በውጭ ምንዛሪ እጥረት ኮካኮላ ፋብሪካ ማምረት አቆመ

በታምሩ ጽጌ (15 March 2009) ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ (ኮካ ኮላ) በአገር ውስጥ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከመጋቢት 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የሚያመርታቸውን የለስላሳ መጠጦች ማምረት ማቆሙን የኩባንያው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞችም የወር ደመወዛቸው እየተከፈላቸው የዓመት እረፍታቸውን እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ የ150ሺ ሰዎች መተዳደሪያ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ 

በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ተገኝተን ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ኃላፊዎች እንደገለፁት፣ ላለፉት ሦስትና አራት ሳምንታት ፋብሪካው ባጋጠመው የጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሳይችል ቀርቷል፡፡

ፋብሪካው እስከ መጋቢት 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ ማምረት ከሚችለው በታች 25 በመቶ ያህሉን ብቻ ሲያመርት ቆይቶ ያለውን ጥሬ እቃ ሙሉ በሙሉ በመጨረሱ ምርቱን ለማቆም መገደዱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቷ ውስጥ በተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ፋብሪካው ለሚያመርታቸው የለስላሳ መጠጦች ግብአት የሚውሉ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ ማምጣት ባለመቻላቸው ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም መገደዳቸውን የሚናገሩት የሥራ ኃላፊዎቹ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት የውጭ ምንዛሪ በብድር መልክ እንዲያስገቡና ከዓመት በኋላ ቀስ እያሉ እንዲከፍሉ ለብሔራዊ ባንክ ማመልከቻ ቢያስገቡም፣ “የብሔራዊ ባንክ መመሪያው ስለማይፈቅድ አትችሉም” የሚል ምላሽ ከመንግሥት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተለይ መሠረታዊ የሆኑ ጥሬ እቃዎች በዱቤ ለማስገባት (ክፍያውን አዘግይተው ለመክፈል) መንግሥትን ቢጠይቁም፤ መመሪያው እንደማይፈቅድና እንደማይችሉ ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ኮካኮላ ሣብኮ መሠረቱ ደቡብ አፍሪካ መሆኑንና በኤዢያና በአፍሪካ አገሮችም ፋብሪካዎች እንዳሉት የገለፁት ኃላፊዎቹ፣ እስካሁን ከኢትዮጵያ በስተቀር በየትኛውም አገራት ምንም ዓይነት ችግርም ሆነ የጥሬ እቃ እጥረት እንዳላጋጠማቸው ገልፀዋል፡፡

“መንግሥት ይህንን ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ ይሰጠናል ብለን እናስባለን” ያሉት ኃላፊዎቹ፤ በሚቀጥለው ሣምንት የድርጅቱ የቦርድ ዳይሬክተሮች አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚሰበስቡና የድርጅቱን የወደፊት እጣ ፈንታ እንደሚወስኑ ተናግረዋል፡፡

ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ የፋብሪካውን ምርቶች ሻጭና አከፋፋዮችን ጨምሮ በቋሚና በጊዜያዊነት የሚሰሩ 150 ሺህ ሠራተኞችና ተጠቃሚዎች እንዳሉት ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ምርት አከፋፋዮች እንደገለፁት፣ የለስላሳ መጠጦቹ እጥረት ከተከሰተ ከሁለት ወራቶች በላይ እንደሆነውና እነሱም በቀጥታ ከፋብሪካ ያገኙት ከነበረው መጠን ከ15 በመቶ በታች ብቻ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ 18 በመቶ ወይም ከ30 ሚሊየን ብር በላይ (66ሺ አክስዮኖች) አክሲዮን ለአቶ አብነት ገ/መሥቀል በቅርቡ መሸጡ አይዘነጋም፡፡

አንዳንድ ምግብ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎችና በህብረተሰቡ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በሚገኙ ሱቆችና ሻይ ቤቶች ውስጥ፣ አንድ ኮካኮላ በ2 ብር ከ75 ሣንቲም መሸጥ ሲገባው እስከ 5 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን የገለፁልን ተጠቃሚዎች፤”ወደፊት እንኳን በ5 ብር ሊሸጥ ራሱ መጠጡ አይገኝም” በማለት ፍርሃታቸውን ገልፀዋል፡፡

ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል ኮካኮላ፣ ፋንታ፣ ፋንታ ቶኒክ፣ ሰፕራይትና ክርስታል የማዕድን ውሃ ይገኙበታል::

Source: Reporter

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 15, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.