ሸራተን አዲስ በሐራጅ አደጋ ላይ

sheratorn_addis.jpgሪፖርተር 16 November 2008 — ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ወስዶ ባለመመለሱ በዋስትና በተያዘው ንብረት ላይ የሐራጅ ጨረታ ለማውጣት ባንኩ መቸገሩን፣ ችግሩን ለመፍታት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የባንኩ አንድ የሥራ ኀላፊ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳረጋገጡት ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ብድሩን ሲወስድ በዋስትና ያስያዘው ሸራተን ሆቴልን ነው፡፡ ሚድሮክ ከባንኩ ወስዶ ያልመለሰው ብድር እስከ ሰኔ 30 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ያረጋገጠው ምንጫችን ስለብድሩ አከፋፈል ጉዳይ በተደጋጋሚ ባንኩ ለሚድሮክ ኮንስትራክሽን ደብዳቤ ቢፅፍም አንድም ጊዜ ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡

ለሌሎች ባለሀብቶች በማይደረግ መልኩ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ብድሩን እንዲከፍል የማስታመም ያህል ባንኩ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢፅፍም ብድሩ የማይመለስበት ምክንያት እንኳን ተጠቅሶ መልስ ማግኘት አለመቻሉ ትልቁ ችግር መሆኑን ምንጫችን ገልፀዋል፡፡

አንድ ተበዳሪ ብድሩን መመለስ ካልቻለ በሕጉ መሠረት የ30 ቀናት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ማስከፈል ካልሆነም በዋስትና ያስያዘውን ንብረት በሐራጅ ለጨረታ እንደሚቀርብ ኀላፊው ጠቁመው በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ጉዳይ ባንኩ በዋስትና የያዘውን ሸራተን ሆቴል ላይ የሐራጅ ጨረታ አውጥቶ መሸጥ የነበረበት ቢሆንም ይህንን ለመወሰን ድፍረት ማጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ አንድ ውሣኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚድሮክ ኮንስትራክሽን 107 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የኪራይና የብረት ዋጋ ዕዳ አለመክፈሉን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከመገናኛ እስከ ሐያት የወሰደውን የ190 ሚሊዮን ብር የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በወቅቱ ማጠናቀቅ ባመቻሉ ፕሮጀክቱን መነጠቁን በተለያየ ጊዜ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሸራተን አዲስ ሆቴል ከሚድሮክ ኮንስትራክሽን በእጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር መውሰዱም የሚታወስ ነው፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 17, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.