ቀደም ሲል ሽፍታ የነበሩት የጋምቤላ የልዩ ኃይል አዛዥ ተገደሉ

የሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ኃላፊም ቆስለዋል፤

የካቲት 12፣ 2004 ዓም |

የጋምቤላ ልዩ ኃይል አመራር መኮንንና አንድ የፖሊስ አባል መገደል እንዲሁም ንብረትነቱ የሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ የሆነው ሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ኩባንያ የፋይናንስ ኃላፊና ሾፌራቸው መቁሰላቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ጥበቃና ቁጥጥር መጠናከሩ ተሰማ።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ምንጮች ከስፍራው በላኩት መረጃ እንዳስታወቁት ግድያውን ያከናወኑት የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአኙዋክ ንጹሃን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት አስቆጥቷቸው የሸፈቱ አማጺያን እንደሆኑ ተገምቷል። የተገደሉት የልዩ ኃይል አዛዥ ኦባንግ አማው ኡቹዶ ቀደም ሲል ከነዚሁ አማጺያን ጋር ሸፍተው የነበሩና በኋላ ግን እጃቸውን በመስጠት የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ የተቀላቀሉ የአኙዋክ ብሔረሰብ አባል ናቸው።

ባለሶስት ኮከብ ማዕረግ ያላቸው ኦባንግ አማው፣ አብረዋቸው አምጸው የነበሩትን ጓዶቻቸውን በመክዳት በ1997 ዓም እጃቸውን ሰጥተው ሲገቡ ወዲያውኑ በህወሃት/ኢህአዴግ አማጺያኑን የማጥፋት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንደተናገሩት፣ በ2001ዓም አካባቢ ከጋምቤላ ከተማ ብዙም ርቀት በሌላት ቦዬ ላይ ከአማጺያኑ ጋር አንድ ቀን የፈጀ የተኩስ ልውውጥ ሲካሔድ ኦፐሬሽኑን የመሩት ኦባንግ አማው ነበሩ።

በወቅቱ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ከአማጺኑ ወገን የተሰለፉት ሰባት ተፋላሚዎች ሲሆኑ፣ ኦባንግ አማው የመሩት ጦር በርካታ ኃይል ያሰለፈና በከፍተኛ መሳሪያ እንዲሁም በፌዴራል ኃይል የሚደገፍ ነበር። በወቅቱ የነበሩ የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት በዕለቱ ሻምበል ኦቻን ዌሎ በመባል የሚታወቁት የአማጺያኑ መሪ ከቆሰሉ በኋላ የገደሉዋቸው ኦባንግ አማው ነበሩ። ሻምበል ከሞቱ በኋላ በምትካቸው የአማያኑን እንቅስቃሴ ይመሩ የነበሩትን ግርማ ኡጁሉ ኦቻንግ በመባል የሚታወቁትን በሌላ ኦፐሬሽን የገደሉት እኚሁ ኦባንግ አማው ነበሩ፡፡ በዚሁ ምክንያት አማጺያኑና በከተማ የሚኖሩ የአማጺያኑ ደጋፊዎች በቀድሞው ሽፍታና በአሁኑ የልዩ ኃይል መሪ ላይ ቂም ይዘው ቆይተዋል።

ኦባንግ አማው ህወሃት/ኢህአዴግን ሲቀላቀሉ ከተሰጣቸው ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ የሶስት ኮከብ ማዕረግ አግኝተዋል። በዚሁ የመኮንንነት ሥልጣናቸው የጋምቤላ ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን የአማጺያኑን ምንጭ ለማድረቅ እየሰሩ ሳለ፣ ባለፈው ሐሙስ የካቲት 8፤ 2004 ዓም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ክልሉ የሰጣቸውን ተሽከርካሪ በመያዝ ወደ ኦቦድ ኬላ ያመራሉ።

ለቀረጥ መሰብሰቢያ አዲስ ተከፈተ የተባለው ኬላ እንደደረሱ በስፍራው ከነበረው የኬላው ጠባቂ ፖሊስ ኦፒዮ ጎራ ጋር ይገናኛሉ። የዚህን ጊዜ በድንገት የታጠቁ አማጺያን ከጫካ በመውጣት ኦባንግና ኦፒዮን መሳሪያቸውን እንዲጥሉ ያዟቸዋል። ምንጮቻችን እንዳስረዱት መሣሪያቸውን እንዲጥሉ የታዘዙት ኦባንግ አማውና ባልደረባቸው ለመተኮስ ሙከራ ሲያደርጉ ሽፍቶቹ ቀደሟቸውና ተገደሉ።

“አስከሬናቸውን ከመንገድ በማንሳትና የፍተሻ ጣቢያውን በመቆጣጠር አማጺያኑ ወዲያውኑ ኬላ የማስተናበር ሥራ መስራት ጀመሩ” የሚሉት ምስክሮች በወቅቱ አማጺያኑ የአገዛዙን የመከላከያ ዩኒፎርም/መለያ ልብስ/ ለብሰው እንደነበር ይናገራሉ። በዚህ መሃልም ነበር የሳዑዲ ስታር ንብረት የሆነች ተሽከርካሪ ብቅ ያለችው። ኬላውን እየጠበቁ ያሉት አማጺያን ገመድ በመወጠር ተሽከርካሪዋን ለማስቆም ምልክት ይሰጣሉ። ተሽከርካሪዋ ፍጥነት በመቀነስ ለመቆም ስትሞክር አሽከርካሪው ደም ይመለከታል። ወዲያው ፍጥነት በመጨመር ኬላውን ጥሰው ያፈተልካሉ። አማጺያኑ አከታትለው በመተኮስ ሹፌሩንና አጠገባቸው የነበሩትን ሲያቆስሏቸው ተሽከርካሪዋ ትቆማለች።

ሰፊ የጋምቤላ ምድር ይዞ እያረሰ ያለው ሳዑዲ ስታር ከኬላው 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በወቅቱ ተሽከርካሪዋ ውስጥ የነበሩት የሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ኃላፊ ከባንክ ገንዘብ አውጥተው እንደነበር አማጺያኑ መረጃ ሳይኖራቸው እንደማይቀር ምንጮቻችን አስተያየታቸውን ሰጠተዋል። የተባለውን ገንዘብ ይዝረፉ አይዝረፉ ባይታወቅም አማጺያኑ ተሽከርካሪዋን ፈትሸው የቆሰሉትን የፋይናንስ ኃላፊና አሽከርካሪ ርዳታ ማግኘት እንዲችሉ መንገድ ዳር ለእይታ በሚያመች መልኩ እንዳስቀመጧቸው ከምንጮቻችን ገለፃ ለመረዳት ተችሏል። በወቅቱ አማጺያኑ “እኛ እናንተን አንፈልግም፡፡ ጉዳያችን መሬታችንን ከሚነጥቁና ህዝባችንን እየረገጡ ከሚያሰቃዩት ኃይሎች ጋር ብቻ ነው” በማለት መናገራቸውንም ጠቁመዋል።

“በመጨረሻም” አሉ የዜናው ባለቤቶች፣ “በመጨረሻም ኬላው ውስጥ የነበረውን መሳሪያና ጥይት፣ የተገደሉትን ግለሰቦች መሳሪያ ጨምረው በመሰብሰብ አማጺያኑ ተሰወሩ”፡፡ የቆሰሉት የሳዑዲ ስታር የፋይናንስ ኃላፊና አሽከርካሪያቸው ለህክምና ወደ ጋምቤላ ቢወሰዱም የፋይናንስ ኃላፊው በከፍተኛ ደረጃ ስለተጎዱ በነጋታው በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ እንደተላኩ ለማወቅ ተችሏል።

በድንገት የተፈጸመው ግድያ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረባቸው የሳዑዲ ስታር የማኔጅመንት አካላት ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል እንዲላክላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል። በሌላ በኩል በክልሉ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የታየው እንቅስቃሴ አስጨናቂ ሁኔታ ፈጥሯል። የህወሃት/ኢህአዴግን መሬት የመሸንሸን ፖሊሲን በመከተል ሳውዲ ስታር በጋምቤላ ክልል የአልዌሮን ወንዝ ተከትሎ ከ10ሺህ ሔክታር በላይ ለም መሬት መውሰዱ ይታወሳል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በዚሁ የጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ ሸንቶዋ ከተማ የመሳሪያ ግምጃ ቤት ተዘርፏ፤ ጎክ ወረዳ ፉኚዶ ከተማ የመከላከያ ማዘዣ ውስጥ ጸጉረ ልውጦች መታየታቸውን ተከትሎ ከመከላከያ ኃይል በተከፈተ የተኩስ እሩምታ በመኝታ ላይ የነበሩ ንጹሃን ተገድለዋል፡፡ በቅርቡ የምስጢር ደኅንነት ሹም ከፕሬዚዳንቱ ቤት ስብሰባ ጨርሰው መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ተገድለዋል፡፡ አሁን ደግሞ አቦቦ ወረዳ አቦድ ኬላ ላይ የጋምቤላ ልዩ ኃይል አዛዥ መኮንንና አንድ የፖሊስ አባል ሲሞቱ በሳዑዲ ስታር ሠራተኞች ላይ አደጋ መድረሱ ያሳሰባቸው ሹመኞች ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ ተስኗቸዋል።

የጋራ ንቅናቄያችና የመረጃ ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞት መኖሪያ ቤታቸው ማደር አቁመዋል፤ ባለሥልጣናትም መታጀብ ጀምረዋል። በክልሉ ውጥረት ከወረዳ ወደ ወረዳ እየተስፋፋ ነው። የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናትን፣ ኢንቨስተሮችንና የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ ስላስጨነቀው ተደጋጋሚ ጥቃት እስካሁን በግልጽ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አልተገኘም። አገዛዙም ሆነ የክልሉ አመራሮች እስካሁን ለተካሄዱት ጥቃቶች ምንም ዓይነት ማስተባበያ አልሰጡም።

በጋምቤላ ሕዝባቸውን በመርገጥ አገዛዙን እያገለገሉ የሚገኙ “ሆዳም” በሚል ስያሜ  ስለሚጠሩ የኦባንግ አማው መገደል እንደተሰማ “አንድ ሆዳም ሞተ” በሚል ነዋሪዎች ስሜታቸውን ሲገልጹ እንደነበር ምንጮቻችን የሰበሰቡትን አስተያየቶች ጠቅሰው ተናግረዋል።     

 

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 21, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.