መነገር ያለበት – ከበልጅግ ዓሊ

ሞት፣
እስትንፋስ ሲበጠስ፣ ልብ ሲቆም ምቱን ፣
ሳይንስ እውነት ይላል፣ የሰው ልጅ መሞቱን።
ሳተ!!! ሳይንስ ሳተ፣
እጅግ ተሳሳተ፤
ከረባቱን አስሮ ፣ ሙሉ ልብሱን ለብሶ፤
ስንት አለ የሞተ።
ቴዎድሮስ ታደሰ 

ጉንተር ግራስ (Günter Grass) የኖብል ተሸላሚና የጀርመን ሃገር የጥበብ ሰው “መነገር ያለበት” (Was gesagt werden muss) በሚል ርዕስ በጻፈው የልብን አድራሽ ግጥም ምክንያት እስራኤል ሃገር እግሩ እንዳይረግጥ በእስራኤል መንግሥት ተወስኖበታል።

ግጥሙ የተጻፈው የጀርመን መንግሥት ባሕር ጠላቂና ኒኩለር ተሸካሚ የሆኑ መርከቦችን ለእስራኤል ለመሸጥ በመስማማቱና ወደፊት ከኢራን ጋር ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን ጦርነት በመቃወም ነበር። በጀርመን ቋንቋ የተጻፈው ይህን ግጥም  የእስራኤል ወዳጅ የሆኑ በሙሉ አውግዘውታል። የጀርመን መንግሥትም የድሮ የናዚ ታሪክ እየጎተተው ይህንን ግጥም እንዲያወግዝ ተገዷል። ጉንተር ግን የጻፈው የሚያምንበትን ነውና ውግዘትን ተቀብሎ እውነትን መጻፉን አምኖ “መነገር ያለበትን ለምን ዝም እላለሁ” በሚል የዓለም ፖለቲካ ምን ያህል አድልዎ የተሞላበት መሆኑን አስረድቶናል። እኔም ለዛሬው ጽሁፌ ይህንን የጉንተርን አርዕስት ልጠቀምበት ተዋስኩት።

የጉንተር ጽሁፍ በሃገራችን የስህተት ድግግሞሽ ብዬ የማምንባቸውን ክስተቶች ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ እንዳደርገው ገፋፍቶኛል። ብዙዎቻችን እነዚህ የስህተት ድግግሞሽ የምንላቸውን ብናውቃቸውም ወያኔን ላለማስደስት፣ የተቃዋሚዎችን ክፍፍልን እንዳናስፋፋ ወይም ትኩረታችን በወያኔ ላይ ይሁን ብለን በዝምታ ብንጠብቅም፣ ዝምታችን የሕዝባችንን ስቃይ አበዛው ፣ ትግላችንንም  ከድጡ ወደ ማጡ ወሰደው እንጂ፣ ከዚህ ከዘረኛ መንግሥት የግፍ አገዛዝ አንድ ስንዝር ሊያላቅቀን አልቻለም።

በዚህ 21 ዓመታት ውስጥ ብዙ የሰላማዊ ፣ የመሣሪያና የሁለገብ ትግሎች ተሞክረዋል። እነዚህ ትግሎች የተወሰኑ ውጤቶችን ቢያመጡም ቀጣይነት ባለማሳየታቸው ከሽፈዋል። ብዙ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመው ነበር። እነዚህም ድርጅቶች ኅብረቶችም መሥርተው ተመልክተናል። ዛሬ ግን እነዚህ ድርጅቶች አንዳንዶቹ መኖራቸው ሲያከትም ሌሎቹ ከስም በላይ የሌሉ ናቸው። ምክንያቱ ምንድነው? ብለን በትክክል አጥንተን የሚቀጥለውን ኀብረትም ሆነ ድርጅትም ያቋቋምንበት ወቅት የለም። ቀደምት የተቋቋሙት ሲፈርሱ ወይም ሲደክሙ አዲስ ይቋቋማሉ። አዲሶቹ ደግሞ ቀናቸው ደርሶ ሲፈርሱ አዲሶች ደግሞ ብቅ ይላሉ። ብዙውን ጊዜ ድርጅቶቹ ይቀያየራሉ እንጂ ተዋንያኖቹ እነዛው ናቸው። ለመረጃ ያህል ከኢዴኃቅ እስከ ቅንጅት ከዛም አልፎ አዲስ የሚቋቋሙትን ኅብረቶች ብንመለከት ብዙ ለውጥ አናይም። ምንአልባት ተዋንያኖቹ አዲስ ድርጅቶች ወክለው ይመጡ ይሆናል እንጂ ብዙዎቹን የለመድናቸው ስሞች ሆነው እናገኛቸዋለን።

ኮሚቴ፣ ኅብረት፣ ጥምረት፣ድርጅት ፣ ፓርቲ ሌሎችም በዚህ ትግል ውስጥ ሲመሰረቱ እኛም ስናጨበጭብ፣ ሲከፋፈሉ ተስፋ ስንቆርጥ፣ በእርስ በርሱ ጭቅጭቅ ደክመው ሲተኙ ሌላ ስናቋቁም እንሰከመቼ ነው የምኖረው? ከዚህ በፊት የተፈጠሩት ኅብረቶች ፣ ድርጅቶች፣ ጥምረቶች  ለምን ቀጣይነት አላገኙም ብለን ችግሩን አንጥረን ካላወቅንና መፍትሄ ሳንፈልግ ወደፊት ለሚቋቋሙት ኮሚቴዎች፣ ኅብረቶች፣ ጥምረቶች ወደፊት ላለመከፋፈላቸው፣ እርስ በርስ አለመፋተጋቸው ምን መተማመኛ ይኖረናል?

ወያኔ አዲስ አጀንዳ በሰጠን ቁጥር አዲስ መፍትሄ ይመስል የቀድሞ ስህተቶቻችንን እንደጋግማለን። እስቲ አንድ ጊዜ ተቋቁመው የፈረሱ ኮሚቴዎችን አስቧቸው። አብሯቸው የባከነውንም ንብረት አስቡት። ወያኔን እንዳናስደስት እየተባለ፣ ትኩረታችን በወያኔ ላይ ይሁን እየተባለ መናገር ያለብንን አለመናገራችን እንግልታችንን እያበዛው እንጂ እያሳጠረው አልመጣም። ስለዚህ እውነቱን መናገር መጀመር አለበት እላለሁ። ይህ ሂደት የድሮ የእረኞች የአዙሪት ዜማ  ያስታውሰኛል።

„ያረሰም ዘራና

የዘራም አጨደ

ያጨደም ከመረ

የከመረም ወቃ

የወቃም አስገባ

ያስገባብ አስፈጨ

ያስፈጨም አቦካ

ያቦካም ጋገረ

የጋገረም በላ

የበላም አረሰ

ያረሰም ዘራና“ ……..

ተመልስን ተመልስን ያረሰም ዘራና ብለን እንጀምራለን።

በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓይነት ሕብረቶች እየተመለከትን ነው። አንዱ በግንቦት ሰባት የተመሠረተው <<ጥምረት ለነፃነት፣ለእኩልነትና ለፍትህ>> በኢትዮጵያ በሚል የተቋቋመ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት ለመፍጠር ወደ ካናዳ ስብሰባ መጥራታቸው ይሰማል።

በግንቦት ሰባት የተቋቋመውን ጥምረት ስንመለከት “ጉልበት አለን፣ መሣሪያ አንስተናል” የሚሉ (ከሆነ ጥሩ ነበር) የተሰባሰቡበት ናቸው። ይህ ደግሞ የወያኔ ኢሕአዴግን ዓይነት አካሄድ ነው የሚሉ አልጠፉም።  በተለይ በአሁኑ ወቅት ሻብዕያ እየፈለፈለ ያለውን የዘር ድርጅቶች ስንመለከት እውነትነቱ እየጎላ ይታያል። ለምሳሌ አስመራ ላይ የከተመ “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ” የሚባል ድርጅትም መግለጫ አውጥቶ አንብቤለሁ።

በካናዳ ሊፈጠር የተጀመረው ኀብረት ደግሞ ብዙ ግልጽነት የማይታይበትና የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን አሰባሰስቤለሁ የሚል ነው። እነዚህ በውስጡ ተሰባስቤለሁ የሚሉት ድርጅቶች ብዙዎቹ ከግለሰብነት አልፈው የድርጅትነትን ቅድመ ሁኔታ የማያሟሉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ደበቅነው አልደበቅነው አባላታቸውን አሰማርተው የሚያመረቃ ትግል ሲያደርጉ አልታዩም። ብዙዎቹ የእነዚህ ድርጅቶች መሪዎች እስከ አሁን የተቋቋሙት ኅብረቶች ውስጥ አባል የነበሩ ናቸው።

ዛሬ ግለሰብ ብቻውን የሲቪክ ድርጅት ሆኛለሁ ብሎ ሊያውጅ ይችላል።  ግለሰብም ፓርቲ ነኝ ለማለት ቆንጆ ድረ ገጽ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ዛሬ እንደ በቅሎ ማሃን የሆኑና አባላት የማያፈሩ ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉን። ዛሬ አንድ የነበሩ ድርጅቶች ካለ በቂ ምክንያት ሁለት ሆነው እያየን ነው። ዛሬ ለምርጫ ብቻ ብቅ የሚሉ ሰላማዊ ታጋዮችን በየምርጫው ወቅት ማየት ልምድ ሆኗል። ዛሬ የግለሰብ የሽግግር መንግሥት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ዛሬ ድሮ የማይቻሉ የሚመስሉን ሁሉ ተችለዋል።

እኔ በበኩሌ የወያኔን እድሜ ለማሳጠር ኅብረት አስፈለጊ መሆኑን አምንበታለሁ። አንድ የፖለቲካ ድርጅት በተናጥል ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲ ይወስዳል ብዬ እምነት የለኝም። እነዚህ ኅብረትን ለመፍጠር የሚጥሩትን ግለሰቦች ላመሰግን ብፈልግም ይህንን እምነቴ ግን የሚፈታተኑ ብዙ ልምዶች በዚህ በ21 ዓመት ትግል ውስጥ ተመልክቻለሁ።

ከአሁን ወዲህ ግን መናገር ያለብንን ቀድመን መናገር አለብን። ይህ የይስሙላ ኀብረት፣ ይህ የዘር ድርጅቶች ስብስብ፣ ይህ ሌሎች ድርጅቶችን በማግለል የሚፈጠር ጥምረት ”ዳግማዊ ኢሕአዴግን” ሊፈጥር ይችል እንደሆን እንጂ ሃገራችንን ወደ ነፃነት፣ ሕዝባችንን ወደ ዴሞክራሲ አይወስድም። በሌላ በኩል ደግሞ አባላት የሌላቸው ድርጅቶች፣ ዛሬ እንደሚታየው ሁለትና ሦስት እየተሆነ በየጎራው የተመሠረቱ የሲቪክ ድርጅቶች፣ የግለሰቦች ኀብረት ይፈጥሩ እንደሆን እንጂ፣ ሌላ የሚፈይዱት ጉዳይ አይኖርም። አጉል ተስፋ ሕዝብን አንመግብ። ነፍስ ያለው ድርጅት ሳይኖር የድርጅቶች ኅብረት እያልን እስከመቼ ነው የምናሾፈው?

በኅብረት ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች እስቲ ለኀብረት በትንሹ የ1000 አባል ፊርማ አምጡ ቢባል ስንት ድርጅቶች ናቸው ድርጅት ሆነው የሚቆሙ?  በተለይ በውጭ ሃገር ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ። መነገር አለበትና ዛሬ ካልተናገርን እንደዋሸን ነው የሚቆጠረው ይላል ጉንተር በግጥሙ መሃል።

ድርጅት ሳይኖር የድርጅቶች ሕብረት የሚለው ቀልድ ቢቆም ይሻላል እላለሁ። ይህ የስህተት ድግግሞሽ በዝቶብናል። እንደ አሜባ ራሳቻንን እየከፋፈልን ከርመን፣ በዚሁ ክፍፍል ላይ ኅብረት ብንጠራ አይሳካም።  በየሠፈሩ ያለ የጎበዝ አለቃ ሁሉ የውሸት ድርጅት እየመሰረተ ግለሰብነቱን ተውኩ ስላለና ብቻውን የኀብረቱ ተሳታፊ ስለሆነ፣ ኅብረት ተፈጠረ ማለት አይደለም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ኅብረት ይሳካል የሚል እምነት የለኝም።

ሕብረት በመፍጠር፣ በየወቅቱ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኮሚቴ በማቋቋም፣ በመከፋፈልና በመሃል ስለባከነው ጉልበትና ንብረት ሳስብ አንድ ጓደኛዬ የወሎ ክፍለ ሃገር የግብርና የዞን ሃላፊ የነበረ ያጫወተኝ ትዝ ይለኛል።  አንድ በውጭ የሚገኝ ድርጅት በወሎ ክፍለ ሃገር ደን ለማስተከል ቦታ ይመርጥና ሁኔታውን ግብርና ሚኒስተር እንዲያስፈጽም ተስማምቶ ከውጭ ገንዘብ ለብዙ ዓመታት ይልካል። ታዲያ  ከዓመታት በኋላ የተተከለውን ደን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ ኮሚቴ ይልካል። የግብርና ሚኒስተርም እነዚህን የውጭ ሰዎች ከአዲስ አበባ ለመመለስ ያደረገው ጥረት ስላልተሳካለት ኮሚቴውን ወደ ወሎ ይልካል። ይህ የፈረደበት ጓደኛዬ ነበር  ማስጎብኘት ያለበት። አስጎብኝቶ ሲጨርስ ፈረንጆቹ በጣም ይደነግጣሉ። ያሰቡትን ያህል ሳይሆን በጣም አነስተኛ የሆነ ደን ይመለከታሉ። ከመካከላቸው አንዱ ጓደኛዬን ጠጋ ብሎ የላክነው ገንዘብ ራሱ ቢተከል ኖሮ ያንን ተራራ ታየዋለህ ? እሱን ያለብስ ነበር አለው።  እስከዛሬም ሃገራቸውን የሚወዱ ዜጎች የሰጡትን ንብረት ራሱን ቢልኩት ኖሮ ጦር ሆኖ ወያኔን ባንቀጠቀጠ ነበር። ግን አለመታደል የሚታገለው ሳይሆን የማይታገለው ለገንዘቡ ታድሏል።

እውነት ይህች ሃገር ችግር ውስጥ ነው ያለችው ብለን ካመንና አደጋውን ከተረዳን፣ በመጀመሪያ መደረግ ያለበት  

1ኛ. የተከፋፈሉ ድርጅቶች(ፓርቲዎች) በተለይም አንጋፋዎቹ ተመለስለው አንድ የሚሆኑበት ወይም ችግራቸው የሚፈታበት መንገድ መፈለግ አለበት።  ይህ ደግሞ በመከፋፈላቸው ምክንያት ከትግሉ የሸሹትን ያሰባስብልናል።

2ኛ. ከዛም የዓላማ ተመሳሳይነት ያላቸው ድርጅቶች የሚዋሃዱበትንና የተሻለ ድርጅት የሚመሠርቱበት መንገድ መፍጠር ይኖርብናል። ይህ ደግሞ ድርጅቶችን ያጠናክራል።

3ኛ. እንደ ድርጅት መቀጠል ያልቻሉ ግን በግለስብ ለይስሙላ የተቋቋሙ ደግሞ ለሃገር አንድነት ሲሉ  ከሌላው መቀላቀል ወይም መፍረስ ይጠበቅባቸዋል።

4ኛ ግለሰቦች ከድርጅት ጋር ራሳቸውን ካቋራኙ ለድርጅቱ ድክመትም ይጠየቃሉና ከዛ ለመሸሽ በግለሰብነት መቆየትና በኅብረቱ ውስጥ ሁነኛ ቦታ ማግኘት የመረጡ ብዙ ናቸው።  በተለይም ደግሞ ለሃገር ብዙ ሊሠሩ፣ ድርጅቶችን ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች ውስጥ ሳይገቡ ብቻቸውን <<በተዋቂ ግለሰብ>> በሚል ስያሜ በኅብረት ውስጥ መግባታቸው ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚጎላው። ይህ ደግሞ የተደጋገመ ጥፋት ነው። ዛሬ በግለሰብ የሚታገሉ በመብዛታቸው ድርጅቶች እርቃናቸውን ቀርተዋል ማለት ይቻለል። ስለዚህ በኅብረት ውስጥ ተዋቂ ግለሰብ የሚለው መሰረዝ አለበት የሚል እምነት አለኝ።

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብዙ መፍትሄዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ውይይቱ በግልጽ መደረግ አለበት። ዛሬ በዚህ ክፍፍል ውስጥ ጉልበታችንን አናባክንም ያሉ ብዙ ሃቀኛ ዜጎች ቤታቸውን ዘግተው በሃዘን ቤታቸውን ዘግተው እንዲቀመጡ ተደርጓል። በዚህ ክፍፍልና የግል ስምን ለማስተዋወቅ የሚደረግ እሽቅድድም ውስጥ መሳተፍን ባለመፈለጋቸው፣ እንደ ተኮላሸው የ97 ዓይነት ሁሉንም ዜጋ የሚያሰባስብ እንቅስቃሴ እየጠበቁ ነው። ይህንን ደግሞ ብዙ ጥረትን ይጠይቃል። ከላይ የጠቀስኳቸውን ካልፈፀምን እነዚህ ግለሰቦች እንደገና ለማግኘት አንችልም።

ለእማኝነት ያህል ቅንጅትን በአውሮፓ ታላቅ ሥራ እዲሠራ ያደረጉ፣ በሕዝብ የሚታመኑ ቆራጦች፣ ከቅንጅት በኋላ በተፈጠሩት የተከፋፈሉ ጓራዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በራቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል። ይህን ዓይነት ክስተት በቅንጅት ብቻ ሳይሆን በብዙ ድርጅቶች የታዘብነው ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ቆራጥ ኢትዮጵያውያንን ወደ ትግሉ ለመመለስ ከተፈለገ በእርግጥ ታስቦበት አሳማኝ ሥራ ሊሠራ ይገባል። እነዚህ ኢትዮጵያውያንን በመተው ከረባታቸውን አሳምረው በተደረደሩ የይስሙላ የድርጅት ተጠሪዎች ስብስብ ኅብረት ማቋቋም ውጤቱ ሌላ ክፍፍል እንዳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን ስጋት ነው።

ከኅብረት በፊት ግልጽ የሆነና ብዙኃኑን የሚካትት ውይይት መደረግ አለበት።  ቀደም የተቋቋሙና የፈረሱ ኅብረቶች መጠናትና መፍትሄው መፈለግ አለበት። ከዚያ በኋላ ነው ጠንካራ ኅብረት መፍጠር የሚቻለው። ይህን በምጽፍበት ወቅት በአሁኑ ጊዜ የሚደረጉትን ጥረቶች መቃወሜ እንዳልሆነ ልተረዱልኝ ይገባል። ግን ደግሞ በችኮላና ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የሚደረግ ኀብረት ደግሞ የሚፈጠውረውን አስከፊ ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋልና ከኅብረት በፊት ጥንቃቄ ያስፈልጋል በማለት ነው ።

ስለ ሃገራችን አንድነት የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ !

በልጅግ ዓሊ     Beljig.ali@gmail.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 9, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.