መለስ ዜናዊና ኢትዮጵያን የመጥላቱ እንቆቅልሽ! (ትርጉም)

በመሳይ ከበደ (ፕሮፌሰር – ዴይቶን ዩኒቨርሲቲ ኦሀዮ) 

መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ዓይን-ያወጣ ጥላቻ ከምን እንደመነጨ የኢትዮጵያን ምሁራን ሲፈትን የሰነበተ ጥያቄ ነው። አንዳንዶች የጥላቻው ምንጭ ግማሽ ኤርትራዊ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ስር-ከሰደደ የብሔር ዘረኛነቱ ጋር የተዛመደ ነው በማለት ይደመድማሉ። በዙዎችም ሰውዬው ለሥልጣን ያለውን ከፍተኛ ጥማት ያነሱና የፖለቲካ ሥልጣኑ መሠረት የሆነችውን አገር የመጥላቱ እንቆቅልሽ ግራ ይገባቸዋል። ግን ሁሉም የሚስማማበት ነጥብ አለ። የሚመራባቸው ፖሊሲዎችም ሆኑ ዕለት-ተለት የሚወስዳቸው ርምጃዎች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት አሟጦና አጥፍቶ ትርፍራፊውን በዘረኝነት መርዝ ለተበከሉ ገንጣዮች ጥሎ መፈርጠጥን ያመላክታሉ። መለስ ብለን ብናይ ኢትዮጵያ ጨካኝ ገዥዎች እንዳጋጠሟት እናስታውሳለን። ይሁን እንጅ ሁሉም በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩና ለሀገራቸው ቀናኢ የነበሩ ናቸው። ይኸኛው ግን በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ በሆነ እሴት ላይ ያለው መንገፍገፍ መገለጫ አይገኝለትም።

አንድ የመለስን የጥላቻ መሠረት የሚገልጽና ሁላችንም የምናውቀውን ነገር ማንሳት የቻላል። ይኸውም ከቤተሰቡ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። የቤተሰቡ ታሪክ ከወራሪው የኢጣለያ መንግሥት አሳፋሪ ታሪክ ጋር ቁርኝነት አለው። አያቱ ለኢጣሊያ መንግሥት ማገልገል ብቻ ሳያሆን ሹምና ተባባሪ ነበሩ። ታዲያ መለስ ከቤተሰቡ የወረሰውን ነውር በትከሻው እንዳንጠለጠለ ይገኛል። ቤተሰቡ በዚህ አሳፋሪ ተግባር መናቁና በሕብረተሰቡ መገለሉ በመለስ ጨቅላ አዕምሮ ውስጥ የበቀልና የጥላቻ ስሜት እንዳሳደረ ሥራው ይመሰክራል።

ታዲያ እንደ መለስ ዓይነት ደዌ ለተጠናወተው ሁለት አማራጮች አሉ። ቀናው አማራጭ በቤተሰብ ሃፍረት የደረሰበትን ሸክም በመልካም ሥራ ለማካካስና ለማበስ መሞከር ነው። ይህም የታደሰ ኢትዮጵያዊነትን በማንጸባረቅ ሊተገበር ይችላል። ይኸኛው የእርቅና የተሀድሶ ጎዳና ሲሆን ራስን በቅጡ መመርመርንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ወኔን የሚጠይቅ ነው። ሆኖም እንደዚህ ዓይነቱ ወኔ የመለስ ጠንካራ ጎን ለመሆኑ ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

ሁለተኛው መንገድ ወኔ የማያስፈልገው አፍራሽና ቃና-ቢስ መንገድ ነው – ክህደት እንደነበረ ሽምጥጥ አድርጎ የመካድ። ይህን ለመተግበር ኢትዮጵያን ማንኳሰስና የኢትዮጵያን ግኝቶች ሁሉ ማናናቅ አማራጭ ሆኖ ይታየዋል። በዚህ መንገድ የቤተሰቡንም የራሱንም የሃፍረት ጫና ያቃለለ ይመስለዋል። “መጀመሪያውኑም የሚካድ ነገር የት ነበርና?” ብሎ ራሱን አሳምኖ ሌሎችንም ለማሳመን የሚደረግ ከንቱ ድካም ነው።

የክህደት መንገድ ጥላቻን ይወልዳልም ያራባልም – ጥላቻ በሌሎች መወገዝንና መናቅን መከላከያ መሣሪያ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በጥላቻ ከተመረዝህ ይሉኝታንም ሩህሩህነትንም ታሺቀነጥርና ጠላቶችህን በማንኛውም መንገድ የማጥቃቱንም የማጥፋቱንም ተግባር እንደ ተገቢ ተግባር አድርገህ ትቆጥረዋለህ። መለስ በወያኔ ትግራይ ፓርቲ አመራር ውስጥ ሊተኮስ የቻለው ይህን ጥላቻውንና ጭካኔውን መሣሪያ አድርጎ እንደሆን መገመት አያዳግትም። መለስ በኢትዮጵያ፤ በታሪኳ፤ በባህሏ፤ በሠራዊቷና ባንድነቷ ላይ ሥር የሰደደ ጥላቻ ስለነበረው ጥላቻን ከርሱ በበለጠ የሚያስተምርና የሚያነሳሳ ካድሬ በወያኔ ሠራዊት ውስጥ ሊገኝ አይችልም ነበር።

የኢትዮጵያን ባንዲራ “ተራ እራፊ” ብሎ ሲያናንቅ፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ የወረራና የጭቆና ታሪክ ነው” እያለ ሲቸክ፤ ያገሪቱን አርበኞችና ጀግኖች ሲያንኳስስ፤ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተገነባ የፖለቲካ መድረክ ያላቸውን የፓርቲ መሪዎች እያሰረ አሳፋሪ የምህረት ደብዳቤ አርቅቆ  እንዲፈርሙ ሲያስገደድ ፍላጎቱ ስውር አይደለም። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያዋረደና ያጠፋ እየመሰለው ነው፤ የነውር ሸክሙን ያቃለለ እየመሰለው። 

የ1997 ምርጫ ውጤት ደግሞ የቆየ ጥላቻውን እጅግ እንዲባባስ አድርጎታል። የኢህአዴግን ሽንፈት በርሱ ላይ የተቃጣ የውርደት በትር አድርጎ ስለቆጠረው ተቃዋሚ ፓረቲዎችና ሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚዘገንን ርምጃ ወሰደ።

ይህን የጻፍሁት መለስ ቢያዳምጠኝ ብየ ነው – ራሱን በጥሞና እንዲመረምር እመኛለሁ። ፖሊሲዎቹና ተግባሮቹ አደገኛ ቁስል እየፈጠሩ መሆናቸውን እንዲረዳና ታላቅ መሪ የመባል ዕድሉን እየበከሉበት ምሆኑን እንዲያውቅ እመኛለሁ። የቆሰለ መንፈስ የሚፈወሰው መጀመሪያ የችግሩን መንስኤ መርምሮ በማወቅ ነው። የህዳሴና የእርቅ ጎዳና አሁንም ክፍት ነውና መልካም ሥራዎችን በመሥራት ሊታደግ ይችላል። ኢትዮጵያን በማዋረድ የተሸከመውን ሀፍረት አስወግዳለሁ በሎ የሚያስብ ከሆነ ተሳስቷል፤ የተዋረደች አገር መሪ ነው የሚሆነውና። በሌላ አነጋገር…መድሃኒቱ የሚገኘው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በማዋረድ ዘመቻ ውስጥ ሳይሆን ከፍ-ከፍ በሚያደርግ ጥረት ውሰጥ ነው!       

>> Translated from English

(Prof. Messay Kebede can be reached at mkebede1@udayton.edu)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 9, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.