ለዳያስፖራው አዲስ ፖሊሲ ረቀቀ

ከአዘጋጁ መልእክት: –  የገና በዓልን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ወጣት አረፈዓይኔ ቦብ ዊን ከወያኔ ፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሟች አስከሬን ትናንት ምሽት ወደ አሜሪካ ተልኳል:: እንዲህ አይነቱን ወንጀል እየፈጸመ ነው ወያኔ ዳያስፖራውን እንደገና አታልሎ ሊዘርፍ የሚፈልገው?
—–

በውድነህ ዘነበ (reporter) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን (ዳያስፖራ) ወጥ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ያስችላል ያለውን አዲስ ፖሊሲ አረቀቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ከዚህ ረቂቅ በተጨማሪ አገሪቱ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በምትመራበት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት አቅዷል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳዮች ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ መብራት በየነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ ለበዓል ወደ አዲስ አበባ ከመጡ 500 ከሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመመካከር ቀን መቁረጡን ገልጸዋል፡፡

ውይይቱ ትኩረት የሚያደርገው ዳያስፖራውን በሚመለከት በተረቀቀው ፖሊሲና በአምስት ዓመት ዕቅዱ ዙሪያ መሆኑን፣ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ዳያስፖራው ሚናውን እንዲገነዘብና ተጨማሪ አስተያየቶቹን እንዲሰጥ ለማድረግ መሆኑን ወይዘሮ መብራት አስረድተዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ውስጥ ኢንቨስት ቢያደርጉ የሚያገኙዋቸው የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ይሁንና ዳያስፖራው በአገሪቱ ልማት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ሊያሳድር የሚችለው መልካም ተፅዕኖ ተለይቶ እንዲታወቅ ለማድረግና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚያገኛቸው ማበረታቻዎችና ጥቅማ ጥቅሞች ዙሪያ ወጥ የሆነ ፖሊሲ ማስቀመጥ ያስፈልጋል በሚል፣ ሚኒስቴሩ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የሌሎች አገሮች ልምድ ተካቶበት ተዘጋጀ የተባለው ረቂቅ ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሸራተን አዲስ ሆቴል ውይይት እንዲካሄድበት መዘጋጀቱንና ስብሰባውንም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ረቂቅ ፖሊሲ በተጨማሪም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለውይይት ይቀርባል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ግዙፉን የአምስት ዓመታት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማግኘት ትኩረት ከተደረገባቸው ምንጮች መካከል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሳሉ፡፡

መንግሥት ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን ለልማት የሚውል ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ሽያጩን ከመጀመሩ በፊት የልማቱን ጥልቀትና ስፋት ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ስብሰባው እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በሁለቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ከዲያስፖራው ጋር የሚያካሂደው ውይይት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀርና በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከወራት በኋላ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ሰፋፊ ውይይቶችን ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

ይህንን ውይይት ለመምራት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የብሔራዊ ባንክ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ተቋማትን የሚመሩ ባለሥልጣናት ቅድሚያውን እንደሚይዙም ታውቋል፡፡

የመሠረተ ልማት ተቋማት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሮች ከሦስት ሳምንት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ በየመሥሪያ ቤቶቻቸው አማካኝነት የተሠሩ ሥራዎችንና ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎችን አጠናቅሮ የያዘ ሰነድ በ10,000 ኮፒ እንዲያዘጋጁ መታዘዛቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 13, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.