ሥልጡኑ(ኢንቬስተሩ) ጎረቤቴና ፌስ ቡክ

በልጅግ አሊ – ሰውዬው የወያኔ ደጋፊ ከሆነ ሰው ጋር ወያኔ ከሥልጣን ይውረድ አይውረድ በሚለው ላይ በፍርሃት ይከራከራሉ። የወያኔው ደጋፊ ሰውዬውን ይጠይቃቸዋል፡

– “ወያኔ አዲስ አበባ ውስጥ ፎቅ አልሠራም ነው የምትሉት?”
– “ሠርቷል” – ይመልሳሉ።
– “መንገድስ አልሠራም?”
– “ሠርቷል” ይላሉ አሁንም በፍርሃት።
– “ታዲያ ወያኔ ለምን ይውረድ ይላሉ?” ብሎ በቁጣ ይጠይቃቸዋል።
– “ብዙ ሠርቶ ደክሞታል። ልጄ ይረፍ ብዬ ነው”። ብለው መለሱለት ይባላል።

የወያኔ ደጋፊ ከሆኑ አድርባዮች ጋር መከራከር ልብ ማውለቅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት አዲስ አበባ ላይ በተሠራው ፎቅ ብዛት ብቻ የሚወሰን ይመስል ሲሰብኩ ይሰማል። በተለይ ከውጭ ገብተው ወያኔ የሰጣችውን ጥቅማ ጥቅም ያግበሰበሱ ክርክራቸው አይጣል ነው። ሃገሪቱ ውስጥ ደሃ እንደሌለ ይሰብካሉ። በእነርሱ “ኢንቬስተርነት”(ወደ በኋላ በሰፊው እመለስበታለሁ) ሃገሪቱ የለማች ይመስል ለወያኔ ቆመው ሲከራከሩ አይጣል ነው። እነሱ ከወያኔ ገዝተው ከሠሩት ቦታ ላይ የድሃ ቤታቸው ፈርሶ፣ በሀገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ሆነው ስለሚጎሳቆሉት ሰዎች ዕቁብም የላቸው። ወይም ከእነሱ ያማረ ቤት በራፍ ባለው መንገድ ዳር ዱር አዳሪ የሆነውን ብዙሃን ድሃ ለማየት ዓይናቸው ታውሯል። የአንድ ሃገር እድገት የሚለካው በመላ ሃገሪቱ እንቅስቃሴ እንጂ በተወሰነ የሃብታሞች መንደር ወይም በአሮጌ ቤቶች ማህል እንደ ጅብራ በተቆለለ ፎቅ አይደለም። የዚህ አይነት ክርክር የሚከራከር ሥልጡን ጎረቤት አለኝ። ሰለ ሥልጡኑ ጎረቤቴ ባለፈው ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጽሁፎች አስተዋውቄያችሁ ነበር። ብዙ ሰዎች ስለራሳቸው ጎረቤት የምጽፍ እየመሰላቸው ይሳሳታሉ። ከብዙ ቦታዎች ይህንን በሚመለከት ብዙ ኢሜል አግኝቻለሁ። የስም ሞክሼ ምን ማለት እንደሆን ታውቃላችሁ። እንደ ስም ሞክሼ በዚህ ወቅት የተግባር ሞክሼዎች ብዙ ናቸውና ስለ እናንተ ጎረቤት የምፅፍ እንዳይመስላችሁ። እኔ የምጽፈው ስለ እኔ ጎረቤት ነው። የእናንተ ጎረቤት የሥልጡኑ ጎረቤቴ የተግባር ሞክሼ ከሆነ ጨምሩበት።

ሰለ ጎረቤቴ ካጫወትኳችሁ ሰነበትኩ።ምን ላድርግ እኔ ሳልሆን ጎረቤቴ ጠፍቶ ነው።አንድ ሰሞን ” ኢየሱስን ተቀበልኩ” ብሎ እንዳመሰን አጫውቻችሁ ነበር።አዲስ አበባ ሄዶ “ተቀበልኩ” ያለውን ኢየሱስን ለማን እንደሰጠው ሳይታወቅ ኢንቬስተር” ሆኖ መመለሱን አጫውቻችሁ ነበር። ምን እሱ ብቻ ! ቅልጥ ያለ ሠርግ ደግሰን የዳርነውን ትዳሩን እንዳፈረሰም ታውቃላችሁ። መቼም የእሱ ጉድ አያልቅም አሁን አንዲት ገና የእናቷ የጡት ወተት ከንፈርዋ ላይ ያልደረቀ ትንሽ ልጅ አዲስ አበባ ላይ አግብቻለሁ ብሎ ፎቶዋን ይዞ ይዞራል። ልጅቷ እዛው አዲስ አበባ ነች።ወደ አውሮፓ አላስመጣትም። ለማስመጣትም ሃሳብ ያለው አይመስልም።ስለ ልጅቷ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? እንዳይቸግራት ፣ ቢቸግራትም እንዲደርሱላት ብዬ ቤተሰቦቼ የሚኖሩበት አካባቢ ቤት ተከራይቼ አስቀመትኳት ብሎኝ ስገረም ነበር። እንዲረዱለት ከሆነ ጥሩ ነው። እንዲጠብቁለት እንዳይሆን እንጂ!

ጎረቤቴ ያኔ ካጨወትኳችሁ በጣም ተቀይሯል። የዘመኑ “ኢንቬስተር ” ሆኑዋል። “ኢንቬስተር “ምንድነው ትሉኝ ይሆናል። እዚህ አውሮፓ የኢንቬስተር ትርጉሙ ጠፍቶናል። ምንአልባት ሌላ ክፍለ ዓለም ያላችሁ ትረዱት ይሆን? በአብዛኛው ኢትትዮጵያ ውስጥ ኢንቬስተር ነን በማለት ወደ አዲስ አበባ የሚመላለሱትን ስንመለከት ትርጉሙ የአውሮፓ መንግሥታት ለችግረኞች የሚሰጡትን እርዳታን እያጭበረበሩ እየተቀበሉ ኑሮዋቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ማለት ሆኗል። በበኩሌ ከዚህ የተለየ ለኢንቬስተር የሚስማማ ትርጉም እስካሁን አላገኘሁም።

ጎረቤቴም እዚህ አውሮፓ ያለውን ቤቱን በድብቅ (በጥቁር የሚለውን ቃል መጠቀም አልፈልግም። አጉዋጉሉን ነገር ሁሉ ጥቁር ብሎ መፈረጁ ይደብረኛል)አከራይቶ እሱ አዲስ አበባ ነው የሚኖረው።

የሚያከራየው ቤት ስል የግል ንብረቱ እንዳይመስላችሁ። የመንግሥት ቤት ነው። ለኑሮው መደጎሚያ በቂ ገቢ ስለሌለው መንግሥት ለቤት ኪራይና ለአስቤዛዉ መግዣ ገንዘብ ይሰጠዋል። ታዲያ እሷን እየሰበሰበ ነው አዲስ አባባ ” ኢንቬስተር ” ነኝ ብሎ የሚመላለሰው። ለነገሩ ይህንን የእርዳታ ገንዘብ ለማግኘት ያለው ዉጣ ዉረድ ብዙ ነው። ጭቅጭቁንና ተያዝኩ አልተያዝኩ ብሎ መጨነቁን የቻለ ይችለዋል። ጎረቤቴ ያለ የሌለበትን ህመም ሁሉ አለብኝ ብሎ ትንሽ እረፍት ሰጥተውታል እንጂ ጭቅጭቁን አይችለውም ነበር።

“ሥልጡኑ ጎረቤቴን” ትቼ “ኢንቬስተሩ ጎረቤቴ” ልበለው እንዴ? ይሻላል መሰለኝ። ከቴም ኢንቬስተርነት ! በአመት አንድ ሁለት መኪና ያስገቡት ሁሉ ኢንቬስተር ነን ማለታቸዉ እዚህ አውሮፓ የተለመደ ሆኗል። ባለፈው ወያኔ ከውጭ ሃገር ለመጡት (ለዲያስፖራዎች) ብሎ የጠራውን ስብሰባ አይታችኋል? ያ ሁሉ እኮ ኢንቬስተር ነው። እንደ ጎረቤቴ በእርዳታ በተሰጠው ገንዘብ የሚዝናና ይበዛበታል። በተለይ ከአውሮፓ ሄደዉ ከሁለት ወር በላይ ሃገር ቤት የሚቆዩትን መጠርጠር ነው።የአመት እረፍት ምን ሞልቶ ቢተርፍ ከስድስት ሳምንት አይበልጥም። ከሁለት ወር በላይ ሃገር ቤት የሚቆዩት እዚህ አውሮፓ ሥራ የሌላቸው በእርዳታ የሚኖሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

 ያችን የእርዳታ ገንዘብ ይዞ ነው ኢንቬስተር ነኝ ብሎ አገር ቤት በድሃው ሕዝብ ላይ የሚጎማለለው። ወያኔ ውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ለመከፋፈል ሲል የሚያድለውን የከተማ ቦታ ተቀብሎ የሚሸጠው ኢንቬስተር ደግሞ የሚገርም ነው። ጎረቤቴ የመሬት ጉዳይ ጀምሮ ነበር በኋላ አጫውታችኋለሁ።

ለምን እንደሆን አላውቅም የዘመኑ ኢንቬስተሮች ኢኮኖሚውን ብቻ አይደለም ፖለቲካውንም በጣም ይወዳሉ።ፖለቲካውን ለሁለት ጉዳይ ሲሉ ይወዱታል። አንደኛው በ97ቱ ምርጫ በደረሰባቸው ድንጋጤ የተነሳ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወያኔ ለፖለቲከኞች የሚሰጠው ጥቅም ጎላ ያለ ነው በሚል ነው። በ97ቱ ምርጫ ለምን ደነገጡ? ትሉኝ ይሆናል።ታስታውሱ የለም በምርጫው ሰሞን ” የሙት ከተማ “የምትባል አድማ ነገር ተጠርታ ነበር። ኢንቨስተሮቹ ሳይዘጋጁ ሃገር ተደበላለቀ። መውጫ መግቢያ ጠፋ። ወደየኤንባሲዎቻቸዉ እየደወሉ የሙት ከተማ አድማዉ እነርሱ ከዚያች ሃገር እስኪወጡ ድረስ እንዳይጀመር የጠየቁም ነበሩ። ኤምባሲዎቹ ጥያቄቸውን ሰምተው አስቆሙት እንጂ ምድረ ኢንቬስተር ጉድ ፈልቶበት ነበር። የ2002ቱ ምርጫ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ አንድም ኢንቬስተር ሃገር ውስጥ አልነበረም። ምርጫው ከመጀመሩ ቀድመዉ ነው ሃገር ጥለው የወጡት። አጠገባችሁ ኢንቬስተር ካለ ጠይቁት ፡-ይነግራችሁዋል። ሁለተኛዎቹ ፖለቲካ ወዳዶች ደግሞ ምክንያታቸዉ በዚያ መንገድ ከወያኔ የሚገኝ ጥቅም አይጠፋምና ፖለቲከኛነት ያዋጣል የሚል ነዉ። ምን ያድርጉ?/ ትላልቆቹ ፖለቲከኞች ግዙፍ የእስፖርት ኮምፕሌክስ ለመገንባት የሚበቃ ካተረፉ እነርሱስ እንደአቅምቲ በሰላም ያስገቧትን መኪና ምነዉ አይሽጡ? ከወያኔ የተሰጣቸዉን የከተማ ቦታ መቸብቸቡስ ይብዛባቸዉ?

ኢንቬስተሮቻችን ጉደኞች ሰለሆኑ ስለእነርሱ ካነሳሁ አላቆምም። የብዙዎቹ ኢንቨስተሮች ተግባር ይመሳሰላል።ፖለቲካ ይወዳሉ ብያችሁ የለም? እውነት ነው ይወዳሉ። የበሰሉቱ ፖለቲከኞች ደግሞ ዴሞክራቶች መሆናቸውን ለማሳየት የማያደርጉት ጥረት የለም። ሰላማዊ ትግል ከሌላው የትግል ዘዴ ትሻላቸዋለች። ለምን ቢባል መልሱ በሰላማዊ ትግል መንግሥት ቢቀየር እንኳ ንብረታቸው የምትተርፍ እየመሰላቸው ነው። ስለ ሥርዓት ለዉጥ የሚደርሱበት ድምዳሜ ደግሞ ጨለምተኛነት የተጠናወተዉ ነዉ።“ወያኔ ከወረደ የዓለም መጨረሻ ይሆናል “ብለዉ ሲሰብኩ ብትሰሙ እንዳትደነግጡ። ምን ማለታቸው እንደሆነ ነው መረዳት ያለባችሁ።ባላገሩን ተገዢ አስፈራርተው ወያኔን በማክረም በፖለቲካ ሸቃይነት የቋጠሩትን ጥሪት ማስጠበቅ ነው።

ኢንቨስተር ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሲሰድብ ሆዱ አይራራም። ወያኔን ለመስደብ ግን ልቡ ይቀልጣል። የልብ ድካም ይይዘዋል። ይህ የሚሆነው በሁለት ነገር ነው። ወይ በፍርሃት ፡ ወይም በፍቅር። ስለሥርዓቱ ያላቸዉን ሒስ እንዲህ ብለው ይጀምራሉ። ” እነዚህ ሰዎች መች ያሠራሉ ! አያሠሩም እኮ !”ይህ የኢንቬስተሮች የምሬት ቃል ነው። እስቲ ረጋ ብላችሁ የትኞቹ ሰዎች? ብላችሁ ጠይቋቸው። ስም ለመጥራት ሲፈሩ አይጣል ነው። ወያኔ በማለት ፋንታ የባጥ የቆጡን ሲቀባጥሩ ትታዘባላችሁ። ወያኔን ላለመንካት ቢሮክራሲውና ሙስናው ላይ ያተኩራሉ። የአሳ ግማቱ ከአናቱ እንደሚጀምር ለመናገር ድፍረቱ የላቸውም።

ስለ ጎረቤቴ ጀምሬ ስለኢንቬስተሮች ቀጠልኩ። መነሻዬ ጎረቤቴ ከዘመኑ ኢንቬስተሮች አንዱ መሆኑ ነዉ። ስለዚሁ ጎረቤቴ ካስነበብኳችሁ በጣም ሰንብቶአል። ለምን እንደገና ላነሳባችሁ እንደተነሳሁ ታውቃላችሁ? ጎረቤቴ ከሰሞኑ ሳይታሰብ ከሀገር ቤት ተመልሷል።ገና ከመድረሱ ነበር ትንፋሹ ቁርጥ ቀርጥ እያለ ከአውሮፕላን ማረፊያ ሆኖ የደወለልኝ።

– ሰላም እንዴት ከረምክ?
– ሰላም— ማን ልበል? አልኩት።
– እኔ ነኛ? ደግሞ ድምፄ ጠፋህ እንዴ?
– ደህና ነህ ወይ? ሌላ ሰው መስለኸኝ። መቼ መጣህ?
– ገና መግባቴ ነው። ቤት እንደሆንክ ለማወቅ ነው።
– ቤት ነኝ። እጠብቅሃለሁ።

ቤቱን እንደሆነ አከራይቶት ነዉ የሄደዉ። ማረፊያ የለውም። ቀደም ሲል የሚመጡለትን ደብዳቤዎች እየከፈትኩ አንብቤ አስፈላጊ ሲሆን እንዲመጣና ጉዳዩን እንዲያስፈፅም የምጠራው እኔ ነበርኩ። አሁን ምን ሆኖ እንደመጣ ሊገባኝ አልቻለም ነበር። እውነቴን ነው። ይመጣል ብዬ ምንም አልጠረጠርኩም ነበር።ነገሩን አልኩ እንጂ እንኳን መጣ –ሚጥሚጣ አልቆብኝ ነበር። ኤንቬስተሩ ጎረቤቴ የጠቀመኝ ጉዳይ ቢኖር ሚጥሚጣና በርበሬ ነው።

ቤት ገብቶ ተቀምጦ ጨዋታ ሲጀመር ነው ተመልሶ የመጣበት ምክንያት የገባኝ።

– እንዴት ነው አዲስ አበባ??
– ደህና ነው። አሁን ሸገርን ብታያት አታውቃትም። ፎቁን ብታየው ከአውሮፓ አይተናነስም።
– ችግር ጠፍታለች በለኛ።
– ችግርማ ምን ይጠፋል። እንኳን እዚያ ከዚህም አልጠፋ።
– ለመሆኑ ቢዝነስ እንዴት ነው?
– እነዚህ ሰዎች መች ያሠራሉ ብለህ?/— ከምንም ይሻላል እንጂ ያው ነው።
– ያ ወደ አቃቂ አገኘሁት ያልከውስ መሬት?
– እሱማ ምን ዋጋ አለው። መሬት እንደ ድሮው አይደለም። አሁን ማንም አይገዛህም።አፋን ከፍቶ ቁጭ ብሏል። መኖሪያ ቢሆን እንኳ ጥሩ ነበር። የሆነ ፋብሪካ እተክልበታለሁ ብዬ ነበር የተሰጠኝ ፣ ያውም ሰንትና ስንት ብር ሙስና ሰርቼበት ( ጉቦ ሰጥቼበት )።

ከላይ ስለ መሬት አንስቼላችሁ ነበር።ባሁኑ ወቅት ኢንቬስተሮች የያዙትን መሬት የሚገዛቸው እንዳጡ ሰምታችኋል። ወያኔም እየተከታተላቸው ነው። ምርጫው እንደሆነ አልቋል- ለምን ይፈልጋቸዋል? እንደጎረቤቴ የመሬት ችግር የደረሰበት ኢንቬስተር ” እነዚህ ሰዎች መቼ ያሠሩና ” ቢላችሁ ስለጉዳዩ ግራ አይግባችሁ፡፡ በምርጫው ሰሞን ወያኔ ያደርግላቸዉ የነበረውን እንክብካቤ ቀነሰ ማለት ነው። የኢንቬስተር መፈክር ” የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ” ነው። ወያኔ መሬት ለውጭ ዜጎች እየቸበቸበ ገንዘቡን ወደ ውጭ ያጉዛል። እነዚህ ደግሞ ከወያኔ መሬት እየወሰዱ እየሸጡ ያተርፋሉ። ጨዋታው እየሞቀ ሲመጣ “ ለመሆኑ እንዴት ነው ፌስ ቡክ የሚገባው?– የሚከራዩት ነገር ነው?“ ብሎ ሲጠይቀኝ ነው ጎረቤቴ ከአዲስ አበባ የተመለሰበት ዋና ጉዳይ የገባኝ። እዉነት እዉነት እላችሁአለሁ ፡ከገባችሁ እንደኔዉ ከልባችሁ ትስቃላችሁ።

ጎረቤቴ ሲበር የመጣው እንደ 97ቱ ምርጫ አብዮት ከፈነዳ በግርግሩ መሃል እጅ ከፍንጅ እንዳይያዝ ነው “ጉዳዩ ሰክኖ እስኪጣራ ገለል ለማለት ፈትለክ ያለው። ፌስ ቡክ ምን እንደሆነም አያውቅም ፡ የሚከራይ መስሎታል። የግብፅ አብዮት በፌስ ቡክ ነው የተጀመረው የሚሉትን ሰምቶ ነው። የእኛ አብዮቱ በፌስ ቡክ ቢፈነዳ እጅ ከፍንጅ ሊያዝ ሆኖ ታሰበዉና ነዉ ሲከንፍ መምጣቱ። – ነገሩ እንዳልገባኝ ሆኜ፡ ” ፌስ ቡክ ምን ይሠራልሃል?“ ብዬ ጠየቅሁት።
– “አንተ ደግሞ ምን ይሠራልሃል ታበዛለህ። ከዚህ በፊት በላፕ ቶፕ ምክንያት ምን እንዳልከኝ ታስታውሳለህ?”

የላፕ ቶፑ ታሪክ እንዲህ ነው። ኮምፒተር ካላጋዛኸኝ ብሎ ጨቀጨቀኝ። አዲስ ምን ይሰራልሃል? ውድ ነው። አሮጌ ግዛና ተለማመድ ከዚያ አዲሱን ትገዛለህ አልኩት። ይህ አነጋገሬ ደስ አላለውም። ቅር ከሚለዉ ብዬ አብረን ሄደን ገዛንና ተገጠመ። ስለአጠቃቀሙም አሳየሁት። ሰንበትበት ብዬ ቤቱ ስሄድ ኮምፒዉተሩን ዳንቴል አልብሶት እንደ ድሮ ግራማፎን ለቤት ማስጌጫነት አስቀምጦት አየሁት። ከካርታ ጨዋታ ያለፈ የረባ ነገር ሠርቶበትም አያውቅም። ግን ጎረቤቴ ከሌሎች አይነስ እንጂ ምን ጨንቆት ! ቆይቶ ደግሞ ከውጭ ሀገር ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ሰዎች ላፕ ቶፕ ይዘው ተመልክቶ ካልገዛሁ ብሎ ይለኛል።” እቤት ያለውንም አልተጠቀምክበትም ምን ይሰራልሃል?“ አልኩት :፡ አዲስ አበባ ስዊስ ካፌ ገብቶ ሌሎቹ ከውጭ የመጡ ተስተናጋጆች ላፕ ቶፓቸውን ከፍተዉ ሲዝናኑ እሱ ብቻ ባዶውን በመቀመጡ እንዴት እንዳፈረ ነገረኝ። ነገሩ “አሳማኝ” ነበርና ተገዛና ይዞት ሄደ። ያንንም ቢሆን ፈጽሞ እንዳልተጠቀመበት ደግሞ እርግጠኛ ነኝ።

አሁን ደግሞ ፌስ ቡክ እንደ ላፕ ቶፕ መስሎት ሊገዛ ወይም ሊከራይ ነው የመጣው። ጎረቤቴ ሰው ፊት አላውቅም ማለትን አይወድም። የግብፅ አብዮት በፌስ ቡክ ነው የተጀመረዉ የሚለዉን ዜና አዳምጦአል። ሁሉም ሰዉ ፌስ ቡክ አለው ሲባልም ሰምቷል። ስለ አዲሱ የግንኙነት መረብ ጠንቅቆ አለማወቁ ይህን ያህል ችግር አልነበረዉም ፡– ፌስ ቡክ ለሁላችንም ቢሆን ገና አዲስ ነገር ነዉ። “ፌስ ቡክ የሚሸጥ አይደለም። ኢንተርኔት ካለህ ፌስ ቡክ መክፈት ትችላለህ ብዬ አስረዳሁ”። መክፈት እንደሚፈልግ ነግሮኝ እንድከፍትለት ጠየቀኝ። እናም ከፈትኩለት። “ የግብጽ አብዮት የት አለ?“ አለኝ። የግብፅ አብዮት በፌስ ቡክ ነው ሲሉት አብዮቱ ፌስ ቡክ ውስጥ ያለ መስሎታል። ስለፌስ ቡክ በደንብ አስረዳሁት።

ኢንቬስተሩ ጎረቤቴና መሰሎቹ ያሳዝኑኛል። ሃብታም ለመሆን በማለም ሕይወታቸውን በቀን ሕልም ይኖሩታል። ሃገር የሚባል ለእነርሱ ትርጉም የለውም። ከጥቂት አሠርታት በፊት ያገር የወገን ችግር እንቅልፍ ያሳጣቸዉ ጀግኖች “መሬት ለአራሹ “ብለው ሲታገሉ ተጨፍጭፈዋል። ጎረቤቴና እርሱን የመሳሰሉቱ የዘመን ጉዶች ደግሞ መሬት ለራሴ ብለው ሊሞቱ ነው።

ለመሆኑ እዚያች ሃገር ዉስጥ አብዮት ቢነሳና ፣በሙስና ከሕዝብ የተዘረፈ ሐብትና ንብረት ሁሉ እንደ ሙባረክ ገንዘብ ይሰብሰብ ሲባል ምን ሊኮን ነው?? ከዚህ ያውጣን . . .። ወያኔ ያፈራው ሃብታም አብዛኛዉኑ በሙስና የከበረ መሆኑንና ስንቶች ደግሞ ለዜጎች መብትና ለአገር ክብር በሚደረግ ትግል ሽፋን ዘዉ ብለዉ ከገቡበት የፖለቲካ ንግድ ለቱጃርነት የሚያበቃቸዉን ያህል ወረት እንዳፈሱ የኢትዮጵያ ህዝብ አሳምሮ ያዉቃል። በቁርጠኛዉ ቀንም ሰልፋቸዉ ከማን ጋር እንደሚሆን ለመገንዘብ ደግሞ ነቢይነት የግድ አይሆንም።”ከራበዉ ለጠገበ አዝናለሁ”ያለዉ ማን ነበር???

ለዛሬው እዚህ ይብቃኝ።

ስለ ሃገራቸው የሚያስቡ ሰላም ይክረሙ !

በልጅግ አሊ Beljig.ali@gmail.com
ሎንዶን የካቲት 2011

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 23, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.