ምርጫ እና የወያኔ ቀልድ – ሪፖርተር እንደዘገበው

funny1.jpg…ብዙ ቦታዎች ላይ የተለጠፈው የምርጫው ቅፅ ከሚከተሉት አንዱን ይምረጡ ይልና ምርጫዎቹ ሀ/ ኢሕአዴግ ለ/ ኢሕአዴግ ሐ/ ኢሕአዴግ መ/ ኢሕአዴግ ሠ/ ኢሕአዴግ የሚሉ ናቸው፡፡ ብቻውን የሮጠ እንደማይሸነፍ ሁሉ አሸናፊም ለመባል አስቸጋሪ ነው? እንዴት? ለአንድ መድብለ ፓርቲ ስርዓትን እከተላለሁ ለሚል ሀገር ደግሞ ጉዳዩ አሳፋሪ ይሆናል፡፡…

ቀዝቃዛው ምርጫ

Sunday, 13 April 2008
በመጀመሪያ ኢሕአዴግ ነበረ፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም አጥብቆ ይሻ ነበር፡፡ በሁለት ብሔራዊ ምርጫዎች ምኞቱ አልተሳካለትም፡፡ በሦስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ግን የልቡ ሰምሮለት ቅንጅትና ህብረት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ቀረቡ፡፡ ኢሕአዴግ ግን መስለው እንጂ ሆነው አይደለም ብሏል፡፡

ምርጫ ቦርድ ያፀደቀላቸውና እነሱ ያንሳል ያሉት የፓርላማ 166 ወንበር እንደ ኢሕአዴግ ባለሥልጣን አባባል የተገኘው በንፋስ ኃይል እንጂ በሕዝቡ ፈቃድ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ምርጫ ግን ሁለቱ ኃይል ተፎካካሪዎችና ኢሕአዴግን በወቅቱ ያራዱት ተቃዋሚ ድርጅቶች የሉበትም፡፡

ዛሬ ከሦስት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ኢሕአዴግ ንፋሱን የገደበ ሲሆን ሁለቱ ዋነኛ ተቃዋሚዎች ያሉበት ሁኔታም ከንፈር ያስመጥጣል፡፡ ቅንጅቱ ለቁጥር ለሚታክት ቦታ ተበጣጥቋል፡፡ የአቶ አየለ ጫሚሶ ቅንጅት ሁለት ጣትን በሁለት እጅ ምልክት ከመተካቱ ውጭ ቅንጅትን ጠንካራ ያደረጉትን አሰራርም ሆነ አባላት እንዳልያዘ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ ስሙን ለዚህ አካል የሰጠውም መሸከም እንደማይችል በሚገባ ስላረጋገጠ ነው ይላሉ እነዚሁ አስተያየት ሰጭዎች፡፡ የአቶ ልደቱ አያሌው ኢዴአፓ መድኅን በድህረ ምርጫ 97 ከተፈጠረበት ችግር እስከአሁንም ያገገመ አይመስልም፡፡ ብዙዎቹን አባላትና አሰራሩን እንደያዘ እየገለፀ የሚገኘውና በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ቡድን እንደ አንድ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ገና ያልተቋቋመ በመሆኑ ምርጫው አይመለከተውም፡፡

ህብረቱን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎ የነበረው ኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በተፈጠረ አለመግባበት ከተበጣበጠ በኋላ ለአቶ ተስፋዬ ቶሎሳ ተሰጥቷል፡፡ የፓርቲውን ብዙሀንና እውነተኛ አባላት አይወክልም ያሉት እነ ዶ/ር መራራ ጉዲና ኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ (ኦህኮ) በማለት አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መሠረቱ፡፡ እንደ ዶ/ሩ ገለፃ ይህ የተደረገው ኦብኮንና ህብረቱን ለማዳከም መንግሥት ስለፈለገ ነው፡፡

በዛሬው ምርጫ ከቀድሞው ቅንጅት አባላት የስሙ ባለቤት የእነ አቶ አየለ ጫሚሶ ቡድንና ኢዴአፓ መድኅን ይወዳደራሉ፡፡ ህብረቱ ግን የውድድር መድረኩ የተመጣጠነ ባለመሆኑ ባለፈው ሀሙስ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን አስታውቋል፡፡

በመሠረቱ ለህብረቱም ሆነ ለቅንጅት መዳከም መንስኤው ኢህአዴግ ነው የሚለው ነገር ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት አይቻልም፡፡ የአባሎቻቸው የታጋይነት መንፈስ፣ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር፣ አስተማማኝ የፓርቲ ዲሲኘሊን በተለይም ደግሞ ተባብሮና ተቻችሎ የመስራት ፈቃደኝነት እንደሌላቸው በገሀድ ታይቷል፡፡

ሀገር ለማስተዳደር በአደባባይ ሲምሉ የነበሩት ፓርቲዎች፣ መሪዎቻቸውን ማስታረቅ ተስኗቸው አንዱ አንዱን ‘የስልጣን ጥመኛ ነው’፣ ‘የመንግሥት ጥገኛ ነው’፣ ‘ዘረኛ ነው’፣ ‘የአመራር ብቃት የለውም’፣ ‘አርጅቷል’፣ ‘ገና ጥሬ ነው’ . . . . እያለ ከእለት እለት ልዩነታቸው ሰፍቶ አንድነታቸው አፋዊ ሆኖ ታይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የሚለኒየም ዓመት ኩርፊያና ፀቡ ቀርቶ በይቅር መባባል እንዲተካ እኔነት በእኛ ተተክቶ ህብረተሰባዊ ብልፅግና እንዲመጣ ዜጎች በቃል ደረጃ ይገባቡ እንጂ ዓመቱ እስከአሁን ብዙ ምስቅልቅሎች አሳይቶናል፡፡ መንግሥት መንግሥትን የዘረፈ እስኪመስል ድረስ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በመሬት አስተዳደርና በመሳሰሉት ቦታዎች ከፍተኛ የሙስና ተግባር ተከስቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከቁይጥር ውጭ እየሆነ ነው፡፡

ፓርቲ ህብረተሰብ አቀፍ ሲሆን የውይይት መድረኮችን ይፈጥራል፡፡ ጥናትና ምርምር በማድረግም የሀገሪቷን ችግሮች አንጥሮና አጥርቶ ያውቃል፡፡ መፍትሔ ለመስጠትም በአባላቱ አቅም ይሞክራል፡፡ የፓርቲው መፍትሔዎች የአስፈፃሚነት ኃይል ስለሌለው ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ ይሁንና በቋሚነት የመንግሥት ፖሊሲ አውጭዎችና አስፈፃሚዎች በሀሳቡ እንዲያምኑ ለማድረግ ድርጅታዊና ማህበረሰባዊ ጫናዎችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ አማራጭ ሀሳቡ ያለ ጥርጥር የመፍትሔው ቁልፍ አካል ከሆነ አስፈፃሚውንና ፖሊሲ አውጭውን በድፍኑ በመተቸት ሳይሆን በስነ አመንክዮና ተፈጥሯዊ ምክንያት በመከራከር በመወያየትና በመተማመን ለእነሱ አማራጭ ሃሳብ ተቀባይነት ያለማቋረጥ መሥራት አለባቸው፡፡

ይህን ስንል ግን ኢሕአዴግ ቅዱስ ድርጅት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ደግሞ አመፀኞች ናቸው እያልን አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አሁንም ለተቃዋሚ ድርጅቶች መጠናከር ተባባሪ አይደለም፡፡ የሕዝብን ንብረት ሚዲያንና ሌሎች የመንግሥት መገልገያ መሳሪያዎችን ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ ይጠቀማል፡፡ በዚህ በመታገዝም አባላቱን በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡ ኢሕአዴግ አባላቱን አራት ሚሊዮን አድርሻለሁ ሲለን የእኛኑ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህት፣ አጎት፣ አክስት . . . እየመለመለ ነው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግን ለመታገል ከቤት ውስጥ የሂሳብ መፋጨት መጀመር ይቻላል ማለት ነው፡፡

ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀዳሚ አጀንዳቸው የሆነውን ሥልጣን መያዝን ባንኮንንም ሌሎች ትኩረት የሚሹ ተግባራትም አለባቸው፡፡ ኀብረት ራሱን ከምርጫ ለማግለል አባላቶቼ እየታሰሩ፣ እየተገፉ፣ እየተገደሉ ነው፡፡ ቢሮዎቼ እየተዘጉ ነው ብሏል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የምናነሳው ቅሬታ ዋጋው ያንስ ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አሳሪዎቹ፣ ገራፊዎቹና ገዳዮቹ ብሎም ቢሮ አሻጊዎቹ የማይደረሱባቸው ዜጎች አይደሉም፡፡ እነሱም የእኛው ወገኖች ናቸው፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መልካም ዜጋ ሀገሪቷ እንድታፈራ፣ ታማኝና ጠንካራ ሚዲያ እንዲኖራት፣ ንቃተ ህሊናው የጎለበተ ሲቪክ ማኀበረሰብ እንዲዳብር፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚሰማው የመንግሥት ሠራተኛ እንዲበራከት፣ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሥራቸውን እንዲሰሩ፣ ፓርላማው ያለ ገደብ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ቦታ እንዲሆን፣ ለድርጅት ሳይሆን ለሀገር ታማኝ የሆኑ አስፈፃሚዎች እንዲኖሩ ለማገዝ የምርጫ ዋዜማን መጠበቅ አይኖርባቸውም፡፡

ኢሕአዴግ 17 ዓመት የመምራት ልምዱን ተጠቅሞ ሰፊ ድርጅታዊ መዋቅር፣ ጠንካራ አቅም፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት፣ የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዳለው እየነገረን ነወ፡፡ ይህ ከሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ያለማቋረጥ አፈና፣ እስር፣ ድብደባ፣ ግድያ . . . እየተፈፀመባቸው እንደሆነ እየገለፁ ነው፡፡ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባቀረቡት እጩ ብቻ ውጤቱ ቢገለፅ ኢሕአዴግ ያለ ምንም ችግር በበላይነት እንደሚያጠናቅቅ ምንም ጥርጥር የለም፡፡

ብዙ ቦታዎች ላይ የተለጠፈው የምርጫው ቅፅ ከሚከተሉት አንዱን ይምረጡ ይልና ምርጫዎቹ ሀ/ ኢሕአዴግ ለ/ ኢሕአዴግ ሐ/ ኢሕአዴግ መ/ ኢሕአዴግ ሠ/ ኢሕአዴግ የሚሉ ናቸው፡፡ ብቻውን የሮጠ እንደማይሸነፍ ሁሉ አሸናፊም ለመባል አስቸጋሪ ነው? እንዴት? ለአንድ መድብለ ፓርቲ ስርዓትን እከተላለሁ ለሚል ሀገር ደግሞ ጉዳዩ አሳፋሪ ይሆናል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ሕዝቡ የእነሱን አመራር እንደሚመርጥ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ሕዝቡ የተጀመረውን ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ብልፅግናና ልማት መቀጠል እንጂ አመፀኞቹን አይመርጥም ቢመርጥም ተታሎ እንጂ በእውቀት አይደለም ነው የሚለው፡፡

ለሕዝቡ የሁለቱም መኖር ያስፈልገዋል፡፡ መናናቃቸውና አለመስማማታቸው ያስከፋዋል፡፡ ሁለቱም ቢጠናከሩ የጋራ አጀንዳ ቢኖሯቸውና ልዩነታቸውም የሀሳብ ብቻ እንዲሆን ይሻል፡፡ የሰው ልጅ የፈለገውን የመምረጥ፣ የማሰብና የመናገር ነፃነቱ ተከብሮ እንዲኖር የዘወትር ምኞቱ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት በሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና መልካም አስተዳደር በኩል ስኬት እንዲያስመዘግብ የሁሉም ዜጋ ፍላጎት ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የተሻለ ለመስራት ለሥልጣን የሚፎካከሩ ከዚያ በመለስም ለመንግሥት እንዲሰራው ለሕዝብ እንዲያየው አማራጭ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ የመራጩንም ሆነ የተመራጩን ዜጋ ንቃተ ህሊና የሚያዳብር ተከታታይ ግፊት (lobby) ያደርጋሉ፡፡

ከዚህ ሰላማዊ ፉክክር ተጠቃሚ የሚሆነው ሕዝቡ ነወ፡፡ ሕዝቡ የራሱን ፍላጎት ለማሟላት ግብአት የሚያደርገውና በስሙ የሚነግድበት አካል አይፈልግም፡፡ አምባገነን መንግሥትና አስመሳይ ተቃዋሚ አይፈልግም፡፡ ከአቅሙ በላይ የሆነበትን ችግር፣ መከራ የሚያጠፋለት ባያገኝ የሚቀንስለት አካል አጥብቆ ይሻል፡፡

ሕዝቡ ከዓመታት በኋላ በሚመጣ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በእለት ከእለት ሕይወቱ መንግሥትንና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቆጣጠር ይችላል፡፡ የሚገቡትን ቃል እንዲያስፈፅሙ መጠየቅ ሲዋሹና ሲያጭበረብሩም እስከ መጨረሻው መጫን ያስፈልጋል፡፡ የማይታየውንና የማይዳሰሰውን ድርጅት በአባላቱ በኩል በቤታችን በጎረቤቶቻችን ያለፍርሃት በነፃነት ጫና ማድረግ አለባቸው፡፡

ለጊዜው ግን የዛሬው ቀዝቃዛ ምርጫ ሲካሄድ መንግሥት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና መራጩ ሕዝብ ከዲሞክራሲ ተቋማት ጋር በመሆን የሞቀ ምርጫ በመጭው 2ዐዐ2 ለማድረግ እንዴት ይቻላል? የሚል ጥያቄ እየጠየቀ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዝቃዜን ሳናውቀው ሙቀትን እንዴት እንወዳለን?

በሰለሞን ጎሹ

Source: Reporter

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 14, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.