ማሞ ውድነህ የህይወት ታሪክ ዳሰሳ

የአቶ ማሞ ውድነህ የቀብር ስነ ስር ዓት ዛሬ በቅድስተ ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል። ከዚህ በመቀጠል አድማስ ሬዲዮ ያቀናበረውን የደራሲውን የህይወት ታሪክ ዳሰሳ አቅርበናል።

በወሎ ክፍለ ሃገር ፣ የዛሬ 81 ዓመት የተወለዱት ማሞ ውድነህ፣ ወላጆቻቸውን በአምስቱ አመት የጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው ያጡት። ማሞ ውድነህ 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁት ገና በ 15 ዓመት እድሜያቸው መሆኑ በጊዜው ተደናቂ ወጣት አድርጓቸው ነበር። ከዚያም ወደ ጽሁፍ ዓለም በመዝለቅ እጅግ በርክታ መጻህፍትን ሲጽፉ፣ ብዙዎች፣ በተለይ በስለላ ሥራ ላይ ያተኮሩ መጻህፍትን ተርጉመዋል።
በ1948 ዓ.ም. መጻፍ የጀመሩት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ የመጀመርያ ጽሑፋቸው ባለ 160 ገጽ የሆነውና በትያትር የተተወነው “የሴትዋን ፈተና – አለፈ በደህና” የሚል ነበር፡፡

በውጭ ቋንቋ የተጻፏት ታሪኮች ወደ አማርኛ በመመለስና በመድረስ እስከአሁን 53 መጻሕፍት ለሕዝብ ያቀረቡት ማሞ ውድነህ፣ በአጠቃላይ ከ200 በላይ ግጥሞች እንዳlቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡ አንዳንድ ግጥሞቻቸው ቀደም ሲል አዲስ አበባና አሥመራ በታተሙ ጋዜጦች መወጣታቸውን ሌሎቹ ደግሞ እንዳይታተሙ ሳንሱር “ከልክሏቸውና ቆራርጧቸው” የቀሩ እንደነበሩም በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

በ1960 ዓ.ም. “ብዕር እንደዋዛ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ ግጥሞቻቸው ለሕዝብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ግጥሞቻቸው የበርካታ ወጣቶች ታሪካዊነትንና መንፈሳዊነትን እንደቀሰሙበት እምነታቸው መሆኑን ገልጸው ነበር።

በአብዛኛው በስለላና በወንጀል የሚያጠነጥኑ የትርጉም ሥራዎቻቸውና ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ቀረኝ የምትለው ነገር አለህ ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት፣ “የምችለውን ያህል ወርውሬያለሁ፤ እኮራበታለሁኝ፤ ቀረኝ የምለው ነገር የለኝም፤” በማለት ነበር፡፡ ማሞ ውድነህ የሥራዎቻቸው ሕዝባዊነትና ባሕል አክባሪነትን አስመልክተው በሰጡት አስተያየትም “ከሕዝብ የወሰድኩትን ነው፤ ወደ ሕዝብ መልሼ የሰጠሁት፤” ነበር ያሉት።
ማሞ ውድነህ ቀደምት ከሆኑት ጋዜጠኞች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ “ፖሊስና እርምጃው” የሚባል ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅም ነበሩ። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በተለይ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በአሥመራም ጭምር ለረጅም ጊዜ ሰርተዋል።

ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አልማዝ ገብሩ፣ 52 ዓመት በትዳር ያሳለፉት ማሞ ውድነህ፣ አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ ተምሳሌት ስለመሆናቸው በሚያውቋቸው ሰዎች አፍ ይመሰከራል። ማሞ ውድነህ “በትዳር ለረዥም ጊዜ ለመኖርዎ ሚስጥሩ ምንድነው?” ተብለው ከዚህ በፊት ተጠይቀው ሲመልሱ፣ “መተማመንና መቻቻል” በሚል በአጭሩ የገለጹት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ልጆቻቸው አንድም ቀን ጭቅጭቅ ሰምተው እንደማያውቁ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ “ችግር ሲኖር ቤት ቆልፈን እንነጋርበታለን” በማለት ልጆቻቸው አንድም ክፉ ቃል ሳይሰሙ ማደጋቸውን ይናገራሉ፡፡

ስድስት የልጅ ልጆችን ለማየት ያዩት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ “ሀብታችን ልጆቻችን ናቸው፤” በማለት ይናገሩም ነበር፡፡ “ራሴ ለራሴ ታማኝ ነኝ፤” የሚሉት ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ውጭ በልተው ሲገቡ አንድም ቀን ባዶ እጃቸውን እቤት ገብተው እንዳማያውቁ መልካም ልምዳቸውን ታዳሚዎች አካፍለዋል፡፡

ባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ ገብሩም “ባለቤትዎ ማሞ ውድነህ፣ አንድም ቀን ጎሸም አድርገዎ አያውቁም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ጎሽሞኝ ቢሆን አንድም ቀን አላድርም ነበር፤” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ማሞ ውድነህ ከሁለት ዓመት በፊት ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አልማዝ ገብሩ ጋር በጋብቻ የተሳሰሩበትን 50ኛ ዓመት በአዲስ አበባ ፣ ሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ሲያከብሩ ….
“እስቲ ልጠይቅሽ እቴ ባለቤቴ
ሳትግደረደሪ ንገሪኝ በሞቴ፡፡
የጥቅምት ጊዮርጊስ በሃምሳ ሁለት
ባሸበረቀችው የማክሰኞ ዕለት
ሃያ ዘጠነኛው የጃንሆይ ዘውድ በዓል
በተከበረበት ሆኖ የአገር ባህል
ከሰዓት በኋላ እቤቴ መጥተሽ
አራዳ ልትሔጅ እንዲያ ተሽሞንሙነሽ?
ከቤት ልትወጭ ስትይ ጎተት ባደርግሽ
በስሜት በፍቅር ወዲያው ተረትተሽ
ሸብረክ አላልሽም ወይ ከድንኳ አልጋ ላይ?
ምን ነበር ምስጢሩ ትዝ ይልሻል ወይ?”
በሚል ግጥም ፍቅራቸውን አስታውሰዋል።
ይህ ግጥም፣ አቶ ማሞ ውድነህ “የአርባ ዓመቱ ጉዞ!” በሚል ርእስ በ53ኛው መጽሐፋቸው “ከመሬት እስከ ኮሜት” የግጥም መድበል ውስጥ ካሰፈሩት ረዥም ግጥም የተወሰደ ነው፡፡ ገጣሚው ሦስት ጉልቻ የጎለቱበትን 40ኛ ዓመታቸውን ለማስታወስ በ1992 ዓ.ም. የገጠሙት ግጥምም ነበር፡፡ አቶ ማሞ ውድነህ፣ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አልማዝ ገብሩ ጋር 50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓላቸውን በሀገር ፍቅር ቴአትር ሰኔ 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ባከበሩ ጊዜም ግጥሙን ዳግመኛ አቅርበውታል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ወደ ሥነ ጽሑፉ በጥልቀት እንዲገቡ ምክንያት የሆናቸውን አጋጣሚ ሲናገሩም … በ1952 ዓ.ም. በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ “የት ትገኛለች?” በሚል ለጻፏት መጣጥፍ “እሱስ የት ይገኛል?” በሚል ከዕውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በተሰጠው ምላሽ ለረጅም ጊዜ ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የወግ ልዩነት አስመልክቶ የተደረገ ሙግትም ነበር፡፡ በወቅቱ በሕዝብ በስፋት ተነባቢ በነበረው በዚሁ ጋዜጣ የቀጠሉት ክርክር እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ አነጋጋሪ ለመሆን እንደበቃ ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ የነበሩት አቶ መኰንን ሀብተ ወልድ “ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው፤” በማለት መጠናት አለበት በሚል እነ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሉበት ኮሚቴ መቋቋሙን በህይወት በነበሩበት ጊዜ ተርከዋል።

ኮሚቴው ሁለቱንም ተከራካሪዎች ጠርቶ ባነጋገራቸው ወቅት፣ ፀሐፊዎቹ ፊት ለፊት ቢገናኙ ይገዳደላሉ ተብሎ በሕዝቡ ይናፈስ በነበረው ወሬ ምክንያት ኮሚቴው ፖሊስ ይዞ ቢቀርብም፣ ተከራካሪዎቹ ማሞ ውድነህና ጳውሎስ ኞኞ ተሳስቀው መሳሳማቸው የኮሚቴው አባላትን ያስደነቀ ክሥተት ነበር ይላሉ፡፡

አቶ ተስፋዬ የተባሉት ፀሐፊ ከደራሲ ማሞ ጋር የሚተዋወቁት ከ50 ዓመት በፊት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከቀድሞ ዝነኛ ጋዜጠኞችና የጋዜጣ መሥራቾች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሚጽፉትና የሚዳስሱት ሐሳብም አነጋጋሪ እንደነበር አውስተዋል፡፡ አቶ ማዕረጉ በዛብህ የተባሉት ጸሃፊም፣ “ስብሐት ገብረ እግዚአብሔና ማሞ ውድነህ፣ ሰው ሰው የሚሸት የጋዜጠኝነት ሥራ መሥራት የቻሉ ናቸው” ብለው መስክረውላቸዋል።

ደራሲ ማሞ ውድነህ እንዲያውም አንድ ቀን ለፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በየካቲት መጽሔት፣ “የአገራችን የባህል ልብስ ለብሰው ቢታዩስ?” በሚል ባቀረቡት ጥያቄ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ማዕረጉ በዛብህ 150 ብር እንዳስቀጣቸው ይናገራሉ፡፡
ደራሲ ማሞ ለሁለት ወራት ያህል በተለያዩ ሆስፒታሎች ተኝተው ሲታከሙ የነበረ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በሆስፒታሎቹ አያያዝና በቂ ህክምናም ማግኘት እንዳልቻሉ ሲያማርሩ ቆይተዋል። ህይወታቸው ከማለፉት ከሁለት ሳምንት በፊት በታዲያስ አዲስ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ቀርበው “ዘፋኝ ሲታምም ብቻ ነው የሚያሳክመው የሚበዛው? እኛ ጸሃፊያንም እኮ ለአገራችን ብዙ ሰርተናል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አድማስ ሬዲዮና ድንቅ መጽሔት ለደራሲ ማሞ የነፍስ እረፍትን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው ደግሞ መጽናናትን ይመኛሉ።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 3, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.