ሞኝ ቢያፍር ዘመዱ ይነፍር

ጥበበኛው
አለመ
ተለመ
ለዓለም ዕጁን ሰጠ
ረከሰ ቀለጠ አረጠ
መክሊቱን ሰበረ
ለሆዱ አደረ
ዓይን ሳለው ታወረ
ጆሮው ተደፈነ አንደበቱን ዘጋው
የውስጥን ፍሰሐ እውነትን ዘነጋው
ጨውና በርበሬ ዛሩን ተረከበው
የጥበብ ሰው ሃብቱ
እውነት ውበት ፍቅር
ገቡ ከመቃብር
እውነትና ንጋት አልታይህ አለው
ከርሱ አይኑን ጋረደው
የጥበብ መክሊቱን ዛሩን መነጨቀው
ሳይኖሩ መኖርን ሆድ አምላክ ሹክ አለው
ከገነት አውጥቶ ጎዳና ላይ ጣለው
ጥበብ እኮ እውነት ናት
ብርሃን የሞላባት
በሸራ በቀለም በብሩሽ በብዕር
አሊያም በአንደበት የሚገለጽባት
የኛ ጠበቢባን ግን ጥበብን አገሟት
በዕለት ኑሮ ጉዳይ በከርስ ለወጧት
ሲነገር የነበር
ስንሰማው የነበር
የጥበብ ሰው ሀብቱ
ሕዝብ ነው ቅሪቱ
ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ ለሰው ልጅ ነፃነት
እንደ ሻማ ቀልጦ ብርሃን ለመስጠት
እሱ ጥሙን ሳይቆርጥ ታዳሚ እንዲረካ
ይህ ነበር ግዳዩ የጥበብ ሰው ዱካ
ማሪያ ማኬቪያ ያቺ እንቁ ድምጻዊት
እንዴት ገለጸቸው የአፖርታይድን እልቂት
እውቁ ሰው ቦብ ማርሌይ የሪጌው አቀንቃኝ
ለሰው ልጅ ነፃነት በቋጠረው ስንኝ
ምንጊዜም ህያው ነው ስራው ያሰጠራዋል
ስንት ዓመት አለፈው ማን ይዘነጋዋል
የኛው ሰው በዓሉ በብዕሩ የሞተው
ጥበብ ከሃብት በልጣ ስለጠራቸው ነው
የኛዎቹ አርቲስቶች ጊዜ የፈጠራቸው
የሕዝብ ጠላት ሆኑ ሕዝብ ሳይጠላቸው
ያ የአገራቸው ሕዝብ ነፃነት የጠማው
ለመብቱ ሲነሳ ጥይት የሚቀምሰው
የጥበብ ሰዎችን ከልብ የሚወደው
ከመሬት አንስቶ ለዚህ ያበቃቸው
ይህንን ምስኪን ሕዝብ አናውቅህም አሉት
ግፍ በደል ስቃዩን አላየንም ብለው ለዘላለም ካዱት
ስብሰባ እንቶፈንቶ ጉባኤ አስጠርቶ
የግድ ሳይመስል ውስጡ ተደስቶ
የጥበብ የዛሩን መክሊቱን ሳይፈራ
ወዶ ተሰልፎ መስመር ገብቶ ተራ
ግድያ ጭፍጨፋው
ስቃይ እንግልቱ
እስርና አፈናው
ስርቆትና ዝርፊያው ይቀጥል እያሉ
አርቲስቶች በአንድ ሆነው አጨበጨቡ አሉ
መክሊት ደህና ሰንብች ቀለጡ አረጡ
ለገዳዩ መሪ ከወርቅ የተሰራ ብዕር አሰቀመጡ

ሐምሌ 5 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም
ዶኑ ከላስቬጋስ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 14, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.