የአንድነት ፓርቲ የጠራው ሰልፍ በድምቀት ተጠናቀቀ – የመስከረም 19 ቀጥታ ዘገባ

ኢ.ኤም.ኤፍ – የዛሬውን ሙሉ ዘገባ ከአንድነት ድረ ገጽ ላይ ለናንተ አቅርበን ነበር። ሆኖም ምሽት ላይ ደግሞ ‘የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምን ይላል?’ ማለታችን አልቀረም። ማምሻውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አነስ ያለ ህዝብ ያለበትን ህዝብ አሳየ… ጉዳዩን ከሙስሊሞች ጋር ለማያያዝ ደጋግሞ በሰልፉ ላይ የተገኙትን ሙስሊሞች አሳየን። የአንዷለም አራጌ ደብዳቤ ሲነበብ… “ኢሳት እና ዘ ሃበሻ ድረ ገጽ የአመቱ ምርጥ ሰው ስላደረጉኝ አመሰግናለሁ” ማለቱን እንደጥፋት አድርገው አሳዩ። በመጨረሻም አቶ ሽመልስ ከማልን ጠቅሰው፤ “ሰላማዊ ሰልፉን ባልተፈቀደላቸው ቦታ ማድረጋቸው ህገ ወጥነት ነው። የተፈረደባቸው ሰዎች ‘ይፈቱ’ ብሎ መጠየቅም ወንጀል ነው” ማለታቸውን ገልጿል። እየዋለ ሲያድር ከአንድ የመንግስት ቴሌቪዥን የማይጠበቅ ተራ የዱርዬ ስራ ሲሰራ እያየን ከማፈር ሌላ ምንም የምንሰጠው አስተያየት አይኖረንም። ስለሰላማዊ ሰልፉ ቀደም ሲል የዘገብነውን ግን አሻሽለን መልሰን አትመነዋል። እንደገና አንብቡት። እውነቱንም ተረዱት።

ታላቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ሰልፉ በጣም ደምቋል። ፖሊሲ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደዉን መንገድ ዘግቷል። ሕዝቡ እየተንቀላቀለ ነዉ። ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይኬድ ፖሊስ ስለዘጋ የፓርቲዉ አመራሮች ለጊዜዉ ወደ ቀበና አደባባይ ቀስ በቀስ ለመሄድ እየገፋ ነዉ። ከዚያም ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ ሙከራ ይደረጋል።


የመስከረም 19 የአዲስ አበባዉ ሰልፍ ቀጥታ ዘገባ
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ በሰላም ተጠናቀቀ (አንድነት ፓርቲ መስከረም 19, 2006)

5፡30 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት )
አሁን ኢትዮጵያ እሁድ መስክረም 19 ቀን ነዉ። ሊነጋ ትንሽ ሰዓታት ይቀራል። ከጠዋቱ 5፡30 AM ( በኢትዮጵያ አቆጣጠር አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል)። የአንድነት ፓርቲ ከሌሎች ሰላሳ ሶስት ድርጅቶች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ የሚደርግበት ቀን ነዉ። የሰልፉ መነሻ ቀበና በሚገኘዉ የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ሲሆን መድረሻዉ የት እንደሆነ በሂደት የምናየዉ ይሆናል።
ገዢዉ ፓርቲ በመስቀል አደባባይ አይደረግም ብሏል። ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ። በአጥር የታጠራበት፣ ረጃጅም ሳር የበቀለበት፣ ለጥምቀት በዓል እንጂ ለሰላማዊ ሰልፍ ፍጹም በማይመች ቦታ ማድረግ ትችላላቹህ እያለ ነዉ።ነገር ግን ጃን ሜዳ ሰልፍ እንደማይደረግ የአንድነት ፓርቲ አሳውቋል።
ገዢዉ ፓርቲ ፍጹም አሳፋሪ አደርባይነት የሞላበት እንቅስቃሴ እያደረገም፣ ይኸው በሚያስደንቅ ሁኔታ ፣ ለዚህ ቀን ደርሰናል።

7፡ 20 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ሌሊቱን ሙሉ ሲሰሩ ነዉ ያደሩት። በርካታ መፈክሮች ተዘጋጅተዋል። አስተባባሪዎች ቦታ ቦታዎችን እየያዙ ነዉ። በአንድነት ጽ/ቤት በርካታ ሰዎች ይገኛሉ። ከቀበና የሚነሱት ሰልፈኞች ወዴት እንደሚሄዱ ገና አይታወቅም። ነገር ግን ገዢዉ ፓርቲ እንደፈለገዉ ግን፣ ጃንሜዳ አይሆንም። ሰልፉ ሲጀመር የሰልፉ ማብቂያ የት እንደሚሆን ይታወቃል።

7፡00 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት )
አዲስ አበባ ነግቷል። የሚደረገዉን እንቅስቃሴ ከአዲስ አበባ በቃሌና ሲቪሊቲ ፓልቶክ ክልፎች በቀጣት ይተላለፋል። በተጨማሪም በቴሌኮንፈራንስ ኦዲዮ በመስማት መከታተልም ይችላሉ።
Teleconference: Sunday, September 29, 2013 at 1:00 AM EST and 7:00 AM CET: Central European Time
Live Broadcasting – You can listen to our live stream by dialing 1-862-902-0100 and use Conference Code:838802

9:00 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት )
በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በርካታ ሕዝብ ተሰብስቧል። መፈክሮች በከፍተኛ ድምጽ እየተሰሙ ነዉ። ሕዝቡ በብዛት እየመጣ ነዉ። ሰልፉ ተጀምሯል። ይሀ ታሪካዎ ቀን ነዉ። አበል ተሰጧቸው ወይንም ፈርተዉ፣ ወይንም ተገደው ሳይሆን፣ ከልባቸው በራሳቸው ፍላጎት ዜጎች እንደዚህ በድፍረት ለመብታቸውና ለነጻነታቸው ሲወጡ ማየት በጣም ያስደስታል። ይህ ለአገር ወዳዶች፣ ነጻነት ናፋቂዎች ድል ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ የዛሬዉን ሰልፍ ከማድረጉ በፊት በደሴ፣ ጎንደር፣ ባሀር ዳር፣ ጂንካ፣ አርባ ምንጭ፣ ፍቼ ሰላማዊ ሰልፍቾ ሕዝቡን ማንቀሳቀሱ ይታወቃል። በዚያ የታየዉ ዛሬ ደግሞ በመዲናችን ፊንፊኔ አዲስ አበባ እየተደገመ ነዉ።

9:20 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
የሰልፈኛው ቁጥር እየጨመረ ነዉ። የፖሊስ ቁጥርም ብዙ ነዉ። መንገድ እስከ አሁን አልተዘጋም። ሰለፈኞች መፈክሮች እያሰሙ ነዉ። ከመፍክሮች የሚከተሉት ይገኛሉ
– አሸባሪ አይደለንም፣ ዲሞክራሲ እንፈልጋለን፣ እኩልነት እንፈክጋለን ፣ የጸረ ሽብር ሕጉ ጸረ-ሕገመንግስታዊ ነዉ ! አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ ፣ ርዮት አለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ናትናዔል መኮንን ..አሸባሪ አይደሉም፤ ድል የሕዝብ ነዉ
በእንግሊዘኛም መፈክሮች አሰምተዋል።
WE NEED FREEDOM ! FREEDOM ! FREEDOM!
WE NEED JUSTICE ! JUSTICE ! JUSTICE !
WE NEED EQUALITY ! EQUALITY ! EQUALITY !

9:30 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ተከበረሽ የኖርሽዉ ባባቶቻችን ደም !
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይወደም !
እያሉ ሰልፈኞች በማዜም በደማቅ ሁኔታ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እያንጸባረቁ ነዉ።
የሚከተለው በፓርቲዉ ጽ/ቤት የነበረዉ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነዉ።

9:40 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ለጊዜዉ ከአዲስ አበባ አንድነቶች የሚያስተላለፉት ዘገባ ተቋርጧል። ስልክ ሲደወል፣ በመሃከሉ ቴሌ በኢቲቪ የሚሰማን ክላሲካል በመልቀቅ ስርጭቱን ጃም አርገዉታል። እንደገና ከኢትዮጵያ ጋር ለመገናኘት ሙከራ እየተደረገ ነዉ።
መስቀል አደባባይ በፖሊሶች ተከቧል። በዚያ አካባቢ በርካታ ሕዝቡ አለ። ሰልፈኞቹ የሚያመሩት ወደ መስቀል አደባባይ እንደሆነ የአመራር አባል የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ገልጸዋል።
በአንድ በኩል የሚያስቅ በሌላ በኩል የሚያሳዝን ሥራ ነው ቴሌ እየሰራ ያለው። በሕግ የተፈቀደን ሰልፍን ኢትዮጵያዉያን እንዳይከታተሉ ማድረግ ምን ያህል አገዛዙ የፖለቲካ ኪሳራ ዉስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነዉ። «99% ሕዝብ መርጥኛል፣ 4.5 ሚሊዮን አባላት አሉኝ፣ ኮንዶሚኔየሞች አስርቻለሁ፣ ልማትን አምጥቻለሁ …» የሚል ድርጅት ምን አስፈርቶት ነዉ ይሄን ያህን እራስን የሚያስገመት ተግባራት ላይ የሚሰማራዉ ?

9:50 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ከኢትዮጵያ ጋር መስመር ማግኘት በጣም እያስቸገረ ነዉ። እስከአሁን ግን በደረሰዉ ዘገባ ፣ ሕዝቡ ወደ ቀበና እየመጣ ነዉ። ከፓርቲዉ ጽ/ቤት አልፎ አስፋልት ላይ ደርሷል። ነገር ግን ወደ ቀበና የሚያመጣ ትራንስፖርት ሁሉ አገዛዙ አቋርጧል። ሕዝቡ በእግር ነዉ የሚመጣዉ። ፖሊስ አላሳልፍም እያለ ነዉ ያለዉ። ወደ መስቀል አደባባይ አትሄዱም እያሉ ነዉ ፖሊሶቹ !!!! የአመራር አባላት ለማነጋገር እየሞከሩ ነዉ።
አንዲትም ጠጠር አትወረወርም ! በሰላም ነዉ ሁሉንም የምናደርገዉ እያሉ ነዉ። ፖሊሶች እጅ ለእጅ ተያይዘው መንግዱን ዘግተዋል። ከአራት ኪሎ የመጡ ወደ ሰልፉ ለመቀላቀል የሚሞክሩትን፣ ፖሊሶች መንገዱን ዘግተዉ አላሳልፍ እያሉ ነዉ።

10:04 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
“የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል አይንበረከክም ! ሙስና የስርዓቱ መገለጫ ነዉ ! የታሰሩ የሕሊና እስረኞች ይፈቱ ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ነዉ ! ”እያለ ሰልፈኞች ሰላማዊነታቸዉን እና ጨዋነታቸውን እያሰሙ ነዉ።
ፖሊስ ሰልፉን ለማደናቀፍ ዘብ ቆሟል:: ፖሊስ ሰልፉን ለማደናቀፍ ዘብ ቆሟል ትራፊክ ፖሊሶችም ትራንስፖርት እንዳይኖር መኪኖችን እያስቆሙ ነው፡፡ይህንን ሁሉ መሰናክል አልፈው ጀግኖቻችን በቦታው እየደረሱ ነው፡፡
ሰልፈኛዉ እንዲቀመጥ ጥሪ ቀርቧል። ፖሊሶች ወደ መስቀል አደባባይ አላሳልፍ ብለዋል። የሚያስገርም ነዉ።

10:30 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
“ፖሊስ የሕዝብ ነዉ” እያሉ ሰልፈኞች እየጮሁ ናቸው። በጣም ብዙ ሕዝብ እየመጣ ነዉ። ወደ መስቀል አደባባይ ብዙ ሕዝብ እየሄደ ነዉ።

Updateይሄን ቪዲዮ ይመልከቱ !

ፖሊሶችን ለማግባባትን ለማሳመን ሙከራ ቢደረግም ፌዴራሎች በጭራሽ ፍንክች አንልም ብለዋል። በሺሆዎች የሚቆጠሩ ወደ ሰልፉ እየመጡ ነዉ። ፖሊስ ወደ አደባባዩ እንዳይመጣ እያገደ ነዉ። አገዛዙ ረብሻ እንዲፈጠር የሚፈልግ ይመስላል። የአንድነት አመራሮችና ህዝቡ ግን በተቻለ መጠን ከፖሊስ ጋር ግጭት ላለማድረግ እየሞከረ ነዉ።ፖሊሶች በየቦታዉ ወደ ሰልፉ የሚመጡትን እየበተኑ ነዉ።
አቶ ትእግስቱ አወሉ፣ የብሄራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ፣ የፓርቲዉ አመራር አባላት ስብሰባ አድርገዉ የፖለቲካ ዉሳኔ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

10:55 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ታላቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ሰልፉ በጣም ደምቋል። ፖሊሲ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደዉን መንገድ ዘግቷል። ሕዝቡ እየተንቀላቀለ ነዉ። ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይኬድ ፖሊስ ስለዘጋ የፓርቲዉ አመራሮች ለጊዜዉ ወደ ቀበና አደባባይ ቀስ በቀስ ለመሄድ እየገፋ ነዉ። ከዚያም ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ ሙከራ ይደረጋል።
ወደ ጃንሜዳ የሚወስደው መንገድ ክፍት ነዉ። አገዛዙ ጃንሜዳ ሄዳችሁ ሰልፍ አደርጉ እያለ ነዉ። ፓርቲዉ ግን ሰልፍ በጃንሜዳ ማድረግ ሕግን መጣስ እንደሆነ በመጥቀስ ፣ «ሕግ እንዲከበር እናደርጋለን እንጂ ለሕግ ጥሰት አንተባበርም» በሚል የጃን ሜዳዉን ዉድቅ አድርገዉታል። የወታደራዊ ካምፕና ትምህርት ቤቶች በቅርበት ባሉበት ቦታ ሰልፍ መደረግ እንደማይቻል የሚጠቅሰዉን ሕግ በማጣቃስና በጃንሜዳ ትምህርት ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች በመኖራቸው ፣ በዚያ ስልፍ ማድረግ እንደማይታሰብ አሳዉቀዋል።

11:00 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
የርዮት አለሙ እህት «የርዮት መታሰር ቢያሳዝነኝም። በሺሆች የሚቆጠሩ ርዮቶችን እንዳፈራች ነዉ የሚያሳየዉ። የሕዝቡ ስሜት በጣም የሚያስደስት ነዉ። መስቀል አደባባይ ለሰልፍ አይመችም ነበር ያሉት። ግን ደመራ ሲብስራበት አይተናል። ይሄ የሕዝብን ድምጽ ማፈን ነዉ»
ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ ሁሉም የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የ33ቱ ፓርቲዎች አመራሮች ሰልፉን ለማደናቀፍ ከተኮሎኮሉት የፖሊስና የደህንነት ሀይሎች ጋር ፊትለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ሰልፉን ሲቀላቀሉ ህዝቡ “ነጋሶ ማንዴላ!! ነጋሶ ማንዴላ!!” በማለት ተቀብሏቸዋል፡፡
ወጣት ሳሙኤል “ ነጻነትን ስለተጠማሁ ነዉ እዚህ የመጣሁት”

11:05 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ሕግን ማስከበር፣ ሕዝብን ማገልገል የሚገባቸው ፌዴራሎች የሕዝብን ድምጽ ለማፈን ፣ ሕዝቡ እንዳያልፍ ለማድረግ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው መንገድ ሲዘጉ !!ሕዝቡ ግን እንደ እነርሱ እንዳልሆነ ለማሳየት «ፖሊስ የኛ» እያለ ነዉ። ፖሊሶች ይሄን እያዩ ከሕሊናቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ነዉ።
«መንግስት በአስቸኳይ ብሄራዊ እርቅ ይጠራ ! ነጻነታችንን ከኢሕአዴግ አንጠበቅም !!!!» ከተሰሙት መፈክሮች መካከል !!! ሰልፈኞቹ ቀናባ መንገዱ ላይ ተቀምጠዋል። ሰልፉ ደምቋል። ህዝቡ በብዛት እየተቀላቀለ ነዉ።

11:20 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ብዙ ሕዝብ በሰልፉ ተገኝቷል። በየቦታዉ መንገዶች በፖሊሲ በመዘጋታቸው እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ ገና ሰልፉን አልተቀላቀለም። በመስቀል አደባባይ አካባቢም ብዙ ህዝብ ይገኛል። ሰልፈኞቹ ወደ ቀበና አደባባይ አካባቢ ናቸው። አገዛዙ መንገዶችን ከለቀቀና ዜጎችን ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ካደረገ ሰልፈኛው ከቁጥጥር ዉጭ ይሆንብናል የሚል ፍራቻ ያላቸው ይመስላል። ሰላማዊ የሆነ የራሱን ሕዝብ እንደዚህ የሚያፍን መንግስት፣ በዚህ ዘመን መኖሩ ያሳዝናል።

11:30 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
የሰው ግድግዳ ላይ ያለ አግባብ ፖስተር ለጥፈሃል በሚል የታሰረው የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል የሚከተለዉን አስተያየት ሰጠዋል፡
«ትላንት የነበረኝ ስጋት መታሰሩ ሳይሆን፣ ለብዙ ጊዜ የሰራንበት ሰልፍ ላይ ላልገኝ ይሆን የሚል ነበር ስጋቴ። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በዋስ ፈተዉኛል። በዚህ ታላቅ ሰልፍ መገኘቴ በጣም አስደስቶናል። በኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ኮርቻለሁ። ከመቶ ሺሆች በላይ ሕዝብ ነዉ አሁን የሚገኘው። በመስቀል አደባባይ ቢኬድ ደግሞ አስቡት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል። አገዛዙ ለህዝብ የማይገዛ መሆኑን፣ ህግን የማያከበር መሆናቸውን አሳይተዋል። ወደ ዘጠኝ አደባባዮች አማራጭ ብንሰጣቸውም አንዱን እንኳ መፍቃደ የመቻል አቅም የሌላቸው ናቸው። »

11:50 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
ዶር ነጋሶ «ከቀበና ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል አድርገን ወደ ጃን ሜዳ እንድንቀሳቀስ ነዉ የሚፈልጉት። ይሄ ደግሞ አይሆንም።አደባባዩን ለመዞር እየሞከርን ነዉ። ከዚያ ወደ አራት ኪሎ እንዞራለን። ከፖሊስ ጋር ለመደባደብ አንፈልግም። እኛ ሰላማዊ ነን። » ዶር ነጋሶ የአንድነት ሊቀመንበር
«ይሄን ሰልፍ ፖሊሶች እየዘጉት ያለዉ በአስተዳደሩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ነዉ። ተጠያቂዉ አስተዳደሩ ነዉ» አቶ ዳንኤል ተፈራ።
ቋጠሮ ፣ አቡጊዳ፣ ዘሃበሻ ፣ ኢትዮጵያን ሪቪው ድህረ ገጾች በአሁኑ ጊዜ አገር ቤት የሚደረገዉን ሰልፍ በስፋት እየዘገቡት ነዉ። የቃሌ፣ ሲቪሊቲ፣ ከረንት አፌር የፓልቶክ ክፍሎችም በቀጥታ ከአዲስ አበባ ስልክ እየደወሉ ሰልፉን እያስተላለፉ ነዉ።

11:55 AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
«አስተዳደሩ አዞናል። እባካችሁ ችግር ዉስጥ አትክተቱን»በሚል ፖሊሶች ልመና አድርገዋል። የአገዛዙ ፓርቲዎች ተደብቀዉ ህዝቡን እና ፖሊሲን ለማጋጨት እየሞከሩ ነዉ። ግን የአንድነት አመራሮች በአገዛዙ ወጥመድ ዉስጥ ላለመግባት በማስተዋልና በእርጋታ ሕዝቡን እየመሩት ነዉ።
«ሃሩር የሆነ ጸሃይ ነዉ። ሕዝቡ ሂድ ስንለው ይሄዳል። ተቀመጥ ስንለው ይቀመጣል። በጣም ጨዋና ሰላማዊ ህዝብ ነዉ።» አቶ ሃብታሙ አያሌዉ
የሕዝብ ማእበል – ፖሊስ ሕዝቡ ሰልፍ እንዳይቀላቀል ሲያከላክል
መፈክሮች !
ሕዝብ አሸማቆ መግዛት አሸባሪነት ነዉ !
ኢሕአዴግነት ከኢትዮጵያዊነት አይበልጥም!
አንድ ናት አገራችን !
ሙስና የስርዓቱ መገለጫ ነዉ !
መብታችንን ከኢሕአዴግ አንጠብቀም !
ይሄ ስርዓት እስኪለወጥ ትግላችን ይቀጥላል።

12:30 PM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
«ፖሊሶች በሚኒሊክ ሆስፒታል አድርጎ ወደ ጃን ሜዳ የሚሄደዉን መንገድ ብቻ ነበር የከፈቱት። ነገር ግን ሕዝቡ እየገፋ ወደ ቀበና አደባባይ ደርሷል። በቀበና አደባባይ፣ ከመቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ይገኛል። በዚያ የአንድነት አመራር አባላት ንግግር እያደረጉ ነዉ። ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ከሚወስደው መንገድ ዉጭ ያሉ ሌሎች መንገዶች በሙሉ በታጠቁ ኃይላትና አመጽ በታኞች በመዘጋቱ፣ ሰልፉ በዚያዉ በቀበና አደባባይ ሳይጠናቀቅ አይቀርም።
አቶ ትእግስቱ አወሎ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ጸሃፊ ንግግር አድርገዋል። በህዝቡ ያላቸውን ኩራት ገልጸዋል። «ነጻነት እስኪሰፍን ትግሉ ይቀጥላል» ብለዋል።
የአንዷለም አራጌ መልእክት ተነቧል።
«ብዙ ፈተናዎችንና አፈናዎችን አልፋችሁ በምታደርጉት በዚህ ታላቅ ሰላምዊ ሰልፍ በካል ባለገኝም በመንፈስ ከጎናችሁ ነኝ። በዚህም ታላቅ ደስታ ይሰመኛል። ፍርሃትን ያላሸነፈ በአዋጅ ነጻ ሊሆን አይቻልም። ፍርሃት ያላሸነፈ ለልጆቹ ነጻ አገር ሊያወርስ አይችልም። ፍርሃትን አሸንፋችሁ ድምጻችሁን ማሰማታችሁ ትልቅ ድል ነዉ። እኔ እዚህ ያቆመኝ (እሥር) የነጻነት ናፍቆት ነዉ» አንዱዋለም አራጌ
ኢንጅነር ኃይሉ ሻዉል የክብር እንግዳ ተደርገዉ ተጋብዘው ነበር። ግን በሕመም ምክንያት በአካል አልተገኙም። ነገር ግን በሰልፉ የሰማቸዉን ደሳት ገልጸዋል።
ከነበቀለ ገርባም የተላለፈ መልእክት ተነቧል።

12:50 PM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
የሰላማዊ ሰልፉ መርሃ ግብር ተጠናቋል። ምንም እንኳን አገዛዙ አይን ባወጣ መልኩ የሕዝብን መብት ቢረግጥ የአዲስ አበባ ሕዝብ ምን ያህል የሰለጠነ እንደሆነም አሳይቷል። አንድ ሰው ሳይጎዳ፣ አንዲት ጠጠር ሳይወረወር ሰልፍ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠናቋል።
ከመርካቶ፣ ከሳሪስ ልደታ የሚመጡ መንገድ ተዘግቶ መምጣት አልቻሉም። በመቶ ሺህ የሚቆጠረዉ በቀበና አደባባይ የተሰበሰበው ሕዝብ በአጭሩ ከአንድ አካባቢ የተሰበሰበዉ ህዝብ ነዉ። ፖሊሶች መንገድ ባይዘጉና፣ ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍሎች ሕዝቡ እንዲያልፍ ቢደረግ ኖሮ ሚሊዮኖች ሊገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ነበር።
ሰልፉን ለመዝጋት ዶር ነጋሶ ንግግር አድርገዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት 70 አመታቸውን እንዳከበሩ የገለጹት ዶር ነጋሶ የተሰማቸዉን ከፍተኛ ደስታ ገልሰዋል።
«እዚህ ያላችሁ አብዛኞቻችሁ የልጄቼ ልጆች ልትሆኑ ትችላላችሁ። ተስፋ የማድረግባችሁ ናችሁ» ብለዋል ዶር ነጋሶ በመጨረሻ የሰልፉ አዘጋጆች መንገዱን ለዘጉባቸው ፖሊስ ሰራዊቶች ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

1:05 PM (ኢትዮጵያ ሰዓት)
«ፖሊሶች ከአቅማቸው በላይ ነዉ። ሕገ መንግስትና በሕግ ሳይሆን በመመሪያ ነዉ የሚተዳደሩት። ሕዝቡ ሰላማዊ ሆኖም ከመርካቶ፣ ከሳሪስ፣ ከሜክሲሶ ሕዝቡ እንዳያልፍ ማድረጋቸው የፍርሃታቸው ጥግ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ነዉ። የሰዉን ሁኔታ የተረዱ ይመስለኛል» አቶ ግርማ ሰይፉ
«ለአይንህ መጨረሻዉን የማታየው ሕዝብን ማየት ያሰደስታል። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በራሱ ግብ አይደለም። ላለፉት 3 ወራት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል ስናደርግ የነበረው የመጀመሪያ ፌዝ አጠናቀናል። የመጀመሪያዉን ፌዝ አጠናቀቅን ስንል ፣ የትግሉ ሂደት ተጠናቀቀ ማለት አይደለም። ከመጣነዉ ይልቅ የሚቀረን እንደሚረዝም ነዉ የምናስበዉ» አቶ ሃብታሙ አያሌው። አቶ ሃብታሙ በቅርቡ በጸረ-ሽብር ሕጉ ዙሪያ በኢቲቪ በተደረገው ክርክር አንድነት ወክለዉ ቀርቦ የነበረ ወጣት የአንድነት አመራር አባል ነዉ።

AFP, Bloomberg News, AL JAzria ….የመሳሰሉ በርካታ የዉጭ ጋዜጠኞች ተገኝተዉ ነበር። ፖሊሶች መንገዱን መዝጋታቸውን ታዝበዋል። «ሰልፉ አልተፈቀደም እንዴ ? ከተፈቀደ ለምንድን ነው መንገድ የሚዘጉትም ? ህዝቡ እንዳይቀላቀል ለምን ያደርጋሉ ? » የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 29, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

2 Responses to የአንድነት ፓርቲ የጠራው ሰልፍ በድምቀት ተጠናቀቀ – የመስከረም 19 ቀጥታ ዘገባ

 1. Pingback: ሰልፉ በጣም ደምቋል – የመስከረም 19 ቀጥታ ዘገባ - EthioExplorer.com | EthioExplorer.com

 2. andnet berhane

  September 30, 2013 at 12:12 AM

  እውነትም የኢቶጵያ ሕዝብ መብቱንና ነጻነቱን በተግባር ማሳየቱ ወያነ በፍርሃት መብረክረኩን ያሳያል የሆኖ ሆኖ ያለፈው አልፋል ሁሉም ዋገን በተነሳበት አላማ የማያወላውል አቛም መውሰድ ይኖርበታል ከንግዲህ ወያነእ ባለምልን መንገድ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ባለሙትና በተቀበሉት ራሳቸው አምነው በቀረጹት የሁሉም ሕገ ህዝብ መሆኑን ማሳወቅና ለወደፊቱ የሚደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ወያኔ በመረጠልን ዐንና ቦታ ሳይሆን ሕዝብ በመረተው አብዮት አደባባይ መሆን እንዳለበት ይህንንም እውን ለማድረግ የሰልፍ እስትራተጂ ማውጣት ያስፈልጋል :

  ድል ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች
  ውድቀት ለጨቋኞችና ሆድ አደሮች
  ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በነሳነት ለዘላለም ይኑሩ