በቻይና ደንደስ… እኛ እንወደስ [የአቤ ቶኪቻው ጨዋታ]

(አቤ ቶኪቻው)
ከመጀመሪ በፊት… በተለያየ ግዜ በተለያየ መልኩ ተግቼ እንድፅፍ ያገዛችሁኝ እና፤“አይዞህ ከጎንህ ነን”ያላችሁኝ ወዳጆቼ በርካታ ናችሁ። እኔም የወዳጆቼን አጋርነት ባየሁ ግዜ ደስ ብሎኛል። እናም በድጋሚ “አለንልህ!” እንዳላችሁኝ አንድዬ አለሁ ይበላችሁ ብዬ ወደዛሬው ወግ አሳልጣለሁ…

አዲሳባ ጎተራ አካባቢ አንድ መንገድ አለ። መንገዱ ማለቅ ለተሳነው ቀለበት መንገድ ታናሽ ወንድሙ ሲሆን ስሙም ማሳለጫ ነው። ግዜ እና ትንፋሽ ያለው ሰው “የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማሳለጫ መንገድ” ብሎ ቢጠራው ሙሉ ስሙን ከነ አያቱ እንደጠራው ይቆጠርለታል። ማሳለጫ ዲዛይኑ ከተሰራበት ቀን አንስቶ ለአዳሳባችን ትምክት ሆኗት ቆይቷል። እንደውም በአንዳንድ አሽሟጣጮች ዘንድ “የሚመካ በማሳለጫው መንገድ ይመካ!” ብላለች አዲሳባ እየተባለ ሲነገርም ሰምተናል።

ይህው ታላቁ ሩጫ እንኳበቤተ መንግስት በኩል መዞሩ ቀርቶ በማሳለጫ መዞር ከጀመረ ሁለት አመት አለፈው። ታላቁ ሩጫን በማሳለጫው በኩል ማዞር ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት “ባለሞያዎች” ይናገራሉ። ዋናው ጥቅሙግን ቀድሞ በቤተመንግስት ዙሪያ ሲሮጥ ህዝቡ በመንግስቱ ላይ ሲሰነዝራቸው የነበሩ ግምገማዎች እና አስተያየቶች ቢያንስ የጉዳዩ ባለቤቶች ዘንድ (መድረሱ ባይቀርም) በቶሎ እንዳይደርስ ይጠቅማል። በሚል ነው። እንደውምኮ አንድ ሰሞን ማደሪያቸውን ቤተመንግስት ያደረጉ ቱባ ቱባ ባለስልጣኖች ታላቁ ሩጫ ደረሰ ሲባል ቤተ መንግስቱን ለ “ዋርዲያ” ጥለው ቻይና ወይ ዱባይ ገበያ ሄድ ብለው ለልጆቻቸው መጫወቻ ለሚስቶቻቸው መዋቢያ ገዝተው ወደ ቤተ መንግስታቸው የሚመለሱት ሩጫው ሲያልቅ ነበር አሉ!!!! (ወዳጄ ቃል አጋኖውን ያበዛሁት ማጋነኔን እንዲረዱልኝ ብዬ ነው)እናልዎ እድሜ ለቻይና አሁን ማሳለጫ መንገድ ተሰርቶልናል። ለአዲሳባም ትምክህት ለመሪዎቻችንም እረፍት ሰጥቶልናል።

ማሳለጫ መንገድ ሙሉ በሙሉ ወጪው የተሸፈነው በአይነ ትንንሾቹበገንዘበ ብዙዎቹ ቻይናዎች ነው። እውነት ግን ቻይና ምን አድርገንላት ነው እንዲህ የምትንከባከበን? ብላችሁ አትጠይቁም? የምሬን እኮ ነው… ይሄንን ያደረገችው ኮሪያ ብትሆን ኖሮ የዛኔ ክፉ ቀን ያጋጠማቸው ግዜ “ጥቃትሽ ጥቃቴ” ብለን የዋልንላቸውን ውለታ ከግንዛቤ አስገብተዋልና “ብድሩን የማይመልስ አገር አይፈጠር!” ብለን እናደንቅ ነበር።“ብድሩን የማይመልስ ሀገር…” ብዬ ስል የሳወዲ አረቢያ ነገር ትዝ አለኝ። ስለ ሳውዲ ኮስተር ብለን እንቀጥላለን፤

ከዛሬ ስንት እና ስንት አመት በፊት በሳውድ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ ሙስሊሞች በጉልበተኞች መቆምያ መቀመጫ አጥተው ነበር። ታድያ ያኔ መሸሸጊያ በጨነቀ በዛን ወቅት፤ ነብያችን እንዲህ አሉ፤ “ሂዱ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች በዚያ ምንም ክፉ አይገጥማችሁም። ህዝቡ እንግዳ ተቀባይ መንግስቱም ሰው አክባሪ ነው።” ብለው ሸኙዋቸው። ሳውዲዎችም በባህር በየብስ አቆራርጠው አኢትዮጵያ ገቡ። እውነትም ምንም ክፉ አልገጠማቸውም። በእስልምናቸው ጠንተው እና ተስፋፈተው መኖር ጀመሩ። እሰይ እንኳንም ተስፋፉ እንኳንም ጠኑ። እዝችው ላይ በዚሁ አጋጣም እንኳን ለነብያችን የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ብለን እንቀጥላለን። ዛሬ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ኑሮ ጭንቅ ሲሆንባቸው በባህር በየብስ አቆራርጠው ወደ ሳውዲ አደረቢያ ይነጉዳሉ። ታድያ አንዳንዴ፤ በተለይም ደግሞ ሰሞኑን ሳውዲዎች በኢትዮጵያውያኑ ላይ እየፈፀሙት ያለውን ለተመለከተ “ወርቅ ላበደረ አመድ መልስለት” አይነት ነው። በሳውዲ ተሰብስበው ገናን ያከብሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ታስረው ለሰሚ የሚከብድ በደል እየደረሰባቸው ነው። አረ ተዉ ሳውዲዎች የነብያችን እና የኢትዮጵያውያን ግንኙነት እንዲህ አይደለም!

ከላይ የተነበበችውን አንቀፅ በሳውዲዎች የቢሮ ቋንቋ ተርጉሞ ላደረሰልኝ ወረታ እከፍላለሁ። ቀጥሎ በሚነበበው አንቀፅ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግስቴ ጋር መነጋገር እሻለሁ።
እናንተ ጉደኞች… ብዬ ብጀምር ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን በአደባባይ መንግስቴን እንዲህ ብዬ ብናገር “መልካም ስሙን” ማጉደፍ ይሆንብኛል እና ይቅር። የምር ግን መንግስታችን ህዝቦቹን ለሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ለሰላማዊ ቦንድ ግዢ ተሳታፊ እንዲሆኑ መጀመሪያ የህይወታቸው ነገር ከአደጋ የነፃ መሆን እንዳለበት መረዳት እንዴት ተሳነው። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአለም አካባቢዎች በተለይም በአረቡ አገራት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመከላከል መንግስታችን ሲሰራም ሆነ ሲፀልይ አይተን አናውቅም። (የሚሉ ብዙዎች ናቸው) ያስታውሱ እንደሆነ መቼለት ነው… አንድ ወንድማችን በሶማሌ ላንድ ስንት ብር እንደሁ እረሳሁት ብቻ፤ “ገንዘብ ካላመጣህ ህይወትህን ታጣለህ!” ተብሎ የተጠየቀ ግዜ መንግስት ባለበት አገር ስለ ልጁ ሲደራደር የነበረው ታዋቂው አርቲስት ቴዲ አፍሮ ነበር። በርግጥ ውጪ ገዳይ ሚኒስትራችን (ታይፕ ግድፈት ካለ እያስተካከላችሁ አንብቡልኝ) ቴዲ አፍሮ ገንዘቡን ሊከፍልለት እና ሊያስፈታው ከተዋዋለ በኋላ ውጪ ጉዳይ ቢሮ ዘግይቶ ብቅ ብሏል። በቡና ቢሆን ኖሮ አቦል እና ቶና አልፎ በረካ ከተጠጣ በኋላ እንደመምጣት ማለት ነው። የእኛ ሰፈር እናቶች ውጪ ጉዳይ ቢሮ እንዲህ ባለው ሰዓት ሲደርስ ቢያዩት “አይ አጅሬ ያለታወቀበት ነጋዴ ነው ማለት ነው!” ይሉት ነበር።፡

አሁን በቅርቡም ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በምታሸጋግረው ማልታ የተባለች ሀገር ላይ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ታስረው መከራቸውን ሲያዩ መንግስት ማን “ሳይለንት” እንዳደረገው እንጃ፤ ምንም ድምፁ አልተሰማም። ይልቅስ “አሸባሪ” ተብለው ሞገስ ያገኙት አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመሩት የ “ትብብር ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ድርጅት” ነው ከማልታ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ደብዳቤ እየተፃፃፈ እና “ስለ ጉልበታችሁ አምላክ፣ ስለ ወዳጅነታችን፣ ስለ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች…” እያለ ዜጎቹ እንዲፈቱ ሲማፀን የነበረው። (እንዲህ ነው እንግዲህ ማሸበር… አይሉልኝም?) መንግስታችን በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የሚጎበኘው ቦንድ ግዙ ለማለት ብቻ ነው። “አረ ሼ…” ይላሉ የአራዳ ልጆች። የአራዳ ቋንቋ ግር ግለሰቦች “አረ ነውር ነው!” ብዬ እተረጉማለሁ።

ይህው ዛሬም በሳውዲ አረቢያ በርካታ ዜጎቻችን ታስረው ኢሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው መንግስት ነብሴ “የዝሆን ጆሮ ስጠኝ… ባትሰጠኝም አልሰማም”ብሎ ፀጥ ብሏል። በእውኑ ለመንግስታችን ልቦና እና ጆሮ ይስጥልን እና ብሪቱን ብቻ “ወዲህ በሉ” እያለ ከመኖር ተፈውሶ ወዲህ ወዲያ እያለ ህዝቡ ያለበትን ሁኔታ እንዲሰማ ያደርገው።
ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ዘወር ስንል፤ ቻይና ዛሬም አንድ ስጦታ ለአዲሳባ፤ ለአዲሳባም ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አበርክታለች። የአፍሪካ ህብረት ህንፃ። ይቺ ቻይና እንዲህ የምትንከባከበን ምን አድርገንላት እንደሆነ እስከ አሁን በቅጡ አልተጣራም።

የሆነ ሆኖ ግዙፉ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ተመርቋል። በምርቃቱ ዕለት የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ንግግር ሲያደርጉ፤ ባለሁበት ሀገር ሆኜ በዲሽ (ወሬ አምጪ ምጣድ ይሉታል!) ስከታተላቸው ነበር። እንዲህም ሲሉ ጀመሩ፤ “ይህ ቦታ ቀድሞ አለም በቃኝ የሚባል እስር ቤት ነበረበት…” ብለው ሲናገሩ ከቴሌቪዥኔላይ ንግግራቸው ተቋረጠብኝ። ይሄኔ ከዚሀ በፊት የሰማሁት አንድ ዘገባ ትዝ አለኝ። መንግስታችን ከዚህ በፊት ኢሳትን እንዳደረገው ሁሉ፤ የኤርትራ ቴሌቪዥንንም ሳተላይት ለሳተላይት እያሳደደ በገንዘብ ናዳ እየደበደበ ለመገደብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ሰምቻለሁ።በዚህ ግዜ ለካስ ከአጠገቡ ያለውም ኢቲቪ አብሮ እተደበደበ ወደውጪ የሚያደርገው ጉዞ ይገደብ ኖሯል። በእውነቱ ግን ሰው ለአባይ ግድብ “መብላት መጠጣቱ ይቅርብኝ” ብሎ ሲያዋጣ ሰው ሳይሆኑ መንግስት የሆኑት ዋናዎቹ አለቆቻችን፤ ቴሌቪዠዥን እና ራዲዮ እንዲሁም፤ ሰብአዊ መብት ለመገደብ ሲያውሉት የአባይ አምላክ እንዴት ያደርጋቸው ይሆን? እንጃ…

የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስሩ ልክ ሲናገሩናገዳቢዎቹ ኤርትራ ቲቪን ለመገደብ ሲቃጡ አብረው ገድበዋቸው ይሁን፤ ወይም ደግሞ ግድብ ከራስ ይጀምራል ብለው ራሳቸውን በራሳቸውገድበው ይሁን እንጃ፤ ግን “ይሄ ቦታ አለም በቃኝ የተባለ እስር ቤት ነበር… “ ብለው ሳይጨርሱ ዲሼ “በቃዎ!” አላቸውና ቀጥ አደረጋቸው። ይሄን ግዜ አጠገቤ የነበረ አንድ ወጣት ንግግራቸውን ለመጨረስ ሙከራ አደረገ። “… በአሁኑ ግዜ ግን በርካታ አለም በቃኝ እስር ቤቶችን ስለገነባን፤ ግፋ ሲልም ሙሉ አገሪቷን እንደ እስር ቤት ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤትስለሆንን፤ቦታውን ለአፍሪካህብረትፅ/ቤት ግንባታእንዲውል አድርገነዋል።” አለኝ። ሰዉ እንዴት እንዴት ይናገር ጀምሯል!?
በነገራችን ላይ ወዳጃችን ውብሸት ታዬ፣ እህታችን ርዮት አለሙ፣ አቶ ዘሪሁን እና ሂሩት ክፍሌ “አሸብራችሁናል” ተብለው እያነዳንዳቸው ላይ በርካታ አመታት እና ብዙ ሺህብሮች ቅጣት ተጥሎባቸው እስር ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል። እስሩስ የተለመደ ነው ብሩ ደግሞ ምንድነው? ብሎ የሚጠይቅ ካለ የራሴን ግምት እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ።

ግምት
ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ሀገር ጥለው በመሰደድ አሁን አሁን አንደኛ እየሆኑ ይመስላሉ። እንደውም አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ ከሆነ በኤርትራ አንድ ልጅ አደግ ብሎ ሲታይ “ይሄማ ለአቅመ ስደት ደርሶ የለም እንዴ ስንቅ አዘጋጁለት እንጂ!” ይባላል ብሎኛል።(እውነቱን ይሁን ውሸቱን አላጣራሁም!) ታድያ አንድ ኤርትራዊ ከአገሩ ሲሰደድ ቤተሰቦቹ ለመንግስት ሃምሳ ሺህ ናቅፋ ቅጣት ይከፍላሉ። ልብ ይበሉልኝ መሰደድ ጥፋት እንኳ ቢሆን እርሱ ላጠፋው ጥፋት ከፋይ ቤተሰቦቹ መሆናቸው አስደናቂ ነው።
ወደ እኛው አገር ስንመጣ አንድ ቤተሰብ ቢያጠፋም ባያጠፋም ከደሞዙ ለልማት ተብሎ ይቆረጥበታል። ከእርሱ ብቻ ሳይሆን ከተማሪ ልጁ፣ ከዲያስፖራ አጎቱ፣ሁሉ መዋጮ ይጠበቃል። ይህንን ሁሉ ቢያደርግም፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ “አሸባሪ” ተብሎ የመከሰስ ዕድሉ የሰፋ ነው። “ያወራ የተጫወተ…” በሚለው ህግ ማን አሸባሪ ያልሆነ አለ? የዛን ግዜ ደግሞ እስር እና በርካታ ሺህ ብሮችን “ወዲህ በሉ” ይባላሉ። እንዴት ነው ነገሩ… ሰው ታስሮም ቦንድ ገዝቶም ይችለዋል? ይገርማል! እና ግምትህ ምንድነው? ያላችሁኝ እንደሆን ምናልባት መንግስታችን ከጎረቤት ኤርትራ በየሰበባ ሰበቡ ገንዘብ አምጡ የማለት ልምድ ቀስሞ ሊሆን ይችላል። (ግምት ነው…)

እኔ የምለው ግን … እኔ የምለው እንኳ አይደለም አንዳንድ ወገኖች የሚሉት ተብሎ ይስተካከል። እነዚህ ሰዎች ጫካ እያሉ፤ በርካቶች መዋጮ ሲያዋጡላቸው እንደነበር ይታወቃል። ያኔ ለትግሉ ገንዘብ ያስፈልግ ነበር። የገንዘብ ምንጭ ደግሞ በቂ አልነበረም። የባንክ ዘረፋም ቢሆን ሁሌ አይሳካም። ስለዚህ መዋጮ ቢጠየቅም አይደንቅም።ዛሬ ደግሞ መንግስት ከሽሮ ተጋቢኖ እንኳ ሳይቀር ቀረጥ እየሰበሰበ ሁሌ አዋጡ የምንባለው በፊት ሲያዋጡ ለነበሩ ሰዎች ብድር ለመክፈል ነው እንዴ? ያስብላል። በዚህ በመዋጮ ጉዳይ ላይ ወደፊት መለስ ብለን እንቃኘው ይሆናል። ለግዜው ዋናውን መስመር እንያዝ…

እና ቻይና ሆዬ ምን እንዳደረግንላት እንጃ ይህው ታሽሞነሙነን ይዛለች። እግዜር እንደስራዋ ይስጣት እንጂ ሌላ ምን ይባላል። ቻይና ባትኖር ኖሮ ግን ኢህአዴግ አገሪቱ አስራ ምናምን በመቶ እድገት አሳየች ብሎ በቴሌቪዥን ሲናገር ምን ያሳይ ነበር። እውነቴን እኮ ነው፤ ላለፉት አመታት ስለ እድገት ሲወራ ግን ባር ቀደም ሆኖ በቴሌቪዥናችን መስኮት ይመጣ የነበረው “ማሳለጫው” መንገድ ነበር። ልብ አድርጉልኝ እርሱ መንገድ ሙሉ ወጪውን የቻለችው ኢህአዴግ ሳትሆን ቻይና ነች። ነገር ግን ጋዜጠኞቻችን ከዚህ የበለጠ እድገት ከየት ይመጣል? ሲሉ ጎላ አድርገው የሚያሳዩት እርሱን ነበር።

አሁን ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ወሬ ከአሁኑ ተጀምሯል።ህንፃውን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገነባነው ይመስል ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ለስብሰባው የመጡ ተሳታፊዎችን ሳይቀርየኢቲቪ ጋዜጠኞች… “ህንፃውን እንዴት አያችሁልን?” የሚለው ጥያቄ ሲጠይቁ በአይኔ በብረቱ አይቻለሁር። የምር ግንወዳጄ የእኔ አስተያየት ምን እንደሆነ ያውቃሉ …? የምሬን መሆኑን ለማስረገጥ በአዲስ መስመር ላይ እጀምራለሁ።

ህንፃው ውብ ነው እውነቱን ለመናገር ለአዲሳባችንም ሞገስ ይሆናታል። ነገር ግን ይህንን ህንፃ አፍሪካውያኑ ራሳቸው አለመገንባታቸው ዘላለም ሲቆጨኝ ይኖራል። በየ ውጪ አገር ባንኩ ገንዘብ በማከማቸት የሚታወቁት የአፍሪካ ባለስልጣናት አንዲት ህንፃ ለመገንባት የሚሆን በጀት እና ፍላጎት አጥተው እንደ ስንዴው ሁሉ የህንፃ እርዳታ ተቀባይ ሲሆኑ በእውኑ ያሳዝናል። መሪዎቻችንም በዚህ ህንፃ ኩራት ሳይሆን አፍረት ሊሰማቸው ይገባል ባይ ነኝ። እናም ይህ ህንፃ ከአካላዊ ውበቱ ይልቅ መንፈሳዊ ጥቃቱ በልጦብኛል።
አፍረት የለሾቹ እነ ኢቲቪ ግን በሁለት አመት ውስጥ፤ ባማረ ዲዛይን፤ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ… ምናምን እያሉ ከማንቆለጳጰሳቸውም በላይ በራሳቸን አቅም የተሰራ ይመስል “እንዴት አያችሁልን?” ከማለት አልቦዘኑም። ምናለ በሉኝ የሚቀጥለው የኢኮኖሚ እድገት ዘገባ ላይ ደግሞ ልክ እንደ ማሳለጫው መንገድ ፊታችን እያመጡ ድቅን ሲያደርጉት ያላየን እንደሆነ…! እናም “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” እንዲል የሀገሬ ሰው፤ በቻይና ደንደስ እኛ ስንወደስ ያናድዳል!

በመጨረሻም
የሼኩ አጥር
ፒያሳ መሀል ትልቅ አጥር ይገኛል። አጥሩ የሼክ መሀመድ አላሙዲን አጥር ነው። ስንት አመት ሞላው… ዉዉ..! አረ የትየለሌ ነው። በአጥሩ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ እንጃ! በፊት በፊት ይህንን ጥያቄ ስናነሳ አንዳንድ ከኛም በላይ ልማታዊ የሆኑ ወዳጆቻችን “የህንፃ ስራ እኮ ቀላል አይደለም፤ መሰረቱ ሲቆፈር ኮንክሪቱ ሲሞላ አርማታው ሲቦካ… ወዘተው ሲወዘት… ብዙ ግዜ ይፈጃል” ሲሉን አምነን ዝም ብለን ነበር። ነገር ግን ይህው እድሜ ለቻይና አንድ ግዙፍ ህንፃ ለመስራት የሚፈጀውን ግዜ ለመረዳት ችለናል። እህስ ሼኩ ምን ይላሉ? “የነ አቶ በረከትን መፀሀፍ ሳሳትም ብር ጎደለብኝ.. ባለስልጣኖቹን ሀኪም ቤት ሳመላልስ ገንዘቤን ጨረስኩ…” ምናም የሚል ምክንያት መቼም አያቀርቡም።
እባክዎን ሼኩ ከገነቡ ይገንቡት። ካልገነቡ አጥርዎን ያፍርሱልንና ኳሳችንን እንጫወትበት … ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት የፒያሳ ልጆች ናቸው!

በመጨረሻም 2
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንጌ
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲሳባ ይሆን ዘንድ በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን በርካታ ክርክር ተደርጎ ከስምምነት ላይ እንደተደረሰ ታሪክ ያስረዳል። ለዚህም በርካታ መከራከሪያ ነጥቦች ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የነፃነት ተምሳሌት ሆና መቆየቷ አንዱ ማሳመኛ ነበር። የሆነ ሆኖ አሁን በቅርቡ ደግሞ “የህብረቱ መቀመጫ የት ይሁን?!” የሚል ጥየቄ ተነስቶ ነበር። የዛን ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ ንግግር አድርገው ነበር ቆረስ አድርግን እናስታውስ… “…መንግስቱም ቢሆን በአገር ውስጥ ጨካኝ ቢሆንም በአፍሪካ ጉዳይ ግን ጠንካራ አቋም ነበረው…!” ብለዋል። ይህንን ንግግር መንግስቱ ሰምተውት ነበር አሉ (አሉ ነው ታድያ…) እናልዎ መንጌ ምን አስተያየት አልዎት ሲባሉ ምን አሉ መሰልዎ… “መለስም ቢሆን በአገር ውስጥ ጨፍጫፊ አሳሪ እና ገራፊ እንደውም ልጨምርለት ቀፋፊ… ቢሆንም በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ግን ከአንዴም ሁለት ግዜ ንግግር አድርጎ ያውቃል!” ብለዋል አሉ። (አሉ ለዘላለም ትኑር!)

ወዳጄ ይቺን ያህል ካወጋን ለፍሬ ያድርግልን… በሚቀጥለው ግዜ እስክንገናኝ…

አማን ያሰንብተን!

abeto2007@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 4, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.