ቃለ – መጠይቅ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር (EMF)

Tesfaye GebreAbበበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመነጋገሪያ ርዕስ የሆነውን ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተሰኘ አራተኛ መፅሃፉን በቅርቡ ያሳተመው ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ፤በመጽሃፉ ዙሪያ በሚነሱ በርካታ ጉዳዮች ላይ ከ EMF ዝግጅት ክፍል ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል:: በቃለ-ምልልሱ ከተነሱት ጥያቄ መካከል ስለ አወዛጋቢ መጽሃፎቹ: በተለይ ስለ “የቡርቃ ዝምታ”: ስለ መለስና ተወልደ: ስለ ዜግነት ጥያቄ: ስለ ኢትዮሚዲያ ኤዲተር (አብርሃ በላይ):  በአሁኑ ሰአት እየገጠሙት ስላሉ ችግሮች…. ይገኙበታል:: በ PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ::

ቃለ – መጠይቅ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር 
 

      ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ፤ ቃለምልልስ እንድናደርግ ላቀረብኩልህ ጥያቄ ፈቃደኛ በመሆንህ በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ።  

      በቅድሚያ ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ለተሰኘው አራተኛ መፅሃፍህ በመብቃትህ እንኳን ደስ ያለህ ስልህ፤ ቀደም ሲል ስላሳተምካቸው ሶስት መፅሃፎች እንድምታ፤ ባጭሩ የምትለን ነገር ይኖራል? 

      እኔም ይህን እድል በማግኘቴ አመሰግናለሁ።  

      “አርባ አመት ያልሞላው ሰው መፅሃፍ ባያሳትም ይመረጣል” የሚለውን አባባል ከሚቃወሙት አንዱ ነበርኩ። ዛሬ ላይ ቆሜ ሳየው ግን አባባሉ ሙሉ በሙሉ ስህተት አይደለም። በወጣትነት ዘመን መፅሃፍ ለመፃፍ መሞከር ጥሩ ነው። ለማሳተም መወሰን ግን ጥንቃቄ እንደሚያሻው ተምሬያለሁ። አንድ ደራሲ ወደሁዋላ መለስ ብሎ፦ “ምነው ይህን ባላልኩ ኖሮ? ምነው ይህቺን በጨመርኩ?” ብሎ ለፀፀት የሚያበቃውን ስራ መስራት የለበትም። ከዚህ አንፃር “ያልተመለሰው ባቡር” እና “የቢሾፍቱ ቆሪጦች” በተባሉት መፅፎቼ ብዙም ርካታ የለኝም። “ያልተመለሰው ባቡር”ን በችኮላ ነው ያሳተምኩት። በወቅቱ ደረጄ ደስታ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጥሩ አድርጎ ተርቦታል። “ያልተፃፈው መፅሃፍ” ሲል ነበር የሰየመው። በርግጥም መፃፍ እንደምችል የታየበት እንጂ መፅሃፉ አልተፃፈም ሊባል ይችላል። “የቢሾፍቱ ቆሪጦች” ላይ መጥፎም ሆነ ጥሩ ትዝታ የለኝም። የአንባብያንን አስተያየት ሳላጣጥም ነው ከሃገር የተባረርኩት። “የቡርቃ ዝምታ” ላይ ግን ሙሉ እርካታ አለኝ።  

      “የቡርቃ ዝምታ”ን ለመፃፍ ያነሳሳህ ምንድነው? ለማንፀባረቅ የፈለግኸው አንኳር መልእክትስ ምንድነው? በበርካታ አንባብያን የተፈጠረውን ቅሬታስ ጠብቀኸው ነበር? ወይስ ዱብእዳ ነው የሆነብህ? 

      “የቡርቃ ዝምታ”ን የወለደው ወቅቱ ነው። ወያኔ የብሄር ድርጅቶችን እየፈለፈለ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነበር። በዚህ ሂደት የኦሮሞ ህዝብ የበለጠ ተጎጂ ሆኖአል ብዬ አምኜያለሁ። ደስ የማይሉኝ ብዙ እመቃዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲፈፀሙ በቅርብ ለመታዘብ ችዬ ነበር። ኦህዴድ ሆን ተብሎ ብቃት በሌላቸው ግለሰቦች መዋቀሩን እያየሁ ነበር። የአማራውን ክልል የተረከቡት እነአዲሱና ተፈራ ስህተት ቢሰሩ ሳያውቁ አይደለም። እነኩማና አባዱላ ግን የሚሰሩትን እንኳ አያውቁም። አንድ ጀርመናዊ ቢሾፍቱ ሃይቅ ላይ የአየር ላይ ባቡር ዘርግቶ ቱሪስቶችን ለመሳብ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። “በዚህ ወቅት የኦሮሞ አርሶአደር ፍላጎት የቅንጦት መዝናኛ ሳይሆን፤ ማዳበሪያ ማግኘት ነው” የሚል መልስ ሰጥተው አባረሩት። ቄንጠኛ አባባሎችን አጥንተው የገዛ አገራቸውን የሚያወድሙ የአእምሮ ድሆች ኦሮሚያን ተረክበው ነበር። እኔ እነዚህን ሰዎች በቅርብ የማወቅ እድል ነበረኝ። ባጫ ደበሌ የኢህዴን ኪነት ጃዝ መቺ ነበር። ከበሮ መምቺያ እንጨቶቹን ግራና ቀኝ ወርውሮ የወለጋ አስተዳዳሪ ሆነ። ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ወገኖቹን የቻለውን ያህል ካንገላታ በሁዋላ፤ “በቃህ! አሁን ደግሞ ጄኔራል ትሆናለህ” አሉት። ባጫ ደበሌ ሃኪም ለመሆን እንኳ የሚስማማ አይነት ሰው ነው። ነጩን ኮት ብድግ አድርጎ ለመልበስ የሚያመነታ ሰው አይደለም። ይህ በኦሮሞ ህዝብ ላይ መቀለድና ማላገጥ መሆኑ ይሰማኝ ነበር። ነጋሶ ጊዳዳ ይህን እያወቁ አለመናገራቸውም አሳሳቢ ነበር። ስለዚህ የቡርቃ ዝምታን ለመፃፍ ወሰንኩ። አኖሌና ሃወኒ የተባሉ ኦሮሞ ዋና ገፀባህርያትን በመቅረፄ የደነገጡ መኖራቸውን አስተውያለሁ። በአማርኛ ስነፅሁፍ ታሪክ ሙሉ የኦሮሞ ስም ያላቸው ዋና ገፀባህርያት ተፅፈው አያውቁም። ጫላና ጫልቱ የሚሉ ስሞችን ለዘበኛና ለገረድ መጠቀም ነበር የተለመደው። ይህን መናገር መከፋፈል አይደለም። እውነት ነው። በአሉ ግርማ ካድማስ ባሻገር ላይ የቀረፃት ሉሊት የተባለችው ዋና ገፀባህርይ ኦሮሞ ናት። በአሉ ግርማ የሉሊት የመጀመሪያ ስም “ጫልቱ ነበር” ብሎ የሚነግረን በሚስጥር ድምፁን ዝቅ አድርጎ ነው። “የቡልቻ ልብ” የሚለው የልጅነት ዘመን ትረካ በአጋጣሚ የመጣ አልነበረም። ይህን መሰል ነገሮች ትኩረቴን ይስቡት ስለነበር አኖሌና ሃወኒ ዋቆ የተባሉትን ገፀባህርያት ፈጠርኩ። ዘመኑ ተለውጦ ነበር። ጊዜውን ልገልፅ ነው የሞከርኩት። ይህን እውነት በመግለፄ ዘረኛ ልባል አይገባም። የቡርቃ ዝምታ ወቅቱን ያንፀባረቀ መፅሃፍ ነው። መራራ ትረካዎችን ማቀፉ ሃቅ ነው። ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩ ግን አይደሉም፤ የሚያቻችሉ ናቸው። በቡርቃ ዝምታ ምክንያት አንኳን የተገዳደለ፤ የተሰዳደደበ ሰውም የለም። ምንም ማድረግ አይቻልም። እኔ በግሌ ለእምዬ ምኒልክ ፍቅርና አክብሮት አለኝ። እሳቸው የዘረጉት የባቡር ሃዲድ ቢሾፍቱን አቋርጦ ያልፋል። አርሲ ላይ አንዱን ወጣት ስለዚሁ ጉዳይ ሳነጋግረው፤ “ ምኒልክን የምናውቃቸው የሬሳ ሃዲድ በመዘርጋት ነው” ብሎኛል። ገበሬዎች ጋር ሰንብቼ የተገነዘብኩትን እውነት ነው ቡርቃ ላይ የፃፍኩት። ትችቶች ሲፃፉ “የቡርቃ ዝምታ’ የተጠላበት ምክንያት” የሚሉ አባባሎችን እሰማለሁ። ይሄ ስህተት ነው። ቡርቃን የኦሮሞ ህዝብ ከምሁር እስከ ተማሪ በክብር አመስግኖ ነው የተቀበለኝ። ስለዚህ የቡርቃ ዝምታ የተጠላ መፅሃፍ አይደለም ማለት ነው። አንድ ተራ ጀማሪ ደራሲ የኦሮሞን ህዝብ አሳሳተው እንዳንል መጠንቀቅ ይገባል። የኦሮሞ ህዝብ ግማሽ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነው። ናይሮቢ ተሰድጄ እንደገባሁ የኦሮሞ ኮሚኒት አባላት ከአውሮፓ ገንዘብ አዋጥተው ልከውልኛል። ከገንዘቡ ጋር “የህዝባችንን ፍላጎት ጠልቀህ ስለተረዳህ፤ የኦሮሞ ህዝብ ምስጋናውን ይገልፅልሃል” የሚል ደብዳቤ ተያይዞ ነበር። የኦሮሞ ህዝብ መፅሃፌን ለምን በክብር ተቀበለኝ? ለኦሮሞች አዲስ ነገር አልነገርኳቸውም። ቀርቤ ነው ያዳመጥኳቸው። እነሱ ያጫወቱኝን እንደነሱ ሆኜ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ኦሮሞ ያልሆነ ሰው ያንን መፅሃፍ በመፃፉ ኦሮሞዎች ከሌላው ህዝብ ይቀራረባሉ እንጂ አይጋጩም። ያን በመፃፌ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ለኦሮሞዎች ብቻ የተተወ አጀንዳ አለመሆኑን ነው ያሳየሁት። አማራን እንደምጠላ ተደርጎ ተቀስቅሶአል። ከየት የመጣ አሳብ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። ክቡሩንና ጀግናውን የአማራ ህዝብ ለመጥላት የሚበቃ የጀርባ ታሪክ የለኝም። እኔ ራሴ አማርኛ ከተባለ ንጥረ ነገር ተጠፍጥፌ የተሰራሁ ነኝ። አማራ ማነው? ብላችሁ ብትጠይቁኝ በቅድሚያ ወደ ጭንቅላቴ የሚመጡት ሶስት ሰዎች ብርሃኑ ዘርይሁን፤ ሃዲስ አለማየሁና ዳኛቸው ወርቁ ናቸው። እስቲ ሶስት ኦሮሞ ጥራ ብትሉኝ ደግሞ በአሉ ግርማ፤ ፀጋዬ ገብረመድህንና ብዙነሽ በቀለ እላችሁዋለሁ። አማራና ኦሮሞን የማለያየት አሳብ እንዴት በኔ አእምሮ ሊፀነስ ይችላል? ይህን መሰል አስተያየት የሚሰነዝሩ ሰዎች በጭፍን ጥላቻ የተሞሉ ናቸው። የሌሎችን መብት ለማክበር ቁርጠኝነት ያለው ሰው የሌሎችን በደል እንደራሱ አድርጎ የማየት ብቃት አለው። የቡርቃ ዝምታ በአሉታዊ መልኩ ይታይ ዘንድ ሚዛን ያልጠበቁ ሃያስያን ብዙ አስተዋፆ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ የምትሰራ አንቺነሽ መኮንን የምትባል አንዲት ጎበዝ ጋዜጠኛ አለች። አንድ እሁድ ተስያት ቤቴ ቁጭ ብዬ ሳለ አንቺነሽ በቲቪ ብቅ አለች። እናም ስለ ቡርቃ ወንዝ መተምረክ ጀመረች። ወንዙ መሬት ለመሬት ውስጥ ውስጡን እንደሚጓዝ በዚያ ወንዛዊ ድምፅዋ ስትተርክ ተመስጬ ቀረሁ። ለመፅሃፌ መቋጠሪያ አሳብም አገኘሁ። እና ቡርቃ ተወለደ። አንቺነሽ የቡርቃ ዝምታን አንብባዋለች። እንደወደደችው ነግራኛለች። አንቺነሽ አማራ መሆኗን እገምታለሁ። አማራና ኦሮሞን ለማጣላት የተፃፈ መፅሃፍ ነው ብላ ለምን ሳታስብ ቀረች? በርካታ አማራዎች የቡርቃ ዝምታን አድንቀው ደብዳቤ ፅፈውልኛል። ችግሩ መፅሃፉ አይደለም። ከመነሻው የቡርቃ ዝምታን በደፈናው ለመጥላት በቂ መነሻዎች ነበሩ። ገና ሲጀመር እኔ ወያኔ ነኝ። “ከወያኔ ምን ይጠበቃል? መከፋፈል ካልሆነ?” ተብሎ ይጀመራል። በመቀጠል ወላጆቼ ኤርትራውያን ናቸው። እኔን “ሻእቢያ” ብሎ በቀላሉ ለመፈረጅ የወቅቱ ፋሽን ነበር። አንዳንድ ሰዎች ቡርቃን በዚህ መነፅር አዩት። መፅሃፍን ያላነበቡትንም በከሏቸው። የቡርቃ ዝምታን የጠሉት በብዛት ያላነበቡት ናቸው። ሃያስያን የፃፉትን አነበቡና ደመደሙ። ርግጠኛ ነኝ በነፃ ህሊና የቡርቃ ዝምታን ማንበብ የቻለ ከቶውንም ሊጠላው አይችልም። መራራ አረፍተ ነገሮችን ማቀፉ ግልፅ ነው። አሉታዊ አባባሎችን እየነጠልን ካልመዘዘን ቡርቃ አማራና ኦሮሞን እንዳማያጋጭ መገንዘብ የሚቸግር አይመስለኝም። ያላነበባችሁ ታነቡትና የራሳችሁን ፍርድ ትሰጡ ዘንድ እጋብዛለሁ። ያነበባችሁት ደግሞ እስኪ በነፃ ህሊና ደግማችሁ አንብቡት? ለማጠቃለል የሃያስያን ሚዛኑን ያልጠበቀ ትችት ተደራስያን መፅሃፉን በተዛባ እይታ እንዲመለከቱት አስተዋፆ አድርጎአል ብዬ አምናለሁ። ሚዛን ያልጠበቁ ትችቶችን ችላ ብሎ መፅሃፉን በነፃ ህሊና የሚያነብ ሰው ለመፅሃፉ አሉታዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል ብዬ አላስብም… 

      ከሃገር እንደወጣህ ከሪፖርተር ጋዜጣ ለቀረበልህ የዜግነት ጥያቄ ምላሽ ስትሰጥ “እሱ ገና የሚጣራ ነው” ብለህ ነበር። ምን ለማለት ፈልገህ ነው? 

      በቃለመጠይቁ ወቅት የተናገርኩት ግልፅ ነበር። “ዜግነትህ ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠሁት መልስ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ! ከተፈጠረው የኤርትራ ችግር ጋር በተያያዘ ግን የዜግነት ጥያቄ መጠይቁ ግልፅ አይደለም። ዜግነት በደም? ዜግነት በትውልድ? ዜግነት በፍላጎት? ለሚሉት ጥያቄዎች የማያሻማ ምላሽ ባለመሰጠቱ ችግር ውስጥ ገብተናል” ብዬ ነበር መልስ የሰጠሁት። አማረ አረጋዊ ቆራርጦ በተዛባ ሁኔታ አተመው። አማረ ያንን ለምን እንዳደረገ አላውቅም። ይህን የመሰለ የጋዜጠኛነት ቁማር መቆመር በአገራችን የተለመደ ነው። ያልከውን በማጣመም ያላልከውን ማጮህ! በመሰረቱ ቃለመጠይቁን ለሪፖርተር ጋዜጣ አልነበረም የሰጠሁት። እለታዊ አዲስ ጋዜጣ ላይ ይታተም ዘንድ ነበር ሄለን መሃመድና መታሰቢያ ተሾመ ቃለመጠይቅ ያደረጉኝ።  

      ያሳተምካቸውን መፅሃፍ ያነበቡ አንዳንዶች የአፃፃፍ ስልትህንና በድፍረት የመፃፍ ብቃትህን በማየት አንተን ከበአሉ ግርማ ጋር ያነፃጽሩሃል። ለመሆኑ የአፃፃፍ ስልትህን ከማን ነው የወረስከው?   

      የበአሉ ግርማ መፃህፍት ወደ ስነፅሁፍ አለም እገባ ዘንድ አቢይ አስተዋፆ አድርገውልኛል። “በድፍረት መፃፍ” ያለጥርጥር ከበአሉ ግርማ ያገኘሁት ልምድ ነው። ከበአሉ ግርማ መስዋእትነት ብዙ ተምሬያለሁ። የበአሉ ግርማ መስዋእትነት ክቡርና ለቀሪው ትውልድም አርአያ ሆኖ አልፎአል። “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ለመፃፍ ብእር ሳነሳ መስዋእትነት መክፈል ሊኖር እንደሚችል ተገንዝቤያለሁ። ህይወትን እስከመክፈል የምጠየቅ ከሆነ ደግሞ ፍርሃትን “ደህና ሰንብት!” ማለት ተገቢ ነበር። በውጭ ሃገር የሚገኙ የመፅሃፌ አንባቢዎች ከበአሉ ግርማ እና ከብርሃኑ ዘርይሁን ጋር እያወዳደሩኝ ሲፅፉ ግን በውነቱ ተሳቅቄያለሁ። ትሁት ለመሆን ብዬ አይደለም። በብዙ መለኪያዎች ብርሃኑና በአሉ የተሟሉና የተዋጣላቸው ደራስያን ነበሩ። እኔ ራሴን ከነሱ ተርታ የማስቀመጥ ድፍረት የለኝም። ጀማሪ ነኝ። ወደፊት ጥሩ ጥሩ የስነፅሁፍ ስራዎችን ለመስራት አሳብ አለኝ። ወደ አፃጻፍ ስልት ስንመጣ ግን እኔ የጎርኪይ፤ የሌርሞንቶቭና የቼኮቭ ምርኮኛ ነኝ ማለት ይቻላል። በተለይ ጎርኪይ ሰብእናውም ሆነ የአፃጻፍ ስልቱ ያሳብደኛል። የጎርኪይን መፅሃፍ ደጋግሜ ባነባቸውም አልጠግባቸውም። ከትናንት ወዲያ የጎርኪይን ደብዳቤዎች የያዘ አንድ መፅሃፍ አገኘሁ። በጣም ደስ ብሎኛል። ማክሲም ጎርኪይ ግልፅነቱና ራሱን የሚያይበት መንገድ በእጅጉ ይማርከኛል። ጉራ የምትባል ነገር አያውቅም። ጉረኛ አለመሆን በጣም ከባድ ነገር ነው። “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ፅፌ ከጨረስኩ በሁዋላ ከሃምሳ በላይ ጉራ ያዘሉ አረፍተ ነገሮችን ቆርጬ ጥያለሁ። ራሴን ከፍ ከፍ የማድረግ ጠባይ የለብኝም። የለብኝም እያልክ ግን ራስህን የጉራ ኩሬ ውስጥ ስትንቦጫረቅ ታገኘዋለህ። በጎርኪይ ትረካዎች ላይ ግን አንዲት ጉራ አዘል አረፍተነገር ማግኘት እነማይቻል መማል ይቻላል። ውስጡን በረጋግዶ ማሳየት የሚችል ጀግና ነው። “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ያነበቡ ሰዎች፤ “ብቻችንን በሳቅ ፈነዳን” እያሉ ይፅፉልኛል። እኔ ኮሜድያን አይደለሁም። በማህበራዊ ህይወቴም ዝጋታም የሚባሉት አይነት ሰው ነኝ። አንባቢዎቼ በሳቅ የፈነዱት መራራ እውነቶች እየገጠሙዋቸው ነው። ጎርኪይ እኔንም እንዲሁ እንዳሳቀኝ ነው። በአንድ ቀልድ ሁለት ጊዜ የሚስቅ ጅል ሊባል ይችላል። ጎርኪይ ግን 50 ጊዜ ያስቅሃል። 

      “እነ መለስ እነ ተወልደ” በሚለው ትረካ ላይ በህወሃት ክፍፍል ዙሪያ ባደረግኸው ዳሰሳ ወደ መለስ ዜናዊ ቡድን አድልተሃል’ የሚሉ አንዳንድ ወገኖች አሉ። ያንተ ምላሽ ምንድነው? 

      ወደ መለስ ዜናዊ የማደላበት መነሻ ምክንያት የለም። የመለስን ሰብእና እንደ በረከት አፍረጥርጬ ያልጻፍኩት ቅርበት ስላልነበረን ነው። የሚታወቁትን ደግሞ አብረን ነው የምናውቃቸው። የምታውቁትን ሁሉ ብደርት ኖሮ ምናልባትም መካከሉ ላይ ስትደርሱ ሰልችቶአችሁ መፅሃፉን ትወረውሩት ነበር።

      “መለስ ብልህ መሪ ነው” የሚል አባባል ተጠቅሜያለሁ። የአብርሃ በላይ ድረገፅ ደግሞ ይቺን አረፍተ ነገር መዝዞ ሊጠቀምባት ሞከረ። አረፍተነገር እየቆራረጡ ያላልከውን አፍህ ላይ የሚያስቀምጡ ሰዎችን እየተከታተልክ ማስተባበል ከባድ ነው። በቅርቡ አውራምባ የሚባል ጋዜጣ ሳነብ ሰለሞን አበበ የተባለ ሰው የፃፈውን መጣጥፍ አገኘሁ። “የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ የማያሳምኑ ታሪኮች አሉበት” ሲል ፅፎአል። አያያዘና ቀጠለ፤ “…ለምሳሌ በዋቢ ሸበሌው ግብዣ ላይ እኔ እንደተገኘሁ ተደርጎ ተፅፎአል። እኔ ግን በግብዣው ላይ አልተገኘሁም” ሲል አስፍሮአል። ይህን ሳነብ ማንበቤን አቋርጬ ሳቅሁ። በጣም ሳቅሁ። እኔ ሰለሞን አበበ ብዬ የጠቀስኩት የኦሮሚያ ማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊውን ነበር። ይሄኛው ሰለሞን ወደ ግብዣው አልተጠራም ብቻ ሳይሆን ማን እንደሆነም አላውቀውም። የሆነው ሆኖ ይሄኛው ሰለሞን አበበ ግብዣው ላይ ሳይገኝ ተገኘ ተብሎ ቢፃፍስ እንዴት ነው የጋዜጠኛው ማስታወሻን ተአማኒነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥለው? ሰለሞን አበበ የቻለውን ያህል ዘባርቆአል። የአጤ ቴዎድሮስን ጀግንነት የሚያናንቅ ግጥም ሞገስ ሃብቱ ፅፎ እኔ እፍታ ላይ እንዳተምኩት ፅፎአል። ይህን መሰል ካለማወቅ የሚመነጩ ትችቶችን እየተከታተሉ ማስተባበል በጣም አድካሚ ነው። የሞገስን ግጥም ብታነቡት ቴዎድሮስን አይደለም የሚተቸው። ይህን ትውልድ ነው። ሰለሞን አበበ ቅኔው አላገባውም። አማርኛ መማር ያለበት ይመስለኛል። የጎንደር ገበሬ ቢሆን ግን ቅኔዋን ባጣጣማት ነበር፣

      “መለስ ዜናዊ ብልህ መሪ ነው” የሚለውም በመፅሃፌ የተጠቀሰው አባባል ሃገሪቱን ከመምራት አንጻር ሳይሆን የስልጣን መንበሩን ከማስጠበቅ አንፃር የተሰነዘረ አስተያየት ነው። 20 አመት ሃገሪቱ ላይ ጢቢ ጢቢ እየተጫወተ ስልጣኑን ያላስነካን መሪ አምባገነን ብቻ አትለውም። ኮሎኔል መንግስቱ የለየለት ጅል ነበር። ወያኔ አምቦ ደርሶ እሱ አባት ጦሮችን “ክተት!” ይል ነበር። አባት ጦሮች ግምባር እንደደረሱ ነበር ለወያኔ ደብዳቤ የፃፉት። ደብዳቤው ወደ ሬድዮ ጣቢያው ተልኮልን ስለነበር አንብቤዋለሁ። ምን ይላል መሰላችሁ?

      “…እኛ አባት ጦሮች በመጦሪያ እድሜያችን ተገድደን ለውጊያ መጥተናል። ለመዋጋቱ አቅሙም የለን። ደሞስ ከትግሬ ጋር ምን የሚያዋጋ ነገር አለን? እንደ ቀድሞአችን በሽምግልና ችግሩን መፍታቱ ይበጃል። የሆነው ሆኖ እኛ አባት ጦሮች ከሁለቱ መንታ ጋራዎች ጀርባ እንገኛለን። አትተኩሱብን፤ አንተኩስባችሁም”

      መንግስቱ ደሞ “አባት ጦሮች ሆይ! ባያቶቻችን ወኔ፤ ለዳርድንበራችሁ! ቅሌን ጨርቄን ሳትሉ!’ እያለ ይለፈልፋል።

      እና ኮሎኔሉ ወንበሩን እንኳ መጠበቅ ያልቻለ ጅል መሪ ነበር። የሚመራውን ህዝብ ስነልቦናም አላወቀም! መለስ ብልህ ነው። ብልጣብልጥ ልትሉትም ትችላላችሁ። ቃላት አያጣላንም። ቴዲ አፍሮን አለሃጢያቱ አሰረውና አጀንዳ አስለወጠ። የቴዲ እስር ቀዝቀዝ ሲል ደግሞ ብርቱካንን ደገማት! ህዝቡ ብርቱካን ቴዲ እያለ ሲጮህ እሱ ይስቃል። አይገድላቸውም። ህዝቡን ያውቀዋል። ጀግኖቹ ሲነኩበት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጡ መሆኑን ያውቃል። እና እራሱ ከሚፈጥረው ችግር የደስታ ዜና ይፈለስፋል።

      ቴዲ ከ6 ወር በሁዋላ ሊፈታ ነው!!!!

      ታላቅ ዜና ተገኘ!! ፈንጠዝያ!!

      መለስ ቤቱ ቁጭ ብሎ መነፅሩን ከፍ ከፍ እያደረገ ይስቃል። ደሞ ያስባል። ሌላ ዜና! ጤፍ አንድ ሺህ ብር ገባ። ሲሚንቶ ጠፋ። አጀንዳ ይለወጣል። ፖለቲካ ይቀርና ወሬው ሁሉ ሰለምግብ፤ ስለኑሮ ውድነት ይሆናል። ከዚያ መለስ መነፅሩን ከፍ ከፍ እያደረገ ስለ ርዳታ ስንዴ ዜና ይናገራል። እና መለስ ከችግሮች እንዴት እየሾለከ እንደሚያመልጥ የሚያውቅ ብልህ መሪ ነው። ይህን ብልህነቱን ለሃገር ፍቅር አውሎት ቢሆን ይህቺ አገር እውነትም በቀን ሶስቴ መብላት በጀመረች ነበር። በተቀረ ወደ መለስ ዜናዊ አድልተሃል የሚያሰኝ ነገር ያለ አይመስለኝም። ያለውን እውነት ነው የፃፍኩት። ይህን ስል ግን ስለመለስ ዜናዊ ከተፃፈው ሌላ የማውቀው የለም ማለቴ አይደለም። ለክፍል ሁለት ያሳደርኳቸው አንዳንድ ታሪኮች አሉ። አንባብያን ከሚያውቁት ጨመርመር ካደረጉልኝ ደግሞ ስለ አግአዚ ጦር አዛዥ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ለመጪው ትውልድ ትተን እናልፋለን። 

      ስለውስጣዊ ማንነታቸው ሳይቀር በደንብ ልትገልፃቸው የምትችላቸውን አንዳንድ ሰዎች እንደ ዘበት ጠቀስ አድርገህ አልፈሃቸዋል ይባላል። የሪፖርተሩ አማረ አረጋዊ አንዱ ነው። ከአማረ ጋር ሽኩቻ እንደነበራችሁ የሚገልፁም አሉ። ስለ አማረ ብዙ ጉድ መፃፍ ስትችል ምንም ያላልከው አማረ በተራው የመልስ ምት እንደሚሰጥህ በማወቅ ሰግተህ ነው ይባላል። በመፅሃፍህ ያነጣጠርክባቸው አብዛኞቹ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ናቸው ይባላል። በዚህ ላይ ምን ትላለህ? 

      አማረ ስለኔ እንዳይፅፍ የምሰጋው ነገር የለም። ማንም ቢሆን እኔ ስለራሴ ካልኩት በላይ ሊል እንደማይችል አውቃለሁ። በተቀረ አማረ አመለካከቱን በየሳምንቱ ጋዜጣ ላይ እየፃፈ ነው። “አማረ የወያኔ ተቃዋሚ መስሎ ውስጥ ውስጡን ለወያኔ ይሰራል” የሚለው ክስ ፀሃይ የጠገበ ወሬ ነው። ሌላ ምንድነው ስለአማረ ማለት የሚቻለው? ስለ ግል ህይወቱ አንዳንድ ጋዜጦች የፃፉትን አይቻለሁ። የረባ ነገር የለውም። ስለ አማረ ባህርይ እንድናገር ከተገደድኩ ግን ጥሩ ነገሮች ይበዛሉና እነሱን ነው የምናገረው።

      ….የበሰለ ሰው ነው። አንባቢ ነው። ሰዎችን የማሰራት ችሎታ አለው። ጥቂት አብረኸው ከቆየህ ደጋፊው ያደርግሃል። በጣም ተናጋሪ ነው። ሲናገር ለዛ አለው። አማረ የሚሳተፍበት ስብሰባ ላይ መገኘት ደስ ይላል። በቁምነገር መሃል ቀልዶች ስለሚጨምር አይሰለችም። ቀልድ በጣም ይችላል። ሰዎችን አያስቀይምም። የሚናገረውን ያውቃል። አለፍ ብለህ ከነካኸው ግን አለቀልህ። የቂመኛነት ጠባይ አለው። ጥርሱ ላይ ከነከሰህ ነፍስህ ካልወጣች አይለቅህም። (ሰሞኑን አብነት የተባለውን የአላሙዲ ሸሪክ እንዴት ነክሶ እንደያዘው አይታችሁዋል።) ፍርሃት አጠገቡም አትደርስ። የመሰለውን ይናገራል። ቁጣው አፍንጫው ላይ ናት። ክብሪት ነው። ነካ ስታደርገው ይቀጣጠላል። ከኔ ጋር የተጋጨነው ነክቼው ነው። ላጫውታችሁ፤

      የዛሬውን አያድርገውና አማረና ሼኩ ደህና ይቀራረቡ ነበር። በዚያው ሰሞንም አማረ የሼኩን የኢንቨስትመንት ስራዎች እያደናነቀ ይዘግብ ነበር። ከኢትዮ ኤርትራ ግጭት በፊት ስለ ኤርትራ አንድ በጎ ዜና ማተም የሪፖርተር ህግ እንደነበረው ሁሉ፤ አንድ ሰሞን ደግሞ የሪፖርተር ወሬ አላሙዲ አላሙዲ ሆኖ ነበር። አንድ ቀን ከስራ ባልደረባዬ ከመኩሪያ ጋር ቢራ እየቀመቀምን ሳለ “የአማረና የአላሙዲን ነገር እንዴት ታየዋለህ?” ስል ጠየቅሁት። “ሳይጠቀልለው አይቀርም” አለኝ። በዚያችው ቅፅበት አንድ ቀልድ ፈጠርኩ። በሚቀጥለው ጋዜጣችን ላይም ቀልዷን አተምኳት። እንዲህ ነበረች፤ 

                  የነበረ – አልታድ!

                  ያለ  –  አልመሽ!

                  የሚመጣ – አልሪፖርተር! 

      በነጋታው ምሳ ሰአት ላይ አማረ ደወለልኝ። ኮረንቲ ጨብጦ ነበር። እኔ በሆዴ እየሳቅሁ፤ ቀልዱን ያየሁት ከታተመ በሁዋላ መሆኑንና ማረሚያ እንደምናወጣ ብነግረውም ቂም ያዘብኝ። በርግጥ እንደ አላሙዲው “ምስለኔ” እንደ አብነት ነክሶ አልያዘኝም። እኔ የማዘጋጃት እፎይታ ጋዜጣ ሻእቢያን የሚጠቅሙ ስራዎችን እንደምትሰራ በገደምዳሜ ጥቂት ነካክቶኝ ሲያበቃ፤ ሁዋላ አዘነልኝ መሰለኝ ተወኝ። በድርቅና እየደወልኩ ሳናግረውም ካንገት በላይ ነበር የሚያዋራኝ። ከኮበለልኩ በሁዋላ አንድ ሁለት ጊዜ ደውዬለት ነበር። ያኔ ግን ቂሙን ረስቶ ነበር። ከምርጫ 97 በሁዋላ አንድ ጊዜ ደወልኩለትና “በሪፖርተር ጋዜጣ ሰዎች እያዘኑብህ ነው” ብዬ ነገርኩት። አልተዋጠለትም። አማረ እንደ ሰው አሪፍ ሰው ነው። በፖለቲካ አመለካከቱ ግን ድብቅ ስሜት ያለው ይመስለኛል። በምርጫም ሆነ በጉልበት ህወሃትን የሚነቀንቅ ሃይል ከመጣ፤ አማረ ጠመንጃውን አንስቶ ከወያኔ ጋር ምሽግ መያዙ የማይቀር ነው። ህወሃት ስልጣን ላይ እንዲቆይና አማረም ተቃዋሚ ሆኖ ወይም መስሎ መቀጠል የሚፈልግ ስለመሆኑ ማስረጃ መደርደር አያሻም። ለዚህ ምን ስም እንደምሰጠው ግን እቸገራለሁ። “ግማሽ ዴሞክራት – ግማሽ ነጋዴ” እንበለው ይሆን? 

      በተቀረ በጋዜጠኛው ማስታወሻ ስማቸው የተካተቱት ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ናቸው የሚለው አባባል ግልፅ አይደለም። ተፈራ ዋልዋና በረከት ከመከላከል አልፈው ማጥቃት የሚችሉ ናቸው። በህይወት የሌለው ክንፈ ብቻ ነው። ክንፈ ተናገራቸው ያልኳቸው ደግሞ ባብዛኛው ሌሎች የቀድሞ ባልደረቦቼ የሚያውቋቸው ናቸው። ክንፈም ቢሆን የጥቃት ኢላማ አይደለም። እስካሁን “ውሸት ተፅፎአል” ብሎ ያስተባበለም የለም። 

      ስለ ኢትዮሚዲያ ኤዲተር ስለ አብርሃ በላይ የፃፍከው ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖአል። አንዳንዶች እንዲያውም ኢትዮሚዲያ ባንተ ላይ ባወጣው ዘገባ በመበሳጨት በቂም በቀል የፃፍካቸው ከእውነት የራቁ ትችቶች ናቸው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳ አብርሃ በላይ የተገለፀውን ድርጊት ቢፈፅምም ጉዳዩን ባሁኑ ሰአት ማንሳቱ ተገቢ እንዳልሆነ ነው የሚገልፁት። በዚህ ላይ ምን ትላለህ? 

      አብርሃ በኔ ላይ የፈፀመው ድርጊት በጣም እንዳበሳጨኝ አልክድም። በየቀኑ ህይወት እንደዋዛ በምትቀጠፍበት ሃገር ነዋሪ ነኝ። ለመቶ ብር ተብሎ ሰው በጩቤ ይታረዳል። ማጅራት መቺዎች “ማን ስንት ብር አለው?” እያሉ እያጠኑ በየቤቱ ዘረፋ ይፈፅማሉ። ተኝተህ እያለ ቤትህ ገብተው ጩቤ አንገትህ ስር አስጠግተው “ዛሬ ከንግድህ የሰበሰብከውን ብር አምጣ?” ይሉሃል። ስንት ሃበሻ ታርዶ ሞቶአል መሰላችሁ። ገንዘብ እያዋጣን ሬሳ ወደ ዘመድ መላክ ከህይወታችን ጋር የተያያዘ ነው። ይህ እለታዊ ህይወታችን በሆነበት ሀገር አብርሃ በላይ 500,000 ብር ይዤ መኮብለሌን ፃፈ። እውነት ቢሆን የሙያ ግዴታውን ተወጣ ይባል ነበር። ውሸት ነው። ማረጋገጫ አልነበረውም። ለማጣራት አልሞከረም። በግንባሬ ትይዩ ጥይት ተኮሰብኝ። ዜናው የወጣ ሰሞን በዙሪያዬ የሚያንዣብቡ የታወቁ ማጅራት ማቺዎችን አየሁ። ስለኔም ያጠያይቁ ጀመር። ብር የሚለውን ዜና ዶላር አደርጓትና የዘረፍኩትን ገንዘብ ወደ 4 ሚልዮን አደረሱት። ወሬውን ሰምተው ለሚጠይቁኝም ማብራሪያ ለመሰጠት ሞከርኩ። መኖሪያ ቤቴንም ቀየርኩ። ብስጭቴ ከበረደልኝ በሁዋላ ለአብርሃ ፃፍኩለት። ቂም አልያዝኩም። አመት ቆይቼ ነው በወዳጅነት መንፈስ የፃፍኩለት። የሰጠኝን ምላሽ መፅሃፉ ላይ አይታችሁዋል። ምን ማድረግ ነበረብኝ? የመጀመሪያው ማስተባበል ነበር። አስተባበልኩ። ሁለተኛው ደግሞ አብርሃ በላይን ማስተማር ነበር። ማስተማር ስል ውሸት ቢዘራም እውነትን እንዲያጭድ ማድረግ። ስለ አብርሃ የተፃፉት ጥቂት እውነቶች ብቻ ናቸው። የወያኔ አባል በነበረ ጊዜ የፈፀማቸውን ሁሉንም አልፃፍኩም። ላስተምረው ስለፈለግሁ ጥቂት ቆንጥሬ ነው ያስታወስኩት። ‘ስለ አብርሃ በዚህ ጊዜ መግለፅ ተገቢ አይደለም’ ማለት ግን አልገባኝም። የፀረወያኔ ድረገፅ ኤዲተር ነው በሚል ይሆን? እንደሱ ከሆነ አዝናለሁ። አብርሃ ጸረወያኔ አቋም አለው ብዬ አላምንም። የአብርሃ አቋም ጥቅም ነው። ይህንንም ከጊዜ ጋር የምናየው ይሆናል። አሁንም ተመሳሳይና አስፀያፊ ተግባር መፈፀሙንም አላቆመም። የሱ ታሪክ የሌለበትን የጋዜጠኛው ማስታወሻ እትም ለህዝብ በትኖታል። የመፅሃፉን ኮፒ ባልጠበቅሁት ቀዳዳ ማግኘት መቻሉን አረጋግጬያለሁ። መፅሃፉ ማተሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት የልመና ደብዳቤ ፅፎልኝ ነበር። ስላተስማማሁ እኔን ለመጉዳትና የሱ ታሪክ ሳይነበብ እንዲቀር የተዛባውን መፅሃፍ በድረገፅ ለቀቀው። አሜሪካ ውስጥ ነዋሪ የሆነ፤ ስለዴሞክራሲና ስለሰብአዊ መብት የሚሰብክ ሰው ይህን ይፈፅማል። ይህን በመፈፅሙ አሁንም ቂም አልያዝኩበትም። በአብርሃ ድርጊት የተበሳጩ የመፅሃፌ አንባቢዎች ‘የባንክ ቁጥርህን ላክልን። ገንዘቡን እንላክልህ’ እያሉ ይፅፉልኛል። መፅሃፉን ድረገፅ ላይ በነፃ ያነበቡ ብዙዎች የታተመውን ኮፒ እንደሚገዙ ነግረውኛል። እና ማነው ቂመኛ?  

      የሃየሎምን ገዳይ አስመልክቶ በመፅሃፍህ ያሰፈርከው ታሪክ ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖአል። ከጀሚል ያሲን ጀርባ ያለው ሃይል ማሪዋና ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መገለፁ፤ በሻእቢያ ሚስጥራዊ ተልእኮ (ምናልባትም በወያኔ ቁንጮ ሰዎች ይሁንታ) በሃየሎም ላይ የተፈፀመውን የተንኮልና የግፍ ግድያ በደረቅ እውነታዎች ለማስተባበል ወይም ሰዎች በጉዳዩ ላይ የያዙትን ጥርጣሬና መረዳት ለማጥፋት ታስቦ የተፃፈ ነው ይላሉ። አንተ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ? 

      ሻእቢያም ሆነ የመለስ ቡድን ሃየሎምን ለመግደል የሚፈልጉበት በቂ ምክንያት የለም። ቢፈልጉ ኖሮ በሌላ መንገድም ቢሆን ሊያደርጉት በቻሉ ነበር። ጉዳዩ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የዋለ ነው። ሃየሎም ከታወቁትና ከተከበሩት የጦር ኮማንደሮች አንዱ ነበር። የሀየሎምን ስም ከሌሎቹ ነጥሎ ገናና ያደረገው ግን ደርግ ነበር። ኢህአዴግ ለሚገጥመው ጦርነት ሃየሎም ወሳኝ ሰው እንዳልሆነ ይታወቃል። ወታደራዊ ሳይንስን በማወቅ ረገድ ሃየሎም ከነ ጆቤ፤ ስዬና ፃድቃን ተርታ የምታስቀምጠው የጦር መሪ አልነበረም። ሃየሎም ከነሳሞራ ጋር በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነበር። በሃየሎም ደረጃ በርካታ አዋጊዎች አሉ። እነ ሰአረ፤ ወዲ መድህን፤ ታደሰ ወረደ፤ እነዚህ ከሃየሎም ጋር በማዋጋት ደረጃቸው ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ነበሩ። ውስጥ አዋቂ ያልሆነ ሰው የሚወራው እውነት ሊመስለው ይችላል። ውስጥ አዋቂ ግን የሃየሎም ግድያ ተራ አጋጣሚ ብቻ መሆኑን ያውቃል። ለነገሩ “የተቀነባበረ ግድያ ነው” ከተባለ እንዴት ነው ጀሚልን በዚህ ግድያ ማሳተፍ የሚቻለው? “ሃየሎምን ገድለህ ስታበቃ ቤትህ ሄደህ ተኛ! ከዚያም መጥተን የገደልክበትን ገንዘብ እንሰጥሃለን” ተብሎ ተነገረው? “ግደል” ከተባለስ “አምልጥ” ይባላል እንጂ ቤትህ ገብተህ ተኛ ተብሎ እንዴት ሊታዘዝ ይችላል? የሃየሎም አሟሟት ድራማዊ ሆኖ ሲወራ ስሰማ የህንድ ፊልም የማይ ነው የሚመስለኝ። 

      በመጽሃፍህ የደህንነቱ ቢሮ ሰነዶች ላንተ ክፍት እንደነበሩ ገልፀሃል። በሚስጥር የታጨቀ ቢሮ ቤተኛ ከነበርክ የሰጠኸን መረጃ በቂ ነው ትላለህ? ወይስ በቀጣይ ሌላ ተመሳሳይ ስራ እንጠብቅ? 

      የደህንነቱ ቢሮ ለኔ ክፍት እንደነበር የገለፅኩት የዳውድ ኢብሳን ገጠመኞች በተረክሁበት ምእራፍ ላይ ነው። ሰነዶቹ ለኔ ክፍት የነበሩት የዘመነ ደርግ ሰነዶች ብቻ ናቸው። ወያኔ የሚፈፅመውን የተመለከቱ ሰነዶች ለኔ ክፍት አልነበሩም፤ ሊሆኑም አይችሉም። በመፅሃፌ ያወጋሁዋችሁ ሁሉ በስራ አጋጣሚ ያወቅሁዋቸውን ብቻ ነው። ወደፊት ክፍል ሁለት “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ን የማሳተም አሳብ ግን አለኝ። የቀሩኝን ለወገኖቼ የማድረስ ፍላጎት አለኝ። 

      በእነ ክንፈ ገብረመድህን የሚመራው የደህንነት ቢሮ መረጃዎችን ከአንዳንድ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ሃይል መሪዎች እንደሚያገኝ በደፈናው ገልፀህ ነበር። መረጃ ለኢህአዴግ ከሚያቀብሉት ዋነኞቹን በስም ልትጠቅስልን ትችላለህ? 

      “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን የፃፍኩት የአፋኙን ስርአት አሰራር ለማሳየት እንጂ ግለሰቦችን ለማጋለጥ አይደለም። በእግረመንገድ ግን ግለሰቦች ሊጠቀሱ ይችላሉ። እገሌ ከወያኔ ጋር ይሰራ ነበር ብዬ ብናገር ጥቅም የለውም። ያ የጠቀስኩት ሰው በድርጊቱ ተፀፅቶ ድርጊቱን አቁሞ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ሌሎች ደግሞ ቀጥለዋል። እነብርቱካን ተሰብሰበው የሚነጋገሩት በማለዳው ጋዜጣ ታትሞ እየወጣ አይደለም እንዴ? ግድግዳቸውን በሙሉ መፈተሽ አለባቸው። አሊያም የማይታዩ ማይክሮፎን ይዘው የሚገቡ እንዳይኖሩ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መቆጣጠር አለባቸው። አንድን ግለሰብ ማጋለጥ ጥቅም የለውም። ነገ ሌላ ይተካል። እንዳልኩት የመፅሃፌ አላማ የአፋኙን ስርአት ውስጣዊ አሰራር ማሳየት ነው። ይህም ለታሪክ ይቀራል… 

      በጋዜጠኛው ማስታወሻ ከተካተቱት ምስጢሮች ከህግ ውጭ የሆኑና የተጠኑ የግድያ ወንጀሎች ይገኙበታል። እነዚህ ወንጀሎች በአለማቀፍ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው። ለመሆኑ ምን ያህሉ በመረጃ የተደገፉ ናቸው? እነዚህንስ መረጃዎች እንዴት ማግኘት ይቻላል? 

      እኔ የማውቀውን ፅፌያለሁ። ጥሬ መረጃዎችን ለታሪክም ሆነ ለፍርድ ቤት የማቅረቡ ተግባር የሌሎች ባለሙያዎች ይመስለኛል። ስማቸውን የጠቀስኳቸው አብዛኞቹ በህይወት አሉ። የተፃፈውን የማመን ወይም የመካድ ግዴታ አለባቸው። የደራራ አሟሟት ምላሽ ያሻዋል። ከአምስቱ የኮሚቴው አባላት አራቱ በህይወት አሉ። 

      በአሁኑ ሰአት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኢህአዴግ መንግስት የገጠሙህ ችግሮች አሉ?  

      በተዘዋዋሪ አንዳንድ ችግሮች እየገጠሙኝ ነው። የመበርገግ ጠባይ ግን የለኝም። ማንኛውንም የገጠመኝን ችግር ተቻኩዬ ከወያኔ ጋር ማያያዝ አልፈልግም። አንዳንድ የኤምባሲው አባላት እኔ ያለሁበትን ከተማ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ግን ሰምቻለሁ። መርጃዎችንም እያሰባሰቡ ነው። ይህን የግል ማስታወሻዬን ’የሻእቢያ እጅ አለበት’ ሊሉ ይችላሉ። ወይም ከኦነግና ከንግቦት 7 ጋር ሊያቆራኙኝ ይችላሉ። እየጠበቅሁ ነው። በመንገድ ላይ ስጓዝ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ ጓደኞቼ መክረውኛል። በተለይም ጋዜጠኞችን በድንጋይ መፈንከት ስለተጀመረ ድንጋይ የያዘ ካየሁ መንገድ የመቀየር ሃሳብ አለኝ። ለነገሩ እዚህ ደቡብ አፍሪቃ ድንጋይ እንደልብ አይገኝም። ድንጋይ ከማግኘት ሽጉጥ ማግኘት ይቀላል። 

      በወያኔ አገዛዝ ውስጥ በጋዜጠኛነት የሰራህባቸውን አመታት ወደ ሁዋላ መለስ ብለህ ስታስታውስ ምን ይሰማሃል? 

      ጥሩ ነበሩ። እውቀት ለማጠራቀምና የመፃፍ ችሎታዬን ለማዳበር ተጠቅሜበታለሁ። ወያኔን ከውስጥ ለማወቅ የቻልኩት ወያኔ ስለነበርኩ ነው። ግራና ቀኝ ለማየት ችያለሁ። በዝባዝንኬ የተሞሉ ረጃጅም ስብሰባዎችን ሳስታውስ ግን ያመኛል።

      አንድ ሌሊት በተለይ አይረሳኝም። ሰብሳቢው መዝሙር ነበር። ስብሰባው መዝሙር መኝታ ቤት ውስጥ ነበር የሚካሄደው። ተሰብሳቢዎቹ አራት የማስታወቂያ ሚኒስቴር መምሪያ ሃላፊዎች ነበርን። አሁን ሳስበው እስቃለሁ። በመሰረቱ ካልጠፋ ቢሮ ለምን የሰው መኝታ ቤት ውስጥ ገብተን ተሰበሰብን? ደግሞ ወንበር አልነበረም። በአልጋው ዙሪያ ነበር የተቀመጥነው። እኩለ ሌሊት ሲያልፍ አማረ መነጫነጭ ጀመረ፤

      “አሁን ይብቃንና ነገ እንቀጥል” ይላል።

      መዝሙር ወይ ፍንክች አለ፣

      በዚህ ጊዜ አማረ ትራስ ሳብ አደረገና ጋደም አለ። እኔን ባይኑ ጠቀስ አድርጎኝ፤ እንድከልለው ነገረኝ። ሰብሳቢያችን እንዳያይ ከለልኩት። እልቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ። መዝሙር አንድ ሰአት ያህል ከተናገረ በሁዋላ አማረ መተኛቱን አየ። ወዲያው ንግግሩን አቋረጠና አማረ ተቀሰቀሰ። ከንቅልፉ እንደነቃ መጀመሪያ የተናገረው፤

      “እስካሁን ተሰብስበናል እንዴ?” የሚል ነበር።

      ከዚያ አጀንዳው ተቀየረና በአማረ መተኛት ላይ መነጋገር ጀመርን። ስብሰባ እየተካሄደ መተኛት አግባብ አለመሆኑን ሁላችንም አስር አስር ደቂቃ ያህል ከተናገርን በሁዋላ አማረ አስተያየት ተጠየቀ። አማረ እያሾፈ የሰጠውን ምላሽ መቼም ቢሆን አልረሳውም፤

      “..ልክ ናችሁ” ሲል ጀመረ “…ተቀብዬዋለሁ። ምንም እንኳን እኩለሌሊት ያለፈ ቢሆንም፤ ምንም እንኳን ብንደክምም በስብሰባ መሃል መተኛት ግለኝነት ነው። ሌሎች ጓዶች ባትሪ እንደዋጠ ሰው ነቅተው ሲሰበሰቡ እኔ ለግል ጥቅሜ በማድላት መተኛቴ ስህተት መሆኑን ተቀብዬዋለሁ…”

      በአማረ አነጋገር መዝሙር ሲናደድ ባየውም እኔ ሳቄን መያዝ አልቻልኩም። ይህቺን ወግ ሰፋ አደርጋትና “ክፍል ሁለት” ላይ ይዤያት እመለሳለሁ። ለማንኛውም ስርአቱ ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም፤ ህዝቡን የጎዳነው ቢሆንም፤ ከቁሳዊ ፍላጎት አንፃር ከወያኔ ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ ለኔ ጥሩና ምቹ ነበር። በርግጥ እንዳሁኑ የህሊና እረፍት አልነበረኝም። ለስልጣን፤ ለውሸት ክብር፤ ለመኪና፤ ለምቾት ሰብእናህን መሸጥ! ያቅለሸልሻል! 

      በቀጣይ ህይወትህ ምን ለመስራት ወይም ምን ለመሆን ታቅዳለህ? 

      ማንበብና መፃፍ! ሌላ እቅድ የለኝም። በብዛት ለማንበብ አስባለሁ። ጥቂት ደግሞ እፅፋለሁ። የስነፅሁፍ ስራዎች ላይ ማተኩር ይመስለኛል። ግን ደግሞ የት መኖር አለብኝ? ወደ ቢሾፍቱ ከተመለስኩ ያስሩኛል። ስደት አንገቴ ጋር ደርሶብኛል። እያስብኩበት ነው። በቅርቡ የቅርብ ዘመዶቼ ዘንድ ሃዘን ለመድረስ አስመራ ሄጄ ነበር። ጆሮአቸው ቢቆረጥ አማርኛ የማይሰሙ ወጣቶች ስለቴዲ አፍሮ መታሰር በቁጭት ሲያወሩ ሰምቼ ማመን አቃተኝ። አበባየሆይን ደግሞ ይዘፍናሉ። ትርጉሙን ግን አያውቁትም። የወላጆቼ ሃገር ወደ ሆነው ወደ ገጠር ሄጄ ነበር። ድባርዋ አካባቢ። በመንገዱ ዳር የተተከሉት የትሩማንትሪ ዛፎች ደብረዘይትን ይመስላሉ። ክረምት ነበር። ከገበሬዎቹ ጋር ብዙ አወራሁ። ሌሊቱንም እዚያ አሳለፍኩ። በቋንቋ እንደልብ ባንግባባም ሁሉም ያው ነው። ወያኔ እስኪወድቅ ድባርዋ ገጠር ገብቼ “ክፍል ሁለት” የጋዜጠኛው ማስታወሻን እዚያ ሆኜ ብጨርስ ሳይሻለኝ አይቀርም። ደራሲ ነኝ! ስለ ኤርትራም ማወቅና መፃፍ አለብኝ! 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 26, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.