“ሕዝብን የሚያሸብር ሁሉ እርሱ ራሱ በማያቋርጥ ፍርሃትና ሽብር የተዋጠ ነው!” አንድነት ፓርቲ

ሕዝብን የሚያሸብር ሁሉ እርሱ ራሱ በማያቋርጥ ፍርሃትና ሽብር የተዋጠ ነው!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ሽብርተኝነት የንፁሀንን ሕይወት በጅምላ የሚያጠፋ፣ አካልን የሚያጎድል፣ የሀገርን ሀብት፣ የልማት አውታሮችንና ተቋማትን የሚያወድም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ ፓርቲያችን በማያወላውል ቁርጠኝነት ያወግዘዋል፡፡ ሽብርተኝነት በሚያደርሰው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ዓላማውም የራስን ፍላጎት በሌሎች ላይ መጫን በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው የእንቢተኞችና የጉልበተኞች ድርጊት በመሆኑ አጥብቀን እንኮንነዋለን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በሽብርተኝነት ስም ሽብር የሚነዛ አካልን አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ [Click here to read the press release in PDF]

የፓርቲያችን አቋምና እምነት ከላይ የተቀመጠው መሆኑንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች በጀት የሚንቀሳቀሰው የመንግሥት የደህንነት አካልም ቢሆን ይህን ያጣዋል ብለን አናምንም፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግልጽ ስናደርገው እንደቆየነው ሁሉ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በዜጎች ላይ ሽብር የሚፈጥር ከመሆን አልፎ በመንግሥት ላይ የሚነሳን ሕጋዊና ሠላማዊ ተቃውምን ማፈኛ ዋና መሣሪያና መገልገያ እየሆነ ነው፡፡ መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ4 ዓም በፓርቲያችን ከፍተኛ የአመራር አባል ም/ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሆኑት በአቶ አንዱዓለም አራጌ፣ በፓርቲያችን የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት በአቶ ናትናኤል መኮንን እና በአቶ አሳምነው ብርሃኑ ላይ የተወሰደው የእስር እርምጃና መታሠራቸውን ተከትሎ ከመንግሥት የተሰጠው መግለጫ ይህንኑ ሀቅ የሚያረጋግጥ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ የማን አለብኝነት እርምጃ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ሁሉ የመጨረሻውም እንደማይሆን ከኢህአዴግ የ2ዐ ዓመታት የአገዛዝ ሥርዓት ባህሪ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የሽብር ድርጊት አራማጆች መሸሸጊያም ሆነ መደበቂያ አይደለም፤ አይሆንምም፡፡ ፓርቲው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችን ተከትለውም የሚወሰዱት እርምጃዎች ሆኑ እንቅስቃሴዎች በዴሞክራሲያዊ አካሄድ በግልጽ የሚከናወኑ ናቸው፡፡

የሽብርተኞች መደበቂያ የሚለው ክስ መነሻውና ሀቁ ግን የፓርቲያችን እየተጠናከረና የሕዝብ አመኔታን እያተረፈ መምጣቱ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ጳግሜ 4 ቀን 2ዐዐ3 ዓም የወጣው የፍትሕ ጋዜጣ የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋማትን ለማስመረጥ በአዘጋጀው መስፈርት መሠረት የሕዝብ አስተያየት ተሰብስቦ አንድነት ፓርቲ አንዱ ተመራጭ መሆኑ ማስረጃ ነው፡፡ ከፓርቲያችን በበጎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋምነት መመረጥ በስተጀርባ ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ አባላት በመኖራቸው ነው፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ ደግሞ በሠላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እየጎላና እየላቀ የመጣ ወጣት ፖለቲከኛ ነው፡፡ በመሆኑም የእሱ በሽብረተኝነት መፈረጅ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ብዙ ቢሆኑም አንዱና ዋነኛው ግን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ከፍተኛውን አመራር እየያዙና ብቃታቸውን እያስመሰከሩ የመጡትና እየመጡ ያሉትን ወጣቶች ከትግል ሜዳው አስበርግጎ ማሸሸት ነው፤ ሳያድግ በእንጭጩ ለማስቀረት፡፡

ዛሬ መንግሥት እንደ ፋሽን የያዘው በሚመስል መልኩ ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያው መብቶች መከበር የሚታገሉ የሠላማዊ ትግል አርበኞችን በሽብርተኝነት መወንጀል ሆኗል፡፡ የታዋቂው ነፃ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሽብርተኝነት መታሠርም ከዚህ ተለይቶ አይታይም፡፡ በአለፉት ሣምንታት የታሠሩት የፖለቲካ ሰዎችና ጋዜጠኞችም ጉዳይ እንዲሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኢህአዴግን መንግሥት ልንጠይቀው የምንፈልገው ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ ሽብርን ወይም የሽብርተኝነትን ድርጊትና ውጤቱን በትክክል ትረዱታላችሁ ወይ? እውነታን በሰከነ አዕምሮ የሚመለከት ተቋምም ሆነ ሰው ‹‹ከሽብር ይሰውረን›› ነው የሚለው፡፡ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በሱማሊያ፣ በኢራቅ በሕንድ በቅርቡ ደግሞ በናይጄሪያ እየተፈፀሙ ያሉ አሰቃቂ የሽብር ድርጊቶችን የሚያውቅ ሁሉ ሽብርን አይመኝም፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌን በሽብርተኝነት መወንጀል በሽብር የሚሰቃዩ ሰብአዊ ፍጡራን ላይ መሳለቅ ይሆናል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ከሚያነሱ በሕግ ታውቀው ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦና ተወያይቶ አገራዊ ችግሮችን መፍታት ሲገባ ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና የተሰጣቸውን መብቶች ሁሉ በሽብርተኝነት ስምና በማንአለብኝነት መናድና ማሽመድመድ ለሠላማዊ ትግል ደንታቢስ ከመሆንም ባሻገር የገዥው ፓርቲ መንግሥትን የሥልጣን ደህንነት ለማረጋገጥ ከመስራት ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡

ሕዝብን በፍርሃት ቆፈን ጠፍሮ አስሮ የነፃነት ትግሉን መቀልበስ እንደማይቻል ገዥው ሥርዓት ሊረዳው ይገባል፡፡ የነፃነት ትግል መንፈስነውና፡፡ አካልን ማሰር ቢቻልም መንፈስን አስሮ ማቆም ግን አይቻልም፡፡ የአምባገነኖች አፈና የትግልን መንፈስ ይበልጥ ሲያጠናክር እንጂ ሲያዳክም በታሪክ አልታየም፡፡

ፓርቲያችን አንድነት ምንጊዜም ቢሆን ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረግ ሁለገብ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም እንደሚሆን ለሕዝባችን ቃል እንገባለን፡፡ ይህ ማለት በሽብርተኝነት ውንጀላ ፍራቻ የሕዝብን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስጠበቅና ብሎም ሕዝብን የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን የጀመርነውን ሠላማዊ እንቅስቃሴ በመጠኑ እንኳን እንገታለን ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር ሆነን ሠላማዊ ትግላችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን ደግመን ደጋግመን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ሕዝቡም በበኩሉ ለመብቱና ለነፃነቱ መከበር በመታገል ትግሉን ሊቀለበስ ወደማይችልበት ደረጃ የማድረስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን በአክብሮት እናስተላልፋለን፡፡ እውቁ የፈረንሳይ ሊቅ ቮልቴር በአንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ፍርሀት ከወንጀል ቀጥሎ ይመጣል የወንጀል ቅጣት ነውና›› ብሏል፡፡ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ወንጀለኛ አይደለም፡፡ ስለዚህም ለፍርሀት ቦታ የለውም፡፡ ወንጀለኞች ይፍሩ እንጂ!፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
መስከረም 5 ቀን 2ዐዐ4 ዓም
አዲስ አበባ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 16, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.