ቀዳማዊ እመቤቶቻችን!

በአቢይ አፍወርቅ |
አንዳንድ ሴቶች ብልህ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ያውቁበታል። በቅርቡ ወደ ሳውዲ አረቢያ የኮበለሉት የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት ቤን አሊ፤ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ያከማቹት ሀብት ቢታገድባቸውም ወደ ድህነት ግን አልወረዱም። እድሜ ላስተዋይዋ ሁለተኛ ሚስታቸው ለላይላ ትራቡልሲ። 1500 ኪሎ ግራም ወርቅ ታጥቀው ነበር የተሰደዱት። ገና ግርግሩ ሞቅ ሞቅ ሲል ነበር ፈጣኗ ላይላ የብሄራዊ ባንክ ገዥውን ወርቅ እንዲያዘጋጅ ያዘዙት። “እንደማልችል ስነግራቸው በባላቸው በኩል አሳዘዙኝ” ይላሉ ገዥው። ላይላ ሁሌም ባላቸውን የሚያግባቡበት ሀይል አላቸው። የኛይቱ እ’ቴ አዜብም ያውቁበታል። ባለቤታቸውን ባሻቸው ሰዓት ጥብቅና ለማቆም የሚያግባቡበት ሀይል አላቸው።

እንዲህ በቅርቡ እንኳ አምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ቀረ ስለተባለ አስር ሽህ ቶን ቡና አንገራጋሪው ሲበዛ መለስ ነበሩ አደባባይ የወጡት። የንግዱን ማህበረሰብ ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት “ያለፈው አልፏል፤ ለወደፊቱ ግን የሚዘርፍ ካለ እጁን ነው የምንቆርጠው ” ሲሉ ፎከሩ። አባባላቸው “የሌቦን ነገር ያነሳ…” ቢሆንብን፡ ‘የሌቦ አድራሻ ርቆ አይርቅም’ ስንል ከረምን። በዚህ ሳምንት ታዲያ “ኢትዮ ሪቪው” የተባለ ድረ ገጽ ‘አለኝ’ የሚለው የመረጃ ቡድኑ ባደረገው ማጣራት የሌቦን ማንነት በተጨባጭ ማረጋገጡን አስነበበን።… እ‘ቴ አዜብ ነቄ ናቸው።

ትዝ ይላችሁ ከሆነ ኑሯቸውን ቤተመንግስት ባደረጉበት የመጀመሪያዎቹ አመታት ላይ ላይናችን እንኳ እንጓጓቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ የሌሎች ሀገራት መሪዎች ከነባለቤቶቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የኛ መለስ ግን እንደወንደ ላጤ ለብቻቸው ነበር የሚያስተናግዷቸው። አዲስአቤ ታዲያ “እኒህ ሰውዬ ያካላቸውን ክፋይ ምንኛ ቢያፍሩባቸው ይሆን” እያለ ሲያብጠለጥል ከረመ።

እ‘ቴ አዜብ ግን ፈጣን ናቸው። ምቾቱን ሲላመዱት፣ የአሽቃባጩ ብዛት ሲሞቃቸው ድንገት ከእልፍኝ ወጡ። ለአይን ያልናፈቁንን በየመድረኩ ላይ በዙብን። አቦይ ስብሀትን ሳይቀር ገፍትረው የ’ትልልቆቹ’ ኩባንያዎች አድራጊ፣ ዘዋሪ ሆኑ። ፓርላማውም፣ የፓርቲያቸው ማእከላዊ ኮሚቴም… እንዲያው ሁሉም አይቅርብኝ አሉ። በተለይ ግን የሐበሻውንም ሆነ የፈረንጆቹን ቀልብ አብዝቶ የጠለፈው ሀብት ያለልክ የማጋበስ ዘመቻቸው ነበር። ባዶ እጃቸውን አራት ኪሎ የደረሱት ‘እመቤት’ በጥቂት አመታት ‘ንግድ’ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ህንጻዎች መስራታቸው ተከካ። ተቦካ። በውጭ ባንኮች ስላከማቹት ሀብት ብዙ ተባለ። ሌላው ቀርቶ የወያኔው ‘ጸሀፊ ትእዛዝ’ የነበረው ተስፋዬ ገብርአብ ሳይቀር በጄኔራል ባጫ ደበሌ ጉዳይ ፈጻሚነት በስፋት ስለተያዘው የእ’ቴ አዜብ የጫት ንግድ ‘አውቃለሁ’ ያለውን ተናዘዘ።

‘ቀዳማዊ እመቤታችን’ አራዳ ናቸው። አራዳ ደግሞ ዘመናይ ነው። ዘመናይ ደግሞ ይዘንጣል። እቴ አዜብም መዘነጥ ፈለጉ። እናም በአንድ የአውሮፓ የገበያ ውሎ ብቻ ለቅያሬ ልብስ 1.2 ሚሊየን ዩሮ መክፈላቸውን አንድ ታዋቂ የስፔን የዜና አውታር የዘገበው ባለፈው ሳምንት ነበረ። ምናለ! – ብሩ ከባንካቸው፤ ኃይሉ ከባላቸው አይደል?

“ከያንዳንዱ ታላቅ ወንድ ጀርባ አንዲት ታላቅ ሴት አለች” የሚል አባባል አለ። የሁሌ እውነት አይሆንም። ብዙ ጊዜ መስራቱን ግን በታሪክ አንብበናል። ሚስቶች በባሎቻቸው ወይንም ሴቶች በወንዶቻቸው ላይ ያላቸውን የተጽእኖ ልክ ለመጠቆም የተነገረ ይመስለኛል። በግልባጩ ግን ከእያንዳንዱ ደካማ ወንድ ጀርባ ስላለች ሴት የተጠቀሰ ነገር ካለ እኔ አላውቅም። አንዳንዴ ግን በከንቱ ሴቶች እየተቃኙ ስለተሰባበሩ ወንዶች በታሪክም በተረትም የተተረኩ ይኖራሉ። ሁሌም ቢሆን ለወንዶቹ ክብረትም ሆነ ክስረት ሴቶቹን ተጠያቂ ማድረጉ ብዙ የሚያራምደን አይመስለኝም።

እርግጥ ነው ‘እመቤት’ አዜብ ኃያል ናቸው። ባለቤታቸውን የማግባባት አቅም እንዳላቸውም ታዝበናል። የተጽእኗቸው ልክ ምን ያህል እንደሆነ ግን በበኩሌ የምገምትበት ሚዛን የለኝም። ለነገሩ የኢትዮጵያ ቀዳማዊ እመቤቶች በአብዛኛው ኃያል ነበሩ። ሀገራችንን በተለያዩ ወቅቶች በመሩ ወንዶቻቸው ላይ ጉልህ ሚና ነበራቸው። ታሪክ የመዘገባቸው ግን ከቶም ዛሬ እቴ አዜብን በምናይበት መልክ አይሆንም። እጅግ አብዛኞቹ ብልህ ብቻ ሳይሆኑ ጥንቁቅም ነበሩ። ንጹህ ባይሆኑ እንኳ በዝርፊያ አልገነኑም። የጥንካሬያቸውን ያህል ቅንነትም ነበራቸው። እስኪ ለንጽጽሩ ያህል ከቀድሞ መሪዎቻችን ጀርባ ከነበሩት እመቤቶች ጥቂቱን እናንሳቸው።

ስለኮለኔል መንግስቱ ባለቤት ስለወይዘሮ ውባንቺ ቢሻው ብዙም ማለት የሚቻል አይመስለኝም። “አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር..” ሲሉን የከረሙት ‘ቆራጡ’ መንጌ ከመቶ ሺህ በላይ ወታደሮችና ከሚሊዮን በላይ ጥይት እያላቸው ወደ ዚምቧቡዌ እርሻቸው እስከሸሹበት ጊዜ ድረስ የፈጸሙትን ግፍና ያወረዱትን መአት ላይጨርሱ የሚተርኩት ብዙ ናቸው። ስለ ባለቤታቸው ስለትየ ውባንች ግን አንዳች እንኳ ክፉ የሚናገር ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። ይልቅስ አለሁ አለሁ የማይሉ፣ ለአለባበሳቸው እንኳ ከሀገር ልብስ ውጭ የማይጨነቁ፣ በማጀቱም ሙያተኛ ሴት ወይዘሮ እንደነበሩ ጥቂት ምስክርነቶችን አንብቤያለሁ። ‘ባለቤታቸውን መግራት ነበረባቸው’ የሚል ካለ ከኮሎኔሉ የባህሪ መዝገብ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ‘እሱ ከገዛ ድምጹ በቀር ማንንም የማይሰማ፤ እንኳን ሌላ ሰው ፈጣሪውንም የማያውቅ…’ የሚለውን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆን አለበት። እትዬ ውባንች ድምጻቸውን አጥፍተው ለባላቸው ልቦና እንዲሰጣቸው በጾም በጸሎት ፈጣሪያቸውን ይለምኑ ከነበረ በራሳቸው መንገድ ብልህ ይሆኑ ይሆናል። ቢያንስ ግን የእ’ቴ አዜብን የጥጋብ ጎዳና ያለመምረጣቸው እንደጥንካሬ የሚቆጥርላቸው ይመስለኛል።

በ15ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የተወለደችው የሀድያ ልእልት ብልህ ሴት ነበረች። ፖለቲካ የጋብቻ ስልጣን ማረጋጊያ በነበረበት በዚያ ዘመን ልእልት ኢሌኒ ላልጋ ወራሽ በእደማሪያም ተድራለች። ባለቤቷ አስር አመት ሲነግስ ኢሌኒ አይነተኛ ተጽእኖ ማሳደር የቻለች ንግስት ሆና ነበር። ከእድገት በኋላ የተቀበለችውን የክርስትና ሀይማኖት አጥብቃ ከመያዟም በላይ ሁለት መንፈሳዊ መጸሐፍትም አሳትማለች። ቅንነቷና ድሆችን ለመርዳት ሳትታክት መጣሯ ተመስክሮላታል። ባለቤቷ ከሞተ በኋላ እንኳን በመጭዎቹ ሶስት አገዛዞች ውስጥ ኢሌኒ ጠንካራ ሚና እንደያዘች ነበር የቆየችው።

የልጅ ልጇ ልብነድንግል ገና በለጋ እድሜው ንጉስ ሲባል ኢሌኒ ነበረች በሞግዚትነት ሀገር ያስተዳደረችው። ከቤተክርስቲያን ግምባታ ባሻገር በግሪክና ባረብኛ የተጻፉ የሀየማኖት መጽሐፍትን ወደግእዝ ያስተረጎመች አንባቢና ጸሀፊም ነበረች።

በአካባቢው ሀገራት የቱርኮች ተንኳሽ እንቅስቃሴ ሲታይም “ነግ ወደኛ መምጣቱ አይቀርም” በሚል አምባሳደር ሰይማ ወደ ፖርቱጋል መላኳና የክርስቲያን ሀገር እርዳታ መሻቷ መጭውን አርቆ መመልከት መቻሏን ካሳዩ ተግባራቷ መሀል የሚጠቀሱ ናቸው።

እውነት ነው ንግስት እሌኒ ብልህ ነበረች። ድሃ ረጂ፣ ቤተክርስቲያን ገምቢ፣ ስነ ጽሁፍ አስፋፊና ድምበር አስከባሪ እንጂ እንደ’ቴ አዜብ ደሃ ቀሚ፣ አገር ከፋፋይ አልነበረችም። በጫትና በወርቅ ንግድም ስሟ አልተነሳም።

በግራኝ መሀመድ ዘመን የነበሩት ሁለት ባላጋራ እመቤቶችም ብልሆች ነበሩ። ሰብለ ወንጌልና ድልወንበሯ ይባላሉ። ወቅቱ አህመድ ኢብን ኢብራሂም በቅጽል ስሙ ‘ግራኝ’ ከትውልድ ቀዬው አዳል የተነሳ አመጽ የቀሰቀሰበት ዘመን ነበር። ባለቤቱ ድልወንበሯ ደግሞ ቀኝ እጁ ነበረች።

በሌላ በኩል ደግሞ የእስልምና ሀይማኖትን የመስፋፋት ዘመቻ ለመግታትና ክርስትናን ለማስከበር የሚታገለው ንጉሱ ልብነድንግል ነበር። ባለቤቱ ሰብለወንጌል በመንግስቱ ትልቅ ሚና የነበራት ሁነኛ አጋሩ እንደነበረች ታሪክ መዝግቧታል።

ግራኝ በቱርኮች እየታገዘ በርካታ የክርስቲያን ግዛቶችን ሲቆጣጠር ታዲያ ሰብለወንጌል ከባሏ ጎን ቆማ ዘመቻውን ለማስቆም ጠንክራ አዋግታለች። የመጀመሪያ ልጇ ሲገደል ሌላው ልጇ ሚናስ ደግሞ በምርኮ ተወስዷል። ባለቤቷም ሸሽቶ ደብረዳሞ ተራራ ላይ እስከ እልፈቱ ድረስ ቆይቷል።

ሰብለወንጌል ግን ብርቱ ነበረች። ሌላው ልጇን ገላውዲዬስን ለንግስ አብቅታ ከፖርቱጋሎች ጋር በመደራደር ውጊያውን በበላይነት ቀጥላ ለድል በቅታለች። ገበሬዎችን እየቀሰቀሰች፣ ቁስለኞችን እያከመች፣ ግራኝ እስኪገደልና ጦሩ እስኪበተን አይነተኛ ሚና የተጫወተች ሃያል እመቤት ነበረች።

ድልወንበሯ አላማዋን ለማሳካትና የባሏን ሞት ለመበቀል እስከተቻላት ተዋግታለች። የኋላ ኋላ ለማምለጥ ብትገደድም ልጇ ሙሐመድ ግን ተማርኮባት ነበር። ሁለቱ ብርቱ ሴቶች ባላጋራ ቢሆኑም የበሰለ ድርድር አድርገው ልጆቻቸውን ለመለዋወጥ ችለዋል። ሚናስን በመሐመድ። ሰብለወንጌልና ድልወንበሯ ጀግኖች ነበሩ። ሁለቱም ላመኑበት ጠንክረው ተዋግተዋል። ሁለቱም ልጆቻቸውን አጥተዋል። ሁለቱም እምነታቸውን በማስጠበቅ ተጋድሏቸው እንጂ የግል ሀብት በማግበስበስ ታሪካቸው አልተጠቀሰም። በየፊናቸው ተከታዮቻቸውን መንከባከባቸው እንጂ በገዛ ድሆቻቸው ስለመነገዳቸው አልታሙም። እነዚህ ሴቶች ብልህ እመቤቶች ነበሩ። እ’ቴ አዜብ ግን ብልጣብልጥ ናቸው።

የአጼ ቴዎድሮስ ተዋበች በተለይም ቁጡውን ባላቸውን የማረጋጋት ብቃታቸው፣ የታሪካችንን ቅኝት ለመቀየር አይነተኛ ሚና የነበራቸው እመቤት ሳያደርጋቸው አልቀረም። ታሪክ እንደሚለው መይሳው ቁጡ ነበሩ። ቁጣቸው ደግሞ ልክ ያለፈ ነበር። በዚህም ሲቆጡ ስህተት ይሰራሉ። ተዋቡ ካለች ግን የ’አንበሳዋን’ ሹሩባ እየፈታችና እየሾረበች፤ እየደባበሰችና እያጫወተች ታረጋጋቸዋለች። እድሜ ለተዋቡ በጥቂት አፍታ ወደልቦናቸው ይመለሳሉ።

ከተዋቡ ሞት በኋላ የቴዎድሮስ ጭካኔ እየከፋ መምጣቱን ታሪክ መዝጋቢዎች ያሳያሉ። ምናልባትም ተዋቡ ባትሞት ኖሮ እስረኛቸው የነበረውን የወሎዋን የወርቂትን ልጅ እንዲገደል ባላደረጉም ነበር። ያ ቢሆን ኖሮ ደግሞ የመቅደላው ጦርነት በመይሳው ሞት ላይደመደም ይችል ነበር። … ያም ሆነ ይህ ግን የተዋበች መኖር በቴዎድሮስ ስኬት ላይ የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና እንደነበረው መስማማት ይቻላል።

እቴጌ ጣይቱ ገናና ሴት ነበሩ። ከሚኒሊክ ዝና ጀርባ የጣይቱ ብጡል ቀኝ እጅነት ሁሌም ሲተረክ ይኖራል። አርቆ ተመልካችነታቸው፣ ወኔያቸውና ቁርጠኝነታቸው በባለቤታቸውም ሆነ በሹማምንቱ ዘንድ ታላቅ ሞገስና ተሰሚነት ያሰጣቸው እመቤት ናቸው። ወዳጅ ይለካው ወይ ጠላት ይስፈረው ውጤቱ ሁሌም አንድ ነው። እውነት ነው እቴጌ ጣይቱ ብልህና አስተዋይ ሴት ነበሩ።

እነኚህ ለአብነት ይብቁን እንጂ ሀገራችን በርካታ ብልህ ቀዳማዊ እመቤቶች ነበሯት። በእ’ቴ አዜብ ልክ ግን ብልጣብልጥ የነበሩ ጭራሽ እንደነበሩም አላውቅም። ብልጠት ደግሞ ብልህነት አይደለም። ቢያንስ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተሰጠው ትርጉም የዛሬን ብቻ ለሚመለከት ሰው ነው። ብልጣብልጥ ልሁን ለሚል። ብልህነት ግን የሩቅ ህልም አለው። ቅንነትም አያጣውም። በታሪክ ፊት የሚኖር መልካም ስምና ዝናም የተሰላበት ሊሆን ይችላል። እቴ አዜብን በሚጠብቃቸው የታሪክ ፍርድ ካሰብናቸው ብዙም የቀድሞ ቀዳማዮችን በረድፋቸው መጥራት የምንችል አይመስለኝም። በጥቂቱ ማመሳሰል ካለብን ግን ምናልባትም ባስረኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደነበረች በአፈ ታሪክ የምናውቃትን ዮዲት ጉዲትን ነው ልናነሳ የምንችለው። ዮዲት ቤተክርስቲያናትን እያሰሰች ስለማቃጠሏ በሰፊው ተተርኳል። እቴ አዜብ ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እያነደደችና ሰርቶ አዳሪ የንግድ ሰዎችን እያሰደደች መሆኑን እያየን ነው።

በየውጭ ሀገራቱ ሀብት እየከመሩ፣ በህንጻ ላይ ህንጻ የገነቡ አምባገነኖች የስደት ቀን ስትመጣ ‘እምጷ ቀሊጦ!’ እየተባሉ መሆኑን እ‘ቴ አዜብ ምን ያህል እንደ አስተዋለችው አላውቅም። ወይ ነቄ ነችና ‘ስትነግስ ብላ’ ማለቷ ይሆን?

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 10, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.