በአለም አቀፍ የሴቶች ቀን የምናስባት ታላቅ ሴት… ብርቱካን ሚዴቅሳ።

Honoring Birtukan on March

[Read the press release in PDF] የአለምን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ ከታላቋ ካትሪና እስከ ንግሥት ቪክቶሪያ፤ ከኢንድራ ጋንዲ እስከ ማርጋሬት ታቸር ድረስ በርካታ የአለማችንን ታላላቅ እንስቶች ይታወሱናል። እነዚህና ሌሎች ታዋቂ ሴቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለአለማችን መልካም ነገርን አበርክተዋልና፤ ከአገራቸው አልፈው በመላው አለም ስማቸውና ታሪካቸው ምንግዜም ከፍ ብሎ ይወሳል።

በአፍሪቃም ከንግሥተ ሳባ እስከ ዮዲት፣ ከንግሥት ጣይቱ እስከ ንግሥት ዘውዲቱ ድረስ፤ ታሪክ በበጎም ሆነ በመጥፎ የሚያነሳቸው መሪዎችን አፍርተናል። አለማችን የሴት መሪዎችን በብዛት ባላፈራችበት ዘመን የነበሩ፤ በዘመናቸውም ህዝብን የመሩ በመሆናቸው ምንግዜም ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ናቸው። እነሆ “መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይኖራል” እንደሚባለው፤ በአዘቦቱም ሆነ በየበአላቱ አጋጣሚ ስማቸውን ከፍ አድርገን እናነሳለን።

ኢትዮጵያ ታላላቅ የአገር መሪዎችን ለአፍሪቃ እንዳበረከተች ሁሉ፤ የመጀመሪያዋን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ፤ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳንም በክፍለ ዘመናችን አፍርታለች። በመሆኑም በህዝብ የታገዘ የፖለቲካ ድርጅት በመምራት… ለፍትህና ለእኩልነት፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለእውነት በመቆሟ ለእስር የተዳረገችውን ብርቱካን ሚዴቅሳን፤ ከአገራችን አልፈን ከሌሎች አፍሪቃዊያንና ሰላም ወዳድ የአለማችን ህዝቦች ጋር በጋራ እናስባታለን።

በመላው አለም “የሴቶች ቀን” ተብሎ በሚከበረው፤ ማርች ስምንት ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳንና እንደሷ በግፍ የታሰሩ፤ ፍትህ ያጡ እህቶቻችንን፤ እንዲሁም መላው የፖለቲካ እስረኞችን እናስታውሳለን። እነሆ ይህም ትውልድ ታሪክን ከመተረክ ባሻገር፤ ታሪክን በመስራት አንድ ምዕራፍ ወደፊት ተሸጋግሯልና… በዚህ ታሪካዊ እለት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድነታችንን የምናድስበት፤ የታሰሩትን የምናስብበት፣ የተሰዉትን የምንዘክርበት ቀን እንዲሆን ልባዊ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

በዚህ ዘመን… ያለፉትን ታላላቅ የአለማችንን ሴቶች ስናስባችው፤ ዛሬ በህይወት ያሉትንና ታላቅ መስዋዕትነትን የከፈሉትን ታሪካዊ ዋጋ በመስጠት ጭምር ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያንና ለፍትህ የቆምን አካላት በሙሉ ይህንን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ስናከብር፤ በሰማይ ላይ እንደሚያንፀባርቁት ከዋክብት፤ ስሟ ለዘላለም ተከብሮ የሚኖረውን ታላቋን ሴት…፤ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የአለማችን ሴቶች በምሳሌነት የምትዘከረውን ብርቱካን ሚዴቅሳ በማስታወስ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ… ይህ እለት አንገታችንን ቀና አድርገን የወ/ት ብርቱካንን ነጻነት እውን ለማድረግ፤ የሰላማዊ ትግል ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ቀን ይሆናል። 

 Andinet Atlanta Humanitarian Support Group

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 7, 2010. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.