ሶስት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ህዝባዊ ስብሰባ በቬጋስ

በቬጋስ የኢትዮጵያ ራእይ የጠራውና ሶስት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ህዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ: ምሁራን ተደራጅተው የነጻነት ትግሉን እንዲያግዙ ተጠይቋል

(ሀብታሙ አሰፋ ሪፖርታዥ- ለኢትዮ ሚዲያ ፎረም ከቬጋስ)

በቬጋስ የኢትዮጵያ ራእይ የተሰኘው ማህበር በከተማዋ ባለፈው ረቡእ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሶስት የኢኮኖሚ ባለሙአዎች የተገኙበት ህዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን በእለቱም ከ6 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በአቶ መለስ አስተዳደር ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም የተጨፈጨፈፉ ንፁሃንን ፊልም በማሳየትና የህሊና ፀሎት በማድረግ ተዘክረዋል።

ዶ/ር ሙሉጌታ ከሳሁን በከተማው የኢትዮጵያ ራእይ ማህበር ሰብሳቢ ስብሰባውን በንግግር እንደከፈቱ፣ ሰማእታቱን በአንድ ደቂቃ ፀሎት በማሰብ እንዲጀመር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ የድህነት ምሳሌ ሆና ልጆቿም በየአቅጣጫው በአስቸጋሪ ሁኔታ እየተሰደዱ፣ በመዲናይቱ አዲስ አበበ ጭምር ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን ከቆሻሻ እየለቀሙ የሚመገቡትንና፤ ህፃናት በምግብ እጦት በት/ቤት የወደቁበትን ሁኔታ የአቶ መለስ አስተዳደር አገኘሁ ካለው ከፍተኛ ኢኮኖሚ እድገት ጋር በማነፃፀር አጣቅሰዋል።

<በዛሬዋ ኢትዮጵያም የአስተዳደሩ ባለስልጣናት እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በሙስናና ብልሹ አሰራር ከሀብት ጣራ የደረሱበትና፤ በአንፃሩ የብዙሃኑ ህዝብ ሕይወት ቀምሶ ለማደር የተቸገረበት ነው>> ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ በሰሜን አፍሪካ የተነሱትም ህዝባዊ አመፆች መሰረታቸው ተመሳሳይ እንደሆነ አስታውሰው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ የኢትዮጵያ ህዝብም ማመፁ እንደማይቀር ጠቁመው፤ አቶ መለስ የዚህ ህዝባዊ አብዮት ሰደድ እሳት እንደሚበላቸው ስላወቁ፤ አቅጣጫ ለማስቀየር ድንገት የአባይ ግድብ የሚል አጀንዳ ይዘው መነሳታቸውን ገልፀዋል።

<<የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ የሰጠ፣ የደቡብና ምእራብ ሰፋፊ ለም መሬት የረጅም ጊዜ ጠላቶችና ለህዝረባችን ደንታ ለሌላቸው አረቦች፣ ፓኪስታኖች፣ በኪራይ የሰጠ መንግስት፤ ስለ አባይ መገደብ ደንታ አለው?>> ሲሉ ጠይቀው ግድቡን የትራንስፎርሜሽን እቅድና የመሬት ቅርምቱን የዋጋ ግሽበቱን በተመለከተ ምሁራኑ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጋብዘዋል።

ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ከ30 አመት በላይ በአለም ባንክ በኢኮኒሚ አማካሪነት በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር የሰሩ፤ በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ግልፅ ባልሆነ ውል ሳቢያ፤ መንግስት የአገሪቱን ጥቅም በማይጠቅም መልኩ መሬትን በርካሽ በሆነ መንገድ ለውጭ ባለሀብቶች እያከፋፈለ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶችን መሰረት አድርገው ጠቅሰዋል።

የውጭ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያ ለወሰዱት 311 ሺህ ሔክታር መሬት በርካሽ በ24 ሚሊዮን ዶላር ሲወስዱ ከመሬቱ የሚያመርቱትን ከአገር እያወጡ፤ አገሪቱ በተቃራኒው በየአመቱ ለምግብ ግዥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን ሰፋፊ እርሻዎችን የማምረት በቂ ልምድ አላቸው ያሉት ዶ/ር አክሎግ ከ1970-1973 ዓመተ ምህረት በሴቲቲ ሁመራ፣ በአዋሽ አርባና በአርሲ በሰፋፊ እርሻዎች ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡትን አመርቂ ውጤት አስታውሰው፤ ዛሬም ያ የማይደረግበት ምክንያት እንደሌለ አብራርተዋል። ከመሬት ኪራዩ የሚገኘው ገንዘብ የውጭ ምንዛሬ አምጥቶ ድህነትን አለመቅረፉን፣ የመሮት ቅርምቱ ገበሬዎችን ማፈናቀሉን፣ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ አጥኚዎች ጭምር መመስከራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አክሎግ፤ መሬትን በርካሽ የማቀራመቱ እርምጃ የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም እንደሚጎዳ በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፈው ለስብሰባው ተሳታፊዎች አቅርበዋል።

የአገሪቱን መሬት በርካሽ ለባእዳን ማከፋፈሉ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ የሚያርሱት መሬት የሌላቸው አርሶ አደሮች ሲኖሩ፤ በእርሻ ላይ ያሉት በአማካይ ከግማሽ ሔክታር በታች ያላቸው ሲሆን በአንዳንድ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ዜሮ ነጥብ ሶስት ሔክታር ብቻ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በሰሊጥ ምርት ገበያ አቅራቢነት ከአለም በ6ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን ያስታወሱት ዶ/ር አክሎግ፤ አሁን መሬቷን በርካሽ ለውጭ ባለሀብቶች ሰጥታ ይህንን የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ምርቷን ጭምር እንዲያመርቱ መፍቀድዋ፤ ራሱዋን እየጎዳች መሆኑን በግልፅ ያሳያል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች አሁን የውጭ ባለሀብቶች የተሰማሩበትን የእርሻ ስራ መስራት እንደሚችሉ የጠቀሱት ዶ/ር አክሎግ፤ ለዚህ ግን የተመቻቸ ሁኔታ ሊኖር ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

ከመሬት ሽያጭ የሚገኘውም የውጭ ምንዛሬ ከመሬታቸው ለተፈናቀሉ ገበሬዎች ያልዋለ፣ አገሪቱ መሬቷን አሳልፋ በርካሽ በመስጠቷ አንዳችም የኢኮኖሚ ጥቅም ያላገኘችበትና ድርድሩም በምስጢር የተደረገ በመሆኑ ጥቅሙ ለውጮቹ ባለሀብቶች ፣ለመንግስት ባለስልጣናቱና በዙሪያቸው በድርድሩ ዙሪያ ላሉ የጥቅም ተጋሪዎች መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላው የዕለቱ ተናጋሪ በኤሊኖይስ ግዛት ሀርፐር ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው የአባይን ግድብና የትራንስፎርሜሽን እቅድን አስመልክቶ በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ አባይን አይገደብ የሚል ሳይሆን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በአባይ ላይ መገንባት ያለበት አንድ ግዙፍ ግድብ ሳይሆን ከዚህ በፊት ለአገሪቱ ጠቀሜታ ያላቸውን በአባይ ላይ ሊሰሩ የሚችሉ አራት አነስተኛ ግድቦችን መገንባት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአቶ መለስ አስተዳደር በትራንስፎርሜሽን እቅዱ ያልነበረ ሌላው ቀርቶ በሁዋላ በሰጠውም ማስተባበያ ፕሮጀክት ኤክስ ተብሎ በአምስት አመቱ እቅድ ያልተጠቀሰ፤ ድንገት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳውን ተቃውሞ አቅጣጫ ለማስቀየር ታላቅ ግድብ በአባይ ላይ እንሰራለን ማለቱን ያስታወሱት ዶ/ር ጌታቸው እነ አቶ መለስ አባይ ሊገደብ ነው ሲባል የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ጊዜ ምኞቱ ስለሆነ ይከተለናል በሚል ያደረጉት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ታላላቅ ግድቦች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እያመዘነ መምጣቱን የጠቀሱት ዶ/ር ጌታቸው፤ ታላቅ ግድብ ብንሰራ በአጭር ጊዜ በደለል ስለሚሞላ የታሰበውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለበዘላቂነት ሊያመጣ የማይችል በመሆኑ፤ ደለሉንም ለመጥረግ ኢትዮጵያ አቅም የላትም። በቀላሉ ደለላቸውን መጥረግ የሚቻሉባቸውን ጥናታቸው ከዚህ ቀደም ያለቀ በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚሰሩ አራት ግድቦች እያሉ፤ አንድ ትልቁ ግድብ ካልተሰራ ብሎ መነሳት ለአገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አለማሰብ መሆኑን ገልፀዋል።

ቻይና 23 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ለ19 አመት የገነባችው ግድብ ችግር ደርሶበት የአገሪቱ መንግስት ሲያስተባብል ቆይቶ፤ የግድቡ ችግር ለመሬት መንቀጥቀጥ ጭምር ምክኒያት መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የሀይል ምንጭ ያስፈልጋታል ያሉት ዶ/ር ጌታቸው በቀላል ወጭና ውጤታማ ሊሆኑ ከሚችሉት ግድቦች በተጨማሪ፤ በዝናብ ውሃ ላይ ብቻ ከተመሰረተ ግድብ ውጭ በነፋስና በፀሀይም መብራት ለማግኘት ስለሚቻል፤ ለዘላቂ መፍትሄ ያንንም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ለአባይ ግድብ ተብሎ የሚሸጠውም ቦንድ አስተማማኝ አለመሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ጌታቸው፤ የኮርፖሬት ቦንድ ዋስትና የሌለውና ድርጅቱ ሲያተርፍ ትርፍ የሚገኝበት ሲሆን፤ የመንግስት ኩባንያ ለሆነው ድርጅት የመንግስት ቦንድ ማድረግ አለመፈለጋቸውን በመጥቀስ አስተማማኝ አለመሆኑን ጠቁመዋል።የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተባለውም የተስፋ ሰነድ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል መሆኑን አመልክተው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ጭምር በዕለቱ በወጣ መረጃ ዕቅዱ የማይሰራ መሆኑን መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

ዶ/ር ሰኢድ ሀሰን በርቀት የስካይፒ መገናኛ ለአዳራሹ እንደገለፁት፤ ምሁራን ለአገር ይበጃል የሚሉትን ሀሳብ በምስጢር እየተገናኙ መወያየት እንዳለባቸው አመልክተው፤ በመሰረታዊ ሃሳብ የአባይን መገደብ የሚደግፉ ቢሆንም፤ ዶ/ር ጌታቸው ያነሱዋቸው ቁልፍ ጉዳዮች ግን ትኩርት ሊያገኙ እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል
ከስብሰባው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ የተሰጠ ሲሆን፤ አንድ አስተያየት ሰጭ በእለቱ በስብሰባው ላይ የምትገኙት ምሁራን ለአገራቸው ጉዳይ ተሳትፎ የሌላቸው እና አንዳንዶችም ትግሉን የሚጎነትሉ ምሁራን ያንን መሰሉን ወያኔን የሚጠቅም ድርጊት አቁመው፤ ወደ አንድ በመምጣት ትግሉን ሊደግፉ እንዲችሉ የማስተባበር ስራ እንድትሰሩ ሲል ሀሳቡ በተሳታፊዎቹም ድጋፍ አግኝቷል።

በቬጋስ ባለፈው አፕሪል 13 አቶ አርከበ ዕቁባይ በተገኙበት የአባይ ግድብ ቅስቀሳ ላይ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ስርዓቱ ከአባይ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን እንዲያቆምና አቶ መለስም በአገዛዛቸው የሚፈጽሙትን ወንጀልን በቃ በማለት በስብሰባው አዳራሽና ከውጭም በሰላማዊ ሰልፍ መቃወማቸው አይዘነጋም።በስብሰባው ላይ በስርዓቱ በግፍ ለተገደሉ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ ተጠይቆ በመከልከሉ አርከበ ሌባ አርከበ ገዳይ መለስ ወንጀለኛ ነው መለስ ስልጣን ለቆ ይሒድ የሚሉት የተቃውሞ መፈክሮች በጊዜው ተደምጠዋል።በወቅቱ አርከበ ዕቁባይ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲሳደቡ ተስተውለው ነበር።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 13, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.