በአሜሪካ ላይ የቀጠለው የወያኔ ተራ የስድብ ዘመቻ…

ሃብታሙ ግርማ (አዲስ አበባ) | 8 May 2009 – [pdf] በየካቲት 18 ቀን 2001 ዓ.ም ይፋ የተደረገውን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ የ2008 ዓ.ም ሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ የአገሮችን አሠራር ሪፖርት ተከትሎ: የመለስ መንግስት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አፋጣኝ የሆነ መልስ በግዜው መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እነሆ ይህ ከሆነ ከሁለት ወራት በኋላ ማለት ይቻላል አዲስ በሆነ መልኩ የመለስ መንግስት በተከታታይ የቴሌቪዝን እና የራዲዮ ስርጭት ሪፖርቱን በሚመለከት ሰፋ ያለ ዘገባ አስደምጠናል፡፡ እናም ከመቼውም ጌዜ በበለጠ የመለስ መንግስት ምን ያህል ለጉዳይ ትኩረት መስጠቱንና ምናልባትም ጉዳዩ ከፍተኛ የራስ ምታትም የሚፈጥር ሳይሆን እንዳልቀረ ከዘገባው ለመከታተል ችለናል፡፡ በእርግጥ የመለስ መንግስት ለቀረበበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት መልስ መስጠት የሚጠበቅበት እና አግባብ መሆኑ ቢታወቅም የሪፖርቱ አጠቃላይ አቀራረብ ግን እጅግ አሳዛኝና የጋዜጠኝነትን መርህ ያልተከተለ በሌላ በኩልም እንደዜጋ የሚያሳፍርም ጭምር ነው፡፡ በአንድ አገር መንግስት የተዘጋጀ ሪፖርት ሳይሆን ተራ የሆነ ዝርጠጣና ትችት የበዛበት ነው፡፡ በተለይም የመለስ መንግስት የራሱን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ከአሜሪካ ጋር በማነጻጸር ለማሳየት የሞከረበት አካሄድ በጣም የሚያስቅም ጭምር ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በአጠቃላይ ስለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ የሰብዓዊ መብቶች የሀገሮች አሠራር ሪፖርትና በተለይም ኢትዮጵያ ላይ ስለ ሚያመጣው ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ተፅኖ የተወሰነ ነገር ለማለት እወዳለሁ፡፡

የአሜሪካን መንግስት ስለ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በይፋ የመናገር ሃላፊነት መውሰድ የጀመረው እ.ኤ.አ ከ 1970 መጀመሪያ ጀምሮ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ በ 1974 ተሻሽሎ የወጣሁ የውጭ እርዳታ ህግ (Foreign Assistance Act) ከአሜሪካ ሀገር እርዳታ የሚቀበሉ ሀገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከግምት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የሰብአዊ መብቶችን አያያዝ ሪፖርት ዝግጅት መሠረት መጣሉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ እ.ኤ.አ ከ 1977 ዓ.ም ጀምሮ በኮንግረስ ትዕዛዝ መሠረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመታዊ የሀገሮችን የሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ በተመለከተ ለኮንግረሱ ሪፖርት ማድረግ ጀመረ፡፡ ይህም ሪፖርት የአሜሪካን መንግስት ከሀገሮች ጋር ለሚያደርገው የፓለቲካ፣ የዲፕሎማሲ የንግድ እንዲሁም የእርዳታ ግንኙነት መሠረት በመሆን በተለይም ለፖሊሲ አውጭዎች መረጃ በመስጠት ያገለግላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ለሌሎች መንግስተት፤ በይነ መንግስታዊ ተቋሞች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሰብዓዊ መብቶች ተከላካዮች እና ጋዜጠኞች በማጣቀሻነት ያገለግላሉ፡፡ በ1974 ዓ.ም የወጣው የውጭ እርዳታ ህግ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው በአንድ ሀገር ውስጥ ተከታታይ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለና ይህም የማይስተካከል ከሆነ የአሜሪካን መንግስት በተለይም ፕሬዚዳነቱ በቀጥታ ለዚያች ሀገር የሚሰጠውን ድጋፍና ዕርዳታ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የመሠረዝ መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡

ነገር ግን ይህንን ጭብጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት ላለፉት 5 አመታት በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በተለይም ኢትዮጵያን አስመልክቶ የወጡትን የሰብአዊ መብት ዘገባዎች እንዲሁም የነበራቸውን ፋይዳ ወይም ተግባራዊ ተፅእኖ ስንመለከት ግን እንብዛም ሆኖ እንመለከተዋለን፡፡

ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም በተለይም ከመስከረም 11/2001 የፀረ ሽብርተኝነት ጥቃት በሆላ የአሜሪካን መንግስት በዋጀው የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ የመለስ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እየሆነ መምጣት፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን የፖለቲካና የጂፕሎማሲ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሻገር አድርጎታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች የምታገኘው እርዳታና ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ችሏል፡፡ በአካባቢው የነበራትም ተፅእኖና ተደማጭነትም በዚሁ ልክ ከፍ ማለት ችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በነዚህ 5 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል ይቀርብ የነበረው የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግሮች በተለይም ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ የተነሱ ከፍተኛ የሆኑ የሰብአዊ መብት ችግሮች በግዜው በነበረው የቡሽ አስተዳደር ምንም አይነት ተደማጭነትና ተቀባይነት ሳያገኘ ቀርቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ የቡሽ አስተዳደር በውጭም በውስጥም ካሉ የተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ የሆነ ወቀሳ ተሰንዝሮበታል፡፡

ነገር ግን አዲሱ የኦባማ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ለሰብአዊ መብት መከበር የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን እየተወሰዱ ካሉት በርካታ እርምጃዎች መመልከት ይቻላል፡፡ ለዚህም እንደአብነት የሚጠቀሰው በቡሽ አስተዳደር ግዜ አሜሪካን ለከፋ ትችት አጋልጣት የነበረውን በኩባ የሚገኘውን የሽብርተኞ እስር ቤት በአንድ አመት ግዜ ውስጥ እንዲዘጋ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በቡሽ አስተዳደር ግዜ የነበረውን ኢ-ሰብአዊ የሽብርተኞች አያያዝን የሚያሳዩ መረጃዎችም ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በእርግጥም ባራክ ኦባማ ሲመታቸው በተካሄደበት ጥር 20,2009 ዓ.ም ቃል እንዳገቡት “አሜሪካ መፃኒ ሰላም እና ክብር ለሚሻ ለእያንዳንድ አገር እና ለሁሉም ወንድ፣ ሴት፣ ሕጻን ወላጅ ናት …” ነገር ግን በሙሰኝነት እና በማጭበርበር ሥልጣንን አጥብቃችሁ በመያዝ ከእናንተ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን የምታፍኑት እናንተ በጨቋኙ የታሪክ ጎን መሆናችሁን እውቀት፣ ሆኖም፣ ቡጢአችሁን ለመክፈት ፈቃደኛ ከሆናችሁ እኛም እጃችንን እንዘረጋላችኋለን….፡፡ እጃቸውን በሌሎች ላይ ከመዘርጋታቸው በፊት ቤታቸውን እያስተካከሉ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡

በቅርብ የተለቀቁ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከዘጠኙ መሠረታዊ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መካከል የስድስቱ አባል ናት፡፡ ማንኛውንም አይነት ይዘር መድልኦ ለማስወገድ የተደረገውን አለም አቀፍ ስምምነት በ1968 ዓ.ም በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውም አድሏዎ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገውን ስምምነት በ1972 ዓ.ም፣ የሕፃናት መብቶች ስምምነት በ1983 ዓ.ም ፣የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳንን በ1985 ዓ.ም ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳንን በ1985 ዓ.ም ማሰቃየትና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸውን፣ ሰብዓዊነት የጎደላቸውን አዋራጅ የሆኑ አያያዞችንና ቅጣቶችን ለማስቀረት የተደረገውን ስምምነት በ1986 ዓ.ም አፀጽቃለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርንም በ1990 ዓ.ም አፀድቃለች፡፡

ኢትዮጵያ ከስድስቱ የተባበሩት መንግስታት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች በተጨማሪ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አራት ወቅቱን የጠበቀ ውዝፍ ሪፖርት እንዳላቀረበች በሚያዝያ 26,2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው የሪፖርት ጋዜጣ አስነብቦናል፡፡ ታዲያ እነደዚህ ያለ ዘርፈ ብዙ ሥራ የሚጠብቃት ሀገራችን ኢትዮጵያ አሜሪካን ከሚያክል ሃያል ሀገር ጋር እርስን እያስተያዩ መገምገምም ሆነ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ መግባቱ እጅግ የማይጠቅማት ብቻ ሳይሆን ሊጎዳትም እንደሚችል የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም ዳፋዉ ለመለስ ብቻ ሳይሆን ለኛ ለተራ ዜጎችም ጭምር የሚደርስ ነውና እጃችንን መሰብሰቡ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ “አልያ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አሊያ“ የተባለው ተረት ይደርሳል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 8, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.