ሴቶችን ጣት ብልት ውስጥ በመክተት እንደሆነ ፍተሻ የተደረገባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በወንዶቹ ላይ የተደረገው ድብደባ በጣም ዘግናኝ እና አሳፋሪ ነገርም እንደሆነ፣ የተጎዱም እንዳሉ በሰልክ ያናገርኳቸው መረጃዎቼ አረጋግጠውልኛል፡፡ በሰዓቱ ሸሪዓውን የሚጋፋ ምንም ነገር እንዳልተሰራ ሊጠጡ ወይም ሊዘሙቱ ሳይሆን የተሰባሰቡት ቤተክርስቲያን ስለሌለ የገና በዓልን ዋዜማ በፀሎት ሊያከብሩ ነበር፡፡ በር ስብረው ገብተው በቁጥጥር ስር አዋሏቸው፡፡ቤቱ ሲፈተሸ ምንም የተገኘ መጠጥም ሆነ ሌላ ነገር የሌለ በመሆኑ ለፀሎት እንደሆነ የተሰባሰቡት ቢናገሩም ሰሚ አላገኙም ባይ ናቸው የደወልኩላቸው ሰዎች፡፡ ለወዳጄ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክም ደውዬ ያለውን ሁኔታ ለማጣራት ሞክሬ ነበር፡፡ በጓንት ብልታቸው ውስጥ ስለተባለው ነገር እዛም በሰፊው እንደሚወራ እና ለማጣራት ሞክሮ መረጃ እንዳላገኘ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አይሰሩም ማለት እንደማይቻል ነው ያወጋኝ፡፡

      ወደ ጋዜጣው ዘገባ ስመለስ ሳዑዲ አረቢያ በ2006ዓ.ም ባወጣችው ህግ ውስጥ ቤተክርስቲያን መገንባት ባይቻልም ቤት ውስጥ በሚደረግ ፀሎት ላይ ጣልቃ እንደማትገባ እና እንደምትፈቀድ አፅድቃለች፡፡ እነዚህም የኦርቶዶክስ አማኞች ሲሆኑ በራሳቸው መሰብሰቢያ ቦታ የበዓሉ ዋዜማ ፀሎት እያደረጉ ነው የተያዙት፡፡ ሁማን ራይት አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶችን ካሉበት እስር ቤት በስልክ አናግሯል፡፡ ታሳሪዎቹ ‹‹የሳዑዲ መንግስት የሌለ ክስ ነው ያቀረበብን፡፡ የጋብቻ ሁኔታ ሳይኖራቸው ወንድ እና ሴት በመደባለቅ..የሚል ነው›› ብለዋል፡፡ ሁማን ራይት ደግሞ ‹‹..የሳዑዲ ህግ ወንድ እና ሴት አንድ ላይ ሲገኙ ወንጀል ነው አይልም›› ብሏል፡፡

     ቤት ሰብረው በመግባት በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው የሀይማኖት ስርዓት ጠባቂ ሼኮች እንደሚሉት ደግሞ፡- የሳዑዲ መንግስት ወንድ እና ሴት መገናኘት ይችላሉ የሚለው ሰው ባወቀበት ሁኔታ ሳይሆን በራሳቸው ቦታ ብቻ እንጂ እንዲህ ተሰባስቦ አይደለም፡፡ ያም ቢሆን በሽርሙጥና እና በሌላ ብልግና ካልሆነ ነው የሚፈቅደው፡፡ የሳዑዲ ህግ ማንኛውንም ከእስልምና ውጭ ያለ እምነት በቤት ውስጥ ብቻ ካልሆነ ከልክሏል ብለዋል፡፡

    ጋዜጣው ፅሁፉን ሲደመድም ኢትዮጵያ ማለት መጀመሪያ ክርስትናን የያዘች ሀገር ስትሆን አሁንም ቋሚ ሀይማኖቷ ነው ብሏል፡፡

      እነዚህ ተከሳሾች ከገና ዋዜማ ጀምሮ በእስር እየተሰቃዩ ሲሆን አሁንም ፍርድ እየጠበቁ ስለሆነ እያንዳንዳችን ድምፃችንን ልናሰማ ግድ ይለናል፡፡ ቢቻል እንዲፈቱ የሚጠይቅ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ቢሞከር እላለሁ፡፡እናንተስ? በኦርቶዶክስ ጉዳይ ከጀመርኩ..አይቀር የመን ላይ የተከሰተ ክስተት ላውጋዎ….

   እዚህ የመን ውስጥ ያለ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄርን ቃል ለመስማት፣ ፀሎት ለማድረስ ስንሄድ ኮሚኒቲ ምርጫ አለ ምረጡ፣ የትግራይ ልማት ስብሰባ ስላለ..፣ ኤምባሲ ስብሰባ አለ..ቅብርጥሴ..ቅብርጥሴ የሚሉት ነገር ሁሌም ያናድደኛል፡፡ ባለፈው አርብ ጥር 25 ቀን ዘውትር እንደምንሰበሰበው ለፀሎት ተሰብስበን ሳለ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮች <<..እየንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአባይ ግድብ የሚውል ቦንድ ግድ መግዛት አለበት..›› አሉ፡፡ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በግዴታ አይነት ስለነበር አነጋገራቸው ሁሉም ተቃወማቸው፡፡ ህዝቡ አሳፍሯቸው ከቤተክርስቲያን ተባረሩ፡፡ ትላንት አናውቃችሁም ያሉትን ህዝብ ሊለምኑ መምጣታቸው አሳፋሪ መሆኑን ቢነገራቸውም በተቃውሞው ሳያፍሩ ‹‹..ካልሆነ ደግሞ ሁሉም አንድ አንድ ሺህ የየመን ሪያል እንዲያዋጣ.›› ጠየቁ፡፡ ባለማፈራቸው እኛ አፈርን፡፡

         ህዝቡ ግን እንደ ሌላ ጊዜው በዝምታ አላለፋቸውም፡፡ ከህዝቡ መካከል ‹‹..የታሰረ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?…የታሰረ ዜጋ አስፈትታችኋል?… ዜጋ ሞቶ ሬሳው የትም ሲቀር፣ ሬሳ ውሰዱ ስትባሉ አናውቅም ስትሉ አልከረማችሁም?… ዛሬ እንዴት አወቃችሁን?.. ሞትን፣ ተጎዳን ድረሱልን ስትባሉ ምነው ዝም ትሉ አልነበር?… ችግር ሲደርስ ዜጋውን እንደዜጋ አይታችሁ የተባበራችሁት የት እና መቼ ነው?.. መቼስ እንደ ዜጋ አይታችሁን ነው ዛሬ ቦንድ ብላችሁ የምትመጡት?…ስንቶች ሲደበደቡ ግፍ ሲፈፀምባቸው ተበደልን ሲሉ ለገረድ አልመጣንም ስትሉ ከርማችሁ ዛሬ ተገርደን ያመጣነውን ለመሰብሰብ ስትመጡ አታፈሩም….እዚህ ሀገር ካለው እልቂት እና መከራ ተርፈን ስላያችሁን ነው? ስራ የለንም ከየት እናመጣለን?.. ያኔ ያላስታወሳችሁን በጦርነት ተፈናቅለን ዞር ብላችሁ ያላያችሁን ዛሬ ደግሞ ቦንድ ትላላችሁ?..እዛ ቤተሰባችንን በቦንድ አራቁታችሁ ለምን ከሞት ተረፋችሁ ብላችሁ ዛሬ ደግሞ እኛን?..›› የመሳሰሉ ብዙ ብዙ መራር ቃላት ዘነበባቸው እና አፍረው ሹልክ ብለው ወጡ፡፡የኤምባሲው ተወካዬች ሌላ ቀን ለፀሎት ቤተክርስቲያን አልታዩም ለልመና ሲሆን ግን..የለማኝ መንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ስለሆኑ መቼ ያፍራሉ? አያፍሩም፡፡ ለመሆኑ በቃ ቤተክርስቲያናችን ፖለቲካ መስበኪያ ሆነ ማለት ነው?      

   ከጋዜጣው እና ከየመኑ ዘገባ ስወጣ ባለፈው በገባሁት ቃል መሰረት ምናቦትን ያበድሩኝ….የዛሬ ሀያ ቀን አካባቢ ሄጄ ወዳየሁት አል-ቀረስ የተባለው ዜጎቻችን ወደ ታጎሩበት ካምፕ እናምራ…እግረ መንገዴን ያየሁትን እያስቃኘዎት ስለምሄድ ቀልቦትን ሰብሰብ አድርገው ይከተሉኝ፡፡ ለትራንስፖርቱ አያስቡ…

  በመጀመሪያ የየመን ዋና ከተማ መሆኑን ከሰነዓ ተቀብላ ወደ ነበረችው ትዕዝ ነው የተጓዝኩት፡፡ ወደ አል-ቀረስ ለመጓዝ ግድ ሆኖ ሳይሆን የመን ከመጣሁ ካላየኋቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ማየትንም እንደ አማራጭ ተጠቅሜ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የመን ውስጥ ማንኛውም ትላልቅ የክፍለ ሀገር አውቶቡሶች የውጭ ዜጋ ስለማያስተናግዱ፣ ለህይወት ሀላፊነት ስለማይወስዱ በሚኒባሶች ነው መጓዝ ያለብኝ ስለዚህ ትንሽ ቢጨምር ነው ትዕዝን ልያት የሚለው ሀሳቤ አመዘነ እና ሚኒባሱ ላይ አንጠለጠለኝ፡፡

እንደ እኛ አቆጣጠር ከ1941-1955 ለየመን ዋና ከተማ ሆና ታገለግል ወደ ነበረችው ትዕዝ ነው የተጓዝኩት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ለየመን ሶስተኛ ከተማ ናት፡፡ ሰነዓ፣ አደን ቀጥሎ ትዕዝ..የህዝቧ ብዛት ከሁለት ሚሊዮን እንደሚበልጥ ይነገርላታል፡፡ ከሰነዓ ጠዋት ሶስት ሰዓት አካባቢ ባብል የመን/old Sana `a/ ከሚባለው በንጉስ አብርሃ ከተቆረቆረው አካባቢ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ከሰነዓ ከተማ ስንወጣ ጀምሮ በተራራና ተራራ መካከል የሚወርደው መንገድ እንደ ጅረት ቁልቁል ወደታች እያምዘገዘገን ነው፡፡ ጠመዝማዛነቱ እንዳለ ሆኖ አልፎ አልፎም ቢሆን ዳገት ቢጤ እያጋጠመን ስለሆነ አንድ ዜማ ትዝ አለኝ፡፡‹‹…ጠመዝማዛው መንገድ ኮረብታ..ሽቅብ ቁልቁለት..በረሃ አቋራጭ ጋላቢ ዳገት የሩቁን ከቅርብ አቀራራቢ….›› የሚለውን ለሾፌሮች የተዜመ የሀገሬን ዜማ እና ጋራ ሸንተረሩን አስታወሰኝ፡፡ ሙቀቱ በጠዋቱ በፍቅር እንደምትማርክ ልጃገረድ ልብስ ማስወለቅ ጀምሯል፡፡ ከመንገዱ ዳርና ዳር የሚታዩት ተራራዎች ያፈሩትን የጫት ምርት እዩት ብለው ለአይን ማረፊያ አድርገውታል፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ሌላ አይነት ምርት አይታይም ሁሉም ጫት….ጫት..በቃ! ትልቁ ተፈላጊ እና አዋጭ ምርት ነው፡፡ ማበር፣ደማር..የሚባሉ መካከለኛ ከተማዎችን ከብዙ ጥቃቀቅን ከተሞች ጋር አቋረጥን፡፡ የሁሉም ፅዳት ከሰነዓ የባሰ ደስ የማይል ነው፡፡

   የደሴን መንገድ ያስታወሰኝ ጠመዝማዛ ጎዳና የገጠመኝ ኤብ ወደምትባለው ከተማ ስንቀርብ ነው፡፡ ኤብ ካየኋቸው የየመን ከተማዎች ሁሉ ፀዳ ያለች እና ፕላን ቢጤ የተቸረች ትመስላለች፡፡ ሶስት ፈርጣማ ተራራዎች መሀል ግርማ ሞገስ ተላብሳ ቁጭ ብላለች፡፡ ትመቻለች፡፡ ወደ ትዕዝ በቀረብን ቁጥር አርባ ምንጭ አካባቢ ያለሁ..  እስኪመስለኝ ድረስ እርከን በእርከን ሆኖ ኮንሶን አስታወሰኝ፡፡ አረንጓዴነት ተላብሷል፡፡ ይህ ሁሉ አረንጓዴ ምርት ግን ደረቃማ እና ድንጋያማ መሬት ላይ ነው ቢባል ማን ያምናል? 

     ትዕዝ መግባታችንን ከጎኔ ያለው ወንበር ላይ የሚኒባስ ጊዜያዊ ጎረቤቴ ሆነው የተሰየሙት አዛውንት አበሰሩኝ፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው የቆሙ ሰዎች ሳይሆን ፋብሪካዎቹ ላይ አይኔን አንከራተትኩ፡፡ መግቢያው ላይ አደራደራቸው አቀባበል የሚያደርጉ ይመስላሉ፡፡ መንገዱ ለጥ ብሎ በቀኝ እና በግራ በተራራ ታጅቦ የተፈጥሮን ውበት ላደንቅ ግድ አለኝ፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዝን በኋላ ደረቱን የሰጠ ደማቅ ከተማ ውስጥ ራሴን አገኘሁት፡፡ በዚህ ቢበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ተራራ ላይ ተጎብሮ ሜዳውን አቆልቁሎ የሚያየው የከተማው እንብርት መሆኑን ሳውቅ ወደዛ ማምራት አማረኝ፡፡ ታዲያ ማን አምሮት ይሞታል ተጓዝኩ እና አየሁት፡፡ የትዕዝ ከተማ አቀማመጧ ከባህር ወለል በላይ 3070 ነው፡፡ አብዛኛው መሬቷ በተራሮች እና እርዝመቱ እስከ ቀይ ባህር ወደጎን ደግሞ እስከ ባብ አል-ማንደብ የተባለው ቦታ ድረስ የተዘረጋ ስምጥ ሸለቆ አላት፡፡ ሁሉ የፍራፍሬ አይነት የሚበቅልባት ትዕዝ ብዙዎቹ ከተማዎቿ ጥንታዊ እና እድሜ ጠገብ ናቸው፡፡

    ትዕዝ ካሏት ጥንታዊ ከተማዎች መካከል ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ ‹‹ጃበል ሀባሺ›› /የሀበሻ ተራራ ማለት መሆኑን ልንገሮዎ../ የተባለው ከተማ ሲሆን በአንድ ወቅት ይህ ከተማ ጠፍቶ እንደ ነበርም ይገለፃል፡፡ ትዕዝ ከተማ እንደ እኛዋ ሐረር ከተማ በግንብ የታጠረች እና አምስት በሮች ያሏት ሲሆን በሮቹ አጠገብ አስራ ሶስት ሜትር ከፍታ ያለው የጠባቂዎች ዋልታ የተሰራለት ነው፡፡ 

   ታዲያ ጥንት ነው፡፡ አሁን ሁለቱ በሮች ብቻ ናቸው ታሪክ እየተናገሩ ቆመው የሚገኙት፡፡ ታክሲውን በሮቹ እንዳሉ በተነገረኝ አልካሂራህ አካባቢ ንዳው አልኩና እብስ… ‹‹አልባብ አልካቢር›› /ትልቁ በር/ እና ‹‹አልባብ ሞዉሳ››/የሞዉሳ በር/ በመባል የሚታወቁት ሁለቱ በሮች እና ትንሽ የግንቦቹ ቅሪቶችን አየሁ፡፡ ትዕዝ ላይ ለአራት ሰዓት አካባቢ ያደረኩትን ቆይታ አጠናቅቄ ወደ የመን ሁለተኛዋ ከተማ አደን አመራሁ፡፡ ስለአደን ከመነካካቴ በፊት ሌላ የትዕዝን ገጠመኝ ላውጋዎ… ባለፈው ሰኞ ጥር 21 ቀን ማታ ስልክ ተደወለልኝ፡፡ ከትዕዝ አይደለም፡፡ ከአዲስ አበባ ነው የተደወለው፡፡ ደዋይዋ ጅማ ከተማ ነዋሪ የሆነችው እህቴ ዓለም ተ/ሀይማት ናት፡፡ ሙራድ የሚባል ልጅ ከእነሱ ጋር ወደ የመን ሊመጣ መሆኑን እና ወንድሙ ሞቶ ለቅሶ እንደሆነ የሚመጣው ገልፃ ኤርፖርት ሄጄ እንድቀበለው ነገረችኝ፡፡ ምንም ታናሽ ብትሆን እህት ነች እና ቃሏ መከበር ስላለበት አደረኩት፡፡

     ወንድሙ የመናዊ እሱ ጅማዊ ሆነው አይደለም፡፡ ወይም በስደት የመጣ ሀባሻ ወንድሙ አይደለም የሞተው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው ሁለቱም፡፡ ከሙራድ ጋር እንደተገናኘን ለዘመዶቹ ደዋወልን፡፡ ቀሪያ /ገጠር/ ለለቅሶ ስለሄዱ እና ኔትዎርክ አስቸጋሪ ስለሆነ ከኢትዮጵያ ሲደውል እንቢ እዳለው ገልፀው እንግዳውን እነሱ ያሉበት እንዳደርስላቸው ጠየቁኝ፡፡ አሞት ስለነበር የእህቴም አደራ አለብኝ እና ያለማመንታት አደረኩት፡፡ በተፈጠረው አጋጣሚ ከሀያ ቀን በኋላ ትዕዝን ለሁለተኛ ጊዜ ላያት ተመለስኩ፡፡ አሁን ትዕዝንም አልፌ ስለሄድኩ ስለቦታው እንዳወራችሁ ነው ይህን ሁሉ ማለቴ፡፡ አቤት እኔ በቃ ያየሁትን መደበቅ አቃተኝ ማለት ነው?

   የያዝናት ቶዮታ ካምሪን ታክሲ ለጥ ያለ እና ጠመዝማዛ መንገድ ስለሆነ የሚጠብቃት ትኩረቴ መንገዱ ላይ ነው፡፡ የሚያወላዳ አይነት አይደለም፡፡ ከቀኑ አስር ሰዓት በኋላ ነው አየሩ አደብ ገዝቶ ማቃጠሉን ጋፕ አድርጎ ስለነበር ሳናርፍ ከትዕዛ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቱርባ ከተማ ደረስን፡፡ ኦሮምኛ ለምታውቁ ሰዎች ማሳሰቢያ ብጤ ትቼ ልለፍ ስያሜዋ ሌላ ትርጉም ስላለው አፈር ከተማ ብላችሁ እንዳትተረጉሙት፡፡ ከዚህች ከተማ በኋላ ሶስት ኪሎ ሜትር ተጉዘን ለቅሶው የሚለቀስበት ቦታ ተቀላቀለን፡፡ የመን ከመጣሁ ካየኋቸው ቦታዎች ሁሉ የፍቅር መንደር ነች፡፡ ከተወሰኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊ በስተቀር እኔ ብቻ ነኝ ሀበሻ፡፡ ልዩ ክብር..ልዩ ፍቅር ነው ያሳዩኝ፡፡ ገጠሩን በሙሉ ዞሬ አየሁ፡፡ ከሶስት ቀን ቆይታ በኋላ ሀሙስ እለት ስንመለስ ትዕዝን እንዳለፍኩኝ አይኔ ሁለት ጥቁርቁር ያሉ ልጆች ላይ አረፈ፡፡ ቆሻሻ ላስቲክ ይዘው በእግር ያዘግማሉ፡፡ ሳያቸው ገና ደሜ መሆናቸውን ደሜ ሲራወጥ አሳበቀልኝ፡፡

   እግር ወዲያው ፍሬን ረገጠ፡፡ ግን በምን እንግባባ የሚለው የማርታ አሻጋሪ ዘፈን ወዲያው ትዝ አለኝ፡፡ ኦሮሚኛ ካልሆነ አይሰሙም አይናገሩም፡፡ እኔ ደግሞ በመስማት ደረጃ እሞክራለሁ እንጂ እሰማለሁ የሚባል አይነት ችሎታ የለኝም፡፡ ‹‹ቢዬ ኬሰን ኤሳ ..›› አልኩ የማውቃትን ያህል ሰባብሬ፡፡ ሙራድ ሳቅ ቢልም አስተካክሎ ነገራቸው፡፡ እረስቼው እንጂ የጅማ ልጅ እያለ ያን ያህል ምን አሳሰበኝ..አስጨነቀኝ ነበር? ዘይገርም ሻሸመኔ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ከሙራድ ጋር አንድ ላይ ጅማ ናቸው፡፡ እነሱ ወደ ገጠር ስለሆኑ ነው፡፡ ርሃብ ከንፈራቸውን ኩበት አድርጎታል፡፡ እኔም ሆንኩ ሙራድ ጥለናቸው መሄድ አልቻልንም፡፡ ያለንን ብናካፍላቸውም አላረካንም፡፡ ወዴት እንደሚሄዱ ጠየቅናቸው፡፡ ረድዓ የምትባለው ቦታ እንደሚሄዱ ነገሩን፡፡ እዛ ለገበሬዎች ተቀጥረው ሰርተው ሳንቲም ሲያገኙ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ነው እቅዳቸው፡፡ እንዴት እዛ ስራ እንዳለ አወቃችሁ? የሙራድ ጥያቄ ነበር፡፡ የተነገራቸው መሆኑን እና እህታቸው ሳዑዲ እንዳለች ገልፀው ሚስኮል እንድናደርግላቸው ጠየቁን፡፡

      ውስጤ ቅጥል አለ መንገዱን ስቃዩን የምታውቅ እህት ሳዑዲ ቁጭ ብላ ነው የጠራቻቸው፡፡ ይሄኛውም ጥፋት ሀላፊነት የጎደለው መሆኑን ባውቅም ይህን ስቃይ ያየች ሴት ወንድሟን ለሞት ትጠራለች ብዬ አላስብም፡፡ 5 ሰው ሆነን ታክሲዋን ሞልተናት ነበር የምንመለሰው የት ላይ እንጫናቸው? ከኋላ እቃ መጫኛውን ከፍተን ውስጤ እያዘነ እንደ እቃ ጫንናቸው፡፡ ወደ 20 ኪሎ ሜትር ወሰድናቸው፡፡ ፍተሻ ያለበት ቦታ ስንደርስ አወረድናቸው እና አቆራርጠው እንዲሄዱ ነገርናቸው፡፡ ከዚህ በላይ ማድረግ አንችልም፡፡ ከዛ በኋላም እኛ ወደ ሰነዓ እነሱ ወደ ረድዓ የሚባል ቦታ አመራን፡፡ 

      በትዕዝ ዙሪያ የምለው ብዙ ቢኖርም ለዛሬ በቂ በሚለው እንለፈውና ወደ አደን ወዳደረኩት ጎዞ እናምራ፡፡ በየቦታው ድልድይ ማየቴን አስታውሳለሁ ግን ውሀ የሚባል የምራቅ ጠብታ ያህል አለመኖሩ ገርሞኛል፡፡ ታዲያ ይህን ግርምቴን ቋጥሬ ከምጓዝ አልኩ እና አንዱን ‹‹ወንዝ ነው እንዳይባል ድልድይ ብቻ ነው ውሀ የለውም ለምንድን ነው?›› አልኩት ‹‹..ኢንሽ አላህ አንድ ቀን ሲዘንብ ወንዝ ይሆናል›› ብሎ አሳቀኝ፡፡ አደን እስክደርስ የተለየ ነገር የለም፡፡ ያው ተራራ፣ የጫት እርሻ ነው፡፡ አደን ካየኋቸው ቦታዎች ግን በሳቲን የገረመኝ ነውና ስለ እሱ በሰፊው ማውጋት ፈለኩ፡፡ በመጀመሪያ የገጠመኝ ኢትዮጵያዊ የኔ ቢጤ ነበር፡፡

           ሰላም እንሰንብት  እንጂ እናወራለን ገና!!!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 8, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.