በኃይል እጥረት ሙገርና መሶቦ ሲሚንቶ ሥራ አቆሙ

በአሰግድ ተፈራ (Reporter) – በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ሳቢያ የማምረት ሥራ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ከደረሳቸው ድርጅቶች መካከል ሙገር ሲሚንቶ እና መሶቦ ሲሚንቶ እንደሚገኙበት፣ በፋብሪካዎቹ ሥራ ማቆም ምክንያት ለሚከሰተው የሲሚንቶ እጥረት መንግሥት 44 ሚሊዮን ብር በመመደብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ከውጭ አገር ገዝቶ በማስገባት ላይ እንደሆነ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የተለያዩ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡ 

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት ጋር በመሆን ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በኃይል እጥረት ሳቢያ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማምረት ማቆማቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን እጥረት “ክፍተት” ሲል ነው የጠራው፡፡ እንደ መግለጫ ሰጪዎቹ አገላለጽ ክፍተቱን ለመሙላት በጀት የተያዘው በበጀት ዓመት መጀመሪያ ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው በኃይል እጥረቱ ሳቢያ የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ የማምረት ሥራቸው እንደሚስተጓጎል አስቀድሞ ስለሚታወቅ ነው፡፡

በሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ቤት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አማረ አስገዶም እንዳስረዱት በመንግሥት ትዕዛዝ በዓመት እንዲገዛ የተወሰነው የሲሚንቶ መጠን 1.5 ሚሊዮን ቶን፣ ወይም 15 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በርብርቦሽ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የሚደረገው 2 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ ይህም መጠን በአገር ውስጥ ካለው ፍላጎት ብልጫ ያለው በመሆኑ በግልም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የተጀመሩ ግንባታዎችና መሰረተ ልማቶች ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል አይከሰትም፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቤቶች ልማት አቅርቦትና የሎጂስቲክ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አጽብሃ ገ/ዮሐንስ ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለው በአራት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ መርከቦችና በሌሎች አገሮች የንግድ መርከቦች የሚጓጓዘው ሲሚንቶ ከጅቡቲ ተፈለገበት የሽያጭ ማዕከል እንዲደርስ 600 የደረቅ ጭነት ማመላለስ ከባድ መኪናዎች ተመድበዋል፡፡ በቅርቡ 100 ተጨማሪ የጭነት መኪኖች ይመደባሉ፡፡ በጥቅሉ የተገዙት መኪናዎች አንድ ሺህ ናቸው፡፡ የግል የትራንስፖርት ዘርፍም ተሳታፊ ይሆናል፡፡

ሙገርና መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት በድምሩ 1.7 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርቱ የገለፁት አቶ አማረ ድሬዳዋ ያለውን ናሽናል ሲሚንቶንና ደጀን የተገነባውን ሲሚንቶ ፋብሪካ የምርት መጠናቸውን አልገለፁም፡፡

ከ30 የሚበልጡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ቢሆኑም በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩት ከሶስት አይበልጡም፡፡

በየዓመቱ 25 በመቶ እድገት ለሚያሳየው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋና ግብአት የሆነው ሲሚንቶ በአገር ውስጥ የማምረቱ ሥራ እስከመቼ እንደሚቆም የታወቀ ነገር ባይኖርም መግለጫ የሰጡት ክፍሎች ለጊዜው ለሁለት ወራት ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለፁት ሙገርን ጨምሮ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ ኃይል እንደሚቋረጥባቸው ተነግሯቸዋል፡፡ በዚሁ ውሳኔ መሰረት ኃይል ከተቋረጠባቸው ኩባንያዎች መካከል ሙገር አንዱ ሲሆን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ደብዳቤ አስገብቶ የቦርዱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ቀድሞውንም ቢሆን በአገር ውስጥ ምርት ብቻ የአገር ውስጥ ፍላጎት እንደ ማይሸፈን የገለፁት መግለጫ ሰጪዎቹ 400ሺህ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የ4 ዓመት እቅድ ይዞ የሚንቀሳቀሰው የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራምና ሌሎች የመንግሥት መሰረተ ልማቶች ከውጪ በሚገዛ ሲሚንቶ እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል፡፡

ግንባታ እያካሄዱ ያሉ የሥራ ተቋራጮች፣ በኢንቨስትመንት ዙሪያ እየተሳተፉ ላሉ አልሚዎችና የግል መኖሪያ ቤት ለሚገነቡ ሲሚንቶ ለማከፋፈል የተመረጡ የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ (ጅንአድ) ነው፡፡

የጅንአድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይማም መሐመድ ጅንአድ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ገበያን ማረጋጋት በመሆኑ፣ ከውጪ በግዢ የሚመጣውንና ከፍተኛ ጥራት እንዳለው የገለፁትን (OPC42) ሲሚንቶ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል የሚሸጠው በ250 ብር ሲሆን ሽያጩ የሚከናወነው በቀጥታ ለተገልጋዩ ክፍል ነው፡፡

በአዲስ አበባ ካሉት ሶስት የሽያጭ ማዕከላት በተጨማሪ አዳማ፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳና ሻሸመኔ አዲስ የማሰራጫ ማዕከላት መከፈታቸውን የገለፁት ዋና ሥራ አስኪያጁ “ሲሚንቶ ማግኘት የሚችለው ህጋዊ የግንባታና የፕሮጀክት ፍቃድና ህጋዊ ማስረጃ ያላቸው አካላት ብቻ ናቸው” ብለዋል፡፡ የግል ነጋዴዎች ከመንግሥት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲሚንቶ ስለማያገኙ ከሥራው እንደሚወጡም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የጅንአድ ሠራተኞችና ተጠቃሚ ነን የሚሉ ግንኙነት ፈጥረው የራስን ጥቅም በማስቀደም፣ እንዳይሰሩ የሚያደርግ አሰራር እንዳለ ለተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ “በጎ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ እየተመካከርን እንሰራለን፡፡ የሚሰጠንን አስተያየት ተቀብለን አሰራራችንን እናስተካክላለን” በማለት ነው የመለሱት፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 14, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.