ስደት ያጠወለገው ልጅነት…. ወደ መርገፍ!!

(በግሩም ተ/ሀይማኖት)

ቃላት ቃላትን ረድተው ሀይል ሆነው ስሜትን መግለጽ እንደሚያቅታቸው ያየሁት አሁን ነው። ዛሬ.. ዛሬ አይኖቼ ደጋግመው የሚያለቅሱበት በስደት የሚያጋጥሙኝ ሰቆቃዎች በርካታ ናቸው። ስደት ወጥተን በሰው ሀገር በበሽታ ማቀው፣ አልጋ ይዘው፣ የሚበሉት አጥተው፣ መድሀኒት አጥተው ማየት ምን አይነት ስሜት ይጭራል? ያሳዝናል የሚለው የሚገልጸው ስሜት አይደለም። በተለይ ህጻናት ላይ የሚደርሱ ሰቆቃዎች ከምንም በላይ ያሳዝኑኛል። በኤች አይ ቪ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት የሚደርስባቸው እንግልት፣ በቫይረሱ ተለክፈው የሚሰቃዩ ህጻናት… ብቻ ሁሉ ነገር ውስጥ ይበጠብጣል። ጤና አይሰጥም። አንድ ታሪክ ላውጋዎት? የእንባ ከረጢቶን ቋጠር ያድርጉት እንዳይዘረገፍ። እባክዎትን ይህ ታሪክ ልብወለድ አይደለም።

ህጻን ሀያት መስከረም 12/2000 ዓ.ም በእቅፍ ነው ስደት የወጣችው። ገና የአንድ አመት ልጅ እያለች ነው በባህር ወደ የመን ከመጡት እናቷ እና አባቷ ጋር አብራ የመጣችው። ድንገት ማንም ሰው በዚህ እድሜው ከሚያየው ስቃይ በላይ ስቃይን አጣጥማለች። እናቷ በሞት የተለየቻት ይህች ህጻን እንዳዛሬው 5 ዓመት ሞልቷት መሳቅ መጫወት ሳትጀምር፣ ርሀብ ጥሟን መናገር ሳትችል፣ ህመሜ እዚህ ጋር ነው በማትልበት ወቅት የ 11 ወር ልጅ ሆና ነው ። አባቷ የወንድ ጡቱን እያጠባት፣ ውሀ ጥም ሲያስለቅሳት ምራቁን እየሰጣት፣ የወንድ ጡት ለጊዜው ለቅሶ ማስታገሻ እንጂ ምን ጠብ የሚለው ይኖራል? ጡቱ ጠብ የሚለው ሲጠፋ ምላሱን እያጠባት ያን በረሃ ይዟት አለፈ።

መንግስቱ ለገሰ ዛሬ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ስሙን ቀይሮ ካሊድ ተብሎ ነው የመን ስደተኛ የሆነው። የስም ለውጡ ታሪኩ ብዙ ነው። ወደ የመን ሲመጡ የባህር ጉዞውን…አጠናቀው ልክ የየመንን መሬት ሊረግጡ ሲሉ ነው እናቷ የሞተችው። በህገ-ወጥ መንገድ በባህር የሚያጓጉዙትን ሶማሊያዊያን ለመያዝ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በጥይት ተመታ ባህሩ ዳር ህይወቷ ያለፈ ሚስቱን አንብቶ ቀበረ። ሀዘን ያቆራመደው ካሊድ ልጁን ማትረፍ ነበረበትና ከላይ እንደገለጽኩት ጡቱን እያጠባ..አደን የሚባለው የየመን ሁለተኛ ከተማ ድረስ ለመድረስ በመሀል በመሀል ያሉት ትናንሽ ከተማዎች ውስጥ እየለመነ ውሀ፣ ወተት.. እያቀመሳት ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት ተጓዘ።

ታሪኩን ሲያወጋኝ አይኖቹ በእንባ ርሰው አሻግሮ ግርግዳው ላይ የትውስታ ስክሪኑን የዘረጋ መስሎ ቡዝዝ..ካለ በሁዋላ መላልሶ ጠረጴዛውን በቡጢ እየደለቀ ነበር። እንኳን ሲነግረኝ አሁን የትውስታ መነጽሬን ዘርግቼ ስከትብ ደም ባይሆንም እያነባሁ ነው። ስደት የወለደው ሰቆቃ የቀጣቸው ወገኖቼን እያየሁ፣ ታሪኩን እየሰማሁ እስኪበቃኝ ሀዘንን አጣጥሜያለሁ። አንብቻለሁ። መቼ ነው ማብቂያው? መቼ ነው ፈጣሪ የሚሰማን?…ሁሌም መሪር እንባዬን ሳፈስ የማነሳው ጥያቄ ነው። በባህር ስመጣ 3 ጀልባ ተከታትለን ነው የተነሳነው። 90 አካባቢ ወገኖቻችንን የጫነች ጀልባ ስትሰምጥ የነፍስ አድን መንፈራገጣቸውን አይቼ ለ14 ቀን እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር እንደ ማበድ አድርጎኝ ነበር። በወገኖቼ እርብርብ ነው የተረፍኩት። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከአለም ህዝብ የተለየ ንሰሀ የማይሽረው ጥፋታችን ምንድን ነው? መቼ ነው?….መቼ ነው? ማብቂያው? በቃ! የሚለን?…
.
አደን የሚባለው ከተማ እንደገቡም ቢሆን በUNHCR የተወሰደው እርምጃ አልቀረስ የሚባለው የኦሮሞ ተወላጆች እና ሶማሊያዊያን የሚሰቃዩበት ካምፕ ግቡ ተባሉ። ከባህር ሲወርዱ ጀምሮ በበሽታ የተለከፈችው ህጻን ለወራት ህክምናውን አገም ጠቀም በሆነ ሁኔታ ተከታተለች። አልዳነችም። ለጊዜው ቢሻላትም በሰዓቱ ወደ ውስጧ የገባው የባህር ውሃ ለተለያየ በሸታ ዳረጋት። በህመምም ለ4 ዓመታት ታግላ ተጓዘች። ዛሬ ግን ችላ መጓዝ አልቻለችም። አሁኑ ሰዓት ሆስፒታል በሞትና ህይወት መካከል ያለች የ5 ዓመት ልጅ ነች።

አይኗ አያይም ጆሮዋ አይሰማም። በምግብ እጥረት ከሚመጣ በሽታ በተጨማሪ የአእምሮ ችግር በሚያስከስት በሽታ አልጋ ላይ ውላለች። ሰውነቷ በጣም ከመጎዳቱ በላይ ሆስፒታል በውስጥ ተኝታ ሳያት ያለች አትመስልም። እንደ ዶክተሮቹ አባባል በጣም ከፍተኛ ህክምና ያስፈልጋታል:፡ ህይወቷ መትረፍ እንዳለበት አምናለሁ። ሁላችንም የምናምን ይመስለኟል። ግን እንዴት??

ከዚህ በፊት እንደማደርገው ሰዉን አስተባብሬ ለማሳከም አልቻልኩም። የመን ያለ ሀበሻ በዚህ ሰዓት ሁሉም መለመን አፍሮ እንጂ ተቸግሯል። እኔም ቢሆን ሱቄን ዘግቼ መኖሪያ ቤቴን ለቅቄ ተሰድጄ ስላለሁ ማድረግ የምችለውን ያህል ላደርግ አልቻልኩም። መድረግ ለምትችሉ ሁሉ እባካችሁ?…እባካችሁ…..በመጀመሪያ ደረጃ የሚያሰፈልጋት የውጭ ሀገር ህክምና ነው። ይህን ማመቻቸት የምትችሉ በህክምናው መስክ የተሰማራችሁ፣ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያላችሁ..ከግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ጋር ግንኙነት ያላችሁ በበርካታ በሽታ የታጠረች ልጅ ለማዳን እንረባረብ። የህክምና ማስረጃው እጄ ላይ ስላለ ለመላክ ዝግጁ ነኝ። ሌሎችም ቢሆን ለምትበላው፣ ለመድሀኒት… የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን አነሰ በዛ ሳትሉ የወገንነታችሁን ለመርዳት ከቻላችሁ የአባቷን ስልክ ቁጥር ከታች ስላስቀመጥኩ ተባበሩ እባካችሁ????
00967735126401 የእኔ ስልክ ቁጥር ሲሆን
00967735241562 የአባቷ ካሊድ ለገሰ ስልክ ነው።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 2, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.