“መንግስት በህዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሀት አለበት” ጋዜጠኛ ሀብታም መዝሙር

habtam mezmur [Read in PDF] ጋዜጠኛ ሀብታም፡ መዝሙር ደስታ ትባላለች፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ እንዲሁም የዜና አገልግሎት ድርጅቱ ሪፖርተር በመሆን አገልግላለች፡፡ ጋዜጠኛ ሀብታም: በዴንማርክ ኮፐን ሀገን ከዲሴምበር 5 እስከ 19 ድረስ ሲካሄድ የነበረውን አለም አቀፍ የአየር ልቀትን መጠን ለመወሰን በተደረገው ጉባኤ ላይ ለመዘገብ ነበር ወደ አውሮፓ የተጓዘችው፡፡ ጋዜጠኛዋ ስራዋን በመሃል በማቋረጥ ለስራዋ የያዘቻቸውን መሳርያዎች በመያዝ የአቶ መለስን መምጣት ይቃወሙ ከነበሩት ወገኖች ጋር ተቀላቅላለች፡፡ ከስካንዲኒቭያ ባልደረባችን አነጋግሯት እንደሚከተለው አቅርቦታል::

በመጀመሪያ ራስሽን ብታስተዋውቂን?

ሀብታም:- ስሜ ሀብታም፡ መዝሙር ደስታ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት በጎንደር ክፍለ ሀገር ሲሆን፣ ሥራዬ የቴለቢዥንና ራዴዮ ጋዜጠኛ ስሆን አገለግልበት የነበረውም መሥርያ ቤት፣በአዲስ አበባ መስተዳድር፣ የቴሌብዥንና ራድዮ ጋዜጠኝነት ነበር፡፡

እዚህ ለምን መጣሽ?

ሀብታም:- የመጣሁት በዴንማርክ ኮፐን ሀገን ከዲሴምበር 5 እስከ 19 ድረስ ሲካሄድ የነበረውን አለም አቀፍ የአየር ልቀትን መጠን ለመወሰን በተደረገው ጉባኤ ላይ ለመዘገብ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በተለያየ ወቅት ይደረጉ የነበሩትን የየእለቱን ውሎ ስዘግብና ሳስተላልፍ ከርሜ፣በተለይ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ውስጥ ረቡዕ የጠቅላይ ሚንስትሩን ውሎ ከዘገብኩ በኋላ፣ሀሙስ ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚቃወሙትን ኢትዮጵያዊ ወገኖች ተቃውሞ ዘግቤ፣በማስተላለፌ፣ሀይለኛ ተግሳጽና ማስፈራራት አገር ቤት ካሉት አለቆቼና፣ጠቅላይ ሚንስትሩን ካጀቡት ደህንነቶች ስለደረሰብኝ፣አርብ እለት የተረከብኳቸውን መቅረጫ ድምጽና የመሳሰሉትን መሳርያዎቼን በመያዝ ካገሬ ልጆች ከሆኑት የአቶ መለስን መምጣት ከተቃወሙት ወገኖች ጋር ተቀላቀልኩ፡፡

ከጋዜጠኝንት ሞያሽ ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ የፕሬስ ነጻነት አለ ትያለሽ?

ሀብታም:- በአገሪቱ ሀሳብን በነጻነት መግለጽና፥መጻፍ የሚሉት መሠረታዊ መብቶች በወረቀት ላይ የሰፈሩ ቢሆንም፣እነኝህ መብቶች ለአፍ ፍጆታና ፈረንጅን ለማጭበርበርያ የወጡ ህግጋት እንጂ በመስክ ላይ ማንኛውም የመንግሥት ጋዜጠኛም ሆነ የነጻ ጋዜጠኛ፣ሀሳቡንና እምነቱን በነጻነት የማይገልጽበት፣ለመዘገብም ወጥተን ያሰባሰብነውን የህዝብ ድምጽና፣የታዘብነውን ሁኔታ ለመግለጽ ስንሞክር በመንግሥት ሃይሎች ሥራዎቻችን ተውስደው እንደገና ባዲስ መልክ ከውነታው ውጭ ተቀባብተው የሚቀርቡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ የተሳሳተ ዘገባ፣ህብረተሰቡ በኛ የመንግሥት ጋዜጦች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያለው ሲሆን፣ባጠቃላይ ለመንግስቱ የግሉ ውሾች፣በህዝቡ ደግሞ ክፉኛ የምንጠላ ሆነናል፡፡

ይህንን የበለጠ ታብራሪልኛለሽ?

ሀብታም:- ለምሳሌ በዘገባ ወቅት የመስክ ስራ ላይ ሆኜ ያየሁትንና የታዘብኩትን የህብረተሰቡን ችግር አጠናቅሬ ወደቢሮ በምመለስበት ወቅት የላይኛው የምንግስት አካል ዘገባዎቼን ወስዶ እንደገና በመከለስ፣ 50 ሰው ተገኝቷል ያልኩትን መላው ህዝብ በመደገፍ ክ500 በላይ ሰው ተገኝቷል በሚል ፈጠራ ዜናው ተለውጦ የሚቀርብ ሲሆን፣ በተለይ የሪፖሩቱን ዘገባ ለነርሱ በሚያስደስት ሁኔታ ካላቀረብኩት፣ በግምገማ ወቅት፣ የነፍጠኞችን አቋም ነው የምታስተጋቢው በሚል ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ደርሶኝ ነበር፡፡

በግሉ ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ጋዜጠኞች በነጻነት የመስራት መብት የለም ነው የምትይው?

ሀብታም:- ምንም አይነት ነጻነት የለም ከላይ እንደገለጹት፣ያልተገነባውን ተገነባ፣ያላደገውን ኢኮኖሚ በዚህ ቁጥር አድጓል ማለት የተሰጠንን ዘገባ ብቻ ነበር የምንሠራው በቲዎሪ መብት እንዳለን መብት ተሰጥቶን ዘግበን ስንመጣ ግን ያው የሚገጥመን ያው የተለመደ አሰራር ነው፡፡

አሁን በአኢትዮጵያ ያሉትን የነጻ ፕሬስ ውጤቶች እንዴት ታይያቸዋለሽ?

ሀብታም:- ነጻው ፕሬስ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አለ ማለት ውሸት ነው፡፡ ለአለም ህብረተሰብ ማታለያ ሲባል በጣት የሚቆጠሩ እንዲንቃሳቀሱ ከመደረጉ ውጭ በተግባር ሲታይ ጋዜጠኞቹን በክፍታኛ ቅጣት በማስፈራራት ተሸማቀው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡ የፕሬስ ፈቃድ የተከለከሉም አሉ፡፡ ማህበሩ በስም እንጂ በእንቅስቃሴ ሲታይ ምንም በጉልህ የሚታይ ስራ አይሰራም፡፡ ባጠቃላይ የወያኔው ተለጣፊ ማህበር ብቻ ነው በነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ስም የሚንቀሳቀሰው፡፡

በመንግስትና በህዝብ መሀከል ያለው ክፍተት እንዴት ነው?

ሀብታም:- በመንግስትና በህዝብ መሀከል ያለው ክፍተት የትዬ ሌሌ ነው፡፡ ህዝብ መንግስትን አያምንም፣መንግስትም ህዝብን አያምንም፡፡ መንግስት በህዝብ ላይ ከፍተኛ ፍርሀት ስላለበት ባጠቃላይ ሲታይ ባህር ላይ ያለ ብቸኛ ደሴት ነው የሚመስለው፡፡ በተለይ አሁን ደግሞ የምርጫው ወቅት በመድረሱ፣ ህዝብን በማሸማቀቅ፣ማስፈራራት በሚል ዘዴ ሚዲያውን በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀመበት የማይፈልጋቸውን የሚያስደነብርበት አሰራር ነው እየተከተለ ያለው፡፡ ለዚህም ምሳሌ አዲስ ነገርን ማስታወስ ይበቃል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 28, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.