ሰበር ዜና: አቡነ ሳሙኤል ታግተዋል

Aba SamuelAbune Paulosደጀ ሰላም፤ ጁላይ 9/2009 –ቅዱስ ሲኖዶሱ ያረቀቀውን ቃለ ጉባዔ ሳያጸድቅ፣ የጀመረውን አጀንዳ ሰይቋጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሜዳ ላይ ጥሎ ወደ ቤቱ ገብቷል። ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ውሳኔ በፊርማ እንዳይጸድቅ ብፁዓን አበው እስጢፋኖስ፣ ኤጲፋንዮስና ጎርጎርዮስ የሞት ሽረት ትግል አድርገው፣ አባቶችን በጥብጠው ውሳኔው እንዲከሽፍ አድርገዋል። በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ በጀመሩት መልካም አገልግሎት በሕዝቡ እየተመሰገኑ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ይህንን ገዳይ አቋም እንዴት ሊይዙ እንደበቁ እንቆቅልሽ ሆኗል። ገሚሱ በገንዘብ ተገዝተው ነው ሲል ሌላው ደግሞ ውስጠ ዘ በሆነ ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል እያለ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ አሸናፊነቱ እየመጡ ያሉት ፓትርያርኩ የበቀል በትራቸውን እንደሚመዙ እየተጠበቀ ነው። የመጀመሪያ ተጠቂዎች የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መሪነት ስብሰባ ካደረጉ በሁዋላ የፓትርያርኩን ድርጊት የሚቃወም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። ከዚህም ባሻገር ይህንን ሁሉ ሕዝብ ያስተባብርብኛል ያሉት ማህበረ ቅዱሳንም ላይ ጥርሳቸውን ነክሰዋል ተብሏል።

የቤተ ክህነቱ ድራማ ዛሬ ሲተወን ጠዋት በማለዳው ስብሰባ እንዳይገቡ የታገቱት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለምን እንደታገቱ ፌዴራል ፖሊስ ራሱ አያውቅም። የደህንነት ክፍሉ ደግሞ ለደህንነታቸው ብዬ ነው ብሏል። ድራማው ሊቀ ጳጳሱን ከስብሰባው በማስቀረት ውሳኔውን ማክሸፍ ከሆነ በርግጥም ዘዴው ሰርቷል ማለት ይቻላል።መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን እያጠናው እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና ፓትርያርኩ የተነሣባቸውን ተቃውሞ ለመስበርና አባቶችን አንገት ለማስደፋት የሚሆን ገንዘብ ራሳቸው በግላቸው ከሚያዙበት ከቁልቢ ገብርኤል ካዝና ወጪ መደረጉ ታውቋል። የብሩ መጠን ለጊዜው ባይታወቅም ገንዘቡ ለአንዳንድ የፖሊስ ሃላፊዎች፣ ደህንነቶችና ጉልበት ላላቸው ሰዎች መበተኑ ሲታወቅ መንግሥት በውስጡ ሌላ መንግሥት ያለበት አስመስሎታል። እስከ ዛሬም በመንግሥት ስም ቤተ ክርስቲያኒቱን እግርተወርች አስረው ሲበሏት፣ ሲግጧትና ሲያዋርዷት የነበሩ ሰዎች የፓትርያርኩ ዘመዶችና ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተንፈራጠጡ ሰዎችም መሆናቸው እየተገለጸ መጥቷል። መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ሕገ ወጦቹ እጃቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንዲያነሱ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል።

ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ አላት ለማለት እንደማያስደፍር አንድ ሊቀ ጳጳስ ተናግረዋል። ከዋሺንግተን ዲሲ ተጠርተው የተሾሙት የሲዳሞ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሥራ አስፈጻሚው አባል ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልም በበኩላቸው “ሀ/ስብከቴን ተረከቡኝ” ማለታቸው ተሰምቷል።

በርግጥም ሊቀ ጳጳሱ እንዲህ ካደረጉ ጳጳሳት የሥራ መልቀቂያ የሚያስገቡበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ሳይሆን በፓትርያርክና በሴት ወይዘሮዎች ብቻ የሚመራ ቤተ ክህነት ይፈጠራል ማለት ነው።

አንድ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት የፊታችን ሰኞ ስብሰባ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ስብሰባው የተጠራው በቅዱስ ፓትርያርኩ ከመሆኑ አንጻር ምንም ተለየ ነገር አይጠበቅም። ቅዱስነታቸው የፊታችን እሑድ በዓለ ሲመታቸውን እንደሚያከብሩ ይታወቃል።

ለማንኛውም ደጀ ሰላም በበኩሏ “ተስፋ አንቁረጥ፣ እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነውና” ትላለች።

ቅ/ሲኖዶስ በአቡነ ጳውሎስ ቦታ “እንደራሴ” ሾመ

(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 9/2009) [PDF]- ትናንት ማታ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ታሪካዊ ስብሰባ በእምቢተኝነታቸው የጸኑትን ፓትርያርክ ሥልጣን በመግፈፍ እንደራሴ ሾመባቸው። ትናንት የስብሰባው ቃለ ጉባዔ በተነበበበት ጊዜ እንደተገለጸው አቡነ ጳውሎስ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች በሙሉ ተገልለው፣ በጸሎት ብቻ ተወስነው እንዲኖሩ፣ ለዚህም አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው፣ በእንደራሴነት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ እንዲሰየሙ ወስኗል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባደረገው ሙከራ አቡነ ጳውሎስ ነገሮችን በጥሙና እንዲመለከቱና በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ አባቶች በእንባ ጭምር የለመኗቸው ቢሆንም ፓትርያርኩ ግን ማንንም ለመስማት ሳይችሉ ቀርተዋል። በርግጥም ቃለ ጉባዔው በሚፈረምበት ቀን ማለትም ሐሙስ ጁላይ 9 ጠዋት ውሳኔው ቀድሞ እንደተነበበው ሆኖ ካለፈ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ ሥራው በእንደራሴው ይመራል ማለት ነው። ይህ ማለት ግን እንደ ቀድሞ ፓትርያርክ ከሥልጣናቸው ወርደዋል ማለት እንዳልሆነ አንድ አባት ለደጀ ሰላም አብራርተዋል። ምናልባት ግን ቅዱስነታቸው በተለመደው ጠባያቸው (የነ ወ/ሮ እጅጋየሁን ምክር ተከትለው) ከሄዱ የአቡነ መርቆርዮስ ዓይነት መጨረሻ ይገጥማቸው ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

ከእንደራሴው ሹመት በተጨማሪ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሹም ሽር የሚደረግ ሲሆን በተዋረድም በቅዱስነታቸው ቤተ ሰቦች ተይዘው የነበሩ ታላላቅ የአገልግሎት መምሪያዎች ሃላፊነቶች በሙሉ ለቦታው በሚመጥኑ ሊቃውንት ይሰጣሉ ተብሏል። ይህንኑ አጠቃላይ ሒደት የተመለከቱ አንድ አባት “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እየሠራ ነው” ብለዋል።

እንደራሴነት ምን ማለት ነው የሚለው ጉዳይ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተመሳክሮ ማብራሪያ መሰጠት እንዳለበት እያመንን ለጊዜው ግን ከዚህ ቀደም የነበረ አንድ ታሪክ ለማስታወስ እንወዳለን። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ (የመጀመሪያው ፓትርያርክ) በዕድሜና ጤና ምክንያት ሥራቸውን መሥራት ባልቻሉባቸው የመጨረሻ ዓመታት ሁዋላ 2ኛ ፓትርያርክ የሆኑት ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ “እንደራሴ” ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ ቆይተዋል። መንበሩ ግን የፓትርያርኩ እንደሆነ ዘልቋል። በቅዳሴ ወቅት የሚነሣውም የእንደራሴው ስም ሳይሆን የፓትርያርኩ ስም ነበር።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 9, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.