በተንቤን ህዝባዊ ስብሰባ ተደረገ! (አብርሃ ደስታ – ከትግራይ)

መቀሌ መነሃርያ ስትገቡ ብዙ ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ሲጠባበቁ ታያላቹ። ረዳቶች ‘የት ናችሁ? እዚህ ግቡ!’ ምናምን እያሉ ይሽቀዳደሙላችኋል፣ ይለሙኗችኋል። በመነሃርያው ብዙ አቅጣጫዎች መኪኖች መልተው ተጓዥ ሰው ይጠባበቃሉ። በአንድ ኮርነር ጥግ ግን ብዙ ተጓዝ ሰዎች የአንድ አውቶቡስ መምጣት ለብዙ ሰዓታት ይጠባበቃሉ። እነዚህ ለሰዓታት የሚንገላቱ ሰዎች ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ የሚጓዙ ሰዎች ናቸው።

ቅዳሜ ጠዋት (ሁለት ሰዓት) ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ ለመሳፈር መነሃርያ ገባሁ። ወደ ዓብይ ዓዲ ከተማ የሚሄድ መኪና የለም። ወደ ሌሎች ከተሞች የሚሄዱ መኪኖች ግን ሞልተዋል። በመነሃርያው የሚቆዩ በቂ ተሳፋሪ እስኪያገኙ ድረስ ነው። ወደ ተምቤን የምንጓዝ ግን የመነሃርያው አቧራ ሳይበግረን በትዕግስትና በተስፋ እንጠባበቃለን። ከሁለት እስከ አምስት ሰዓት ጠበቅን። ሲጨንቀን የትራንስፖርት ሓላፊዎቹ አማከርን። ‘ሁሌ እንደዛ ነው! ጠብቁ! ይመጣሉ’ አሉን።

ሁሌ እንደዛ መሆኑ አዋቅ ነበር። ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ ስጓዝ ለሦስተኛ ግዜየ ነው። በሦስቱም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞኛል። ‘ግን ለምንድነው ወደ ተምቤን የሚሄዱ መኪኖች የሌሉ?’ ብለን ጠየቅን። ‘መንገዱ ችግር ስላለበት ሹፌሮች ወደ ተምቤን መሄድ ስለማይፈልጉ ነው’ የሚል መልስ አገኝን። ሚኒባሶች ጭራሽ አይሄዱም። የተወሰኑ አውቶብሶች ብቻ ናቸው ወደ ዓብይ ዓዲ የሚመላለሱ።

ምን ማድረግ እንዳለብን ጠየቅናቸው። ‘ፐርሰንት ከፍላቹ ከባለባሶች ጋር መደራደር ትችላላቹ’ አሉን። ለመደራደር ወስነን ተስማማን። ሰልፍ ይዞ የነበረ ህዝብ ግን ብዙ ነው። በአንድ አውቶቡስ ሊጫን አይችልም። በሃይል ሩጠን፣ ተረጋግጠን፣ ሴቶችና ህፃናት አልፈን ገባን (ሰብአዊነት ቀረ)። የተወሰንን ተሳፈርን አብዛኛው ቀረ። ሁለት ሰዓት መነሃርያ የገባን ሰባት ሰዓት ጉዞ ጀመርን።

ተምቤን ዓብይ ዓዲ ከመቀሌ በስተ ምእራብ (?) በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ነው። መንገዱ በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ሰባት ሰዓት ተነስተን አስራ አንድ ሰዓት ደረስን። ለዘጠና ኪሎሜትር ርቀት አራት ሰዓት ፈጀብን።

ዓብይ ዓዲ የጥንት ከተማ ነው። ከዉቅሮ ቀጥሎ ለመቀሌ ቅርብ የሆነ ከተማ ዓብይ ዓዲ ነው። ሁሉም ዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ከመቀሌ የሚያገናኝ አስፋልት መንገድ ተገንብቶላቸዋል (ከዓብይ ዓዲ ከተማ ዉጭ)። የኢህአዴግ መንግስት ዓብይ ዓዲ ከመቀሌ ከተማ ጋር በአስፋልት መንገድ ለማገናኘት ሃያ ሦስት ዓመት ፈጅቶበታል።

የተምቤን ህዝብ በ1996 ዓም ጥያቄ አስነስቶ ተቃውሞውን በሰለማዊ ሰልፍ ገልፀዋል። በወቅቱ ከተነሱት ጥያቄዎች የፍትሕ እጦት፣ የመብራትና የውኃ አገልግሎቶች፣ የአስፋልት መንገድ ጉዳይ ዋናዎቹ ነበሩ። የተቃውሞ ሰልፉ መሰረታዊ ምክንያትም ህወሓት በተምቤን ህዝብ ላይ አድልዎ እየፈፀመ ነው፤ ልማት እንዳናገኝ ተደርገናል፣ የተለየ ዓፈና ይደርስብናል ወዘተ የሚል ነበር።

ህወሓት ጥያቄያቸውን ከመመለስ ይልቅ ‘የተምቤን ህዝብ ከተነሳ ለስልጣን አደጋ ይሆናል’ በሚል ምክንያት የተቃውሞው አስተባባሪዎች በማስፈራራት ከተምቤን መሬት ለቀው እንዲጠፉ ተደረገ። አስተባባሪዎቹን በማባረር የተቀረውን በሃይል መጨፍለቅ ጀመሩ። የተቃውሞው መንፈስ አዳከሙት። አሁን የተምቤን ህዝብ አንድነት ፈጥሮ እንዳይታገላቸው በመስጋት ህዝቡ ይከፋፍሉታል፣ እርስበርሱ እንዳይተማመን ያደርጉታል። ጥያቄ ያነሳ ካለ ከሀገሩ ያባሩታል።

የተቃውሞ ሰልፉ ይመሩት ከነበሩ ወላይ ጫዓ አንዱና ዋነኛው ነበር። ወላይ ጫዓ ከተምቤን ተባሮ በሌላ ቦታ ለብዙ ግዜ ከተቀመጠ በኋላ አሁን ወደ ዓብይ ዓዲ ተመልሷል (በዓብይ ዓዲ ከተማ በ አካል አግኝቼው ነበር)። በ1996 ዓም የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር የነበሩ አለቃ ፀጋይ በርሀ ወላይ ጫዓን በጣም ይፈሩት እንደነበር የዓብይ ዓዲ ኗሪዎች አጫውተውኛል። አለቃ ፀጋይ ወላይ ጫዓን ከመፍራታቸው የተነሳ የተቃውሞ ሐሳብ የሚያነሳ ሁሉ ‘ወላይ ጫዓ’ ይሉ እንደነበር ነው የተነገረኝ።

በ1996 ዓም የተጠየቁ የመብራትና የዉኃ ችግሮች እስካሁን ድረስ ተገቢ መልስ አልተሰጣቸውም ብለው ኗሪዎች ያምናሉ። የአስፋልት መንገዱ ጉዳይ ግን ከአስር ዓመት በኋላ አሁን ተጀምሯል (ይቅርታ ከተመጀመረ ዓመታት ተቆጠረዋል፣ ግን እስካሁን ድረስ 30% እንኳን አልተጠናቀቀም)። በመንገዱ ጥራትም ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመንገዱ የተወሰነ አካል ይሰራሉ፤ ከወራት በኋላ ደግሞ ችግር አለበት ተብሎ አስፋልቱ ሳይጨርሱ መጠገን ይጀምራሉ።

በዓብይ ዓዲ ከተማ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ህዝቡ የመንግስት አገልግሎት በአግባቡ አያገኝም። ‘የራሳችን ሰዎች ያስተዳድሩን’ የሚል ጥያቄ አለ። ህወሓት ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የዓብይ ዓዲ ህዝብ በተምቤን ተወላጆች እንዲተዳደር ለማድረግ ሞክሮ አልተሳካለትም። የዓብይ ዓዲ ከተማ ከንቲባ ለመምረጥ ሦስት የተለያዩ የተምቤን ተወላጆች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። የተምቤን ተወላጆቹ ግን ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ። የተምቤን ተወላጆቹ ‘የከንቲባነት ስራ ለመስራት ከተፈለገ ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ነፃነቱ ሊሰጠን ይገባል! የህዝቡ ጥያቄዎች ለመመለስ ሊፈቀድልን ይገባል’ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች አቀረቡ። ህወሓቶች አልተቀበሉትም። በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት የዓብይ ዓዲ ከተማ ለብዙ ግዜ ያለ ከንቲባ ቆየች። አሁን ሲጨንቃቸው ግን በሙያው ያልሰለጠነ የከተማው የፖሊስ አዛዥ የነበረ የከተማው ከንቲባ እንዲሆን መርጠውታል።

ዓረና መድረክ ዕለተ እሁድ ከተምቤን ህዝብ ጋር ለመወያየት ዕቅድ ይዞ ስለነበር ከአራት ቀናት በፊት ነበር ቅስቀሳ የጀመረው። ከዚህ በፊት በሌሎች አከባቢዎች ባደረግናቸው ቅስቀሳዎች (በቅስቀስ ወቅት) የተምቤን ያህል በአስተዳዳሪዎች ተፅዕኖ አልደረሰብንም። የዓረና መድረክ የተምቤን የቅስቀሳ ቡድን በየጭላ፣ ወርቅ አምባ፣ ሀገረሰላምና ዓብይ ዓዲ ታስረዋል። ይህ የተደረገው የቅስቀሳ ሂደቱ ለማሰናከል ነበር።

የተምቤን አስተዳዳሪዎች (በሌሎች አከባቢዎችም እንደሚደረግ ሁሉ) ህዝብ በስብሰባው እንዳይሳተፍ ለማፈን በየዘርፉና በየአከባቢው በዕለተ እሁድ የራሳቸው ስብሰባ ጠርተዋል። በተለየ ሁኔታ የዓብይ ዓዲ መምህራን ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች በዓረና ስብሰባ እንዳይካፈሉ ለማድረግ ባልተለመደ መልኩ ለእሁድ ስብሰባ ተጠሩ። የኮለጁ አባላት ብዙ ጥያቄዎች አሉዋቸው።

እሁድ ጠዋት የማዘጋጃቤት ሰራተኞች፣ የፖሊስ አዛዦች፣ የዓብይ ዓዲ ከተማ የእያንዳንዱ ቀጠና ተጠሪ ካድሬዎች በስብሰባው አደራሽ በር አከባቢ ተቀመጡ። ለስብሰባ የመጣ ሰው እነሱን አይቶ ሰግቶ እንዲመለስ ለማድረግ ወይም በስብሰባው የተሳተፈ ሰው ለመመዝገብ ነበር የተቀምመጡት።

ህዝቡ ግን እነሱን ሳይፈራ በድፍረት ወደ አደራሹ መግባት ጀመረ። አደራሹ መልቶ ነበር ማለት ይቻላል። የተምቤን ስብሰባችን ለየት የሚያደርገው ህዝቡ ለመከልከል የተሰማሩ ካድሬዎች ራሳቸውም በአደራሹ ገብተው የስብሰባው ተካፋይ ሁነው፣ ጥያቄዎች መጠየቃቸውና መከራከራቸው ነበር። ካድሬዎቹም አመስግነናል (ከኛ ጋር መከራከር በመቻላቸው)። በስብሰባ ገብቶ የመከራከር ባህል ሊዳብር የሚገባ ነው።

ሞቅ ያለ ዉይይት ተደረገ። ደስ የሚል ነበር። ህዝቡ ስለሚደርሰው ችግር ተናገረ። ስለ የራስ አሉላ አባነጋ ትምህርትቤት ስያሜ መቀየር ያለው ቅሬታ ገለፀ። የተምቤን ህዝብ ለማዳከም ለሁለት መከፈሉ እንደሚቃወም አስረዳን። ደጉዓ ተምቤን ወረዳ ከዋናው ተምቤን ተነጥሎ ወደ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል። ተምቤን ራሱ የቻለ ዞን መሆን እንዳለበትም ተነስቷል። ተምቤን ዞን እንዲሆን ሕግም ይፈቅድለታል። ምክንያቱም አንድ አከባቢ አራትና ከዛ በላይ ወረዳዎች ካሉት የዞንነት ደረጃ የማግኘት ዕድል አለው። ተምቤን አራት ወረዳዎች አሉት፤ (1) ደጉዓ ተምቤን፣ (2) ጣንቋ አበርገለ፣ (3) ቆላ ተምቤንና (4) ዓብይ ዓዲ።

የተምቤን ህዝብ ለውጥ ፈላጊ ነው። ለለውጥ የሚመራው የተደራጀ ሃይል ብቻ ነው የሚያስፈልገው። የህወሓት ሰዎችም የተምቤንን ህዝብ በተለየ ሁኔታ ይፈሩታል። በተምቤን ህዝብ አጠራር ህወሓት ‘ቂመኛ’ ነው። ቂም ይዞ ነው ተምቤኖችን የሚበድለው።

ባጠቃላይ የተምቤን ስብሰባችን ተስፋ ሰጪ ነበር። በድልም ተጠናቋል። ቀጣዩ ጉዟችን ወደ ዓዲ ግራት ወይ ሽሬ ይሆናል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 23, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.